Thursday, January 19, 2017

የአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ: ለስምሪት ሲዘጋጁ እጅ ከፍንጅ የተያዙ 9 የተሐድሶ ኑፋቄ ምልምሎችን አባረረ፤“ሃይማኖታቸውን የካዱ የእናት ጡት ነካሾች ናቸው!”/ኮሌጁ/

 • በኑፋቄው ዓላማና እንቅስቃሴ ሠልጥነው በፓስተሮቻቸው ‘ሲመረቁ’ በቪዲዮ ተቀርፀዋል
 • በሐቀኛ ደቀ መዛሙርትና በሰንበት ት/ቤቱ የነቃና የተቀናጀ ክትትል ሲደረግባቸው ቆይቷል
 • በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዘው ማሕበር ሰላማ፣ የታገዱትን ለማስመለስ በድብቅ እየሠራ ነው
 • በኅቡእ በሚሠለጥኑ ሌሎች ስመ ደቀ መዛሙርት ላይም ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው
*                    *                    *
 • በደብረዘይት፣ ኅቡእ ሥልጠናዎችን የተሳተፉ የኮሌጁ ምልምሎች ተለይተው ታውቀዋል
 • በጠቅላይ ጽ/ቤት እና በየአድባራቱ የተሰገሰጉ ሰርጎ ገቦች፥ ያስተባብራሉ፤ ያሠለጥናሉም
 • ዋነኞቹ አስተባባሪዎች፦ ከኮሌጁ ተመርቀው የወጡና በድኅረ ምረቃ እየተማሩ ያሉ ናቸው
 • ከአ/አበባ መኳንንት ተገኝ፣ ከሰበታ ገበየሁ ይስማው፣ ከአዳማ አዲስ ይርጋለም ይጠቀሳሉ
*                    *                    *
 • በጠ/ጽ/ቤቱ የሊቃውንት ጉባኤ የሚሠራው አእመረ አሸብር በተደጋጋሚ በማሠልጠን ተሳትፏል
 • መኳንንት ተገኝ፥ አማሳኙ ጎይትኦም ያይኑ በአ/አበባ አድባራት በቅጥር ከሰገሰጋቸው አንዱ ነው
 • “የነገረ መለኰታውያን ማኅበር” በሚል በኮሌጆች የኑፋቄው ፈጻሚ ቡድን ለማቋቋም መክረዋል
 • ‘ማኅበረ አኃው’ በሚል ፈቃድ ያወጣው የኑፋቄ አራማጅ፣ በሤራው አብሯል፤ በፈንድ ይደግፋል
*                    *                    *kesate-birhan-college


በሀገር አቀፍ ደረጃ የመማር ማስተማር ሥርዓትን በመዘርጋት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት መሠረትና የዕውቀት ማዕከል ናት፡፡ በየገዳማቱና በየአድባራቱ የሚገኙትን ጥንታውያኑን የአብነት ት/ቤቶች ጨምሮ በአኹኑ ጊዜም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር የሚተዳደሩ ሦስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት(ኮሌጆች) እና በአህጉረ ስብከት የሚመሩ በርካታ የካህናት ማሠልጠኛዎች አሏት፡፡ በበላይ ሕጋችን እንደሰፈረው፥ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን፣ የራሷን ማሠልጠኛዎችና ትምህርት ቤቶች የማቋቋምና የተቋቋሙትንም እስከ ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ የማሳደግና ዕውቅና የመስጠት መብት አላት፡፡
የአብነት ት/ቤቶቻችን፥ የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥርዐተ አምልኮት፣ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የማንነትና የሀገር በቀል ዕውቀቶች መካን በመኾን ለታላላቅ አበው፣ ሊቃውንትና አገልጋይ ካህናት ምንጭ ኾነው እንደቆዩት ኹሉ፤ ማሠልጠኛዎቹና ኮሌጆቹም፣ በዘመናዊው ዘይቤ የሠለጠነ የሰው ኃይልን በማፍራት በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ናቸው፡፡ ከማስተማር በተጓዳኝም በሚያከናውኑት ልማት ለቤተ ክርስቲያናችን ቋሚ ንብረት የማፍራትና ዘላቂ ገቢ የማስገኘት ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
የትምህርትና ማሠልጠኛ ተቋሞቻችን መዳከምና መጥፋት ከቤተ ክርስቲያናችን መዳከምና መጥፋት ተለይቶ የማይታይ በመኾኑ፣ ጥንካሬአቸውንና ጥራታቸውን ለመጠበቅ፣ ለማሳደግና ለማስፋፋት ተግቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤያትና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደረጃ በየጊዜው ተገልጿል፡፡ በበጀት ምደባ ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸውና ይኸውም ማእከላዊነቱን የጠበቀና የተቀናጀ እንዲኾን፤ ከገንዘብ ድጋፍም ጋር በአካል እየተገኙ መምህራኑንና ተማሪዎችን በሞራል ማበረታታቱ እንዲጠናከር የጋራ አቋም የተያዘበት ነው፡፡
ከዚኽም በላይ ዋነኛው ግን፦ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት፣ ሥርዓትና ታሪክ ሳይዛባ በስፋትና በጥራት እንዲሰጥ፤ ተማሪውንም በትክክል ለመለወጥና ለመቅረፅ የሚያስችል ብቁ አሠራር የማስፈኑ ጉዳይ ነው፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን፣ የካህናት ማሠልጠኛዎቻችንና መንፈሳውያን ኮሌጆቻችን፦ “ሰባክያንና መምህራን የሚፈልቁባቸው የሃይማኖታችን ምንጮች ናቸው፤” ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ድፍርስ ያይደለ ጥሩ ምንጭ ይኾኑ ዘንድ ትንሣኤያቸውን የሚያበሥር፣ ዕድገታቸውንና ጥራታቸውን የሚያፋጥን ጠንካራ መሠረት መቀመጥ ይኖርበታል፤ ብለዋል – በጥቅምት 2006 ዓ.ም.፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አሰምተውት በነበረው የመክፈቻ ቃለ ምዕዳን፡፡
ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት፣ “ምንጩ ድፍርስ ከኾነ የተጠማው መንገደኛ ውኃ ለመጠጣት ይቸገራል፤ ጥሩ ምንጭ ከኾነ ግን የጠማው ብቻ ሳይኾን ያልጠማው መንገደኛም ቢኾን በውኃው ጥራት ከመጎምጀቱ የተነሣ ሳይቀምሰው አያልፍም፡፡ ተቋማቱን፥ በብዛትም፣ በጥራትም በአደረጃጀትም በአዲስ አሠራርና በወሳኝ መልኩ በማስተካከልና በማብቃት፣ በሃይማኖቷ እንከን የሌላት ቤተ ክርስቲያናችን፣ በአያያዝና በአመራር ምክንያት የምትወቀስበትና ልጆችዋን የምታጣበት ታሪክ መገታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የትምህርትና የማሠልጠኛ ተቋሞቻችንን ጥሩ ምንጭነት ከሚያደፈርሱ ችግሮች ዋነኛው፣ መምህራኑንና ተማሪዎቹን በመጠቀም ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሰርጎ ለመግባትና ህልውናዋን አጥፍቶ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ በተለያዩ ስልቶችና መንገዶች የሚሠሩት “የእናድሳለን ባዮች” እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህም የምዕራባውያን የፕሮቴስታንት አቀንቃኞች(ፓስተሮች) ስልትና መንገድ ሲኾን፣ ከተቋሞቻችን መካከል የምኞታቸው ማስፈጸሚያና የዕቅዳቸው መነሻ ዋና ማዕከል ያደረጉት የቴዎሎጂ ኮሌጆቻችንን ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት የነበረ ቢኾንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጠንካራ ኹኔታ በመደራጀት፥ በውጭ ትምህርት ዕድል፣ በሥልጠና እና በልምድ ልውውጥ ስም የመለመሏቸውና የለወጧቸው አንዳንድ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች፥ኦርቶዶክሳውያኑን በማጥላላት እያሸማቀቁና ኑፋቄአቸውን እየዘሩ ነው፤ ጥቂት የማይባሉቱም በግልጽ ተቃዋሚና አፍራሽ ኃይሎች ኾነው እየወጡ ነው፡፡
“በተዋሕዶ እና በተሐድሶ መካከል ከፍተኛ ውስጣዊ ጦርነት እንዳለ” በይፋ እስከ መጻፍ የደረሱ ግንባር ቀደም ምዕራባውያን አዝማቾቻውም፤ ኮሌጆቻችንን ስትራተጅያዊ የትኩረት ማእከሉ ያደረገው የኑፋቄው የሰርጎ ገብነት ስልት፣ የተሐድሶ ማኅበራትንና አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን በበላይነት መምራትና ቤተ ክርስቲያናችንን በአጭር ጊዜ ፕሮቴስታንታዊ የማድረግ ሕልምን ማሳካት የሚችል እንደኾነ ተንትነዋል፡፡
ይህም፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ሉዓላዊነትና ተቋማዊ መብቶች የሚፃረር ግልጽ የወረራና የቅሠጣ ተግባር በመኾኑ በነቃ መከላከልና በተጠናከረ መቋቋም ሊጋለጥና ሊደመሰስ የሚገባው የህልውና ስጋት ነው፡፡ በገዢው ሕጋችን እንደሰፈረው፥ ቤተ ክርስቲያናችን በአቋቋመቻቸውና ዕውቅና በሰጠቻቸው ማሠልጠኛዎችና ትምህርት ቤቶች፦ ሃይማኖቷንና ቀኖናዋን የማስተማርና የማስፋፋት፣ የማጠናከርና የምስክር ወረቀት የመስጠት መብቱ የሌላ የማንም ሳይኾን የራስዋ ነውና፡፡
የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኞች፣ ይህን ሕጋዊ መብትዋን በመጋፋት፣ ኮሌጆቻችንን የትኩረት ማዕከል ባደረጉበት ቅሠጣቸው፣ ሁከት እየፈጠሩ መኾናቸውን፣ ደቀ መዛሙርቱን የላኩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና አህጉረ ስብከት፣ በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ወቅት ባቀረቧቸው ሪፖርቶችና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባካሔዷቸው ውይይቶች ተረጋግጧል፡፡ ኑፋቄው ውስጥ ለውስጥ ቤተ ክርስቲያንን እየጎዳና በአገልግሎቷ ላይም ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ እንዳለ የአህጉረ ስብከቱ ሪፖርቶቹ ጠቁመዋል፡፡ “ቤተ ክርስቲያንን እንወዳለን፤ አባቶችን እናከብራለን” ቢሉም፣ የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ እየበሉ ስውር ዓላማቸውን እንደሚያካሒዱና ሕዝበ ክርስቲያኑን በመከፋፈል በቤተ ክርስቲያን ላይ መሠሪ ተግባራቸውን እንደሚፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶሱ በስፋት ተወያይቶበታል፡፡
ከአየህጉረ ስብከቱ ወደ ኮሌጆቹ ሲላኩ ጤናማ የነበሩ ደቀ መዛሙርት፣ ተመርቀው ሲወጡ ሌላ ሰው ኾነውና መስለው መመለሳቸው፣ “እያንዳንዱን ኮሌጅ ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባዋል” ብሏል ምልአተ ጉባኤው፡፡ የችግሩ ምንጮች በመኾናቸውም፦ የሚማሩባቸውና የሚያስተምሩባቸው እነማን እንደኾኑና የሚያስተምሩበት ሥርዓተ ትምህርትና የመማሪያ መጻሕፍታቸው እንዲፈተሹና በማስረጃ የተደገፈ ጥናት እንዲቀርብ ወስኗል፡፡ የደቀ መዛሙርቱ አመራረጥና አቀባበል፤ የመምህራኑ ክህሎትና የሃይማኖታቸው ጉዳይ፤ የካሪኩለም አቀራረፅና የመማሪያ መጻሕፍቱ ዝግጅት አጽንዖት የተሰጠባቸው የፍተሻውና የምርመራው ዋነኛ ነጥቦች ናቸው፡፡
እየተማሩ ሳሉም ኾነ ተመርቀው ከወጡ በኋላ በኑፋቄው የሚገኙትን በተመለከተም፥ እየተመረመሩ በቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ ስለሚመለሱበት አልያም ስለሚታገዱበት፤ ከኮሌጆቹና ከአህጉረ ስብከቱ አቅም በላይ ከኾነም ለበላይ አካል ሪፖርት ስለሚደረግበት አሠራርም ቅዱስ ሲኖዶሱ በውሳኔው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በተጨማሪም፣ ሦስቱንም ኮሌጆች፣ ለበለጠ ዕድገት ለማብቃት የሚያስችል “የውስጥ ይዘት ጥናት” እንዲካሔድ ሦስት ብፁዓን አባቶች የሚገኙበትን ልኡክ መሠየሙም የሚታወስ ነው፡፡
ዘመኑ የሚጠይቀውን፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅም የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት በመጣር ላይ ያሉት የቴዎሎጂ ኮሌጆቻችን፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና አቅጣጫ መሠረት፣ የኑፋቄውን ተጽዕኖ ከነአቀንቃኞቻቸው ለማጋለጥና ለማጥራት ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንዳሉ ከሚወስዷቸው ርምጃዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡
አንጋፋው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የመተዳደርያ ደንቡን ያገናዘበ “የእውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ስምምነት አንቀጽ” በማዘጋጀት የዲስፕሊን ቁጥጥሩን አጠናክሯል፤ በመደበኛው ይኹን በማታው መርሐ ግብር የኑፋቄው ቅጥረኞች ኾነው የተገኙትን በተከታታይ በመመንጠር አባሯል፤ ሽፋን የሚሰጣቸውን አንድ ሓላፊም ከቦታው መንግሎታል፤ ስለተወሰደው ርምጃም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ማብራሪያ በመስጠት በተገቢነቱና በቀጣይነቱ ላይ ተግባብቷል፡፡
የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የአስተዳደር ሓላፊዎችን፣ መምህራንንና ደቀ መዛሙርትን ያካተተ ውይይት፣ በግልጽ መድረክና በተደጋጋሚ በማካሔድ በኑፋቄው አደጋ ዙሪያ ማኅበረሰቡን አንድ ልብና አንድ ሐሳብ ያደረገ ግንዛቤ አስጨብጧል፤ ተጨባጭ ማስረጃ የተገኘበትን ከደቀ መዝሙርነት ያስወገደ ሲኾን፣ በጥርጣሬ በተያዙት ላይም ምርመራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

መቐለ የሚገኘው የቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሠልጥነው ለሥምሪት ሲዘጋጁ እጅ ከፍንጅ የያዛቸውን ዘጠኝ የኑፋቄውን ምልምሎች፣ ከደቀ መዝሙርነት ሙሉ በሙሉ እንዳሰናበታቸው ባለፈው ሳምንት ኃሙስ፣ ጥር 4 ቀን አስታውቋል፡፡ ከየአህጉረ ስብከታቸው የተላኩበትን አደራ ወደ ጎን በመተው ከኮሌጁ ውጭ በፕሮቴስታንት ፓስተሮች እየሠለጠኑ፣ በግቢው ውስጥ ደግሞ፣ በቃልም በድርጊትም ቤተ ክርስቲያንን ሲያንቋሽሹና ኑፋቄአቸውን ሲያራምዱ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የኮሌጁ ሐቀኛና ቀናዒ ደቀ መዛሙርትም፣ ለሚመለከተው የኮሌጁ አስተዳደር በመረጃ ደረጃ ቀደም ብለው ጥቆማ ያደረሱ ሲኾን፣ በማስረጃ ለማረጋገጥም፣ መቐለ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት ጋር የነቃና የተቀናጀ ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸው ተጠቅሷል፡፡ በዚኽም መሠረት የተሐድሶ ኑፋቄው ምልምሎች፣ በመቐለ ዩኒቨርስቲ ዓዲ ሓቂ ካምፓስ አቅራቢያ ባለው የመናፍቃን አዳራሽ ሲሠለጥኑ መቆየታቸው ተረጋግጧል፡፡ ሥልጠናቸውን በማጠናቀቅ ባለፈው ታኅሣሥ 23 ቀን፣ ከከተማው ውጭ በኵሓ፣ “በመንፈስ እናጠምቃችኋለን” በሚሉ ፓስተሮቻቸው ‘እየተመረቁ’ ለስምሪት በሚዘጋጁበት ወቅት እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ታውቋል፡፡
ለክትትሉ የተመደቡ የሰንበት ት/ቤቱ አባላት ትዕይንቱን በምስል ወድምፅ ለማስቀረት የቻሉ ሲኾን፤ ይህንኑ ዘግይተው የተረዱት የኑፋቄው ምልምሎች ማስረጃውን ለማጥፋት በማሰብ ጥቃት ቢሰነዝሩም፣ ፈጥኖ በደረሰው የፖሊስ ኃይል መገታታቸው ተገልጧል። የምልምሎቹ ቀንደኛና በቅጽል ስሙ አርዮስ የሚባለው ኤፍሬም ማተቤ በሩጫ ለማምለጥ ቢሞክርም በቀላሉ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ ማስረጃውም፣ ለኮሌጁ አስተዳደር ሳይዘገይ ደርሶ፣ ዘጠኙም የኑፋቄው ምልምሎች፣ ታኅሣሥ 27 ቀን ግቢውን ለቀው እንዲወጡና ጉዳያቸውን በውጭ ኾነው እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡
ቅ/ሲኖዶስ፣ በግንቦት 2004 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው ካወገዛቸው 8 የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራት አንዱ ማኅበረ ሰላማ፣ እገዳውን ለማስነሣትና ምልምሎቹን ለመመለስ በአንድ አባሉ አማካይነት ውስጥ ለውስጥ ጥረት ቢያደርግም እንዳልተሳካላት ተዘግቧል፡፡ በአንፃሩ፣ ማስረጃውን ከቀደሙት ጥቆማዎች ጋር በማገናዘብ የተመለከተው የኮሌጁ አስተዳደር፣ የኑፋቄው ምልምሎች፣ ከኮሌጁ ሙሉ በሙሉ እንዲሰናበቱ ወስኗል፡፡
ኮሌጁ፣ ጥር 4 ቀን ባወጣው ማስታወቂያው፣ ባሳዩት የሃይማኖት ክሕደት የእናት ጡት ነካሾች ኾነው ስለተገኙ ከኮሌጁ ሙሉ በሙሉ የተሰናበቱ መኾናቸውን እናስታውቃለን፤ ብሏል፤ ቀሪ ጉዳያቸውም፣ በየመጡበት አህጉረ ስብከትና በቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚወሰን አክሎ ገልጿል፡፡ በስም ዝርዝራቸውም፡-
 1. ቤተ ማርያም ወዳጄ ከቤንች ማጂ ሀ/ስብከት የተላከና በዲፕሎማ የ3ኛ ዓመት ተማሪ የነበረ፤
 2. መለሰ ለማ፦ ከሐዋሳ ሀ/ስብከት የተላከና በዲፕሎማ የ3ኛ ዓመት ተማሪ የነበረ፤
 3. ኄኖክ አስማረ፦ ከዋግ ኽምራ ሀ/ስብከት የተላከና በዲፕሎማ የ3ኛ ዓመት ተማሪ የነበረ፤
 4. ወልደ ብርሃን ካህሳይ፦ ከመቐለ ሀ/ስብከት የተላከና የ3ኛ ዓመት ዲፕሎማ ተማሪ የነበረ፤
 5. ዐማኑኤል ደምሴ፦ ከምሥራቅ ሸዋ ሀ/ስብከት የተላከና በመጀመሪያ ዲግሪ የ4ኛ ዓመት ተማሪ የነበረ፤
 6. ወንድዬ ደበበ፦ ከአፋር ሀ/ስብከት የተላከና በመጀመሪያ ዲግሪ የ4ኛ ዓመት ተማሪ የነበረ፤
 7. ታምራት አልታዬ፦ ከጉራጌ ሀ/ስብከት የተላከና በመጀመሪያ ዲግሪ የ4ኛ ዓመት ተማሪ የነበረ፤
 8. ተስፉ ገብረ ሚካኤል፦ ከሶማሌ ሀ/ስብከት የተላከና በመጀመሪያ ዲግሪ የ5ኛ ዓመት ተማሪ የነበረ፤
 9. ኤፍሬም ማተቤ(አርዮስ) ከምሥራቅ ሸዋ ሀ/ስብከት የተላከና በመጀመሪያ ዲግሪ የ3ኛ ዓመት ተማሪ የነበረ፤ ናቸው፡፡

የቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር፣ እንደ ኹለቱ የቴዎሎጂ ኮሌጆቻችን ኹሉ፣ ሲኖዶሳዊውን የዕቅበተ እምነት ውሳኔና አቅጣጫ በማስፈጸም ለፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎው ያለውን አጋርነት በዚኽ ወቅታዊ ውሳኔው በተግባር አሳይቷል፡፡ ይኸው ኮሌጅ፣ በተለይም “ሲም”ን (Serving in Mission) በመሳሰሉትና የተሐድሶ እንቅስቃሴን ለማበረታታትና ለመደገፍ በይፋ በሚንቀሳቀሱ የፕሮቴስታንት እምነት ድርጅቶች ትኩረት ያረፈበትና በተጽዕኖ ውስጥ ያለ እንደመኾኑ፣ ከዚኽም የላቀ ክትትልና ቀጣይ ማጥራት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ የነገረ መለኰት መምህራንንና ደቀ መዛሙርትን በጎራው በማሰለፍ ቤተ ክርስቲያናችንን ለመውረርና በአጭር ጊዜ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ፣ ኮሌጆቻችንን መሠረት አድርገው በተነሡ ፕሮቴስታንታዊ ድርጅቶች ድጋፍ በኅቡእ የሚሰጡ ሥልጠናዎችን እየተሳተፉ ያሉና መጋለጥ የሚገባቸው የስም ደቀ መዛሙርት ገና አሉ፡፡ ተሳትፏቸው፣ በዓላማም ይኹን ባልጠረጠሩት መንገድ፣ ብቻ ከወዲኹ ታውቀውና ተለይተው አስፈላጊው እርምት ሊወስድባቸው ይገባል፡፡ ለዚኽም በቅርቡ፣ በደብረ ዘይት በኅቡእ ተሰጥቶ በነበረው ሥልጠና፦ በሠልጣኝነት፣ በአስተባባሪነትና በአሠልጣኝነት የተሳተፉትን በማስረጃነት መጥቀሱ ይበቃል፡፡
ሥልጠናውን ያዘጋጀውና በገንዘብ የሚደግፈው፣ “ማኅበረ አኃው” በሚል ስያሜ የሚኒስትሪ ፈቃድ ያወጣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ ድርጅት ሲኾን፣ በቴዎሎጂ ኮሌጅ መምህራንና ደቀ መዛሙርት ላይ በማተኮር እንደሚያሠለጥን ተገልጧል፡፡ ቀሲስ’ ኪዳኔ የተባለው መሥራቹና ሰብሳቢውም፣ ከቴዎሎጂ ኮሌጅ መመረቁን ይናገራል፡፡ በደብረ ዘይት፣ ቤተ ልሔም ት/ቤት አካባቢ በተለምዶ ዝቋላ እየተባለ በሚጠራው ሰፈርበተከራየው ቤት፣ ከሦስቱም ኮሌጆች በኅቡእ የመለመላቸውን የስም ደቀ መዛሙርት በተከታታይ በኑፋቄው እያሠለነ ይገኛል፡፡
በዚኽ ዓመት ብቻ በኹለት ዙሮች 60 የኑፋቄውን ምልምሎች ማሠልጠኑ ተነግሯል፡፡ ከታኅሣሥ 12 እስከ 14 ቀን በነበረው ኹለተኛው ዙር ሥልጠና፣ ከአጠቃላይ ተሳታፊዎቹ፣ ከቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ የተመለመሉት ሠልጣኞች ከ10 በላይ እንደኾኑ ዝርዝራቸው ያሳያል፡፡ ከዚኽም ጋር አሳሳቢው ጉዳይ፣ ሥልጠናውን በዋናነት የሚያስተባብሩት በኮሌጁ የቅድመ ምረቃና የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች ተምረውና ተመርቀው የወጡና በመማር ያሉ መኾናቸው ነው፡፡
በስም ለመጥቀስ ያኽል፡- በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ናዝሬት የአንድ ደብር አገልጋይ የኾነው አዲስ ይርጋለም እና በተፍኪ በኋላም በሰበታ አድባራት ሰባኪ የነበረው ገበየሁ ይስማው የሥልጠናው ተጠቃሽ አስተባባሪዎች ናቸው፡፡ በአኹኑ ወቅት፣ በወልቂጤ ከነበረው እንደ ጌታቸው ይርጋለም እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅርስ ክፍል ሓላፊ ከኾነው እንደ ኢዮብ ይመር ካሉት የኑፋቄው ግንባር ቀደሞች ጋር በኮሌጁ የድኅረ ምረቃ ትምህርት በመከታተል ላይ እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡
mm
ቀሣጢው መኳንንት ተገኝ የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ እየበሉ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ድርጅቶች ከሚሠሩት አንዱ፤ በሥራ አስኪያጁ ጎይትኦም ያይኑ ትእዛዝ በአ/አበባ ሀ/ስብከት አያት ኪዳነ ምሕረት ደብር ተቀጥሯል
በሥልጠናው አስተባባሪነት፣ በአጠቃላይ ከተዘረዘሩት ስድስት ግለሰቦች ጋር ስሙ የተነሣው ሌላው ግለሰብ፣ መኳንንት ተገኝ የተባለው ቀሣጢ ነው፡፡ ዲፕሎማውን ከአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ ቀደም ብሎ የወሰደና በኋላም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በዲግሪ መርሐ ግብር መጨረሱ ተገልጿል፡፡ ቀሣጢው መኳንንት፣ አጭበርባሪነቱና የተሐድሶ ቅጥረኛነቱ ተጋልጦ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ርምጃ የተወሰደበት አሰግድ ሣህሉ፣ ግልጽ ኑፋቄውን ሲረጭበት በነበረው “ቃለ ዐዋዲ” በተሰኘው የኢቢኤስ ቴሌቭዥን ፕሮግራም የሚታወቅ ሲኾን፤ በአኹኑ ወቅት፣ በአ/አበባ ሀ/ስብከት አያት ኪዳነ ምሕረት ደብር በሰባኪነት ተቀጥሮ ይገኛል፡፡
የተለያዩ የምዝበራ ሰንሰለቶችን በመዘርጋት የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ሓላፊዎችንና ሠራተኞችን በዝውውር፣ ባልተጠናና ሕገ ወጥ የደመወዝና የአበል ጭማሬዎች ስም እየዘረፈ ራሱን በማበልጸግ ላይ የሚገኘው፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተላላኪው ሥራ አስኪያጅ ጎይትኦም ያይኑ በሌብነቱም በኑፋቄውም መሥመር እየተሳሳበ፣ በየአጥቢያው በቅጥር እየሰገሰጋቸው ካሉት የኑፋቄው አራማጆች አንዱ ነው – ቀሣጢው መኳንንት ተገኝ!
ቅጥሩ፦ በአገልግሎት መዋቅሩ ቦታ ይዞ ከውስጥ የመንቀሳቀስ የተሐድሶ ኑፋቄው ዓይነተኛ ስልት ማሳያ ነው፡፡ ይኸውም፣ መኳንንት በደብሩ ይቀጠር እንጂ የኑፋቄው ምልምሎች በየስፍራው በሚሳተፉባቸው ሥልጠናዎች መካፈሉንና ማስተባበሩን መቀጠሉ ነው፡፡ ከደብረ ዘይቱ ሥልጠና በኋላ፣ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ “ታላቁ ተልእኮ”/Great Mission Commission/ የተባለ ሌላ አውሮፓዊ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ ድርጅት በባሕር ዳር ያዘጋጀውን የኹለት ቀናት ሥልጠና ተካፍሏል፡፡ ሠልጣኞቹም፣ ከምዕራብ ጎጃምና አዊ ዞኖች እንዲኹም ከጎንደር አድባራት የተውጣጡ የኑፋቄው ምልምሎች እንደነበሩ ተመልክቷል፡፡
mt8
የፖሊቲካ/የሲቭል ከፍተኛ ባለሥልጣናትን፣ በተለያዩ መስኮች የተካኑ ሞያተኞችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን
 በኑፋቄው አጥምዶ ለተልእኮው በማሰለፍ ላይ አተኩሮ የሚሠራው ድርጅቱ፤ “Nehemiah Building – የፈረሰውን ለመሥራት” በሚለው የተሐድሶ ክንፉም፣ እንደ መኳንንት ተገኝ በመዋቅር ውስጥ ያሉ ሰባክያነ ወንጌልን፣ መምህራንን፣ ተማሪዎችን፣ አገልጋይ ካህናትንና ምእመናን መልምሎ በመሣርያነት እየተጠቀመ ይንቀሳቀሳል፡፡
የሥልጠናዎቹ አርእስትና ጭብጦችም በዚኹ ዓላማ የተቃኙና ግቡን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያኽል፣ በ“ማኅበረ አኃው” የተዘጋጀው የደብረ ዘይቱ ሥልጠና፦ “በመንፈስ ቅዱስ መሞላት”፣ “የዘመኑ አገልጋዮች ገጽታዎች”፣ “አገልጋይ ለጤናማ ቤተ ክርስቲያን”፣ “መንፈሳዊ ተልእኮ” የሚሉና መሰል አባባሎች ያሉት ነው፡፡ አጠያያቂው ጉዳይ፣ “መንፈሳዊ ተልእኮ” በሚል የሥልጠናው የመጨረሻ ቀን(ታኅሣሥ 14) አሠልጣኙ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሊቃውንት ጉባኤ አባል ኾኖ እየሠራ ያለው መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር መኾኑ ነው፡፡
በዚኽ መልኩ የሚሠለጥኑት የኑፋቄው ምልምሎች፣ “መንፈሳዊ ኮሌጆች ላይ አጥብቀን መሥራት አለብን!” በሚል አጽንዖት መክረዋል፡፡ ዓላማቸውን ለማስፈጸምም፣ “የነገረ መለኰታውያን ማኅበር” በሚል አንድ ቡድን ለማቋቋም በማቀድ መተዳደርያ ደንብ አርቅቀዋል፡፡ በሤራቸው ተባባሪና በገንዘብም ደጋፊያቸው ‘ቀሲስ’ ኪዳኔ ጸሎትም ተሰነባብተዋል፡፡
ጠላት፣ ሐዋርያዊትና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያናችንን፣ ማንነቷን አጥፍቶ ባለችበት ለመውረስ አልያም ማዕከላዊ አንድነቷን አናግቶና ከፋፍሎ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ በዚኽ መልኩ በተለያየ ስልትና መንገድ እየሠራ ነው፡፡ በእያንዳንዷ ቀን፣ በውስጥ ምልምሎቹ እየታገዘ የሚሸርበው ሤራና የሚያደርሰው ጥፋትም ከባድ ነው፡፡
ይኹንና፣ እንደ ቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ ያሉ ሐቀኛ ደቀ መዛሙርትና እንደ መቐለ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል የሰንበት ት/ቤት አባላት ያሉ ትጉሃን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መስተጋድላን እስካሉ ድረስ፣ አሳሳቢ እንጂ አስፈሪ አይኾንም፡፡ መፍትሔው፣ አደጋውን በሚመጥን የአገልግሎት ዝግጅት ተገቢውን ስልት ነድፎ የተቀናጀና የላቀ ሥራ መሥራት ብቻ ነው!!
source: Hara Tewahedo
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤