Thursday, October 29, 2015

ቅ/ሲኖዶስ: የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴው በቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ ወሰነ፤ አደረጃጀቱ ከጠቅ/ቤተ ክህነት እስከ አህጉረ ስብከት ይወርዳል

  • የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን በትምህርት ይከላከላል፤ ማስረጃዎችን እያቀረበ ያጋልጣል
  • የጠቅ/ቤተ ክህነቱ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ኮሚቴ በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ይመራል
  • ቋሚ ኮሚቴው፣ ከሰርጎ ገቦች የጸዳና አባላቱም በሃይማኖታቸው እንከን የሌላቸው ሊኾኑ ይገባል
South and West A.A Archbishop
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፤የካፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ
የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ እና ታሪካዊ ትውፊት እንዳይፋለስ መጠበቅ እና ማስጠበቅ፤ አገልግሎቷ እና አስተዳደሯ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲመራ የማድረግ ሓላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ÷ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን ለመከላከል እና ለማጋለጥ በመካሔድ ላይ የሚገኘው ኹለ አድማሳዊ ተጋድሎ እና እንቅስቃሴ፣ በቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ ወሰነ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው÷ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐተ እምነት እና ክርስቲያናዊ ትውፊት በመበረዝ እና አስተዳደራዊ አንድነቷን በማናጋት ለመከፋፈል አልያም ባለችበት አዳክሞ ለመውረስ ወደ መዋቅሯ ሰርገው የገቡትን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችንና የዋነኛ አዝማቾቻቸውን ሤራ በማስረጃ የማጋለጥ እና በትምህርት የመከላከል ተልእኮ የተሰጠው ሲኾን ዓላማውን የሚያስፈጽምበት መዋቅርም በዘላቂነት እንዲዘረጋ ነው የተወሰነው፡፡ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አህጉረ ስብከት እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ የሚዘረጋው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ኮሚቴ በበላይነት የሚመራው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሲኾን በቋሚ ኮሚቴው አባልነት የሚመረጡት ሊቃውንት፣ ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችም በእምነታቸው እንከን የሌለባቸው፤ በቀናዒነታቸው፣ በዕውቀታቸው እና በሕይወታቸው የተመሰከረላቸው ሊኾኑ እንደሚገባ ቅዱስ ሲኖዶሱ በውሳኔው ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ተጠሪ ኾኖ በማእከል የሚቋቋመውንና እንቅስቃሴውን በበላይነት የሚያስተባብረውን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ኮሚቴ እንዲመሩ፣ የቅኔ እና የመጽሐፍ መምህሩ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፤ የካፋ ሸካ ቤንች ማጂ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ በምልአተ ጉባኤው ምርጫ ተሠይመዋል፡፡
የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ፣ ከአህጉረ ስብከት የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አደረጃጀቶች ጋር እየተናበበ የሚካሔዱ እንቅስቃሴዎችን በሪፖርት ያቀርባል፤ የሚሰበሰቡ ማስረጃዎችንም በመተንተን እያጠናቀረ በቅዱስ ሲኖዶሱ በማስወሰን ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡ ከኅትመቶች ዝግጅት ጀምሮ እንቅስቃሴው ስለሚገኝበት ደረጃ ጥናቶችን በቀጣይነት በማካሔድ የኑፋቄው ሤራ በተሟላ ገጽታው እንዲነቃበትና እንዲጋለጥ፤ ተቋማት፣ ካህናትና ምእመናን ራሳቸውን ከኑፋቄው እንዲጠብቁና በኦርቶዶክሳዊ ማንነታቸው እንዲጸኑ በማድረግ ተልእኮውን ይወጣል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው መመሥረት፤ በተለያዩ አደረጃጀቶች ማኅበራዊ መሠረቱ እየሰፋና የተጋድሎ ስልቱ በብዙኃን መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ጭምር እየታገዘ በመፋፋም ላይ ለሚገኘው ኹለ አድማሳዊ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ተጋድሎ ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊ እና ሞራላዊ ድጋፍ ከማስገኘቱም በላይ ርምጃውንም የተቀናጀ፣ የሚለካ እና በውጤት የታገዘ ያደርገዋል፤ ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ “እጅግ ወቅታዊ እና ተፈላጊ ውሳኔ” ማሳለፉን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በግንቦት 2004 ዓ.ም. ምልአተ ጉባኤው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄን የሚያራምዱ 16 ግለሰቦችንና ስምንት ድርጅቶችን በውግዘት የለየ ሲኾን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ በውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴ የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ ለመቋቋም ስብከተ ወንጌልን በበቂ መጠን ማስፋፋት እና ማጠናከር፤ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን አስወግዶ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እንደሚገባ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ ተሳታፊዎችም፤ ባለፈው ሳምንት ኃሙስ ባጠናቀቁት 34ኛው ዓመታዊ ስብሰባቸው“ገለልተኛ አስተዳደር”  በመፍጠር ጭምር የቤተ ክርስቲያንን ማእከላዊነት እየተፈታተኑ የሚገኙት ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን ለቀጣይ ህልውና ስጋቶች መኾናቸውን በመግለጽ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ መልካም አስተዳደርን በሚያስፈኑ የተቋማዊ ለውጥ እና የዕቅበተ እምነት ርምጃዎች አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያስገኝ በጋራ መግለጫቸው ጠይቀዋል፤ በዚኽ ረገድ ቅዱስ ሲኖዶሱ ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊነት የበኩላቸውን ለመወጣትም ዝግጁነታቸውን አስታውቀዋል፡፡

Source: https://haratewahido.wordpress.com

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤