Thursday, June 9, 2016

የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ እስከ ሰኔ 30 የዕጩዎችን ዝርዝር ያቀርባል፤ የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል

Holy Synod00
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት፣ ላለፉት 16 ቀናት ሲያካሒደው የቆየውን የ2008 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ስብሰባውን ዛሬ አጠናቋል፡፡
ግንቦት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. የተጀመረው ጉባኤው፣ ዛሬ፣ ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋድ ላይ የተጠናቀቀው፣ ባለ17 ነጥቦች መግለጫ በማውጣት ነው፡፡
በቅዱስ ሲኖዶሱ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ መግለጫውን በንባብ ያሰሙት ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ምልአተ ጉባኤው ጠቀሜታ ባላቸው አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ማሳለፉን አስታውቀዋል፡፡
ከውሳኔዎቹ ዓበይት ነጥቦች መካከል፣ የአዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በምልአተ ጉባኤው የታመነበት ሲኾን፤ በዕቅዱ መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በአስረጅነት የሚገኙበትና ሰባት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉ ተገልጧል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው፣ ዕጩ መነኰሳቱን፥ መርምሮ፣ አጥንቶና አጣርቶ ውጤቱን እስከ ሰኔ 30 ቀን እንዲያቀርብ ተወስኗል፡፡ በዕጩነት የሚቀርቡት ቆሞሳትና መነኰሳትም፡-
 • ፈተናውንና መሰናክሉን ኹሉ አልፈው ዕውቅና ያገኙትን፤
 • በብሔር አቀፍና በዓለም አቀፍ ትምህርት የበሰሉትን፤
 • የወቅቱንም ችግር ይፈታሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸውንና የሚጣልባቸው መኾን እንደሚገባቸውም በመግለጫው ተዘርዝሯል፡፡በየሦስት ዓመቱ በሚደረገው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪጅ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ምርጫ ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል፡-
 • ብፁዕ አባ ዲዮስቆሮስ ሊቀ ጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
 • ብፁዕ አባ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ኾነው ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠዋል፡፡
በብፁዓን አባቶች ኅልፈት፣ ዕርግና እና ሕመም የተነሣ ከጠቅላላው አህጉረ ስብከት፣ ሊቃነ ጳጳሳት የሌሉባቸው በመብዛታቸው፣ በቋሚነት የሚሠሩ አባቶች እስከሚመደቡ ድረስ ተጨማሪ ምደባዎችን መስጠቱም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ሀ/በሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅና ሰሜን ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት
 • ለጊዜው በብፁዕ አባ ሙሴ፣ የደቡብ ምዕራብና የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ አህጉረ ስብከት ተደርቦ እንዲሠራ፤
ለ/በአውስትራልያ ሀገረ ስብከት
 • በብፁዕ አባ ኄኖክ፣ የምዕራብ ወለጋና የአሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
ሐ/የምሥራቅ አፍሪቃ ኬንያ እና ጅቡቲ አህጉረ ስብከት
 • በብፁዕ አባ ዳንኤል፣ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
መ/የምሥራቅ አፍሪቃ ሰሜን ሱዳንና ግብፅ አህጉረ ስብከት
 • በብፁዕ አባ ሉቃስ፣ በክልል ትግራይ ዞን ወልቃት ጸገዴ ሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ ኾኖ በተጨማሪም የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ሓላፊ ኾነው እንዲሠሩ፤
ሠ/ደቡብ ሱዳን ሀገረ ስብከት
 • በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የጅማ የኢሉባቦርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ ሲል ምልአተ ጉባኤው በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኗል፡፡
የብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ዕረፍት ተከትሎ ቀደም ሲል ምደባ ተደርጎበት የነበረውን የአርሲ – አሰላ ሀገረ ስብከትን ጨምሮ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ጥያቄ ላቀረቡ ብፁዓን አባቶችም ምደባዎች ተሰጥተዋል፡፡ በዚኽም መሠረት፡-
 • ብፁዕ አባ ያሬድ ሊቀ ጳጳስ፡- የኢትዮጵያ ሱማሌ ሀ/ስብከት ሥራን እንደያዙ በአርሲ ሀገረ ስብከት፤
 • ብፁዕ አባ እንጦንስ ሊቀ ጳጳስ፡- በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት፤
 • ብፁዕ አባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳስ፡- በደቡብ እና ምዕራብ አፍሪቃ ሀገረ ስብከት፤
 • ብፁዕ አባ እንድርያስ ሊቀ ጳጳስ፡- የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ሓላፊነቱን ሥራ እንደያዙ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ሓላፊ በመኾን ተመድበው እንዲሠሩ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
ስለ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶሱ የተወያየ ሲኾን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 50 መሠረት፣ ብፁዕ አባ ሕዝቅኤል በያዙት የሀገረ ስብከት ሥራቸው ላይ ደርበው እስከ ጥቅምት 2009 ዓ.ም. ድረስ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ ተስማምቷል፡፡
ስለ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አደጋ የመከረው ምልአተ ጉባኤው፥ ችግሩን በማስረጃ ለማጋለጥና በትምህርት ለመከላከል የሚያስችሉ ቋሚ ጉባኤያት በየደረጃው እንዲቋቋሙ ቀደም ሲል ያሳለፈውን ውሳኔ በማጽናት፣ የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ እስከ አኹን ድረስ ተከብሮና ተጠብቆ እንደኖረ ኹሉ፣ አኹንም ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው የመንፈሳዊና የማኅበራዊ አገልግሎት መዋቅር በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
ሌሎች የውሳኔው ዓበይት ነጥቦች፡-
 • የቅ/ሲኖዶሱን ዓመታዊ ሪፖርት በማዳመጥ፣ በውሳኔዎች አፈጻጸም ክትትል ይደረግ ተብሏል፤
 • የቃለ ዓዋዲው መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ፣ በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እንዲጸድቅ ተወስኗል፤
 • የቅዱስ ፓትርያርኩ እንደራሴ በምን ሕግ መሠረት እንሚመረጥ የሚያጠና አካል ተሠይሟል፤
 • ለአስተዳደሩ ቀልጣፋነትና ቅንነት፤ ለልማት አውታሮች ውጤታማነት ሠርቶ ማሠራት ይገባል፤
 • በውጭ አህጉረ ስብከት ካሉት ብፁዓን አባቶች ጋር ለሰላሙ አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል
*                    *                     *
 • በሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት፣ ዕጓለ ማውታን ማሳደጉና ማስተማሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል
 • በድርቅ ለተጎዱት ርዳታ እና የተፈናቀሉትንም ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያን ጥሪ አስተላልፋለች
 • ለኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት የሚያገለግል ሕንፃ ለመገንባት፣ ጠቅ/ጽ/ቤቱ ቦታ ያመቻቻል
 • ለሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት፣ መላው ኅብረተሰብ የድርሻውን እንዲፈጽም ቅ/ሲኖዶሱ አሳስቧል
 • በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ የተጎዱ መጽናናትና መረጋጋት እንዲያገኙ ቅ/ሲኖዶሱ ይጸልያል፤
የመግለጫው ሙሉ ይዘት ከዚኽ በታች ይመልከቱ  Holy Synod Ginbot2008Holy Synod Gin2008b
Source: https://haratewahido.wordpress.com/
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤