Thursday, April 6, 2017

  • ክፉኛ የተጎዱት ሥራ አስኪያጁ፣ በዲላ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ነው
  • በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን የደበደቧቸው 2 የኑፋቄው ቅጥረኞች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል
  • በጥቃቱ እና ጉዳያቸው እየታየ በሚገኙ ከ23 በላይ የኑፋቄው ተጠርጣሪዎች ውሳኔ ይሰጣል
  • ጥቃቱ፣ የወረዳውን አድባራት፣ የፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ ጥረትና ውጤታማነት አመላካች ነው
  • በፀረ ተሐድሶ ተጋድሎው፣ ወላጆችና ሰንበት ት/ቤቶች ወሳኝ ሱታፌና ትብብር አሳይተዋል
                                           * * * በሲዳማ ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞኖች አህጉረ ስብከት፣ የዲላ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የኾኑት፣ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ታዬ ወርቁ፣ ዛሬ፣ መጋቢተው 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠዋት፣ በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቅጥረኞች በተፈጸመባቸው ድብደባ ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸው ተገለጸ፡፡ ሥራ አስኪያጁ፣ ከጠዋቱ 2፡00 ገደማ፣ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ፣ ቀደም ሲል በውትድርና አገልግሎት ውስጥ የነበሩ ኹለት የኑፋቄው ቅጥረኞች ከፍተኛ ድብደባ ያደረሱባቸው ሲኾን፣ በግቢው በነበሩ ምእመናት የድረሱልን ጩኸት ተርፈው ወደ ዲላ ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸው ታውቋል፡፡ የድረሱልን ጩኸት መሰማቱን ተከትሎ ጥቃት አድራሾቹ ቅጥረኞች ከአካባቢው ለማምለጥ ቢሞክሩም፣ በከተማው ፖሊስ ክትትል ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተጠቅሷል፡፡ ሥራ አስኪያጁን መሬት ጥሎ ሥራ አስኪያጁን መሬት ላይ ጥሎ የደበደበው ዋነኛው ቅጥረኛ፣ ፈቃዱ ወንድወሰን እንደሚባልና ሌላውም ማስረሻ ገዛኽኝ እንደሚባል ተገልጿል፡፡ የአድባራቱ ሰበካ ጉባኤ፣ ስለ ጥቃቱ፣ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ ለፖሊስ ጽ/ቤት እና ለኮማንድ ፖስት ያሳወቀ ሲኾን፣ በጥቃት አድራሾቹም ላይ ምርምራ እየተካሔደ እንዳለ ተመልክቷል፡፡ ኹለቱ ቅጥረኞች፣ ከዛሬው ጥቃት ቀደም ብሎ፣ ሰሞኑን፣ ወደ ሥራ አስኪያጁ እየመጡ፣ “አንበሳው በጋሻው ይመጣል፤ ያኔ ሥርህን ነው የምንነቅልልኽ” እያሉ ሲዝቱባቸው እንደነበር፣ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ታዬ ከሆስፒታል ለፖሊስ በሰጡት ቃል ተናግረዋል፡፡ በአንድ አስተዳደር የሚመሩትን የከተማውን፥ የበኣታ ለማርያም የቅድስት ሥላሴ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና ዳማ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት በእልቅና፣ የወረዳውን ቤተ ክህነት ደግሞ በሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ታዬ፣ አጥቢያዎቹን ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄና ከኑፋቄው ርዝራዦች ለማጥራት የሚፈጸመውን አገልግሎት በትጋት የሚመሩና የሚያስተባብሩ አባት መኾናቸው ተመልክቷል፡፡ ኑፋቄው፣ በእናት ቤተ ክርስቲያን ማንነትና መዋቅራዊ አንድነት ላይ የጋረጠውን የህልውና ስጋት፣ በትምህርት ለመከላከልና በማስረጃ ለማጋለጥ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፣ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ በቅንጅት እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈው ውሳኔ፣ በወረዳው አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉና በሚገባ በመተግበሩ፣ ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡ በየጊዜው በሚካሔዱ ጉባኤያት፣ በማስረጃ ተደግፈው በሚቀርቡ ትምህርቶችና በሚተላለፉ መልእክቶች፣ ልጆቻቸውን ሳይቀር ያጋለጡ ወላጆች መኖራቸው፣ ተጋድሎውን በከፍተኛ ደረጃ አጠናክሮታል፤ ለውጤትም አብቅቶታል፡፡ የኑፋቄው ተጽዕኖ አይሎ ይታይባቸዋል ከተባሉት መካከል የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት፣ ትክክለኛውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አመራርና የአባላት ይዞታ እስኪኖረው ድረስ ሙሉ በሙሉ ማጥራት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት በወላጆች ጥያቄ እንዲዘጋ መደረጉ ተገልጧል፡፡ የወረዳው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኮሚቴ እስከ አኹን በአደረገው ማጣራት፣ የማያሻማ ማስረጃ ያገኘባቸውን ከ23 ያላነሱ የኑፋቄውን አቀንቃኞች፣ አጠቃላይ ማንነትና እንቅስቃሴ የሚገልጽ ሰነድ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የላከ ሲኾን፣ ውሳኔውም ባለፈው እሑድ ለምእመኑ ይፋ ይኾናል ተብሎ እየተጠበቀ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ዛሬ፣ በሥራ አስኪያጁ ላይ የተፈጸመው የቅጥረኞች ጥቃት፣ ከዚኹ ተጠባቂ ውሳኔ ጋራ በቀጥታ ሊያያዝ እንደሚችል በስፋት የታመነበት እንደኾነ እየተነገረ ነው፡፡ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ መረጃው እንደደረሰው አስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጠ ሲኾን፣ እስከ መጪው እሑድ፣ ጥቃቱን በተመለከተና ሲመረምረው በሰነበተው ሰነድ ላይ መግለጫና ውሳኔ ይሰጣል፤ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሐራ ዘተዋሕዶ

 Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤