Monday, January 23, 2017

የዋልድባ ቅን አምባ ኪዳነ ምሕረት የደናግላን ገዳም በፌደራል ወታደሮች ቤተመቅደሱ ተመዘበረ

Related image


በሰሜን ጎንደር ዋልድባ ገዳም አካባቢ የሚገኘው የዋልድባ ቅን አምባ ኪዳነ ምሕረት የደናግላን ገዳም ትላንት ረፋዱ ላይ በፌደራል ወታደሮች መወረሩን የአካባቢው የዓይም ምሥክሮች የደረሰውን ውዝግብ እና የመንግሥት ወታደሮች በሃይማኖታችን ላይ እያደረሱት ያሉትን መጠነ ሰፊ የሆነ ምዝበራ እና ቤተመቅደስ የማዋረድ ሥራቸውን እግዚአብሔር እንዲያስታግስልን ምዕመናን በጸሎት እንዲያግዙን ብለው መልዕክታቸውን አስተላልፈውልናል።


ላለፉት በርካታ ወራት የመንግሥት ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በቤተክርስቲያናት አካባቢ በመምጣት በአገልጋይ መነኮሳት ላይ ብዙ እንግልት እያደረሱ እንደሚገኙ የአካባቢው የዓይን ምሥክሮች አክለው ገልጸውልናል፣ ምክንያታቸውም መሣሪያ ለግንቦት ሰባት ወታደሮች ደብቃችኋል አውጡ፣ የአካባቢው ጫካ የገቡ ነዋሪዎች መሣሪያ እዚህ ነው የሚደብቁት፣ የተቃዋሚዎች መሣሪያ መቀባበያ ናችሁ በሚል ሰበብ በገዳሙ በመግባት አረጋውያን መነኮሳትን ደብድበዋል፣ አዋርደዋል፣ በቤተ መቅደሱም ከነመሳሪያቸው እና ከነ ጫማቸው በመግባት ጽላቱን በማንሳት ፍተሻ ነው በሚል እጅግ የሚቀፍ ጸያፍ ሥራዎችን በሃይማኖታችን ይልቁንም በተቀደሰው ቤተመቅደሳችን ላይ እያደረሱብን ነው፣ ለማን አቤት እንበል፣ የሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከትም ሆነ የአካባቢው ሃገረ ስብከት ለችግራችን ምንም መልስ ሊሰጡን አልቻሉም፥ ነገር ግን ጥፋቱ ግን እየጨመረ ከእለት ወደ እለት እየከፋ ትላንት እጅግ በሚያሳዝን መልኩ ወደ ቤተመቅደሱ በመግባት የተለመደ ጸያፍ ተግባራችውን በቤተመቅደሳችን ላይ ፈጽመዋል በማለት በምሬት ቃላቸውን ሰጥተውናል።
ዋልድባ ገዳም ከዛሬ 5 እና 6 ዓመት ጀምሮ በርካታ ግፎች እና በደሎች በመነኮሳቱ እና በማኅበረ ገዳማውያኑ ላይ እየተፈጸማቸው እና ብዙ እንግልቶች ቢደርሱም ቤተክህነቱም ሆነ የክልሉ ሃገረ ስብከት ምንም ሳያደርጉ በችግር በግፍ እስከ አሁን ድረስ መፍትሄ ሳይሰጣቸው ከነችግራቸው እንደቀጠሉ ይገኛሉ፣ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በዋልድባ አበረንታንት መድኅኒዓለም ገዳም አካባቢ ሸንኮራ በማልማት የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም እና የፖርክ ይዞታዎችን ለመከለል መንግሥት ሲንቀሳቀስ ቢቆይም፣ በመድኃኒዓለም ጥበብ ለወራት የተገደቡትን ግድቦችን እንደ ዓይን ጥቅሻ ድራሹን ሲያጠፋ፣ ለሸንኮራ ልማት የተፈሉትን ችግኞች በአንድ ቀን ዝናም ጠራርጎ ሲወስደው፣ በኮንትራት የመጡትን ከባድ የጭነት መኪናዎች በአንድ ቀን ዘጠኙን መቀመቅ ገደል ሲጨምራቸው፣ ለሥራ የመጡትን መሃንዲሶች በቀናት በሽታ በሞት ሲወሰዱ፣ ድልድዮችን በጎርፍ ሲወሰዱ፣ እንዲሁም በርካታ ተዓምራቶችን ሲሰራ የቆየው የቦታው ባለቤት ኤልሻዳይ የዓለም መድኅኒት ክርስቶስ፣ እድሜ ለንሰሃ እየሰጣቸው እስከ አሁን ድረስ እነዚህ የዲያብሎስ ልጆች በችግር ላይ ችግር በገዳማውያኑ ላይ ማድረሳቸው በእጅጉ ያሳዝናል፣ በእጅጉ የቆረቁራል የሃይማኖት አባቶች በዝምታ ተሸብበዋል፣ ምዕመናን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል ከጥቂቶች በስተቀር ዛሬ ላይ ተረፈ አርየሳውያን እንዲህ በሃይማኖታችን ላይ ፈተና ሲያበዙልን ወደ ፈጣሪያችን አቤት ማለት አይቀሬ ነው እና እናቶች አባቶች፣ እህቶች ወንድሞች በጸሎታችሁ ወደ ፈጣሪ እንድታመለክቱ በገዳማውኑ ሥም ለማሳሰብ እንወዳለን።
እርግጠኞች ነን ጽዋው ይሞላል፣ ይህ ሁሉ እንባ በጽህረ አርያም ያስተጋባል በሥላሴ መንበር ስር ይጣራል በመሆኑም እነዚህ ተረፈ አርዮሶች ወየውላቸው፣ ዛሬ ላይ ቆም ብለው ማሰብ ካልቻሉ እና ነገን መመልከት ካልቻል ሰማይና ምድር የማይችሉት መድኅኒዓለም ክርስቶስ ለስም አጠራሩ ምስጋና ይግባው እና እድሜ ለንሰሃ ሰጥቷቸዋል ቢጠቀሙበት አለበለዚያ ግን ፈርዖንን ያየህ ተቀጣ ነው እና ከዛ ንፍር ውሃ እንዲሰውራቸው ቤተክርስቲያንን ማሪኝ ብለው ቤተመቅደሳችንን ማርከሳቸውን በአስቸኳይ እንዲቆሙ በታላቅ ምክር እንለግሳለን፣ አለበለዚያ ግን እናምናለን የእኛ አምላክ ምሕረቱ በዝቶ እንጂ እንደነሱ ቢሆንማ ኑሮ ቀድሞ ነበር የሚያጠፋቸው፣ እባካችሁ ተመከሩ እንላለን ከዝግጅት ክፍላችን
ቸር ይግጠመንLet's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤