Thursday, March 10, 2016

ቅ/ሲኖዶስ: በመላው ገዳማት፣ አድባራትና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ዐወጀ፤“ባሳለፍናቸው ሳምንታት ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖችን በመሪር ሐዘንና በጸሎት እናስባቸዋለን”


Synod declaration yek2008aየካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
ኅሡ ሰላማ ለብሔር እስመ በሰላመ ዚአሃ ይከውን ሰላምክሙ፤
(የአገርን ሰላም እሹ ፈልጉ የአገራችኹ ሰላም የእናንተ ሰላም ነውና)
 የተወደዳችኹ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የሀገርና የወገን ፍቅር ያለው ሕዝብ፥ ሰላም ከእግዚአብሔር መኾኑን ያውቃል፤ ሰላም ለሰው ልጆች ከማናቸውም መሠረታውያን ፍላጎቶች በላይ ተቀዳሚ ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ተቻችለውና ተረዳድተው የሚኖሩባት የዓለም ምሳሌ ናት፡፡ ይህን ዓለምን የሚያስደንቅ ገጽታችንን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲከተለው ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የተወደዳችኹ ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያውያት፤
ኢትዮጵያ አህጉረ ሰላም(የሰላም አገሮች) ከሚባሉት ከዓለም አገሮች አንዷ ስትኾን በአኹኑ ጊዜ በአንዳንድ ክልሎችና ከተሞች የሚታየው አለመረጋጋት ኹሉንም የሚያሳሳብ ኾኖ አግኝተነዋል፡፡
ከዚኽም ጋር ባለፍናቸው ሳምንታት በተከሠተው ያልተጠበቀ ችግር፡-
  1. በአንዳንድ አካባቢ የሰው ሕይወት ሲጠፋ፤ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ፤ የንግድ ተቋማት፣ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ሲወድም፤ የሕዝባችን የዕለት ከዕለት ኑሮ ሲናጋ ኹሉም ኅብረተሰብ የችግሩ ተጠቂ ኾኗል፤ የዚኽ ዓይነቱ ድርጊት በዚኽ ኹኔታ ከቀጠለ የሕዝባችን ህልውናና የትውልዱም የወደፊት ዕድል አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡
  2. ባሳለፍናቸው ሳምንታት በተከሠተውኹኔታ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች በመሪር ሐዘንና በጸሎት እናስባቸዋለን፡፡ ስለዚኽ ኹላችሁም ልጆቻቸን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ሳትሉ ችግራችኹን ሰላማዊ በኾነ መንገድ ለሚመለከተው እንድታቀርቡ፣ መንግሥትም የሕዝቡን ችግርና ሰላማዊ ጥያቄ በመገንዘብ መፍትሔ በመስጠትና ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን የዕለት ከዕለት ጥረት እንዲቀጥልበት በቤተ ክርስቲያናችን ስም እናሳስባለን፡፡
  3. ሕዝባችንና ሀገራችን በረኀብ፣ በድኅነትና በበሽታ ቸነፈር በተቸገረበት ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት መሠረታዊ ወደኾነው የልማት የሰላምና የድርቅ ጉዳይ በማተኮር መልስ ሰጭ መኾን ይገባዋል ብለን በጽኑ እናምናለን፡፡
  4. ወገኖቻችን ሆይ፣ በአኹኑ ጊዜ የወቅቱ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ(ብሎገሮችና የፌስቡክ) ተጠቃሚዎች በሙሉ ኢትዮጵያውያን ከሞያችኹ ከዕውቀታችኹ ተጠቃሚዎች የመኾን ምኞታቸው የላቀ ነው፡፡ ኾኖም መልካሙንና ለዕድገት የሚያግዛቸውን ዕውቀት እንጂ ኅብረተሰቡን የሚለያይና የሚያራርቅ መረጃ(ኢንፎርሜሽን) ዕለት ዕለት ብታስነብቡት ትርፉ መራራቅን እንጂ መቀራረብን፤ መለያየትን እንጂ መግባባትን አያመጣም፤ ከዚኽ አንጻር የእናንተም ጥረትና ድካም ከንቱ ኾኖ ይቀራል፡፡ በመኾኑም የተከበረ ዕውቀታችኹን፣ ሞያችኹን፤ ለሕዝባችን ፍቅርና አንድነት፤ ለሀገራችን ሰላምና ዕድገት እንድታውሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትጠይቃለች፡፡
የተወደዳችኹ ኢትዮጵያውያን፤
ተቻችሎና ተረዳድቶ የመኖር የተቀደሰ ነባር ባህላችንን የሚያጎድፍ ማናቸውንም አስተሳሰብና እንቅስቃሴ በአንድነት መቋቋም እንደሚገባ አበክረን እየገለጽን፣ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ወገኖቻችን በሙሉ፣ በተለይም አገር ተረካቢ ትውልድ የኾናችኹ ወጣቶች፣ ሁከትና ብጥብጥን ከሚያስከትሉ መጥፎ ድርጊቶች እንድትቆጠቡ፤ ለሀገር ሰላምና ልማት ጠንክራችኹ እንድትቆሙ በልዑል እግዚአብሔር ስም አጥብቀን እያሳሰብን በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የሀብትና የንብረት ውድመት፣ በተለይም የሕዝብ መገልገያ የኾኑ የእምነት ተቋማት መቃጠል የተሰማንን ሐዘን እንገልጻለን፡፡
ይልቁንም ከኹሉም በላይ ኹሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር አምላካችን፤ ለኢትዮጵያ ለሀገራችን ሕዝቦች ሰላሙን፣ ፍቅሩን፣ አንድነቱን ይሰጥልን ዘንድ፤ ድርቁን ረኀቡን አስታግሦ መጪው ጊዜ ዝናመ በረከቱን ይሰጠን ዘንድ በያዝነው በዐቢይ ጾም ሱባኤ ጸሎተ ምሕላ በመላ ሀገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ 
የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.
አዲስ አበባ

Source: haratewahido  
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤