Tuesday, July 7, 2015

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት በ፴፪ኛው የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ በዓል ተሳትፎ አደረገ

ከሰኔ ፳፩ እስከ ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓም በተደረው የESFNA ፴፪ ኛ ዓመታዊ በዓል ላይ ተሳተፈ
በበዓሉ ላይ IUEOTCFF በርካታ ሥራዎችን ለኢትዮጵያውያን በማቅረብ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ተሞክሯል
በዚሁ በዓል መጠናቀቂያ ላይ IUEOTCFF ትልቅ ጉባኤ በሃዋርድ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ አዘጋጅቶ ለምዕማናን በገዳሙ ላይ እየደረሰ ያለውን እና በገዳሙ አካባቢ የደረሰውን ተዓምራት ለምዕመናን ተገልጿል
ይሄንኑ የESFNA በዓል ተከትሎ የማኅበሩ አጠቃላይ ጉባኤ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ጉባኤውን አድርጎ የውሳኔ ሃሳቦችን አስተላልፏል

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት ከተመሠረተበት ሦስት ዓመታት ከግማሽ ጀምሮ ጉባኤ ዘርግቶ ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ ሰላማዊ ሰልፎችን በማዛጋጀት ለትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን ላልሆኑ የዓለም ማኅበረሰብ የተለያዩ መግለጫዎችን በማውጣት፣ ለዓለም ማኅበረሰብ ደብዳቤ በመጻፍና በአካል በመገናኘት ገለጻዎችን በማድረግ ብሎም በተለያዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመገኘት እየደረሰ ያለውን ጥፋት እና እንግልት ለኢትዮጵያውያን ሲያስገነዝብ እና የእምነቱ ተከታዮችን አለኝታነታቸው እንዲያሳዩ ሲያሳስብ መረጃዎችን ሲያደርስ ቆይቷል። አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን ሰሜን አሜሪካ ፴፪ኛው ዓመታዊ በዓል ላይ በመገኘት ለምዕመናን እንዲሁም በአጠቃላይ ለኢትዮጵያውያን በዋልድባ ገዳም ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ስውር ደባ፣ በምዕመናን ላይ እየተፈጠረ ያለውን ውዥንብር ለኢትዮጵያውያን በተለያዩ ዘዴዎች ለማድረስ ጥረት ተደርጓል፤ ከነዚህም መካከልo   በርካታ መረጃዎችን የያዘውን DVD በማሳተም በነጻ ለኢትዮጵያውያን አድርሷል 

o   በራሪ ጽሑፎችን በማሳተም ኢትዮጵያውያን እምነታቸውን እንዲያውቁ ሁለት የተለያዩ ጽሑፎችን አዳርሷል

o   ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተሰሩትን ጉልህ ሥራዎች እንዲሁም በርካታ ጥናቶችን የያዘ መጽሔት በማዘጋጀት በቀላል ዋጋ ለኢትዮጵያውያን ለማድረስ ተሞክሯል o   የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዚህ ዘመን የሚያስፈልጋት እራሱን ዝቅ በማድረግ በትሕትና የሚያገለግሉ ካህናት እና የሚገለገለገሉ ምዕማናን እንደሚያስፈልጋት ለማጠየቅ የማኅበሩ ዓባላት እራሳቸውን ዝቅ በማደረግ ጫማ በመጥረግ ለዋልድባ ገዳም እና ማኅበሩ ለሚሰራቸው መጠነ ሰፊ ሥራዎች የሚያግዝ የገንዘብ እርዳታ ለማሰባሰብ ተሞክሯል
o   በርካታ በተመጣጣኝ ዋጋዎች ምዕመናን ገዝተው ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ነገሮችን ለምሣሌ:
o   ከቅድስት ሃገር የመጡ የቅዱሳት ሥዕላት ያላቸው የቁልፍ መያዣዎችን
o   የቅዱሳን ሥዕላትን
o   የአንገት መስቀሎችን
o   የመኪና ውስጥ የሚለጠፉ ጥቅሶችን
o   እንዲሁም በርከት ያሉ ምዕመናንን ሊያንጹ የሚችሉ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ምዕመናን እቃዎችን ገዝተው እንዲቀሱበት እግረ መንገዳቸውን የማኅበሩን በርካት ራዕዮች እውን ለሚደረገው ጥረት ማገዣ እንዲሆን በመገግዛት በርከት ያሉ ሥራዎች ተሰርተዋል
በዚህ በዓል መጠናቀቂያ ላይ ማለትም ትላንት እሑድ ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በሃዋርድ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ ጉባኤ ዘርግቶ ለኢትዮጵያውያን በማኅበሩ ከምሥረታው እስካለንበት ጊዜ ድረስ የተሰሩትን በርካታ ሥራዎች በዝርዝር በማኅበሩ ሊቀመንበር የቀረቡ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች በርከት ያሉ መርኃግብሮችን ያካተተው ጉባኤ በቅደም ተከተል ለምዕማን ቀርበዋል ከነዚም መካከል ለአብነት ለመጥቀስ ያህል
·         ማኅበሩ ያከናወናቸው ሥራዎችን በቅደም ተከተል እንዲሁም ለምን ማኅበሩ መመሥረት እንዳስፈለገ ለምዕመናን ትልቅ ግንዛቤ ለመሰጠት ተሞክሯል
·         የወቅቱ የቤተክርስቲያን ፈተናዎች እና ከምዕመናን ምን ይጠበቃል በሚል ሰፋ ያለ ጊዜ ተወስቶ የቀረበ ጥናታዊ ጽሁፍ ምዕማናኑን ነገስ ከእኛ ምን ይጠበቃል በሚል በእያንዳንዱ ተሳታፊ አዕምሮ ውስጥ የወቅቱን ፈተናዎች እና ከእኛ ምን እንደሚጠበቅ ያስገነዘበ መልዕክት ተላልፏል
·         በደብረ ምሕረት ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የወቅቱን የሕይወት ፈተናዎች የሚያሳይ ትምሕርታዊ ጭውውት የቀረበ ሲሆን፤ በወቅቱም ምዕመናን ከጭውውቱ ትልቅ ትምህርት እንደወሰዱ እና እንደሚጠቀሙበት የሚያጠይቅ የወቅቱ የደውል ድምጽ መሆኑን ልብ ይሏል
·         በዋልድባ ገዳም አካባቢ የሚደርሱ ፈተናዎች እና የሰማይና የምድሩ ፈጣሪ መዳኅኒዓለም ያደረጋቸው ተዓምራት ለምዕመናን በጽሁፍ ቀርበው የእግዚአብሔርን ተዓምራት ለመገንዘብ አስችሏል
·         በመጨረሻ በዚህ ዓመት በተደረው በዓል ላይ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት ለማኅበሩ በተለያዩ ሙያዎች አስተዋጽዖ ያበረከቱ ግለሰቦች በወቅቱ የክብር እንግዳ የሰርተፊኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዚሁ የጉባኤው መዝጊያ ጸሎት ላይ የክብር እንግዳው ምዕመናን በዚህ ዘመን በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ፈተና በቸልታ መመልከት እንደሌለባቸው እና ሁላችንም የበኩላችንን አስተጽዖ እንድናደርግ በማሳሰብ እያንዳንዱ ምዕመን በያለበት ለቤተክርስቲያናችን ሰላምን ለምዕመናን ደግሞ ረደኤት በረከቱን እንዲያሳድርብን በጸሎት ወደፈጣሪያችን እንድናመለክት አደራ በማለት የጉባኤው መዝጊያ ጸሎት በማድረግ ተፈጽሟል።
በዘንድሮው ዓመት የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን ሰሜን አሜሪካ ፴፪ኛው በዓል ላይ በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ የቆየው የማኅበሩ የኮሚቴ አባላት በቀን በበዓሉ ላይ ከጠዋት 11:00 am ጀምሮ እስከ ምሽቱ 10:00 pm. ድረስ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሲሰሩ ቆይተው በማታ ደግሞ እስከ 3 እና 4:00 am.  ድረስ በስብሰባ ስለማኅበሩ እስከ አሁን የተጓዘበትን መንገድ እና የወደፊቱን አካሄድ የማኅበሩን የሥራ እና የፋይናንስ ሪፖርት አዳምጦ በርከት ያሉ ግምገማዎችን በማድረግ በቀጣይነት ሊሄድበት የሚችልበትን መንገዶች ጠቋሚ የሆኑ ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት ችሏል።
የማኅበሩ አባላት ከተለያየ ስቴቶች እንዲሁም ከካናዳ ጨምሮ እረጅም ሰዓት በመንዳት ለዚህ ሥራ መጥተው ሰለቸን ሳይሉ በቀን በበዓሉ  ላይ በማታ በስብሰባ ተጠምደው ላለፉት አምስት ቀናት በርካታ ሥራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል። በዚህ ዓመታዊ የሥራ ሪፖርት በቀረበበት ስብሰባ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ተመልክቶ ወደፊት በምን መልኩ ማለፍ እንዴት እንደሚቻል፣ የተሰሩ ሥራዎችን ተመልክቶ በበለጠ ለመሥራት ምን መደረግ አለበት የሚለውን በሪኮማንዴሽን መልክ ለመጪው ዓመት መሠራት ያለበትን በእቅድ መልክ፣ ያልተፈጸሙትን ሥራዎች ደግሞ እንዲፈጸሙ የተለያዩ አስተያየቶችን ከአባላት ተቀብሎ ሥራዎችን በአዲስ መልክ ለመሥራት አምላከ አበውን አጋዥ በማድረግ በድጋሚ ለቅድስት ቤተክርስቲያን እና በየበረሃው እና በየፍርክታው እራሳቸውን ጃንደረባ በማድረግ ለፍቅረ ክርስቶስ እራሳቸውን ያስገዙ ገዳማውያን አባቶች እና እናቶችን ለመደገፍ እና በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የሚደርስባቸውን መከራ እና ስቃይ እየተከታተልን ለምዕመን ለማሳወቅ በድጋሚ ቃል ገብተናል።
በመጨረሻም የማኅበሩ አባላት ቀጣዩን ዓመታዊ ጉባኤ በየት እና እንዴት መደረግ እንዳለበት ሲመክር ቆይቶ ከዚህ በኃላ በየዓመቱ ዓመታዊ ጉባኤዎችን በተለያዩ ቦታዎች ለማዛጋጀት እና አባላትን ለማጠናከር በዝርዝር ተነጋግሮ እቅዶችን በማውጣት ሊሰራ ተነጋግሮ የዘንድሮው የ፳፻፯ ዓ.ም. ጉባኤ ፍጻሜ ሆኗል። በዚህ ጉባኤ ላይ እስከ ዛሬ በተለያየ መንገድ ሲተባበሩን ለነበሩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በሙሉ በያሉበት እግዚአብሔር አምላክ ጸጋውን እንዲያበዛላቸው እና ሥራቸውንም እንዲባርክ ከልብ እየተመኘን የከርሞ ሰው ይበለን በማለት የጉባኤውን እንዲኊም የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል። አነሳስቶ ያስጀመረን፣ አስጀምሮ ለፍጻሜ ያበቃን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው በማለት እኛም በዚሁ እንሰናበታለን።

እግዚአብሔር አምላክ ቅድስት ሃገራችን ኢትዮጵያያን እንዲሁም ሕዝቦቿን በረደኤት ይጠብቅልን አሜን  

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

1 comment:

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤