Tuesday, January 26, 2016

የራስ እያለ የሰው ቅልውጥና (ከመጋቤ ጥበብ በእምነት ምትኩ)

Hydraulis, which is from ancient Greece.  Ctesibius of Alexandrea, who lived about B.C 200
ከሰሞኑ ከካሊፎርኒያ አዲስ የሚመስል ነገር ግን ውስጥ ውስጡን እንደ በረሀ ውሃ ሲሄድ የኖረው ነገረ ኦርጋን በአደባባይ ተሰምቷል። ይኸውም 95 ዓመቱ አረጋዊ ሊቀ ጳጳስ የተናገሩት ቃል ነው። አባቶቻችን አንድ ትልቅ ምርቃት አላቸው። ይኸውምከቁንጅና ጋር ዕብደት፣ ከሽበት ጋር ቅሌት፣ ከገንዘብ ጋር ስስት ከዕውቀት ጋር ትዕቢት አይስጥህይላሉ። ሽምግልና ትልቅ ስጦታ ነው። ቅዱስ ሰሎሞንየሽማግሌ ሽበቱ ዘውዱ ነው” (ምሳ 1631) ይላል። ሽማግሌዎች አምላክ በጸጋ የሸለማቸውን የሽበት ዘውዳቸውን ደፍተው የተጣላ ያስታርቃሉ፣ የተጣመመ ያቃናሉ፣ የጎደለ ይሞላሉ። የሽማግሌ ዐይን ጉልበት ይሰብራልና ሽማግሌ ፊት ቆሞ አሻፈረኝ የሚል ማንም ሰው አይገኝም።አማካሪ የሌለው ንጉሥ ያለአንድ ዓመት አይነግስእንደሚባለው ነገሥታትም ቢሆኑ ሽማግሌ ሳይዙ ሀገር ማስተዳደር አይችሉም። ሸማግሌ የማይፈታው ችግር የለምናሰማይ ተቀደደ ቢሉ ሸማግሌ ይሰፋዋልእንደተባለ። በአንጻሩ ከሽበት ጋር ቅሌት ከመጣ ግን እጅግ አሳዛኝና አደገኛ ነው የሚሆነው ምክንያቱም ከሽምግልና ጋር የሚመጣ ቅሌት ሚዛን ያሳጣል፣ መማለጃ (ጉቦ) ያስመኛል፣ ፍርድ ያስታል፣ በአንደበት ሐሰት ያናግራል፣ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ያጣላል። ከሰሞኑም የኾነው ነገር ይኸው ነው።

እንዴት እኚህን በሚያህሉ አረጋዊ ሰው አንደበት ሐሰት ይነገራል? በሚል ብዙ እናቶችና አባቶች፣ ወንድሞችና እህቶች እጅግ አዝነዋል፣ አንገታቸውን ደፍተዋል፣ አንጀታቸው እርር ብሏል። ይንን ቃል ሲናገሩ የነበሩ ሰዎች ብዙዎቹ በአፍረት ሲሸማቀቁ ተስተውለዋል። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ነገር ለክርስቲያኖች የሚደንቅ ነገር አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረውእስመ እኩይ መዋዕሊሁ - ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው” (ኤፌ 515” እንዳለው የዘመኑ ፍጻሜ ላይ ስለምንገኝ እንኳን እንዲህ ዓይነቱን ነገር ቀርቶ ከዚህም የበለጠ ነገር እንሰማ ዘንድ ግድ ነው። በአባ መልከጼዴቅ እና የአይጥ ምስክር ድንቢጥ በሆኑ ጥቂት ደጋፊዎቻቸው የተላለፈው መልዕክት ግን ትክክል ነው? ወይስ አይደልም? የሚለውን ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር በማገናዘብ መመርመር ተገቢ ነው።
በቅድሚያ ኦርጋን እና አርጋኖን አንድ ናቸውን? የሚለውን ማየት አለብን። አንድ ቃል ከሌላ ቃል የሚወረሰው ወራሹ ቃል ከተወራሹ ቃል ጋር ግንኙነት ወይም ዝምድና ሲኖረው ነው። ዝምድና ወይም ግንኙነት የሚኖረው ደግሞ ሁለቱም ቃላት በአንድ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ ሲገኙ ነው። ለምሳሌ፦ ሥላሴ የሚለው ቃል ሠለሰ ከሚለው የግእዝ ግስ የተወረሰ ወይም የተገኘ ነው ስንል ሥላሴ የሚለው ወራሹ ቃልም ሆነ ሠለሰ የሚለው ተወራሹ ቃል ሁለቱም የግእዝ ቃላት ስለሆኑ ነው። መብላት የሚለው በላ ከሚለው የአማርኛ ቃል ይወረሳል ወይም ይገኛል። ምክንያቱም ሁለቱም ቃላት የአማርኛ ቃላት ናቸው። ነገር ግን ኢት (eat) የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል በላ ከሚለው ከአማርኛ ቃል ነው የተገኘው ቢባል ግን ፈጽሞ የማይሆን ወይም የማይመስል (ridicules) ነው። እንግዲህ የአቡኑ እና የደጋፊዎቻቸው የኦርጋን ብያኔ (definition) እንዲሁ ነው። ኦርጋን የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አርጋኖን ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው ወይንም ሁለቱ አንድ ናቸው እያሉን ነው። ይኼ አባባል በእውነቱ የተናጋሪዎቹንም ሆነ የሰማዕያኑን ዕውቀት (የዘመናዊ ዕውቀትም ሆነ መንፈሳዊ ዕውቀት) ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው። አንዳንድባሕታውያንነን የሚሉ ሰዎች ልክ እንደነ አባ መልከጼቅ ዓይነት ትርጉም ስለ ቡና ይተረጉማሉ። ይኸውምበስመ ብኑ ተሰምየ ቡነ - በብኑ ስም ቡና የሚለው ቃል ተገኘበማለት ብኑ በተባለው የሤሩህ ልጅ አማካኝነት አምልኮተ ጣዖት ስለተጀመረ እና ቡናም ከዚሁ ከብኑ ስም የተገኘ ስለሆነ ቡና አይጠጣም ይላሉ። ነገር ግን ብኑ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ነው፤ ቡና የሚለው ደግሞ የአማርኛ ቃል ነው። እንዴት ሁለቱ ቃላት ተዛመዱ? ሲሏቸው መልስ የላቸውም። እኛ ቡና አልነው እንጂ ፈረንጆቹ ኮፊ (coffee) ነው የሚሉት ቻይናኛው እና ራሻኛው ደግሞ የተለየ ነው። ወይንስ ቡና የሚለው አማርኛ ስለሆነ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ነው ቡና መጠጣት የተከለከለው?
ኦርጋንና አርጋኖን እና የሚሉት ፊደላት ስለተመሳሰሉ (overlap) ስላደረጉ በውድም ሆነ በግድ ትርጉማቸው አንድ መሆን አለበት ማለት ነው? “ቁራን ሊበሏት ሲፈልጉ ጅግራ ናት ይሏታልእንዲሉ አባቶቻችን በኦርጋን መዘመር ያስፈልጋል ካሉ አራምባና ቆቦ የሆኑ ሁለት ቃላትን ለማመሳሰል ከመሞከር ይልቅ በግልጽ እውነተኛ ምክንያታቸውን ይኸውም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሥርዋጽ በማስገባት ቀስ በቀስ መቀየር እንፈልጋለን ቢሉ በተሻለ ነበር።
አርጋኖን በቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንደየአገባቡ የተለያየ ትርጉም ይዞ እናገኛዋለን። ለምሳሌ አርጋኖን ምስጋና የሚል ትርጉም ይዞ እናገኘዋለን። እሴብሕ ጸጋኪ ዘእግዝእትነ ማርያም ላይበነቀልቃለ ስብሐት ሁኪዮ ለአርጋኖነ ሕሊናየ ከመ ኢያርምም ስብሐታተ ፍቅርኪ - በሚቀጣጠል ምስጋና የሕሊናዬን ማመስገኛ ቀስቅሺው ሕሊናዬ ወይም ልቡናዬ የፍቅርሽን ምስጋና ከማመስገን ዝም እንዳይል ይላል። በመልክአ ውዳሴ ዘሠሉስ ላይነሢአ ነፍሰነ አርጋኖነ ኵሎ ዘመነ ለልደትኪ ታበውዕ ቊርባነ - ነፍሳችን ሁልጊዜ ምስጋናን ታነሳለች ለልደትሽም ምስጋናን ታቀርባለችይላል። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም አርጋኖን ዘእግዝእትነ ማርያም የተሰኘ ድርሰት አለው። ይኬንንም እነዚሁ መፍቀርያነ ኦርጋኖች ሲጠቅሱት ተመልክተናል። እንግዲህ ይህ ማለት የእመቤታችን ኦርጋን ማለት ነው? እንዴት ያሳፍራል። አርጋኖን ዘእግዝእትነ ማርያም ማለት የእመቤታችን መመስገኛ ምስጋና ማለት ነው። ምስጋናዋንም በሳባቱ ዕለታት ከፍሎ አመስግኗታል። በሌላ በኩል ደግሞ አርጋኖን ልዩ ዜማ፣ ልብን የሚመስጥ፣ ቃና ያለው ዜማ ማለት ነው። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ አርጋኖን የሚለውን ቃል ሲተረጉሙአርጋኖን ማለት የማኅሌት ዕቃ፣ መዝሙር፣ በገና፣ ውዳሴ፣ ምስጋና፣ መልካም ዜማ፣ ለዦሮ የሚመስጥ ደስ የሚያሰኝ ድምጽ ማለት ነውይላሉ።
ሌላኛው መፍቀሬ ኦርጋን የሆኑት ሰው ደግሞሰባኬ ወንገል ዮሐንስ አርጋኖነ ትንቢት ዘይደምጽ ለቤተ ክርስቲያንየሚለውን ቃል ሲተረጉሙሰባኬ ወንጌል  ዮሐንስ ለቤተ ክስቲያን መልካም ድምጽ የምትሰጥ በትምህርትህ የምትመስጥ የቤተ ክርስቲያን አርጋኖን/ኦርጋን ነህማለት ነው ብለው የራሳቸውን አዲስ ቃል ጨምረው ይከራከራሉ። እግዚአብሐር ያሳያችሁ ከላይ በግእዝ ከተጠቀሰው አረፍተ ነገር ውስጥ ኦርጋን የሚለው እሳቸው የጨመሩበት ቃል የቱ ጋር ነው ያለው። አባቶችየደንቆሮ ለቅሶ መልሶ መላልሶእንደሚሉት በእነርሱየሊቃውንትትርጓሜ ኦርጋን ማለት አርጋኖን ማለት ነው። ነገር ግን ፈጽሞ የተሳሳተ መሆኑን ካለይ ተመልክተናል። ቃሉ ሲተረጎምየወንጌል ሰባኪ የሆነው ዮሐንስ መልካም የሆነውን የትንቢት ቃል ለቤተ ክርስቲያን ያሰማልማለት ነው። ይህ ቃል ቅዱስ ያሬድ የተናገረው ለዮሐንስ ወንጌላዊ ሲሆን መልካም የሆነው የትንቢት ቃል የተባለው ደግሞ በፍጥሞ ደሴት ላይ ሆኖ ስለመጪው ዘመን የጻፈውን ራእዩን ነው።
ወደ አቡኑ ንግግር እንመለስና ኦርጋን የሚለው ቃል በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን በታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመዝሙር 150 ላይ ይገኛል ይሉናል። ለመሆኑ በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ታትሟል የሚለው ቃል መቼ የተፈበረከ አዲስ ግኝት ነው? እርግጠኛ ነኝ አይደለም የእሳቸው ኦርጋንና አርጋኖን ሚለው የግእዝ ቃል በየትኛውም ዘመን በተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ካለ ደግሞ እስቲ ያሳዩን! በጣም የሚገርመው ቃል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ ታተመ የሚለው አዲስ ግኝት ነው። በየትኛው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ እንዲህ ዓይነቱ ድርሰት ይገኝ ይሆን? ነው ወይስ እኔ አረጋዊ ነኝ እና ታሪክ ፈጥሬ መናገር እችላለሁ እያሉን ነው? አልያም እኔ በውጪ ስለምገኝ በኢትዮጵያ የሚገኙት ሊቃውንት በአፍም ሆነ በመጽሐፍ እንዳይረቱኝ ያለሁት በርቀት አሜሪካ ስለሆነ አያገኙኝም ብለው ነው? ይህቺንማ ስርዋጽ የንጉሠ ነገሥቱ ቀራቢ መሆናቸውን ተጠቅመው ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ነገር እንደመስራት የፈረንጅ ቆርቆሮ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስገብተው እንደነበር ዓለም ይመሰክራል። ነገር ግን በወቅቱ በነበሩ የተዋሕዶ የቁርጥ ቀን ልጆች በአፍም ሆነ በመጽሐፍም ድል ተደርገውና አፍረው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ድምጹ እንዳይሰማ ተደርጓል። ይኼን ላደረጉ አባቶች ክብር ይግባቸውና ቤተ ክርስቲያኒቱን አስከብረዋት ይኖራሉ። በየትኛውም ታሪክ ውስጥ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን እንደታተመ የሚናገር ማስረጃ አይገኝም። ካለም ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነውና ይቅረብ። መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሱን ለማሳተም ሲዘጋጁ ድንገት የጣሊያን ጦርነት ስለተጀመረ ሳይሳካ ቀርቶ በኋላም በስደት ወደ ለንደን ሲሄዱ በእጅ የተጻፈው በመኪና ተተይቦ ስላላቀ በእጅ በቁም ጽሑፍ የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዳለ በማይክሮ ፊልም ተነስቶ እንዲባዛ ተገርጓል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በእጃችን ውስጥ ይገኛል። በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መዝሙር 150 ላይ እንኳን ኦርጋን አርጋኖን የሚለው ቃል ፈጽሞ አይገኝም።
ሌላው መታወቅ የሚገባው ነገር እነርሱ የሚሉት ኦርጋን የተጀመረው በጥንታዊቷ ግሪክ 200 ወይም 300 ዓመት ቅድመ ክርስቶስ እንደሆነ “The History of Organ” ብላችሁ ብትፈልጉ ታገኙታላችሁ። በቅድሚያ በጥንታዊው ግሪኮች የተፈለሰፈው ኦርጋንና አሁን ያለው ኦርጋን በፍጹም አይመሳሰሉም። የጥንቱ ፓይፕ ኦርጋን የሚባል ሲሆን በአፍ የሚነፋ ነገር ነው። አንድ ናቸው እንኳን ቢባል ቅዱስ ዳዊት የነበረው ከክርስቶስ ልደት 1000 ዘመን አስቀድሞ ሲሆን ኦርጋን የመጣው ደግሞ ከክርስቶስ ልደት 200 ወይም 300 መቶ ዘመን አስቀድሞ ነው፤ ታዲያ ቅዱስ ዳዊት ከየት አግኝቶት ነው በኦርጋን አመስግኑ ያለው? እንዲሁም በሌላ ቦታ ላይ 1 ዜና 632 ላይ ኦርጋን (በእነርሱ አነጋገር አርጋኖን) የሚለው ቃል ተጽፎ እናገኛዋለን ይላሉ። በጣም የሚገርመው ግን እንዲህ ዓይነቱ ቃል 81 ሆነ 66 መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈጽሞ አይገኝም።
ሌላው አንድ ቀሲስ ነኝ የሚል የፕሮቴስታንት ተላላኪ ፓስተር ደግሞ በፌስ ቡክ ገጹ ላይትልቅማስረጃ አግኝቶ ሞቶ ጥቅስ ጠቅሶ ለኦርጋን መመታት ማስረጃ ያቀርባል። አልፎም የቅዱስ ያሬድን ስም ይጠቅሳል። ይኸውምወሰምዐ በህየ  ቃለ እንዚራ ወቃለ አርጋኖን ወቃለ መሰናቅው እንዘ ይሴብህዎ ወይዌድስዎ ወየአኩትዎ ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር በስብሐት ወበማኅሌት በቅኔ ወበልዑል ዜማ ነግህ ወሠርክ ይሴብሕዎ ለንጉሥ ዐቢይ በዐውደ መንበሩ ቅዱስ- በዚያም የእንዚራን የአርጋኖን የመሰንቆ ድምጽን እንደዚሁም ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ገናናው ንጉሥ እግዚአብሔርን በምስጋና በማኅሌት በቅኔ በጠዋትና በሠርክ ከፍ ባለ ዜማ (ካህናተ ሰማይ መላእክት) በተቀደሰ ዙፋን ሲያመሰግኑ ሰማ  …” (ጥንታዊ ሥርዓተ ማኅሌት ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ ገጽ 23 – 24) የሚለውን ቃል በማስረጃነት ያቀርባል። በመሠረቱ እዚህ ጥቅስ ውስጥ ኦርጋን የሚለው ቃል የለም። በመቀጠል አርጋኖን የሚለው ቃል ኦርጋን ወይም ፒያኖ ከሆነ ደግሞ አሁን እነርሱ የሚያንኳኩት አስቀድሞ በግሪኮቹ የተፈለሰፈው በኋላም በፈረንሳዮቹ የተስፋፋው የዘፈን መዝፈኛ በዓለመ መላእክት አለ ማለት ነው። ምክንያቱም በመንበሩ ዙሪያ የሚያመሰግኑትን መላእክትን ሰማሁ ነው የሚለው ቃሉ። በጣም የሚያሳዝን ነው። የጥንቱም ሆነ የአሁኑ ኦርጋን በራሱ የሚሰራ አይደልም። የጥንቱ በነፋስ ሓይል የአሁኑ ደግሞ በኤሌትሪክ የሚሰራ ነው። ታዲያ በዓለመ መላእክትም ውስጥ በሆነ ሓይል (በነፋስ ወይም በኤሌትሪክ) የሚንቀሳቀስ መሳሪያ አለ ማለት ነው። ነገር ግን የአርጋኖን ትርጉም በዚህ አገባቡ ደግሞ አላቃ ኪዳነ ወልድ እንደተረጎሙት ሁለተኛውን ትርጉም ማለትም በገና ወይም መለከት ማለት ነው።
መፍቀሬ አርጋኖን የሆኑት ሰው ይቀጥሉናከበሮው የዘፈን መሳረያ ሆኗልብለው የዘፈኑ ኦርጋን ቤተ ክርስቲያን ቢገባ ችግር የለውም የሚያሰኝ ውሃ የማይቋጥር ሙግት ያመጣሉ። እኛም እያልን ያለነው ዓለማውያኑ. መናፍቃኑ ከእኛ ይውሰዱ እንጂ እነንዴት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሥርዓት የደመቀችው፣ በትውፊት ያሸበረቀችው፣ ዓለም ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ሄዶ የሚጎበኛት ሙሉና ስንዱ የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ከዓለማውያኑ ትወስዳለች? ሰሞኑን መናፍቃን የእነሱን ቆርቆሮ ኦርጋን ጥለው የእኛን ከበሮና ጸናጽል ይዘው ተመልክተናል። ቅልውጥና የማይሰለቻቸው፣ የራሳቸውን የጎደላቸው ከእኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ይቀላውጡ እንጂ እንዴት ተገልብጦ ቤተ ክርስቲያናችን ከሌላ ትቀላውጣለች። ይኼ ከጀርባው ሌላ ሚስጥር አለው። ቤተ ክርስቲያኒቱን በተኩላ ለማስበላት ቀስ ብሎ ወደ አዳራሽነት ለማስቀየር ከሚደረገው ትግል መካከል አንዱ እንደሆነ ግልጽ ነው።
እንግዲህ ኦርቶዶክሳውያን ነቅተን ቤተ ክርስቲያናችን እንጠብቅ። አቡኑ እንደሆነ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት በጉልምስናቸው ዛሬ ደግሞ በስተርጅናቸው ልጣቸው ተርሶ፣ ጉድጓዳቸው ተምሶ የማይለወጡ ናቸው። ለዚህም ልናዝንና ልንጸልይላቸው ይገባል። በዘመናቸው ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚከፋፍል፣. ምዕመናኑን የሚለያይ ሀሳብ በማምጣት በአንዲት ቤተ ክርስቲያኒያን ውስጥ ውዥንብር በመፍጠር የኖሩ ይህም የሚያስደስታቸውጭር ሲል አልወድምበማለት በግልጽ የሚናገሩ ሰው ናቸውና ከዘመናቸው ፍፃሜ አስቅድሞ ወደ ልቦናቸው እንዲመልሳቸው አምላከ ቅዱሳን ይርዳቸው። እኛ የተዋሕዶ ልጆች ግን ቅዱስ ሰሎሞንየአባቶችን ድንበር አታፍልስ” (ምሳሌ 2228) እንዳለው በየትኛውም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቶያን ውስጥ የማይገኝ አልፎ ተርፎ እኚሁ ሰው አቋቁሜዋለሁ በሚሉት በውጪሲኖዶስስር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንኳን እሳቸው ካሉበት ኦክላንድ መድኃኔ ዓለም የመናፍቅ እንደራሴው የትላንቱ ፓስተር የዛሬውቀሲስነኝ ባዩ ሰው ከሚገኝበትና በሲያትል በሚገኘው “በስደተኛው ሲኖዶስ“ ገብርኤል በስተቀር የትም አይገኝም። ይህ ደግሞ በሁሉም ቦታ የሚገኙት የተዋሕዶ ልጆች ቤተ ክርስቲያናቸውን አጥር ቅጥር ሆነው እግዚአብሔር የረዳቸዉ ቤተክርስቲያናቸውን እየጠበቁ እንድሚኙ በግልጽ የሚያመለክት ነው ይህንን የአባቶቻችንን ድንበር አጠናክረን እንድንጠብቅ እግዚአብሐር ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን። የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ከፈተና ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ከመከፋፈል፣ ምዕመናኖቻችንን ከሃይማኖት ስደት ይጠብቅልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር                                                      

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

5 comments:

 1. እግዚአብሔር ልባቸውን ይመልስላቸው እውነት ቤተክርስቲያን ችግሯ የሙዚቃ መሳሪያነው ወይስ እነሱ ጥማታቸው ሙዚቃ ሰለሆነ ነው፡፡ በአሁን ጊዜ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሮ ከእንስሳ ባነሰ አኖኖረ ሲኖር በረሃብ፣ ጤና በማጣት እና በስደት ነብሱን ለማዳን ሲታመስ ቤተክርሲቲያን ውስጥ ያለን እኛ የክርስቶስ ማደሪያ የሆነው ስው ሲሰቃይ ቤተክርሲቲያናችን ምን ያህል ችግሩን ለመፍታት ስርታ ነው የሙዚቃ መሳሪያ ችግራችን የሆነው? ባጠቃላይ አሳፋሪ እብደት ነው ከማንም አለማዊ ስው አይጠበቅም፡፡

  ReplyDelete
 2. እግዚአብሔር ልባቸውን ይመልስላቸው እውነት ቤተክርስቲያን ችግሯ የሙዚቃ መሳሪያነው ወይስ እነሱ ጥማታቸው ሙዚቃ ሰለሆነ ነው፡፡ በአሁን ጊዜ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሮ ከእንስሳ ባነሰ አኖኖረ ሲኖር በረሃብ፣ ጤና በማጣት እና በስደት ነብሱን ለማዳን ሲታመስ ቤተክርሲቲያን ውስጥ ያለን እኛ የክርስቶስ ማደሪያ የሆነው ስው ሲሰቃይ ቤተክርሲቲያናችን ምን ያህል ችግሩን ለመፍታት ስርታ ነው የሙዚቃ መሳሪያ ችግራችን የሆነው? ባጠቃላይ አሳፋሪ እብደት ነው ከማንም አለማዊ ስው አይጠበቅም፡፡

  ReplyDelete
 3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

  ReplyDelete
 4. EGZIABHER AMLAK Yagelglot Zemenih Yabark Kale Howot Yasemalin

  ReplyDelete
 5. AMLAKE KIDUSAN EGZIABHER Kale Hiwot Yasemalin Yagelglot Zemenkin Ybark Amen !!!

  ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤