Wednesday, December 21, 2016

እንኳን ለታላቁ ጻድቅ "አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ" እና ለሰማዕታት "አንቂጦስ ወፎጢኖስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

የዝክረ ቅዱሳን Saints Of  The Orthodox Church ምስል
ታኅሣሥ 12
 እንኳን ለታላቁ ጻድቅ "አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ" እና ለሰማዕታት "አንቂጦስ ወፎጢኖስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ
 አባ ሳሙኤል ዘዋሊ
ሃገራችን እልፍ አእላፍ ቅዱሳንን አፍርታለች:: እንኩዋን በተባረከው በቀደመው ዘመን ይቅርና ዛሬም ከሃገር ተርፈው ለዓለም የሚጸልዩ : በየበርሃውና በየፈርኩታው የወደቁ ብዙ አባቶችና እናቶች አሉን:: በኢትዮዽያ ውስጥ ከተነሱ ቅዱሳን "ሳሙኤሎች" ልዩ ቦታ አላቸው:: 20 ዓመታት ልዩነት ብቻ 6 ሳሙኤሎች ተነስተው ከቅድስና ሕይወት እስከ ስብከተ ወንጌል : ከገዳማዊ ሕይወት እስከ ምናኔ በጐውን ጐዳና አሳይተዋል::
እነዚህም:-
1.ሳሙኤል ዘዋልድባ
2.ሳሙኤል ዘጣሬጣ
3.ሳሙኤል ዘቆየጻ
4.ሳሙኤል ዘግሺ
5.ሳሙኤል ዘሃሌ ሉያ እና
6.ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ናቸው::


በተመሳሳይም በግብጽ የደብረ ቀልሞኑን ኮከብ ጨምሮ (መልአኩን ቀውስጦስን ከጌታ ያማለዱት) ብዙ ሳሙኤሎች ተነስተዋል:: የድሮ እናቶቻችን በእውነት ስም መሰየሙን ይችሉበታል:: "ሳሙኤል" ማለት "ሰምዓኒ እግዚአብሔር ስዕለትየ - እግዚአብሔር ልመናየን ሰማኝ" ማለት ነውና:: ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ታላቁ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ አቡነ ሳሙኤል ዘዋሊ የተወለዱት 13ኛው መቶ /ዘመን (1295) በምድረ አክሱም ነው:: ወላጆቻቸውም እስጢፋኖስና ዓመተ ማርያም ይባላሉ::የዘር ሐረጋቸው ከካህናት ወገን ነውና ጻድቁ ገና በልጅነት ምሥጢራተ ሃይማኖትን ጠጥተዋል:: ለዚህም ይመስላል ገና ሕጻን ሳሉ ምናኔን የተመኙት::

ከልጅነታቸው ጀምረው ወላጆቻቸውን ያገለገሉት ሳሙኤል ትምሕርታቸውን ሲፈጽሙ የተጉዋዙት ወደ ደብረ በንኮል ነበር:: በጊዜውም የጻድቁ ወላጆች ዐርፈው እንደ ነበር ይነገራል:: ደብረ በንኮል ማለት የታላቁ ኮከብና አበ መነኮሳት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ነው:: መድኃኒነ እግዚእ ለሃገር ብርሃን የሆኑ ቅዱሳንን ያፈሩ ዘንድ ሲተጉ እግዚአብሔር 7ቱን ከዋክብት ሰጣቸው:: ክእነዚህ መካከልም ቀዳሚው አቡነ ሳሙኤል ናቸው:: ቀሪዎቹ ደግሞ እነ አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ : ሳሙኤል ዘጣሬጣ : ሳሙኤል ዘቆየጻና ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን የመሰሉ ናቸው::

አቡነ ሳሙኤል 6 ባልንጀሮቻቸው ጋር ሆነው በደብረ በንኮል ተጋድሎን አሐዱ አሉ:: እንጨት ይሰብራሉ:: ውሃ ይቀዳሉ:: እህል ይፈጫሉ:: በፍጹም ልባቸውም ይታዘዛሉ:: ጐን ለጐን ደግሞ ከቅዱሱ አበምኔት መድኃኒነ እግዚእ ጽንዓትን : ትሕትናን : ትሕርምትን ይማሩ : ሥርዓተ ገዳምንም ያጠኑ ነበር:: ከአገልግሎታቸው ማማር የተነሳ ሁሉን ደስ ማሰኘት ቻሉ:: በዚህ ጊዜም ጻድቁ አበ ምኔት አቡነ ሳሙኤል ዘዋሊንና 6ቱን አበው ጠርተው ለምንኩስና አቀረቧቸው:: "ይገባችኋ!" ሲሉም ከአመክሮ ወደ ምንኩስና አሸጋገሯቸው:: በዚያች ቀን 7 ሲመነኩሱ ከሰማይ ብርሃን ወርዶ በመታየቱ ቅዱሳኑ "ከዋክብት ብሩሃን" ተባሉ:: ለተወሰነ ጊዜም በዚያው በገዳሙ አገለገሉ:: የአቡነ ሳሙኤል ዘመዶች ግን እየመጡ ጻድቁን ስላስቸገሩ 7ቱም ቅዱሳን ተመካክረው : ከአባታቸው መድኃኒነ እግዚእ ተባርከው ከደብረ በንኮል ወጡ:: ሁሉም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራቸው ሲሔዱ 3 (ማለትም ሳሙኤል ዘዋሊ : ያሳይ ዘመንዳባና ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤ) ወደ ጣና ሔዱ:: በዚያም ለጥቂት ጊዜ አብረው ከቆዩ በሁዋላ ለአገልግሎት ተለያዩ:: አቡነ ያሳይ "መንዳባን" : አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ "ጉጉቤን" ይዘው እዛው ጣና አካባቢ ሲቀሩ አባ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ ሔዱ::

ዋልድባ 5ኛው መቶ /ዘመን በጌታ ፈቃድ የተመሠረተ ሲሆን 860 መሥራች ቅዱሳን በመሠወራቸው እንደ ጠፍ ይቆጠር ነበርና አቡነ ሳሙኤል እንደ ገና አቀኑት:: ጻድቁ በዋልድባ የመጨረሻውን ትሕርምት ከመያዛቸው በፊት በጊዜው ከፍተኛ የሆነ የወንጌል አገልግሎት ሰጥተዋል:: ቀጥለውም ኑሯቸውን ከግሩማን አራዊት ጋር አድርገዋል:: በስዕለ አድኅኖው እንደምናየው ለዘመናት በአንበሳ ጀርባ ላይ ተጭነዋል:: ጧት ማታም ብዙ ግሩማን አራዊትን እያስከተሉ ለአገልግሎት ደክመዋል:: ጻድቁ ከትሕርምት ብዛት እህል ትተው የሻገተ ጐመንና መልኩን የለወጠ ውሃን ለቁመተ ሥጋ ይጠቀሙ ነበር:: አንድ ቀንም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ እርሳቸው መጥቶ ባረካቸው:: አካላቸውንም በቅዱስ ምራቁ አትቦ ቀባቸው:: በዚህ ጊዜም ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ተመሉ:: የክርስቶስን ሕማማት እያሰቡም እልፍ ጊዜ ይሰግዱ: ጀርባቸውን ይገርፉም ነበር:: እግራቸውን በሰንሰለት አሥረው ይጋደሉም ነበር:: በዚህ ግብራቸው አጋንንትን አሳፍረው: ፈጣሪያቸውን ደስ አሰኙ:: ከቆይታ በሁዋላም ዋልድባ በመነኮሳት ተሞላ:: ደቀ መዛሙርት በዙ:: ቀዳሚው ግን አባ ዘሩፋኤል ጻድቅ ነው::

አቡነ ሳሙኤል ከድንግል እመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር ነበራቸው:: ዘወትር ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን በተመስጦ ያደርሱላት: ፈጽመውም ያመሰግኗት ነበር:: ይህንን ሲያደርጉ ከመሬት ክንድ ከፍ ብለው ይንሳፈፉ ነበር:: ተከታዮቻቸው ሲርባቸውም ውሃውን በቅዳሴ ማርያም ነጭ ሕብስት ያደርጉት ነበር::
"ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ::
ረሰዮ ሕብስተ ሳሙኤል ጽጌ ሃይማኖት ዘሐቅለ ዋሊ::
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ እኅሊ::
ስረዪ ኃጢአትየ ወዕጸብየ አቅልሊ::
እስመ ኩሎ ገቢረ ማርያም ትክሊ::" እንዳለ ሊቁ:: (ማኅሌተ ጽጌ)

እመ ብርሃንም ስለ ፍቅር ነጭ እንቁ ሰጠቻቸው:: ሰማያዊ ሕብስትን መገበቻቸው:: ንጹሕ ዕጣንንም አበረከተችላቸው:: 12 ዓመታትም ከሰማይ ካህናት ጋር አጠኑ:: ድንግል ማርያም "እንዳንተ ውዳሴየንና ቅዳሴየን በፍቅር የሚደግምልኝን አማልደዋለሁ" ስትላቸው:- ጌታ ደግሞ ገዳማቸውን ዋልድባን ቀድሷታል:: ቀድሞም በስደቱ ባርኳት ነበርና:: የጻድቁ ዜና ፈጽሞ ብዙ ነውና ለዛሬ በዚህ ይብቃን:: የዋልድባው ኮከብ አቡነ ሳሙኤል ያረፉት ታሕሳስ 12 ቀን 1395 ሲሆን ዕድሜአቸውም 100 ዓመት ነበር::
 የጻድቁ ረደኤ በረከት በሃገራችን ኢትዮጵያ እና በሕዝቦቿ ላይ ይኑር አሜን!!


 ቅዱሳን አንቂጦስ ወፎጢኖስ
እነዚህ ቅዱሳን በሥጋ ወንድማማቾች ሲሆኑ የዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች ናቸው:: ዜና ሕይወታቸውን ሳስበው ይገርመኛል:: በእሳት የወጣትነት ዘመናቸው በሃይማኖት ጸንተው: ፍቅረ ክርስቶስ እንደ እሳት በላያቸው ላይ ይነድ ነበር:: በእውነት ክርስቶስን በከንፈር ያይደለ በፍጹም ልቡና መውደድ እንዴት ያለ መታደል ነው! ክርስቶስን የወደደ የድንግል እናቱና የቅዱሳን ወዳጆቹ ፍቅር ይበዛለታል እንጂ አይቀንስበትም::

ቅዱሳኑ አንቂጦስና ፎጢኖስ ወጣትነት: የዓለም ኑሮ ሳያታልላቸው ለሰማዕትነት ራሳቸውን አዘጋጁ:: እንኩዋን ሰውን አራዊትን የሚያስበረግግ የስቃይ ዓይነት ተሰልፎ ሳለ በፍጹም አልደነገጡም:: መጀመሪያ አንቂጦስን አቀረቡት:: ገረፉት: ምንም አልሆነም:: በእሳት አቃጠሉት: ምንም አልነካውም:: ለአንበሳ ሰጡት: እነርሱ ግን ሰገዱለት:: ከዳር ሆኖ ይህንን ሁሉ ሲመለከት የነበረው ወንድሙ ፎጢኖስ ዘሎ ወደ መከራ አደባባይ ገባ::

ወንድሜ የክርስቶስ ነውና መቼም አታሸንፈውም" ሲል ጮኸ:: በዚህ ጊዜም በሥፍራው የነበሩ ብዙ አሕዛብ "የእነዚህ ወጣቶች አምላክ አምላካችን ነው" አሉ:: መኮንኑም 2ቱን ቅዱሳን ከብዙ ሕዝብ ጋር አሰይፏቸዋል:: እንደ እኔ ያለ ኃጢአተኛም በስማቸው እንዲህ ሊጸልይ ይገባል:-
"ሰላም ዕብል ለአንቂጦስ ማሕበሮ::
እለ በእሳት ፈጸሙ ረዊጸ ወተባድሮ::
ያብጽሑኒ እሉ ምስለ መላእክት ድርገተ ዘምሮ::
ህየ አኀሉ ወሬዛ ነዳየ ኩሉ አዕምሮ::
ኀበ ይዘብጣ ደናግል ከበሮ::" (አርኬ)

አምላከ ሳሙኤል በምጃቸው ሃገራችን ከጦርነት: ሕዝቦቿን ከስደት ይሰውርልን:: ሞልቶ ከተረፈ በረከታቸውም አይንሳን::
ታሕሳስ 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
2.ቅዱሳን አንቂጦስ ወፎጢኖስ (ሰማዕታት)
3.አባ ነድራ
4.ቅዱስ ዮሐንስ ተአማኒ
5.ጉቡዓን ኤዺስ ቆዾሳት

ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
5.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
6.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቅ

 የሚያሳድዷችሁን መርቁ . . . ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ:: ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ:: እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ:: የትዕቢትን ነገር አታስቡ:: ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ:: (ሮሜ. 12:14-16)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የዝክረ ቅዱሳን ምስል

ምንጭ: ዝክረ ቅዱሳን የፌስ ቡክ ገጽ የተገኘ
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤