Sunday, September 18, 2016

የወቅቱ የሃገራችንን ሁኔታ በተመለከተ ከዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት የተሰጠ መግለጫ

                                         የወቅቱን የአገራችንን ሁኔታ በተመለከተ
ከዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት የተሰጠ መግለጫ

መግለጫውን በPDF ለማንበብቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ ህዝቦቿን በፍቅርና በባህል በማስተሳሰር ነፃነቷንና አንድነቷን ጠብቃ የኖረች በየትኛውም የውጪ ወራሪ ያልተንበረከከች ለአፍሪካና ለጠቅላላ የጥቁር ዘር ፋና ወጊ የሆነ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት አገር ናት በዚህም የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጉልህ አሻራ አላት ።ይህም  በውጪ አገር ጸሐፊዎች ሳይቀር ተመስክሮላታል።


ይሁን እንጂ ይህ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ታሪክ እንዲጠፋና የአገሪቱ አንድነት እንዲናጋ አዲስ ሕግ ተቀርጾና አዲስ ታሪክ ተፈብርኮ ወገኖቻችን በዘርና በጎሣ፣ በቋንቋና በመንደር ተከፋፍለው እንደጠላት እንዲተያዩና የመለያየትን መንፈስ እንዲያቀነቅኑ ሲደረግ ቆይቷል። አንዱ ወደ ሌላው ክልል ገብቶ እንዳይኖርና ሠርቶ እንዳይበላም ግልፅ የሆነ የቂም በቀል ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና የጥላቻ ሀውልት በማቆም ብዙዎችን ያሳዘነ እኩይ ተግባር በመንግሥት ካድሬዎች ሲፈፀም ሁለት አሠርት ዓመታትን አሳልፈናል። ሕዝቡ ግን ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለውና ፍፁም ሃይማኖተኛ በመሆኑ በካድሬዎቹ የልዩነት ስብከት ሙሉ በሙሉ ተጠልፎ ሳይወድቅ ፈተናውን ተቋቁሞ ሃያ አምስት ዓመታትን ዘልቋል። በአሁኑ ወቅትም ሕዝቡ የጥል ግድግዳውን እያፈረሰ ይበልጥ በአንድነቱ ላይ በማተኮር በሕብረት ቆሞ የብሶቱን ድምፅ በማሰማት ላይ ነው። ፍቅርንና አንድነትን የሚጠላው በአገሪቱ መሪዎች ልብ የጥላቻና የልዩነትን ዘር የዘራው ሠይጣን ደግሞ አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ ወገኖቻችንን ደም ለማፋሰስና እርስ በእርስ ለማጨራረስ የመጨረሻዎቹን ቀስቶች እየወረወረ ይገኛል። እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ኢሕአዴግ ሕዝቡን በዘርና በኃይማኖት ለመከፋፈል ያደረገው ጥረት እንዳይሣካ የአገር አንድነትና የሕዝቡ ፍቅር ተጠብቆ እንዲቆይ የተለያዩ አካላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን በተለይ ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶች፣ የግብረ ሠናይ ድርጅቶች፣ የሕዝብና የማኅበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የቤተክርስቲያን ማኅበራትና ወጣቶች በአጠቃላይ በተለያየ እርከን ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ይልቁንም ኢሳት ውጤት ያለው በጎ ተግባር የፈጸሙ ስለሆነ ከፍ ያለ ምሥጋና ሊቸራቸው ይገባል።
አብዛኞቹ የመንግሥት ባለሥልጣናት በጥላቻና በፍቅረ-ንዋይ የተነደፉ እግዚአብሔር የሰጣቸውን የሥልጣን ወንበር በእራሳቸው ጥረት ብቻ እንዳገኙ የሚቆጥሩ፣ የእግዚአብሔር ስም በፓርላማው ውስጥ ሲነሳ የሚስቁና የሚያፌዙ አላዋቂዎች ህዝቡን ብቻ ሳይሆን ጥንታዊት፣ ብሔራዊትና ሐዋርያዊት የሆነችውንና ለአገራችን ለኢትዮጵያ በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ አገልግሎቶችን በሁሉም አቅጣጫ ለሁሉም ወገን በእኩልነት ስታበረክት ዘመናት ያሳለፈችውን ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአማራ ዋሻ ናት ብሎ በአደባባይ ከመዝለፍ አንስቶ ገዳማቷን የመድፈር፣ ክብሯን የማዋረድ፣ ቅርሶቿንና ንብረቶቿን የማዘረፍና የማቃጠል፣ በዓውደ ምሕረቷ ግድያ የመፈፀምና ቤተ መቅደስ ድረስ ገብቶ የንጹሃንን ደም የማፍሰስ፣ ይዞታዋን የመንጠቅ፣ምዕመናኖቿን የማሸማቀቅና ሕልውናዋን የመፈታተን በርካታ ተግዳሮቶች ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ አድርሰውባታል።
ከዚህም በተጨማሪ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፮ ቁጥር ፲፰ ላይ እንደተጠቀሰው በጽኑ ዓለት ላይ የተመሠረተችውንና የገሃነም ደጆች ወይም የሰይጣን የግብሩ ፈጻሚዎች አይችሏትም ብሎ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረላትን ቅድስት ቤተ-ክርስቲያን አከርካሪዋን ሰብረናል የሚል ድፍረትና ትዕቢት የተሞላበት ቃል በመናገር  ሲያሳዝኗት ቆይተዋል። አቅሟን ለማዳከምና የምዕመናኖቿንም ቅስም ለመስበር ለዘመናት ተከባብረውና ተቻችለው የኖሩትን የሃይማኖት ተቋማት እርስ በእርስ በማጋጨትና አንዱን ልጅ ሌላውን የእንጀራ ልጅ አድርጎ በማቅረብና በማሰልጠን ቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነች ተከታዮቿ በሌሎች የሃይማኖት ተቋማት በተለያየ መልኩ ሲጠቁ ኖረዋል። እስከዛሬ ድረስም ይህ ሁኔታ ባለመቆሙ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህን መልኩን እየቀያየረ የሚመጣውን ፈተና በማስተናገድ ሐዘኗን ሁሉ ወደ ኃያሉ አምላክ ስታቀርብ ቆይታለች።
መዋቅሯን ለማዳከምና ሀብቷንም ለመዝረፍ በዘር ሐረጋቸውና በፖለቲካ አቋማቸው የተመለመሉ ካህናት ነን ብለው የቄሣርን ተግባር የሚያስፈጽሙ ምንደኞች ከላይ እስከ ታች የቤተ ክርስቲያኒቱን ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች እንዲይዙ ተደርጎ የመንግሥትን ፍላጎት እየተገበሩና ሀብቷን ያለከልካይ እየዘረፉ ይገኛሉ። በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መንፈሳዊነት ጠፍቶ ሥጋዊነት ብቻ እንዲሰፍን በብርቱ እየተሰራ ነው። ወጣቱ ትውልድም ለአገሩም ሆነ ለኃይማኖቱ ደንታ እንዳይኖረው፣ በውጪ ባሕል ላይ እንዲያተኩርና በአጉል ሱስ እንዲጠመድ ሁኔታዎች ሁሉ በሚገባ ተመቻችተውለታል። ይህ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚታየው መንፈሳዊነት የጎደለው ተግባርና ብልሹ የሆነ አሠራር ብዙ ወንድሞችና እህቶች ከቤተክርስቲያን እንዲርቁና እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗቸዋል። ስለዚህ እነዚህ ወገኖች ይህ የፈተናና የመከራ ዘመን አልፎ ቤተክርስቲያኒቱ ወደ ቀድመ ክብሯ እንደምትመለስ ተረድተው ወደ እናታቸው ቅድስት ቤተክርስቲያን ጉያ እንዲመለሱ በዚህ አጋጣሚ መልእክታችንን እናስተላልፍላቸዋለን።
ወደ ዋናው ነገር ስንመለስ በመንግሥት ባለ ሥልጣናትም ሆነ በተከታዮቻቸው ውስጥ ፈሪሃ እግዚአብሔር ባለመኖሩና ፍትሃዊ አሠራር በመጥፋቱ በአገሪቱ ላይ ሥርዓተ አልበኝነት እየተስፋፋ ይታያል። ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቡን በፍቅርና በአንድነት እንዲሁም በእኩልነት መምራት የሚገባው መንግሥት ሕዝቡን በዘርና በጎሣ፣ በቋንቋና በነገድ ከፋፍሎ  ከፍተኛ ሤራ እየሸረበና የጥላቻ ሐውልት እያቆመ አንዱን በአንዱ ላይ በጠላትነት በማነሣሣትና እርስ በእርስ በማጋጨት ወንድም ወንድሙን እንዲያጠፋና በጥላቻ እንዲተያይ ለሃያ አምስት ዓመታት የፈፀመው -ሰብዓዊ ድርጊት ሳያንሰው አሁን ደግሞ በየቦታው መብታቸውን ለመጠየቅ አደባባይ በወጡ ወገኖቻችን ላይ ማንም ሰብዓዊ ተፈጥሮ ያለው ሰው ሊያደርገው የማይገባውን ጭካኔ የተሞላበት የደም ማፍሰስ ተግባርና አሰቃቂ የሆነ የግድያ ወንጀል እንዲሁም የእስርና የማሳደድ ዘመቻ በአገሪቱ ላይ ባሰማራቸው ሠራዊቶቹ አማካኝነት በገፍ እያካሔደ ይገኛል።
ስለሆነም ይህንን እያየንና እየሰማን በዝምታ ለማለፍ የሚያስችል ሕሊና ስለሌለን ከዚህም ባሻገር አገር ከሌለ ሃይማኖት ሊኖር እንደማይችል ስለምናምን ከዚህ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ ለማውጣት ተገደናል።
በዚህም መሠረት፦
፩ኛታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልዕክቱ ምዕራፍ ፫  ቁጥር ፲፮ እና ፲፯ ላይ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ፣ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ። በማለት የጻፈውን መሠረት በማድረግ ተዋሕዶ ኃይማኖታችን ሰው በልዑል እግዚአብሔር አምሳልና አርአያ የተፈጠረ የእጁ ሥራ ክቡር ቤተ መቅደሱ እንደሆነ ታስተምራለች። በመሆኑም የልዑል እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የቅዱስ መንፈሱ ማደሪያና የድንቅ ሥራው መገለጫ የሆነውን ሰው ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ መግደል፣ ማጥፋት፣ ማሰቃየትና ማንገላታት እግዚአብሔርን መቃወም፣ ቤተ መቅደሱን ማፍረስ ስለሆነ በጽኑ እናወግዘዋለን።
፪ኛይህ በሰዎች ላይ ሊፈፀም የማይገባ አረመኔያዊ የሆነ የደም ማፍሰስ ተግባርና -ሰብዓዊ የሆነ የግድያና የእስር
ዘመቻ አገረ እግዚአብሔር በምትሰኘው ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ ሊፈጸም ቀርቶ ሊሰማ የማይገባ ሠይጣናዊ ተግባር በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም አጥብቀን እንጠይቃለን።
፫ኛክቡር በሆነው በሰው ፍጡር ላይ ይቅርና በእንስሳ ላይ እንኳን ሊፈጸም የማይገባውን አሰቃቂ ድርጊትና የግድያ ዘመቻ የፈጸሙና ያስፈጸሙ ባለ-ሥልጣናትም ሆኑ የሠራዊት አባላት ለፍርድ እንዲቀርቡ በአጽንዖት እንጠይቃለን።
፬ኛበአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በርካታ አካባቢዎች በመንግሥት ላይ እሮሮ የማያሰማና ብሶቱን የማይገልጽ ዜጋ እንደሌለ በገሃድ እየታየ ከመሆኑም በላይ መንግሥትም ለሕዝቡ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ሁኔታውን በማረጋጋት ፈንታ እጅግ ዘግናኝ የሆነ እርምጃ በመውሰድ የሰው ልጆችን ቀርቶ ሁሉን ቻይ የሆነውን ኤልሻዳይ ጌታ የሚያሳዝን -ሰብዓዊ ድርጊት እየፈጸመ ነው። ስለዚህ ሕዝቡን እንዲያገለግል የተቀመጠ መንግሥት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ዜጋውን እየጨፈጨፈ መቀጠል ስለማይችል የልዑል እግዚአብሔር የቁጣው መዓት ከመውረዱ በፊት ሥልጣናቸውን ሕዝቡ አምኖ ለሚወክላቸው የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች እንዲሁም በእውቀትና በምግባር ለሚታወቁ ምሁራን በማስረከብ እንደ ፈርዖን የደነደነ ልቡናቸውን አለስልሰው ቀሪ ሕይወታቸውን በንስሐ እንዲመሩ አበክረን እንመራለ

፭ኛሁሉን ነገር ማድረግ የሚችል ኃያሉ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በመሆኑ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ወገኖች በሙሉ ዘርና ቋንቋ፣ ኃይማኖትና ክልል ሳንለይ ሁላችንም በፍቅርና በአንድነት ጸንተን በመቆም አገራችንን ከመጠበቅ ጋር ወደ አምላካችን እየጮህንና እያለቀስን ለወገን የሚቆረቆርና ለፈጣሪው የሚታዘዝ እንደ ሙሴ ያለ ቅን፣ አስተዋይ፣ ደግና ኃይማኖተኛ መሪ እንዲሰጠን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አብዝተን እንድንጸልይና ሳንታክት እንድንለምን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
እግዚአብሔር አምላክ ቅድስት ሃገራችንን እና ሕዝባችንን በረደኤት ይጠብቅልን አሜን


    
ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተከርስቲያን እምነት ተከታዮች አንድነት
        ሰሜን አሜሪካ

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!


No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤