Thursday, February 18, 2016

በጸሎት ያልተጀመረውና የእነ ሊቀ ሊቃውነት ዘኦርጋን ፍሬ ከርስኪ የስልክ ኮንፍረንስ (ክፍል አንድ)

የዘወትር የዝግጅት ክፍላችን ተሳታፊ እና በብዙ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ወንድማችን/ አባታችን ዛሬም እንደተለመደው ምልከታቸውን ልከውልናል፣ ሰሞኑን በየማኅበራዊ መድረኩ ትልቅ መወያያ የሆነው ”የኦርንና“ ፥ የአርጋኖን ጉዳይ መላውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ከሊቅ እስከ ደቂቅ እያወያየ ይገኛል፣ ይሄንንም ተከትሎ የጉዳዩ ባለቤቶች ሰሞኑን አንድ የሥልክ የመወያያ መድረክ ከፍተው ነበርና በስልኩ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እና ከአጀማመሩ እስከ ፍጻሜው የተመለከቱትን ለአንባብያን ለማድረስ ለዝግጅት ክፍላችን ልከውልናል እኛም እንደወረደ ለአንባብያን አቅርበነዋል ተከታተሉት ፥ አንድ ነገር እንደሚገነዘቡ እናምናለን መልካም ምንባብ። 

የስልክ መንፈሣዊ ጉባኤ

ከመጋቤ ጥበብ በእምነት ምትኩ (LLB)

አንድ መንፈሳዊ ጉባኤ መንፈሳዊ የሚያሰኘው ምንድ ነው? ጉባኤ ማለት ስብስብ፣ በጋራ መገናኘት፣ በኅብረት መወያየት ማለት ነው። ጉባኤ በቤተ ክስቲያን ወይም ከቤተ ክርስቲያን ውጪ በዓለማውያኑ ዘንድ ይደረጋል። ጉባኤያት ሁሉ አንድ አይደሉም። አንድን ጉባኤ መንፈሳዊ የሚያሰኘው በጉባኤው ላይ በሚነሱት ነጥቦች ወይም የመወያያ ርዕሶች ብቻ አይደሉም። ምክንያቱም መንፈሳዊ የሆኑ ሀሳቦች በሌሎችም ጉባኤት ሊነሱ ይችላሉና ነው። የመንፈሳዊ ጉባኤ መገለጫውና ልዩ ጠባዩ በጸሎት መጀመሩ ነው። የጸሎት ቁንጮ የሆነው፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ያስተማረው (ማቴ 6፡9)፣ ሲወጋ እንጂ ሲወረወር የማይታየው፣ የሁሉ መንፈሳዊ አገልግሎት መጀመሪያና ማሳረጊያው “አቡነ ዘበሰማያት - አባቶችን ሆይ” የሚለው ጸሎት ነው። በዚህ ጸሎት አማካኝነት ፈቃደ እግዚአብሔር ተጠይቆ የሚጀመር ጉባኤ ብቻ መንፈሳዊ ጉባኤ ይባላል።


          እንግዲህ ከሰሞኑ በውጪ “ሲኖዶስ” ነን የሚሉ ሰዎች፣ “ሕጋዊ” ነው የሚሉት የሲኖዶስ ራስ የሆኑት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ያልተገኙበት ሌሎችም አባቶች ያልተሳተፉበት ነገር ግን ጥቂት ግለሰቦችና የዘወትር የኦርጋን አቀንቃኙ ሊቀ ጳጳስ የተካፈሉበት የስልክ ስብስብ ተስተናግዶ ተመልክተናል። ይህ ስብስብ ገና ከጅምሩ መንፈሳዊ አለመሆኑን ያሳበቀ፣ እንኳን መንፈሳዊ ሊሆን የመንፈሳዊነት ለዛና ቃና የሌለው ይብሰተ ክርስትና የተጸናወተው ስብስብ ነበር። ሕሊናቸው በነገር የተበተበ፣ አንደበታቸው በስድብ የተሳለ፣ ብቻ የያዙትን በኦርጋን ካልተጨፈረ፣ መዝሙር በሚል ሙዚቃ ካልተቀነቀነ፣ ዳንኪራ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ካልተደለቀ ሞተን እንገኛለን የሚሉ ግለሰቦች ይህንኑ ሀሳባቸውን ለመናገር ከመስገብገብ ይሁን ከሌላ ዓላማ አቡነ ዘበሰማያት - አባቶችን ሆይ ለማለት እንኳን ጊዜ አልነበራቸውም። መንፈሳዊነት እኮ መንፈሳዊ ነን በማለት፣ አንደበትን በማለስለስና በማሳመር አይደለም። ጌታችን በቅዱስ ወንጌል “ወእምፍሬሆሙ ተአምርዎሙ - ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” እንዳለው መንፈሳዊነት የሚገለጸው በምናፈራው ፍሬ፣ በምንፈጽመው ተግባር ነው። ተግባራቸው ሌላ፣ አንደበታቸው ሌላ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ገና ሩቅ ሳይሄዱ ከጅምሩ እንደ ጅብ ሲያነክሱ ከአካሄዳቸው ያስታውቃሉ።
በጣም የሚገርመው ጸሎት አድርጉ ተብለው የተሰጣቸው ሊቀ ጳጳስ “በዚህ ምሽት ያንተን ብቻ ስም እንጠራለን፤ ክብር ምስጋና እናቀርባለን” በማለት ጸሎቱ ቀርቶ በፍጥነት ወደ ስድብና ወደ ተለመደው ማንጓጠጣቸው ገቡ።፡እንዲህ ዓይነቱ ስብስብ ምንጊዜም የሚጀምረው “አንተን ብቻ አንተን ብቻ” እናመሰግናለን፣ እናመልካለን በሚሉ ቃላት የታጨቀ ነው። ታዲያ ማን ነው ከእርሱ ውጪ የሚያመልክ? ነገሩ ወዲህ ነው። “ብቻ” የምትለዋን ቃል ዛሬ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውጪ ተደጋግሞ ስትነገር እንሰማለን። ምክንያቱ ግልጽ ነው። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜም ለሥላሴ “ስብሐት ለአብ፣ ስብሐት ለወልድ፣ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ - ለአብ ምስጋና ይገባል፣ ለወልድም ምስጋና ይገባል፣ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል” ካልን በኋላ “ስብሐት ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ - አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያምም ምስጋና ይገባል” በማለት ከሶስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ አካል ዘእምአካል፣ ባሕርይ ዘእምባሕርይ ነስቶ ሥጋዋን የተዋሐደውን፣ ለድኅነታችን ምክንያት የሆነችውን፣ ከአምላክ ጋር የተዛመድንባትን እመቤታችን ድንግል ማርያምን እናመሰግናለን። ቀጥሎም ሥጋውን የቆረሰበትን፣ ደሙን ያፈሰሰበትን፣ ነገረ ድኅነት የተፈጸመበትን ቅዱስ መስቀሉን እናመሰግናለን። እንዲሁም ከዘመድ ባዳ፣ ከሀገር ምድረ በዳ፣ ከሕገ ሰብእ ሕገ መላእክት ይሻለናል ብለው ለጽድቅና ለእግዚአብሔር ክብር ሲሉ መከራ የተቀበሉትን፣ በኑሯቸው አምላካቸውን ያስደሰቱትትን፣ በተሰጣቸው አምላካዊ ስጦታ አማልክት ዘበጸጋ የተባሉትን ቅዱሳንንም እናመሰግናለን። እንግዲህ የዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ትታደስ ባይ ፕሮቴስታንቶች የሚያቀነቅኑት ለእግዚአብሔር ብቻ እንጂ ለሌላ ምስጋና አይገባም ነው የሚሉት። ምስጋና ለእርሱ ብቻ እያሉ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሳይገልጿት አያልፉም። የሚገርመው ግን “ላንተ ብቻ!” አሉ እንጂ ስብስቡ የተጠራራው እግዚአብሔርንም ለማመስገን ስላልነበረ  እርሱንም ሳያመሰግኑ፣ መመስገኛው የሆነውን ጸሎት ሳያቀርቡ ወደተጠራሩበት ስድብና ዘለፋ ገቡ። እግዚኦ! እግዚኦ ማለት ይሄን ጊዜ ነው።
          ምነው በእዚህ ዘመን ስንት ሃይማኖታዊ ችግሮች በበዙበት፤ አልፎ ተርፎ ቤተ ክርስቲያኒቱ ልትመልሰው የሚገባ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች ከጫፍ ጫፍ በተንሰራፉበት ዘመን በኦርጋ ካልተደለቀ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እሸሼ ገዳሜ ካልተባለና በጭፈራ ካልተምነሸነሽን ታንቀን እንሞታለን ብሎ ሀቅልን መሳት፣ ሕሊናን ማጣት ምን የሚሉት ጉድ ነው? ምንስ ይሆን ምክንያቱ? እኔ በበኩሌ በሕይወቴ እንደዚህ ቀን አዝኜ አላውቅም። ምክንያቱም ፕሮቴስታንታዊ ዘመቻ አሁን ኦርጋንን አስገብቶ፣ በኋላ ቀስ ብሎ ከበሮና ጸናጽል አስወጥቶ፣ ሌላው ሌላው ደግሞ ቀስ እያለ ይቀጥላል ብዬ ነበር የማስበው እንጂ እንዲህ በአንድ ጊዜ ፈጥኖ፣ አይን አውጥቶ በመሄድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ የሆነውን አቡነ ዘበሰማያት ይቀራል ብዬ አላስብም ነበር። ይህ ደግሞ እንደልማዳቸው ሐሰት ነው እንዳይባል ከጅምሩ አንስቶ የተቀዳ ስለሆነ ሊንኩን ለሚፈልግ ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ። ይሄም እንግዲህ ስለላ ከሆነ እሰይ አበጀን ከማለት ውጪ ምን ይባላል? እንደ እናነተ ኃጢያት ሰርቶ አልሰራሁም፣ ክዶ አልካድኩም የሚል ነጣቂ ተኩላ ባለበት ዘመን ሰላይ መኖሩ ምን ያስደንቃል? ነው ወይስ ስለላለው ያቀዳችሁትን ቤተ ክስቲያንን ወደ አዳራሽ የመቀየር ስትራተጂ ባዶ አስቀረባችሁ? ሌባ ካለ ፖሊስ እንደሚኖር አታውቁም እንዴ? ነው “ማኅበረ ቅዱሳን ሰላይ ነው” ብሎ መጮህ ምን የሚሉት ድርቅና ነው? በራሳችሁ አታምኑም እንዴ? ለነገሩ ሌባ ሁልጊዜ ትኩር ብሎ የሚያየውን ሁሉ “ሊጠቁመኝ ነው” እያለ ሲሸበር ይኖራል። እውነተኛ ሰው ግን አይሸበርም። “እስመ ጽድቅክሙ ያግዕዘክሙ - ጽድቃችሁ (እውነት) አርነት ያወጣችኋል” (ዮሐ 8፡32) እንዳለ ጌታችን እውነተኛን ሰው የሚያሸብረው ነገር የለም። “እንዲህ ተብለናልና ስለዚህ እንዲህ የሚለው ደም አፍሳሽ ነው፣ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ሰላይ ነው” የሚሉ ውሃ የማይቋጥሩ፣ ለጆሮ የሚቀፉ፣ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ ቁጭ ብሎ በሬ ወለደ እንቶ ፈንቶ አይናገርም።
          ይልቁንስ ቤተ ክርስቲያኒቱ የማታውቀውን፣ በየትኛውም ዘመን ተጠቅማበት የማታውቀውን፣ ዛሬም ቢሆን በየትኛውም አብያተ ክርስቲያናት (በገጠርም ይሁን በከተማ) የማይገኘውን ኮልኮሌ ኦርጋን ካልገባ ብላችሁ ከምትጮሁ፣ ኦርጋን ማለት በግዴታ አርጋኖን ማለት ነው እያላችሁ የሞኝ ለቅሷችሁን እየደጋገማችሁ ከምታለቅሱ ቤተ ክርስቲያኒቱ በየትኛውም ቦታ የምትጸልየውን፣ ኦርቶዶክሳዊ የሆንን ሁላችንም ስንበላና ስንጠጣ፣ ስንተኛና ስንነሳ በማንኛውም ተግባረ ሥጋችን ሁሉ የምንጸልየውን ጸሎት መጸለይ፣ ስለጸሎት ማስተማር አይሻልምን?
          በስብስቡ ሶስት ተናጋሪዎች የነበሩ ሲሆን ከሁሉም አንድ አንድ በጣም አስገራሚ የሆኑ ነገሮች ለዛሬ ላንሳና ላብቃ። በቀጣይ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉንም እንዳስሰዋለን።
          1ኛ. የመጀመሪያው ተናጋሪ ከሲያትል ሲሆን በኦርጋን ላይ ያደረገው “ሰፊ ጥናት” እንዳለ ገልጾ ከጥናቱ መካከል በመዝሙር 150 ላይ በእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኦርጋን የሚል እንዳለ ገልጾልናል። በመሠረቱ በሕግ ትምህርት አንድ ዓለም አቀፋዊ መግባቢያ (consensus) አለ። ይኸውም በአማርኛ የተጻፉ ሕግጋት ወደ እንግሊዘኛ ትርጉም ወይም በእንግሊዘኛ የተጻፉ ወደ ሌላ ቋንቋ ሲተረጎሙና በመካከላቸው ልዩነት ካለ ውሳኔ ሚሰጠው ወይም በማስረጃነት የሚቀርበው ወይም ገዢ ትርጉም የሚሆነው (Authoritative document) በመጀመሪያ የተጻፈበት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ቀድሞ የተጻፈው በእንግሊዘኛ አይደለም። እንደውም ቀድሞ የተጻፈው በግእዝ ነው። ከግእዝ አስቀድሞ በግሪክ (ሰባ ሊቃናት የተረጎሙት)፣ ከዛም በፊት ደግሞ አብዛኛዎቹ በዕብራይስጥ ተጽፈዋል። ስለዚህ አንድ ተመራማሪ ነኝ ባይ ማቅረብ ያለበት ማስረጃ ከመጀመሪያ ዶክመንት (original document) እንጂ የእንግሊዘኛ ትርጉም አይደልም። እንዲሁም ስለ ኦርጋን አመጣጥ ይኸው መጋቤ ሐዲስ ነኝ ባዩ ሲነግረን ኦርጋን ከክርስቶስ ልደት 300 ዓመት በፊት እንደተፈጠረ ነው። ታዲያ ቅዱስ ዳዊት የነበረው ከልደተ ክርስቶስ አንድ ሺህ ዓመት በፊት ነው። በሁለቱ መካከል ደግሞ የሰባት መቶ ዘመናት ልዩነት አለ። ምነው ጥናቱ ይህንን አልተመለከተውም?
          ይኸው “ተመራማሪ” በተደጋጋሚ አርጋኖን ካለ በኋላ “ወይም ኦርጋን” የምትለዋን ሳይጨምር በፍጹም አያልፍም። እሴብሕ ጸጋኪ ዘእግዝእትነ ማርያምን (የማርያምን ስም የጠሩት እዚህ ጋር ብቻ እንደሆነ ልብ ይለዋል) ለኦርጋን ማስረጃ አድርጎ ያቀረበ ሲሆን ስለመሰንቆ፣ ስለ እንዚራ ሲናገር “ወይም” የሚል ቃል አልተጠቀመም። ልክ አርጋኖን የሚለው ጋር ሲደርስ ግን “ወይም ኦርጋን” በማለት የራሱን ልብ ወለድ ይጨምርበታል። “ተመራማሪው” አርጋኖን ኦርጋን ማለት አይደለም ለሚለው አነጋገር መልስ ሲሰጥ  እኛ የማናውቀውን “አዳዲስ” ነገር የነገረን ሲሆን “ኦርጋንና አርጋኖን ልክ ወተር (water) ማለት ውሃ እንደ ማለት ነው” ብሎ ከዚህ ቀደም “ኦርጋን አርጋኖን ከሚለው ቃል የወጣው ነው” ከሚለው ምርምሩ ትንሽ ዞር ያለ ልብ ወለድ ዲስኩሩን ያብራራል። ይህንን “ምርምሩን” በስድብ ያስደግፈውና (citation መሆኑ ነው) “የቤተ ክርስቲያኒቱ ቋንቋ ባዕድ የሆነባቸው” ብሎ ራሱን እንደ ሊቅ ሌላውን ደግሞ እንደ አላዋቂ አድርጎ የሌሎቻችንን “አርጋኖን ማለት ኦርጋን ማለት አይደለም” የምንለውን ሰዎች ዕውቀት ለማንኳሰስ ሞክሯዋል። ይህ ግለሰብ አዋቂ መሆኑ እንዳለ ይሁንና የቤተ ክርስቲያኒቲ ቋንቋ ባዕድ የሆነባቸው እነማን ናቸው? እኔ እስከሚገባኝ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቋንቋ ባዕድ የሆነባቸው መገለጫቸው ኦርጋን የሚለው በግድ አርጋኖን ከሚለው ቃል የወጣ ነው የሚሉ ሰዎች መሆናቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። ሊቁ አለቃ አያሌው ታምሩ፣ ሌሎችም ሊቃውንት ስለዚህ የሰጡትን መልስ አዳምጦ የቤተ ከርስቲያኒቱ ቋንቋ ለማን ባዕድ እንደሆነ መመልከት ይቻላል።፡ እንዲሁም ስለ ኦርጋንና አርጋኖን ልዩነት ከዚህ ቀደም ስላብራራሁ ተመልሼ አልገባም። ግን ይገርማል!
          2ኛ. ሌላኛው ተናጋሪ ይቀጥላል። ሎስ አንጀለስ ላይ ላለፉት ዐርባ ዓመታት በኦርጋን ማስደለቁን እንደ ትልቅ ጀብዱ ከገለጸልን በኋላ እርስ በእርሱ የሚጋጭ በሕግ ቋንቋ ፋላሲ (Fallacy) የሆነ አንድም ተጨባጭነት የሌለው “ማኅበረ ቅዱሳን ደም አፍሳሽ ነው” የሚል ፍሬ ከርስኪ የሆነና እልህ የተሞላበት፣ ከግል ጥላቻና ስሜት ያልጸዳ ንግግር አሰምቶናል። ትልቁ ያቀረበው ማስረጃ “እኔ ምስክር ነኝ” የሚል ነው። ይህ ደግሞ ከመግረምም አልፎ ያስቃል። ይሄ እኮ በኮንፍረንስ ውስጥ ያለውን ሰው መናቅ ነው። እንዴት አንድ ሰው ራሱ ከሳሽ ሆኖ እራሱ ምስክር ይሆናል? ይቀጥልና አሜሪካ ያለውን ሰው “ሐረር ሂዱና ጠይቁ” ይለናል። ይሄ ደግሞ ለበጣ ነው። የሚገርመው ግን ሐረር መሄድ ሳያስፈልግ ይኸው ግለሰብ ራሱ በአንደበቱ ፕሮቴስታንት እንደነበረ እና ይሄም ድርጊቱ ዘላለም እንደሚያሳፍረው በራሱ አንደበት ተናግሯል። ይህ ሰው በየንግግሩ መሀከል “የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ይከበር” ይላል። በጣም ጥሩ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ይከበር ከተባለማ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚለው “ከሃይማኖት ወጥቶ የተመለሰ ሰው አስቀድመው ሥልጣነ ክህነት ከነበረው ወደ ዝቅተኛ ማዕረግ ይውረድ” ነው የሚለው። (ፍትሐ ነገስት አንቀጽ 45) ታዲያ እነፓስተር ፓስተርነታቸውን ጥለው ሲመጡ ዲያቆን ነበሩ። ወደ ዝቅተኛ ማዕረግ ማለት ደግሞ ምዕመን ማለት ነው። እርሱ ግን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ተላልፎ የተሰጠውን ቀኖና እንኳን ሳይፈጽም ወደ አሜሪካን በመምጣት የኦርጋን አቀኝቃኝ በሆኑት ሊቀ ጳጳስ አማካኝነት “ቅስና” ተሰጥቶኛል ይላል። እንግዲህ እግዚአብሔር ያሳያችሁ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ ሰው እንዴት ሥለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራል? በጣም ይገርማል!
          3ኛ. ሶስተኛው ተናጋሪ ከዴንቨር የገባው ደግሞ ከአልበሙ ውስጥ ለማስታወቂያ አንድ “መዝሙር” ካሰማን በኋላ ኦርጋንን አሞካሽቶና አወድሶ ከቀድሞ ጀምሮ ሲዘመርበት እንደቆየና አሁን ግን በአንድ ማኅበር አማካኝነት እንደቆመ አጽንኦት ሰጥቶ ነገረን። በጣም ጥሩ! እዚህ ጋር እኔ ያልገባኝ የዚህን ያህል ኦርጋን በዚህ ሰው ልቡና ውስጥ ይህን ያህል ቦታ ከነበረውና አስፈላጊ ዕቃ  ከነበረ ምነው እስከዛሬ ድረስ በየዓመቱ በሚያሳትመው ካሴት ውስጥ በኦርጋን አልዘመረም? ሌሎች ዘማርያን ከጥንት ጀምሮ ከተቀሙበት ምነው እርሱስ ሳይጠቀምበት ቀረ? አሃ! “ይቅርታ” ላካስ ካሴቶቹን ያሳተመው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ስለ ኦርጋን የተገለጸለት ወይም በእነርሱ ቋንቋ የበራለት አሜሪካ ከመጣ በኋላ መሆኑ ነው። በጣም ይገርማል!
          ለሁላችንም አንድ ጥያቄ፦ በኮንፍረንሱ ውስጥ “በተደጋጋሚ “አባቶች አባቶች” ሲባል ሰምተናል።፡በብዙ ከተጠሩት አባቶች ግን የሰማነው የአንድ ወይም የሁለት ሊቀ ጳጳስ ድምጽ ነው። የሌሎችን “አባቶች፣ አባቶች” የምትሏቸውን ድምጽ አንድም ቦታ አልሰማንም። ታዲያ የት አሉ? እስቲ ከአባ መልከጼዴቅ ውጪ የሌሎችን ድምጽ እንስማ። በተለይም በኦርጋን እንድትዘምሩ የውጪ “ሲኖዶስ” እንደወሰነ ደጋግማችሁ ነግራችሁናል። “እመሰ አማን ጽድቀ ትነቡ” እንዳለ ቅዱስ ዳዊት እውነት ከሆነ ርዕሰ መንበሩ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ናቸውና በሚቀጥለው ቴሌ ኮንፍረንስ አስገቡና ውሳኔውን ያሰሙን። መቼም አቡነ መልከጼዴቅ አይደሉም ፓትያርኩ። “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንደተባለው በተለመደው ቴክኒክ ፓትያርክነቱ ካልተጠለፈ (hijack) ካልተደረገ ማለቴ ነው። ይህን ካደረጋችሁ እውነትም የእናንም “ሲኖዶስ” ወስኗል። “የሲኖዶስ” ውሳኔ ከሆነ ደግሞ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ይደረጋል ማለት ነው። ካለበለዚያ ግን … ይቆየን።

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

5 comments:

 1. Kale hiwot yasemalene Yemigerem eyeta new

  ReplyDelete
 2. መጋቢ ጥበበ አምላከ እስራኤል በድሜ በጤና ይጠብቅልን…… ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን በጋራ ልንጠብቅ ይገባናል ልክ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ካሉ የቤተክርስቲያን ልጆች ጋር በመሆን….

  ReplyDelete
 3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን::ክፍል ሁለትን በጉጉት እንጠብቃለን::

  ReplyDelete
 4. bewushet layi yetemeserete mekelakel yetim ayaderisim. yesidib gubaeyachew betselot mejemerun ene erase teketatiyewalehu. silezih yih akahed enesu endiaterfu enji egna anashenifibetim. benegerachin layi bezia kirkr ashenafiwoch enesu nachew. leziam yimesilal yemiashenfubatin mertew wotirew yetekerakeru.
  lenegeru behulutum bekul yesidib afi yehonu temelikichalehu.

  ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤