Friday, October 7, 2016

ከፍተኛ የብአዴን አመራሮች አቡነ አብርሃምን አነጋገሩ፤ “ሃይማኖታዊ ግዴታዬን ነው የተወጣኹት”/ብፁዕነታቸው/

 • በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ፣ መንግሥት ምን ማድረግ እንደሚገባው፣አባታዊ ምክር ሰጥተዋል
 • መናገር ያለብኝን ነው የተናገርኩት፤ ሃይማኖታዊ ግዴታዬን ነው የተወጣኹት፤” ብለዋል
  *               *               *
 • ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ሰው አላት ያሰኘና እውነትን መሠረት ያደረገ ወቅታዊ መልእክት ነው
 • ኹሉም ብፁዓን አባቶች፣ እንዲኽ፣ የኅሊናቸውን እውነት የሚናገሩበት ቀን ሩቅ አይኾንም!!
/አስተያየት የሰጡ ምእመናን/
Aba Abre
በብጹዕ አቡነ አብርሃም የባሕር ዳር፥ የም/ጎጃም፥ የአዊና የመተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ(አዲስ አድማስ፤ መታሰቢያ ካሳዬ፤ ቅዳሜ፣ መስከረም ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)
በባሕር ዳር ከተማ መስቀል ዐደባባይ በተካሔደው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኙትና የሰሞኑ አገራዊ የመወያያ አጀንዳ የኾኑት፣ የባሕር ዳር፣ የምዕ/ጎጃም፣ የአዊ እና የመተከል ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን፣ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ከትላንት በስቲያ አነጋገሯቸው፡፡
ከውስጥ ዐዋቂ ምንጮች ባገኘነው መረጃ መሠረት፤ የብአዴን ከፍተኛ አመራር ከኾኑት የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል፡- የፌዴራል እና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንና በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ህላዌ ዮሴፍ ናቸው፣ ሊቀ ጳጳሱን ያነጋገሯቸው፡፡ የመነጋገርያ አጀንዳቸውም፣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይና መደረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደኾነ ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
በባለሥልጣናቱ እና በብፁዕ አቡነ አብርሃም መካከል ስለተካሔደው ውይይት ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ባንችልም፣ ባለሥልጣናቱ፣ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ መንግሥት ምን ማድረግ እንደሚገባው አባታዊ ምክራቸውን እንዲሰጡ ብፁዕነታቸውን መጠየቃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ መስቀል ዐደባባይ በተከናወነው የደመራ በዓል ላይ፣ ብፁዕነታቸው በሰጡት ትምህርትና ቃለ ምዕዳን፣ “እንደ ፖሊቲካ አይደለም የምናገረው፤ እንደ ሃይማኖት ግን መናገር ያለብኝ ነገር አለ ብዬ አምናለኹ፣ መንግሥትንም በተመለከተ፡፡ በፖሊቲካ ከመነዘረው የእርሱ ጉዳይ ነው የሚኾነው፤ ምንጊዜም ችግር የመሪው እንጂ የተመሪው ሕዝብ አይደለም፤ የሕዝቡ ጥያቄ መመለስ አለበት፤ ወታደሩ ከዚኽ በኋላ የሰላምን ምላጭ እንጂ የመሣርያን ምላጭ መሳብ የለበትም፤ በመሣርያ ሰላም አይገኝም፤ አይተነዋል፤ እያየነውም ነው፤ ሊኾንም አይችልም፡፡ ጉልበታችን ሊያስመካን አይገባም፡፡ ሊያስመካን የሚችል ቢኖር መስቀሉ ብቻ ሊኾን ግድ ነው፤” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዐደባባዩ የመስቀልን በዓል ለማክበር የተሰበሰበው ምእመን፣ በሊቀ ጳጳሱ ንግግር በመደሰት ስሜቱን በእልልታ እና በጭብጨባ የገለጸላቸው ሲኾን፤ ብፁዕነታቸውም፣ “…ግዴለም፣ ግዴለም አጨብጭቡልኝ እያልኩ አይደለም፤ ዝም ብላችኹ ስሙ፤”  በማለት ጭብጨባም ይኹን ሙገሳ እንደማያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡ የደመራው ክብረ በዓል ሲጠናቀቅም፣ “በዐደባባዩ የተሰበሰበው ምእመን በሰላም ወደ ቤቱ መግባቱን ሳላረጋግጥ ከዚኽ አልሔድም፤” በማለት ሕዝቡን ወደየቤቱ በማስቀደም ነው ዐደባባዩን የለቀቁት፡፡
የብፁዕ አቡነ አብርሃም ንግግር በማኅበራዊ ሚዲያው የመነጋገርያ አጀንዳ ኾኖ ሰንብቷል፡፡ ሊቀ ጳጳሱ በክብረ በዓሉ ላይ ያስተላለፉት መልእክት፣ የብዙዎችን ስሜት በእጅጉ የነካና ለበርካታ የሃይማኖት አባቶች ትምህርት አርኣያ ሊኾን እንደሚችል፣ አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመውናል፡፡ መልእክታቸው፣ ምእመኑ በቤተ ክርስቲያንዋ ላይ የነበረውን ተስፋ የመቁረጥ ስሜት፣ በአስገራሚ ኹኔታ የቀየረና ኹሉንም የእምነት ተከታዮች አንድ ያደረገ መኾኑን የገለጹልን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑት አቶ ማስረሻ ተስፋሁን፣ “ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ሰው አላት ያሰኘና፣ እውነትን መሠረት ያደረገ መልእክት ነው፤” ብለዋል፡፡
“አቡነ አብርሃም፣ እንደ ሃይማኖት አባትነታቸው ማድረግ የሚገባቸውን ነገር ነው ያደረጉት፤ መገረም ካለብን የምንገረመው፣ እንደ ብፁዕነታቸው ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን ሳይጠብቁ የሃይማኖት አባቶች ነን፣ በሚሉት ነው፤” ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ፣ኹሉም የሃይማኖት አባቶች ለኅሊናቸውና ለሃይማኖታቸው አድረው እንዲኽ በዐደባባይ እውነትን የሚመሰክሩበት ቀን ሩቅ እንደማይኾን ተስፋ አደርጋለኹ፤” ብለዋል፡፡
HIs Grace Abune Abreham
ከሰሞኑ የአቡነ አብርሃም ንግግር ጋር በተያያዘ፣ በባሕር ዳር ከተማ ዙሪያ ግምገማ መካሔዱንም ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው ብፁዕ አቡነ አብርሃም በሰጡት ምላሽ፣ “በወቅቱ የተናገርኩት መናገር ያለብኝን ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ግዴታዬን ነው የተወጣኹት፡፡ ከዚኽ በዘለለ ለጋዜጠኞችም ይኹን ለሌላ አካል መግለጫ መስጠት አልፈልግም፤” ብለዋል፡፡ምንጭ፡ ሐራ ዘተዋህዶLet's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

1 comment:

 1. እንዲህ አይነት አባቶች ስላሉን የእኛ አባቶች በምሆናቸውም እንኮራለን፥ አቡነ አብርሃምን እግዚአብሔር አምላክ እድሜ ከጤና ያድልልን እያልን ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን አትረሳዎትም ቤተክርስቲያንም ዝንተ ዓለም ታስቦታልች በሉልን በተረፈ ሌሎች አባቶች ቤተክርስቲያን የላትም እንዴ እኮ ነው የሚያስብለው፥ እንዲህ ህዝባችን እንደ ቆሎ ሲረግፍ ምነው ዝምታችሁ አባቶቻችን? እረ ምነው ጸጥታችሁ በዛ
  የኢትዮጵያ አምላክ ፍርዱን ይስጥ ሌላ ምን እንላለን
  ዋልድባዎች በርቱ

  ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤