Saturday, April 16, 2016

በአብረንታንት ዋልድባ የመጋቢት መድኃኒዓለም ተሳላሚዎች በታጣቂዎች ተዘረፉ

መቆየት ጉድ ያሰማል
·         ለመጋቢት መድኅኒዓለም ክብረ በዓል የመጡ ምዕመናን በመንግሥት ታጣቂዎች ንብረታቸው ተዘርፏል
·         ዓመታዊው የአበረንታንት መድኅኒዓለም ክብር እጅግ በጣም የሚታወቅ እና በርካታ ምዕመናን በሚመጡበት ጊዜ ትግርኛ ተናጋሪ ታጣቂዎች የመልቃይት ታጣቂዎችን እንፈልጋለን በማለት ቀን በቀን ምዕመናን ሲንገላቱ፣ ሲዘረፉ፣አድዳንዱም ሲደበደቡ ነበር
ባለፈው የመድኅኒዓለም ክብረ ለማክበር ወደ ዋልድባ አበረንታንት ሲጓዙ የነበሩ በርካታ ምዕመናን እናቶች፣ አባቶች፣ ወንድሞች እና እህቶች ትግሪኛ ተናጋሪ በሆኑ የመንግሥት ታጣቂዎች በሆኑ ሰዎች መንገድ በመጠበቅ በርካታ ምዕመናን ሲያንገላቱ እና ሲያስጨንቁ እንደነበር የዓይን እማኞች ገልጸዋል፣ እነዚህ ሰዎች የመንግሥት ተወካዮች ነን፣ የምንፈልገውም የወልቃይት ታጣቂዎችን ነው በማለት የሚመጣውን ምዕመን በሙሉ ከላይ እስከ ታች በመፈተሽ በእጃቸው የገባውን ገንዘብ፣ ካሜራ፣ የእጅ ስልኮችን ጨምሮ ከምዕመናን ላይ በመንጠቅ ሲወስዱ እና ምዕመናን ሲያንገላቱ እንደነበሩ በወቅቱ በስፍራው ከነበሩ እማኞች ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸውልናል።
ዛሬ ዛሬ የታላቁን የወልድባን ገዳም እናንተ የትግራይ ተወላጆች አይደላችሁም፣ ይሄ የትግራይ መሬት ነው በማለት በበርካታ ገዳማውያን ላይ እና ምዕመናን ላይ በሙሉ ብዙ መከራ ሲያደርሱ እና ሲያሰድዱ እንደነበር ለበርካታ ጊዚያት እኛም በድኅረገጻችን ለምዕመናን ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል፥ የእስከ ዛሬውም በግልጽ ባልሆነ ጉሰማ እና በተለያዩ ዘደዎች በመጠቀም በተለይ ገዳማውያን አባቶችን እናንተ ወደ ክልላችሁ ተመለሱ በማለት ብዙዎችን ሲያሰድዱ እና ሲያስሩ ሲገርፉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። እነዚህ እምነት የሌላቸው አሪዎሳውያን እስከ ዛሬ ባለው በተለያዩ የገዳሙ አባቶች እና መነኩሳይት ላይ ሲያደርሱት የነበረው ይህ ነው የማይባል ግፍ እና በደል ሲፈጽሙ መቆየታቸው ሳያንሳቸው ዛሬ ደግሞ እምነቱን፣ እና በረከት ፍለጋ የመጣውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት አማኞችን በእንዲህ አይነት መልክ ቀን በቀን፥ በጠራራ ጸሐይ መዝረፍ እና ማንገላታት ይቅርታ የማያሰጠው በደል እንደሆነ ማናቸውም በወቅቱ በደል ከደረሰባቸው በአጠቃላይ መላው ምዕመናን በመላው ዓለም የሚገኝ ሁሉ የሚስማማት ጉዳይ ይመስለናል።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማት፣ ታሪካዊ እና ትላልቅ የበረከት አድባራት፣ የጥምቀት እና የመስቀል ቦታውች፣ የቤተክርስቲያን አጸድ ሳይቀር በዚህ መንግሥት የቤተክርስቲያኒቱ ቦታዎች እየተወሰዱ ለባለሃብት ይቸበቸባሉ፣ ከዓለም ርቀው በገዳም ተከልልው የተቀመጡ ገዳማውያን ሳይቀሩ በዚህ መንግሥት ይሄ ነው የማይባል ግፍ እና እንግልት ሲደርስባቸው እንደነበር እና እስከ አሁን ድረስም የግፍ በደላቸው እንደቀጠለ እንደሆነ ለማንም ግልጽ እና የአደባባይ ምሥጢር ነው። ላለፉት ሃያ እና ሃያ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል እና እንግልት እራሱ የሰማይ እና የምድር ፈጣሪ መድኅኒዓለም በሚያውቀው የሰው ልጅ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ጥቂቱን እንጥቀስ ከተባለ በርካቶች ናቸው ለናሙና ያህል ግን በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ግፍ ነገር ግን ሰሚ ያላገኙ ተመልካች የተነፈጋቸው በርካቶች ናቸው ነገር ግን ዋና ዋናዎቹን እንጥቀስ
1) የደብረ ወጋግ አሰቦት ገዳም በተደጋጋሚ የእሳት ቃጠሎ መነሳቱ፥ ገዳማውያኑ መኖር አልቻልንም ብለው አቤቱታ ለክልሉ መንግሥት ተወካዮች ቢያቀርቡም ሰሚ አለማግኘታቸው፥
      2)   ታሪካዊው የደብረ ከዋክብት የዝቋላ አቦ ገዳም ባሉ ነዋሪዎች እንዲሁም በአንዳንድ ነውጠኛ ነዋሪዎች በተነሳ የእሳት ቃጠሎ፣ የቅዱስ አባታችን የአቡዪበረከታቸው ተጨምሮ በምዕመናን እርዳታ ቃጠሎው ለመጥፋት መቻሉ፥ የመንግሥት ተወካዮች የቤተክህነቱም ተወካዮች “ቃጠሎ በማንኛውም ጊዜ ሊነሳ የሚችል ነገር ነው፥ ስለዚህ ተረጋጉ” የሚል መልስ ለምዕማናና ለገዳማውያኑ መልስ መሰጠቱ፥
      3) በሃይቅ ደቃ እስጢፋኖስ ገዳም በተደጋጋሚ እሳት እያስነሱ በርካታ የታሪክ መዛግብትን እና ቅርሶችን ንብረቶችን ለመዛረፍ እና ለማዛረፍ እንዲህ አይነት አደጋ ሲደርስ መንግሥት ምንም አይነት ምርመራም ሆነ ክትትል ሳያደርግ በዝምታ መቀመጡ የክልሉ መንግሥትም ምንም መልስ አለመስጠቱ፣ የሚደርሰውንም ተከታታይ አደጋ መርምሮ የጉዳዩን ፈጻሚዎችን ለፍርድ አለማቅረብ፥
      4) በወልቂጤ ወረዳ የእናታችን የቅድስት ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን በመግንሥት ፈቃድ እንዲፈርስ በፍርድ ቤት መታዘዙን፣ ብሎም የአካባቢው ነዋሪዎች ቀን በቀን በእሳት በማቃጠል ንብረት ማውደማቸውን ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍርድ የሚያቀርብ መንግሥት መጥፋቱ ለተበዳዩችም ምንም መልስ አመስጠት አለመቻሉ፥
      5)  በደብረዘይት፣ በባሕር ዳር፣ በፍሰሐ ገነት አርባ ምንጭ፣ በአዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ እንዲሁም በተለያዩ የሃገራችን ክልሎች እና ከተሞች መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ሕዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓላትን እና የመስቀል በዓልን ለማክበር የሚጠቀምበትን ቦታ ሆን ተብሎ በሃይማኖታችን ላይ ቀጥተኛ የሆን ጥቃት ለመፈጸም ታስቦ በሚመስል መልኩ በርካታ ቦታዎች በመንግሥት በመወሰት ለባለሃት በመቸብቸብ የገንዘቡም ተጠቃሚዎች እራሳቸው ጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ መሆን በቤተክርስቲያን ላይ በርካታ በደሎችን ፈጽመዋል፥
     6) ያለ ቤተክርስቲያን እና ያለ ምዕመናን ፍላጎት በአጠቃላይ በማስገደድ ጳጳሳትን ሾመውልናል፣ ፓትርያሪክም ሾመውልናል፥ የቀራቸው ነገር ቢኖር ቀድሰው ማቁረብ ብቻነው እሱንም ስላልቻሉ ብቻ ነው እንጂ እናድርግ ሳይሉ እንደማይቀሩ የታመነ ነው፥ 
      7) ታሪካዊና ቅዱሳን ገዳማት፣ እና አድባራት በእነዚህ እምነት የለሽ የመንግሥት ሰዎች ቦታዎቻቸው ተወስዶ (ተዘርፎ) “ለልማት” በሚል ሰበብ በርካታ ቦታዎች እና ይዞታዎች ተዘርፈዋል በውስጡ የሚገኙም መናንያን ከአምላካቸው እንዳይገናኙ የጸሎት ቦታቸው ተወስዷል እነሱም ተባረዋል ከነዚህ ገዳማት መካከል ቅዱሱ የዋልድባ ገዳም አንዱ ሲሆን በምዕራብ ጎንደር የታወቀው እድሜ ጠገቡ የመድኅኒዓለም ገዳም ቦታው ተወስዶ ለሱዳን ተሰጥቷል፣ የዳገት እየሱስ ገዳም በታጣቂዎች በቃጠሎ ወድሟል፣ የጎንደር የታሪክ መዛግብት ሆን ተብሎ በእሳት ተቃጥሏል እረ ስንቱ ቤት ይቁጠረው . .  .  
           8) በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች አዲስ አበባን ጨምሮ የጸሎት ቦታዎች አድባራት፣ ቤተክርስቲያናት በባለ ጊዜው የመንግሥት ሰዎች በግድ በትራክተር ቤተክርስቲያናት ፈርሰዋል አቤቱታ የሚያዳምጥ የመንግሥት መዋቅርም የለም በአጠቃላይ ከላይ እስከ ታች የሕዝቡን አቤቱታ የሚሰማ ሰው ከመጥፋቱ የተነሳ ያሉት የቤተክርስቲያን ተወካዮች እንኳን “ምን ማድረግ ይቻላል” በማለት ዝም ነው ምዕመኑም ዝም ነው . . . ቤተ እግዚአብሔርም ሲፈርስ ዝም ነው እስከ መቼ ይሆን ዝምታችን በዚህ ከቀጠለስ ምን ሊመጣ ይችላል?
      9)በርካቶች የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ለቤተክርስቲያናችን የወደፊት ተተኪዎችን በማፍራት ትልቅ አስተዋጽዖ በማድረግ የሚገኙትን ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠላቶችን በማስገባት አስተምህሮውን በመበረዝ የሃገሪቱን ባሕል፣ ቅርስ፣ እና ስነ ምግባር በማጥፋት ይህ ነው የማይባል የሚያደርሱት እነዚህ የመንግሥት አካላት መሆናቸው ለማንም የተሰወረ አይደለም፥ ለዚህም ደግሞ ማሳያው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቤተ ክህነት ሥር ከሚገኙት 22 መምሪያዎች ውስጥ 19 ወይንም ከዚያ በላይ የሚሆኑት መምሪያዎች የተያዙት በእነዚሁ የመንግሥት ካድሬዎች፣ ጎሰኞች፣ ከእለት ጉርሳቸው ሌላ ለቤተክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ የወደፊት እጣ ፈንታ ለአንድም ቀን አሳስቧቸው የማያውቁ ግብረ በላዎች መሆናቸው የታወቀ ነው፤
እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከላይ እስከ ታች የተወረረችው በእነዚህ ግብረበላዎች እና ቀማኞች በመሆኑ እምነቱን እንኳን በነጻነት ለማምለክ፣ በረከት ለመቀበል ወደ ተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ወደሚገኙት ገዳማት እና አድባራት የሚሄደውን ምዕመን በመንገድ በመጠበቅ ብዙ እንግልት እና ዝርፊያ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ መመልካት ይቻላል፥ አዎ ዛሬም እንደበፊት የክልሉ መንግሥትም፣ የሰሜን ጎንደርም ሃገረ ስብከት ወይንም በአጠቃላይ ቤተክህነቱም በአጠቃላይ የፌደራል መንግሥቱም በምዕመናን ላይ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ እንግልት ተመልክተው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው እንበፊቱ ዝም ብለዋል። ምዕመናን በሃገራቸው በነጻነት ወጥተው አምልኮታቸውን ፈጽመው መመለስ ከማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል ለዚህም የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካላትም ሆኑ የሃገረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከማቅረብ እና መፍትሄ ከማሰጠት ይልቅ “እኛ አልሰማንም፣ ዓይናችንን ግንባር ያደርገው” ምህላቸውን ቀጥለውበታል፥ ምዕመናንስ እስከ ማቼ እምነታቸውን በነጻነት ማምለክ እንደማይችሉ፣ እስከ መቼ በነጻነት በሃገራቸው የተለያዩ ገዳማት እና አድባራት በመሄድ እምነታቸውን ፈጽመው በሰላም መመለስ እንደማይችሉ፣ መንግሥትስ እስከ መቼ የዜጎች እኩልነት፣ የዜጎች በነጻነት የፈለጉትን የማምለክ ነጻነት፣ የዜጎች በነጻነት ወደ ፈለጉበት የሃገራቸው ክፍል ደርሶ የመመለስ ነጻነት ተነፍገው ይኖራሉ? ይሄ ማለት ደግሞ ምዕማን ወይንም የሃገሪቱ ዜጎች እነዚህን የተመለከቱትን እውነታዎች በነጻነት ማድረግ እስካልቻሉ ድረስ የግድ ነጻነታቸውን ወደ ሚፈልጉበት መንገድ መሄዳቸው አይቀሬ ነው፣ ከዚህ በተጨማሪ በዳዮች፣ ቤተክርስቲያናትን በጠራራ ጸሃይ የሚያቃጥሉት፣ ምዕመናንን የሚያንገላቱት፣ የዜጎችን መብት በመንፈግ የሚኖሩትን ግብረበላዎች በአስቸኳይ ለፍርድ በማቅረብ ፍርዳቸውን እንዲቀበሉ እንዲያደርግ የማንኛውም ምዕመን ፍላጎት እንደሆነ የታመነ ነው። ምክንያቱም በአንድ ሃገር ላይ አንዱ ነዋሪ ሌላው አኗኗሪ የሚባል የመደብ ልዩነት እስከሌለ ድረስ የሁሉም ዜጎች መብት ተጠብቆ በእኩልነት የማምለክ፣ ተዘዋውረው እምነታቸውንም የመፈጸም መብታቸውም እንዲከበርላቸው የማንኛውም ሰላም ወዳድ ማኅበረ ሰብ ፍላጎት እንደሆነ የእኛም ፍላጎት እንደዚያው ነው።
ይቆየን

ቸር ይግጠመን
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

1 comment:

  1. ዛሬም ዝም ብለናል ነገም ዝም ነው ስለዚህ አንድ ቀን አባይ ጸሐዬን በመቅደስ ልብሰ ተክህኖውን ለብሶ በፓትርያሪክ ማትያስ መሪነት እስክናያቸው ድረስ ዝም ነው በኃላስ? ምን ልንል ነው ለማንኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በሙሉ እነዚህ ለሃገርም ለወገንም ለእምነታችንም የማይጠቅሙንን ነቀርሳዎች ተባብረን ወደ መጡበት በጥሻ ወርውረን ነጻነታችንን፣ እምነታችንን እንዲሁም የሃገራችንን አንድነት እና ልዕልና እናስከብር ብዬ እጠይቃለሉ።
    ዋልድባዎች እግዜር ይስጣችሁ ለምታደርጉት ነገር ሁሉ በርቱ ከጎናችሁ ነን፣ እምነትን መጠበቅ ሃገርን መጠበቅ ማለት ነው

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤