Thursday, June 16, 2016

በጅማ ሃገረ ስብከት በሰኮሩ ወረዳ ቁንቢ ቀበሌ ውስጥ የሚገኘው ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ላይ በአክራሪ እስልምና አራማጆች የደረሰው ሰቆቃ

" አቤቱ፥ የሆነብንን አስብ"
(ሰቆቃው ኤርምያስ 5:1)
በጅማ ሃገረ ስብከት ሰኮሩ ወረዳ ቁንቢ ቀበሌ ውስጥ በሚገኘው ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ–ክርስቲያን በ08/10/2008 ዓ·ም ንጋት ላይ ኪዳን ለማድረስ ከሄዱት ምዕመናን መካከል ወሰንየለሽ ፍቃዱ እና ወለላ ፍቃዱ የተባሉ እህትማማቾች ላይ "ጀሀድ" በሚል አላማ አራት ግለሰቦች መላ ሰውነታቸውን በጥቁር ልብስ በመሸፈን ከፍተኛ ጥቃት አድርሰዋል።ይህ የግድያ ሙከራ የተደረገው ከ20 የማይበልጡ ክርስቲያን አባውራ በሚኖሩባት የቁንቢ ቅ/ሚካኤል ቤተ–ክርስቲያን የተፈፀመ አስከፊ ጥቃት ሲሆን ከአራቱ ጥቃት አድራሾች ሦስቱ ባዘጋጁት መኪና ወደ ጅማ መስመር ያመለጡ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለፁልን "መሐመድ ሰኒ" የተባለው አክራሪ በስፍራው የነበሩ ግለሰቦች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ በቁጥጥር ስር ውሏል።አክራሪዎቹ ጥቃት ያደረሱበት የስለት መሳሪያ በአብዛኛው የአረብ አገራት ላይ በስፋት የሚታይ ሲሆን መርዛማ መሳርያ መሆኑም ታውቋል።ክርስቲያኖችን ማጥፋት አላማቸው አድርገው የመጡት አክራሪ ቡድኖች ክርስቲያኖችን በሰይፍ ሲያርዱ በዝምታ መመልከት ያላስቻላቸው የአካባቢው ሙስሊም ወንድሞች በመሀል በመግባት በሚያገላግሉበት ወቅት ሁለቱ ሊጎዱ ችለዋል።ጉዳቱ ከደረሰባቸው ከሁለቱ እህትማማቾች አንዷ የሆነችው ወሰንየለሽ ፍቃዱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን በአሁኑ ሰአት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በህክምና ላይ ትገኛለች።የኢ/ኦ/ተ/ቤተ–ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስን ጨምሮ የተለያዩ ብፁአን አባቶች እንዲሁም ብዛት ያላቸው ምዕመናን በጥቁር አንበሳ በመገኘት እህታችንን በመጠየቅ እና በአደጋው የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን እየገለፁ ይገኛሉ። 
በዚህ መጠነ ሰፊ በሆነው ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች፣ ምዕመናን እና ምዕመናት ብሎም በጅማ ሃገረ ስብከት በተፈፀመው የፅንፈኛ አክራሪ ቡድን የመግደል ሙከራ ዋልድባን እንታደግ (ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት)ልባዊ ሀዘናችንን እየገለፅን አምላከ ቅዱስ ሚካኤል ለተጎዱት እህትና ወንድሞች ፍፁም ምህረትን እንዲሁም ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን እንዲሰጥልን እናመኛለን!!!

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

Thursday, June 9, 2016

የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ እስከ ሰኔ 30 የዕጩዎችን ዝርዝር ያቀርባል፤ የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል

Holy Synod00
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት፣ ላለፉት 16 ቀናት ሲያካሒደው የቆየውን የ2008 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ስብሰባውን ዛሬ አጠናቋል፡፡
ግንቦት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. የተጀመረው ጉባኤው፣ ዛሬ፣ ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋድ ላይ የተጠናቀቀው፣ ባለ17 ነጥቦች መግለጫ በማውጣት ነው፡፡
በቅዱስ ሲኖዶሱ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ መግለጫውን በንባብ ያሰሙት ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ምልአተ ጉባኤው ጠቀሜታ ባላቸው አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ማሳለፉን አስታውቀዋል፡፡
ከውሳኔዎቹ ዓበይት ነጥቦች መካከል፣ የአዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በምልአተ ጉባኤው የታመነበት ሲኾን፤ በዕቅዱ መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በአስረጅነት የሚገኙበትና ሰባት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉ ተገልጧል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው፣ ዕጩ መነኰሳቱን፥ መርምሮ፣ አጥንቶና አጣርቶ ውጤቱን እስከ ሰኔ 30 ቀን እንዲያቀርብ ተወስኗል፡፡ በዕጩነት የሚቀርቡት ቆሞሳትና መነኰሳትም፡-
  • ፈተናውንና መሰናክሉን ኹሉ አልፈው ዕውቅና ያገኙትን፤
  • በብሔር አቀፍና በዓለም አቀፍ ትምህርት የበሰሉትን፤
  • የወቅቱንም ችግር ይፈታሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸውንና የሚጣልባቸው መኾን እንደሚገባቸውም በመግለጫው ተዘርዝሯል፡፡