Saturday, October 14, 2017

“ወልደ አብ” በተባለ የኑፋቄ መጽሐፍ ጉዳይ: ለብፁዕ አባ ማርቆስ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ፤“ሊያስወግዝዎና ከአባልነት ሊያሰርዝዎ ይችላል”/ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ/

 • ወልደ አብ” የክሕደት መጽሐፍ እንዲታገድና ምላሽ እንዲሰጥበት፣ አሳታሚዎቹም በሕግ እንዲጠየቁ የሀገረ ስብከቱ ካህናትና ምእመናን ቀደም ሲል ያቀረቡትን አቤቱታ በዚህ ፒዲኤፍ ፋይል ይመልከቱ፡፡
†††
 • በምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ገዳማት፣ በድብቅና በስፋት እየተሠራጨ ነው
 • የሊቃውንት ጉባኤ ክሕደቱን መርምሮ እንዲያቀርብ በቋሚ ሲኖዶሱ ታዟል
 • ሊቀ ጳጳሱ፥በማውገዝ ፈንታ በዝምታ መደገፋቸው፣ ምእመናንን አስቆጥቷል
 • በንቀትና ትችት በፈጸሙት የቀኖናና የሕግ ጥሰትም፣አቤቱታው ተጠናክሯል
†††
 • በደላቸውን የሚያጣራ ልኡክ ቢመደብም፣ በፓትርያርኩ እንዲዘገይ ተደርጓል
 • ፓትርያርኩ ይኹንታ በሰጡት፣ፀረ ማኅበረ ቅዱሳን አድማቸው ቀጥለውበታል
 • ማኅበሩ፣ ከፍተኛ ድጋፍ የሰጠበትን ኹለገብ ሕንፃ፣በፓትርያርኩ ያስመርቃሉi
 • ለ5 ጊዜ አቤቱታ ቢያቀርብም፣ያልተደመጠው ምእመን፣እንዲያናግሩት ይሻል!
†††
ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የ“ወልደ አብ” መጽሐፍን ክሕደት ገልጸው ምእመናን እንይቀበሉት ቃለ ውግዘት ያስተላለፉበት ደብዳቤ


በሰሜን አሜሪካ የኒው ዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፣ ወልደ አብ እና ምሥጢረ ሃይማኖት” በሚል ርእስ በምሥራቅ ጎጃም በሚገኝ አንድ ገዳም አሳታሚነት የተሠራጨውን የክሕደት መጽሐፍ፣ የሀገረ ስብከታቸው ምእመናን እንዳይቀበሉት ያወገዙ ሲኾን፤ ኅትመቱንና ሥርጭቱን በዝምታ ተመልክተዋል፤ ያሏቸውን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስን ደግሞ፣ ስለ ቸልታቸው በመገሠጽ በጥብቅ አሳሰቧቸው፡፡
“መምህር ገብረ መድኅን እንዳለው” በተባለ ግለሰብ ተዘጋጅቶ፣ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴ/ጒንደ ወይን/ ወረዳ በምትገኘው፣ የምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት ዐጸደ ኤዎስጣቴዎስ አንድነት ገዳም አሳታሚነት የታተመው መጽሐፉ፤ ወደ ሰሜን አሜሪካ ደርሶ ምእመናንን እያወከና እያጠራጠረ እንደሚገኝ፣ ቅሬታዎች እንደ ደረሷቸው ብፁዕነታቸው ገልጸዋል፡፡
መጽሐፉ፣ “ክርስቶስ በቅብዐተ መንፈስ ቅዱስ ከበረ፤” ብሎ ምሥጢረ ተዋሕዶን በመንቀፍና መጻሕፍትን በመቆነጻጸል ያሰፈረው ክሕደት፣ በንጉሥ ሱስንዮስ ዘመን፥ ካቶሊኮች፣ ጸጎችና ቅባቶች ያሠራጩት እንደነበር ጠቅሰው፤ ክሕደቱን የተቃወሙት የተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመናን፣ እንደ በግ መታረዳቸውን እንደ ሽንኩርት መቀርደዳቸውን ዘክረዋል፡፡
የመጽሐፉ ኅትመትና ሥርጭት፣ አያሌ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ሰማዕት በመኾን የተቋቋሙትንና አባቶቻችን ሊቃውንት ጉባኤ ሠርተው የረቱትን ክሕደት መልሶ ለማምጣት የተደረገ ሙከራ በመኾኑ፣ እንዳወገዙት አስታውቀዋል፤ በሰሜን አሜሪካ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንም፣ መጽሐፉን እንዳይቀበሉት በውግዘታቸው በጥብቅ አሳስበዋል፡፡
ይኸው የክሕደት መጽሐፍ፣ በሰሜን አሜሪካ ብቻ ሳይኾን፣ በታተመበትና በድብቅ እየተሠራጨ በሚገኝበት በምሥራቅ ጎጃም፣ “በየቀበሌውና በየገበሬ ማኅበሩ ምእመናንን እያወከና እያበጣበጠ ይገኛል፤” ያሉት ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፤ ድርጊቱን የሚገታ አንዳችም ርምጃ ባለመውሰድ በቸልታ እየተመለከቱ ባሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አባ ማርቆስ ማዘናቸውንም በይፋ ገልጸዋል፡፡
 የመጽሐፉን ኅትመትና ሥርጭት በዝምታ በመመልከት የክሕደቱን መስፋፋት እየደገፉ ላሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አባ ማርቆስ የጻፉላቸው ተግሣጽና ማሳሰቢያ፤
ትላንት፣ መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ በቁጥር 158/2010፣ ለብፁዕ አቡነ ማርቆስ በአድራሻ በጻፉላቸው ደብዳቤ፣ “ወልድ ተፈጠረ”የሚል ፍጹም ውጉዝ አርዮሳዊ ትምህርት ይዞ በሀገረ ስብከታቸው በታተመውና እየተሠራጨ በሚገኘው የክሕደት መጽሐፍ፣ ክርስቶስ አምላክ እንዳልኾነ የሚያመላክት ትምህርት እየተሰጠ መገኘቱ በእጅጉ እያሳዘናቸውና እያስተከዛቸው እንዳለ ገልጸውላቸዋል – “ሰላም በክርስቶስ ስልዎ፣ እጅግ እያዘንሁ እና እየተከዝሁ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በሀገረ ስብከትዎ፣ ክርስቶስ አምላክ እንዳልኾነ የሚያመላክት ትምህርት እየተሰጠ ነው፤”ብለዋል፣ ብፁዕነታቸው፡፡
ከመጽሐፉ ገጽ 126፣ “ከእግዝእትነ ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከተከፈለ ደመ ድንግልና ጋር ተዋሕዶ ተፈጠረ፤” የሚለውን ለማስረጃነት የጠቀሱት ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፣ ወልድ ተፈጠረ” የሚለውን ትምህርት ሰምቶ ዝም ማለት ዲያብሎሳዊነት ነው፤” ሲሉ የክሕደቱን አሠቃቂነት በመግለጽ ሊቀ ጳጳሱን ብፁዕ አባ ማርቆስን ገሥጸዋቸዋል፡፡
የሊቀ ጳጳሱ ዝምታም፣ የኑፋቄው “ወራሾች ነን” ባዮች፣ ለመጽሐፉ ክሕደት ድጋፋቸውን በዐደባባይ እንዲገልጹ እያበረታታቸው እንደኾነ አመልክተዋል፡፡ የሉማሜ ወረዳ ነዋሪ የኾነና አንተነህ ምትኩ የሚባል ግለሰብ፣ በመጽሐፉ ላይ ያስተላለፉትን ውግዘት ተቃውሞ፣ “በፍጹም የቅባት መጽሐፍ፣ ከአባቶች እንደወረስነው ወደፊትም ያስተምራል፤ ይቀጥላል፤” በማለት በፐብሊክ ሚዲያ መናገሩን ብፁዕነታቸው ጠቁመው፣“የቅባቱ መጽሐፍ ያስተምራል፤ ይቀጥላል፤” የሚለው “ወልድ ተፈጠረ” የሚለውን እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
ይህ ፍጹም አርዮሳዊ ክሕደት፣ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርቱዕ ነገረ መለኰታዊ አስተምህሮ፣ ከጥንቱም መሠረት ይዞ ትርጓሜውና ምሥጢሩ ሲተነተንና ሲራቀቅ በኖረበት በጎጃም ምድር፣ ሲሰበክና ሲታወጅ በዝምታ መመልከቱ በከፍተኛ ደረጃ ሳያስጠይቃቸውና ጥብቅ ርምጃ ሳያስወሰድባቸው እንደማይቀር አስጠንቅቀዋቸዋል!! – ብፁዕ ወንድማችን አቡነ ማርቆስ፥ ይህ “ወልድ ተፈጠረ” የሚል አርዮሳዊ ክሕደትን የያዘ መጽሐፍ አስተምህሮ፣ በታላቁ ሲኖዶሳዊ መንበር ጎጃም ሀገረ ስብከት ሲሰበክና ሲታወጅ ዝም ብለው በመመልከትዎ፣ ሊያስወግዝዎና ከቅዱስ ሲኖዶስ አባልነትዎ ሊያሰርዝዎ እንደሚችል ላሳስብዎ እወዳለሁ፡፡” ብለዋል – ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፡
ብፁዕነታቸው፣ ይህንኑ የማሳሰቢያ ጦማራቸውን፡- ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤትና ለመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት በግልባጭ አስታውቀዋል፡፡
በተመደበበት ሀገረ ስብከት ለሚገኙ ገዳማት፣ አድባራትና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ካህናትና ምእመናን፣ መንፈሳዊ አባትና መሪ እንዲኾን የተሾመ የአንድ ሊቀ ጳጳስ መቅድማዊ ተግባሩና ሓላፊነቱ፣ ኖላዊነት ነው፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች፥ ሃይማኖታቸውን፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናቸውንና ኦርቶዶክሳዊ ትውፊታቸውን አጽንተው እንዲኖሩ ብርቱ ጥበቃ ማድረግ ነው! የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት፣ የሀገር ፍቅርና አንድነት በሰላም ተጠብቆ እንዲኖር መድከም ነው!!
ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፣ “ወልደ አብ” የክሕደት መጽሐፍን ከማውገዛቸውና ብፁዕ አባ ማርቆስንም ከማሳሰባቸው ቀደም ሲል፣ የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን፣ ሥርጭቱ እንዲታገድና መጽሐፉን ለማሳተም ከምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት ዐጸደ ኤዎስጣቴዎስ አንድነት ገዳም ወጭ የተደረገው ገንዘብ ተመርምሮ፣ ገንዘቡን ወጭ ያደረጉ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ ሲማፀኑ ቆይተዋል፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አባ ማርቆስም፣ ስለ ጉዳዩ ቢነገራቸውም፣ በማውገዝ ፈንታ በዝምታ ድጋፍ እየሰጡ በመኾኑ፣ ከሀገረ ስብከቱ እንዲነሡላቸውም ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመጠየቅ ላይ እንደሚገኙ ይታወሳል፡፡
ጉዳዩ የቀረበለት ቋሚ ሲኖዶስ፣ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ፣ መምህር ገብረ መድኅን እንዳለው በተባለ ግለሰብ ጸሐፊነትና በምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት ዐጸደ ኤዎስጣቴዎስ አንድነት ገዳም አሳታሚነት የወጣው፣ “ወልድ አብ እና ምሥጢረ ሃይማኖት” የተሰኘው የክሕደት መጽሐፍ፣ በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮ እንዲቀርብለት ማዘዙ ታውቋል፡፡
የብፁዕ አባ ማርቆስ ሃይማኖታዊ ችግር ግን፣ በዚሁ የክሕደት መጽሐፍ ኅትመትና ሥርጭት ብቻ ያልተወሰነ፣ ከዚያም በፊት የቆየና ዘርፈ ብዙ መኾኑን፣ ምእመናኑ፣ ካለፈው ዓመት ግንቦት 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በየጊዜው ወደ መንበረ ፓትርያርኩ እየተመላለሱ ያቀረቧቸው አቤቱታዎች ያሳያሉ፡፡ ቀኖናዊ መነሻ ያላቸውና የብፁዕ አባ ማርቆስን ስሑት አቋም የሚያጋልጡ እንደኾኑ ከዝርዝሩ ለመረዳት ይቻላል፡፡ እንደ አቀራረባቸው ለማስቀመጥ ያህል፡-
 1. ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ታኅሣሥ 28 ቀን መከበር እንደሌለበት ሲያስረዱ፣ “እንደዚህማ ከኾነ ጥምቀትም በ10፣ ግዝረቱም በ5 መኾን ይኖርበት ነበር፤” በማለት የቅዱስ ሲኖዶስን ቀኖና መጋፋታቸው፤
 2. ሰኔ ጎልጎታ የሚጸልየውን ምእመን፣ “ይህ ልብ ወለድ ነው፤ ከእግዚአብሔርም አያገናኝም፤” በማለት በጸሎቱ እንዳይጽናና ማድረጋቸውና ያልጸኑ ምእመናን በክብረ ቅዱሳን ጥርጣሬ እንዲገባቸው መኾኑ፤
 3. የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መጻሕፍት በኾነው በፍትሐ ነገሥት መሠረት፣ የጌታችን የጾም ወራት በሚታሰብበት፣ በጾመ ኢየሱስ(ዐቢይ ጾም)፥ በአርምሞ፣ በጾምና ጸሎት፣ በንሥሓና ቅዱስ ቁርባን በመቀበል፣ በሱባዔ፣ የጌታን ሕማማተ መስቀል እያሰቡ ማዘን፣ ማልቀስ የሚገባ በመኾኑ ከበሮ የማይመታ፣ የማይጨበጨብ ቢኾንም፤ ብፁዕነታቸው፥ ይህን ሥርዓት በመተው፣ ምእመናን፣ “አለመድንም፤ ከበሮ አንመታም፤ አናጨበጭብም” እያሉ፣ “እኔ ሊቀ ጳጳሱ ተቀምጩ፣ እኔ ፊታችሁ እያለሁ” በማለት በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኘው ጽርሐ ጽዮን አብማ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በተደረጉ ጉባኤያት፣ ምእመኑ ሳይፈልግ በማስገደድ በወርኃ ጾም ከበሮ አስመትተዋል፤ አስጨብጭበዋል፤
 4. የሰንበት ት/ቤቶች በአጽዋማት ጊዜ፣ ምእመኑን በማሰባሰብ፣ የጸሎተ ኪዳኑንና የቅዳሴውን ሰዓት በማይነካ መልኩ ሰዓቱን በማመቻቸት ከተጀመረ ከ25 ዓመታት በላይ የኾነውንና በአባቶች ጸሎተ ማዕጠንት እየተደረገ ይካሔድ የነበረውን የጋራ ጸሎትና ስግደት፣“አያስፈልግም፤ ይልቁንም በምትኩ ትምህርት እናስተምራችሁ፤ ያለበለዚያ ጸሎትና ስግደት አያስፈልግም፤” በማለት የተሰበሰበው ምእመን በየአጥቢያው እንዲበታተን አድርገዋል፤
 5. ብፁዕነታቸው፣ ነገረ ቅዱሳንን በተመለከተ ግራ የሚያጋባ አቋም ያላቸው ሲኾን፤ የሀገረ ስብከቱን ሰባክያነ ወንጌልን በመንበረ ጵጵስናው ሰብስበው፣ ክርስቶስን ስበኩ እንጅ አቡሀይ እሙሀይ አትበሉ፤” በማለት ስለ ቅዱሳን ያላቸውን አመለካከት ተናግረዋል፤
 6. የአብማ ጽርሐ ጽዮን ማርያም ቤተ ልሔም ሲመረቅ፣ ከባረኩ በኋላ፣ “ቤተ ልሔሙን እንደ ማብሰያ፣ ቤተ ክርስቲያኑን እንደ አዳራሽ ቁጠሩት፤” በማለት የንቀት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ራሳቸውን፥ ከኹሉም የተለየ፣ የማይገኙ፣ የማይተኩ፣ እርሳቸው ያሉትን የማይቀበል ያልዳነና ያልገባው እንደኾነ በመግለጽ በካህናቱና ምእመናኑ ላይ ትችት፣ ንቀት፣ ስድብና እርግማን የሚያወርዱት የብፁዕ አባ ማርቆስ በደል፣ በብልሹ አስተዳደር፣ በጎጠኝነትና በገንዘብ ምዝበራ እንደሚገለጽም አቤቱታው አመልክቷል፡፡
አስተዳደራዊ ችግሮች፡-
 1. ብፁዕ አባ ማርቆስ ወደ ሀገረ ስብከቱ ከመጡ ጀምሮ ብዙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ስብከቱ ቢኖሩም፣ ፊደል ይቁጠርም አይቁጠርም ከላይ እስከ ታች(ከሀገረ ስብከቱ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን) ያስያዙት በቅርብ ዘመዶቻቸው ነው፤ በአብያተ ክርስቲያናቱም ፍትሕ ርትዕ ጎድሏል፤ ጠፍቷል፤
 2. በቃለ ዐዋዲው መሠረት የተቋቋሙትን የሰንበት ት/ቤቶች፣ በ2005 ዓ.ም.፣ “ወንበዴዎች፣ ሌቦች፣ አሸባሪዎች” ብለው በሕዝብ ፊት ተሳድበው ለሰዳቢ ከመስጠታቸው በተጨማሪ፣ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ የሰንበት ት/ቤቶችን ማሸግ፤ ውስጥ ለውስጥ የሰንበት ት/ቤቶችን ማዳከም፤ ብሎም በመምሪያ ደረጃ በተሐድሶ ኑፋቄ የሚጠረጠር ሰው እንዲመራው ማድረግ፤
 3. ቃለ ዐዋዲውን ያልተከተሉ፣ ተቋማዊ መዋቅሩን የጣሱ ዝውውሮችና ሹም ሽሮች በማካሔድ ካህናት ተረጋግተው እንዳይሠሩ ማድረጋቸው፤ ለአብነት ያህል በመጡበት አምስት ዓመት ውስጥ፦ በአብማ ማርያም አራት፣ በዋሻው ቅዱስ ሚካኤል አምስት፣ በደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ አራት፣ በኪዳነ ምሕረት አምስት እና በእንድማጣ ደብረ ኢየሱስ ስድስት አስተዳዳሪዎችን በማፈራረቅ ተረጋግተው እንዳይሠሩ አድርገዋቸዋል፡፡
 4. በቃለ ዐዋዲው መሠረት እየሠሩ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት በአግባቡ የሚቆጣጠሩ የመንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ አባላትን ሕዝብ ባላወቀው መንገድ መሻርና አብያተ ክርስቲያኑን ለምዝበራ ማጋለጥ፤ ምሳሌ፡- የደብረ ሕያዋን ዋሻው ቅዱስ ሚካኤል በአንድ ወር ውስጥ አራት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላትን ሽረዋል፤
 5. “የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናችሁ፤” በሚል፣ ምእመናን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባልነት እንዳይመረጡና በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ፤ ከተመረጡም ወዲያውኑ እንዲሻሩ ማድረግ፤ ምሳሌ፡- ሉማሜና የባሕረ ጥምቀቱ ኮሚቴ፤
 6. ወደ ምሥራቅ ጎጃም ከመምጣታቸውም በፊትም ኾነ ከመጡም በኋላ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ ተስማምተው አለመሥራታቸው ቢታወቅም፣ አኹን ግን ከምንጊዜውም በላይ፣ “ማኅበሩ የሸዋ ነው፤ ዳግም ጥምቀት ያጠምቃል፤ ለራሳቸው ስለት ይቀበላሉ” እያሉ ስም ከማጥፋታቸው በተጨማሪ፣ የግለሰቦችን ስም እየጠሩ፣ “ስለት የሚቀርብላቸው ታቦት ናቸው፤” በማለት በ30/08/2009 ዓ.ም. የቅዱሰው ማርቆስን በዓል ለማክበር ለመጣው ሕዝብ በዐውደ ምሕረት በመናገር አሳዝነዋል፤ ሕዝቡም ይህን ሲሰማ ጥሏቸው ወጥቷል፡፡
 7. በዚሁ የቅዱስ ማርቆስ የንግሥ ክብረ በዓል፣ የዩኒቨርሲቲ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በግቢ ጉባኤ መንፈሳዊ ትምህርት እንዳይማሩ፣ የመንግሥት አካላት እንዲያስቆሙላቸው በመናገራቸው፣ ምሥጢሩን የሚያውቀውን ሕዝበ ክርስቲያን አንገት አስደፍተዋል፡፡
የፋይናንስ እና የቁጥጥር ችግሮች፡-
 1. የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴን ማዋቀርና ማፍረስ፤ ከብፁዕ አባ ማርቆስ ልዩ መገለጫ አንዱ፣ ኮሚቴ ማዋቀር ሲኾን፤ አንድን ፕሮጀክት ለማስፈጸም በራሳቸው መልካም ፈቃድ ካቋቋሙና ያሰቡትን የገንዘብ ማሰባሰብ ‘ፕሮጀክት’ ካስፈጸሙ በኋላ፣ ምን ያህል ገንዘብ እንደተሰበሰበና ወደፊት ምን ምን ዓይነት ሥራዎች እንደሚሠሩ ምሥጢሩን የሚያውቀውን የኮሚቴ አባል ያባርሩና እንደገና በአዲስ ያቋቁማሉ፤ ለምሳሌ፡– የሀገረ ስብከቱ የሕንፃ ግንባታ ኮሚቴና የባሕረ ጥምቀቱ ኮሚቴ፤
 2. ቤተ ክርስቲያንን ለመባረክና በጉባኤ ለጥቂት ሰዓታት ለመገኘት፣ ከፍተኛ ክፍያ መጠየቅና ዘመድ አዝማዶቻቸውን እያስከተሉ በመሔድ ለኹሉም አበል እንዲከፈላቸው ማድረጋቸው፤
በአጠቃላይ፣ ብፁዕ አባ ማርቆስ ወደ ምሥራቅ ጎጃም ከመጡበት ኅዳር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በካህናት፣ በዲያቆናትና በሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ዘንድ ያልተለመዱ፣ በርካታ እንግዳ ኹኔታዎች ተከሥተዋል፤ ምእመናንንም ግራ እያጋቡ፣ ለመናፍቃን ሰርጎ ገብነትም በር የከፈቱና የሚከፍቱ ናቸው፡፡ በሀገረ ስብከቱ ያደረሱት ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ በደል ከላይ ለማሳያ ያህል የተዘረዘሩት ብቻ አይደሉም፤ “የቤተ ክርስቲያንንና የአባቶችን ክብር የሚያስደፍሩ በመኾናቸው አላካተትናቸውም፤” ብለዋል ምእመናኑ በአቤቱታቸው፡፡
እነኚህን ዘርፈ ብዙ ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ለመፍታት ከብፁዕነታቸውና ከመንግሥት አካላት ጋራ ተደጋጋሚ ውይይት ለማድረግ ምእመናኑ ቢሞክሩም፣ ብፁዕ አባ ማርቆስ በሚያሳዩት፣ “አባታዊ ያልኾኑ ንግግሮችና ድርጊቶች” ምክንያት ውጤታማ ሊኾኑ እንዳልቻሉገልጸዋል፡፡ ይብሱኑ፣ የቤተ ክርስቲያንን እሴት የሚያንኳስሱ አሠራሮች ከዕለት ዕለት እየበዙ በመምጣታቸው፣ መዋቅሩን በጠበቀ መልኩ ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ለማቅረብ እንደተገደዱ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም መሠረት፣ ወደ ቦታው አምርተው፣ ችግሩን ጥንቃቄ በተሞላበት ኹኔታ አንድ በአንድ አጣርተው ውጤቱን በሪፖርት እንዲያቀርቡ፣ ሦስት የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ልኡካን ተሰይመው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ባለፈው ነሐሴ 23 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በቁጥር 798/1064/2009፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፊርማ ወጪ የተደረገ ደብዳቤ ለአጣሪ ልኡካኑ በየስማቸው ቢደርሳቸውም፣ ስምሪታቸው በፓትርያርኩ እንዲዘገይ ተደርጓል፤ ተብሏል፡፡
ለስምሪቱ መዘግየት የተለያዩ ሰበቦች ቢጠቀሱም፣ ኹነኛው ምክንያት ግን ከሰሞኑ ግልጽ ኾኖ እንደታየ የጉዳዩ ታዛቢዎች ይስማማሉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን፣ በዓመቱ መባቻ በአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ የ7 ሰዓት ሳምንታዊ ፕሮግራም መጀመሩን ተከትሎ ፓትርያርኩ የጫሩት ውዝግብ፣ ለብፁዕ አባ ማርቆስ፣ በሀገረ ስብከታቸው ከተነሣባቸው ሕዝባዊ ተቃውሞና ውጥረት የመሸሸጊያ ዕድል የፈጠረላቸው መስሏል፡፡ የማኅበሩን የአየር ሰዓት ለማሳገድ፣ “ከመንግሥት አጻፍኩት” ያሉትን ደብዳቤ ይዘው ከመንቀሳቀስ ባሻገር፣ በፓትርያርኩ ይኹንታ የተሰጠውንና ጥቂት አበሮቻቸው የሚሳተፉበትን አድማ በመምራትና ከዕለት ዕለት በማጠናከር ማኅበሩን እንደሚያጠፉ በግልጽ እየዛቱ ይገኛሉ፡፡
“ከጊዜው የፈጠነ ነው፤” የተባለ የኹለገብ ሕንፃ ምረቃ መርሐ ግብርም አዘጋጅተዋል፡፡ በነገው ዕለት ወደ ደብረ ማርቆስ የሚያመሩት ፓትርያርኩ፣ የፊታችን ቅዳሜ ኹለገብ ሕንፃውን እንዲመረቁ መርሐ ግብር ተይዞላቸዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ደብረ ማርቆስ ማእከልም፣ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ እንዲገኝ ጥሪ ደርሶታል፡፡ ትልቁ ምፀትም፣“ስእለት ይበላል” እያሉ በየዐውደ ምሕረቱ ስሙን ያጠፉት ማኅበረ ቅዱሳን፣ በዋናው ማእከሉና በማእከሉ ግቢ ጉባኤያት በኩል ለሕንፃው ግንባታ ከፍተኛ የገንዘብና ልዩ ልዩ ድጋፎችን ያደረገ መኾኑ ነው፡፡
ሊቀ ጳጳሱ፣ የተነሡባቸውን ዘርፈ ብዙ ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮችን ለማድበስበስ የሚሞክሩበት አጋጣሚ እንደሚኾን ከወዲሁ ቢታወቅም፣ ለአምስት ጊዜ ያህል በራሳቸው ከፍተኛ ወጪ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ እየተመላለሱ አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ የቆዩት የሀገረ ስብከቱ ምእመናንም፣ ከፓትርያርኩ ጋራ በግልጽ መድረክ ለመወያየት በእጅጉ እንደሚሹ ነው የተጠቆመው፡፡
በብፁዕ አባ ማርቆስ፣ እንደ ሕዝብ የተሰደበበትን ትችት፣ ንቀትና እርግማን ችሎ፣ በቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ መዋቅሩን ጠብቆ በትዕግሥትና በሰላማዊነት ሲያቀርብ ለከረመው አቤቱታ፣ አባታዊ ፍቅር የተመላበትና የኖላዊ ኄር ሓላፊነት የሚታይበት ኹነኛ አያያዝና ምላሽ ይጠብቃል፡፡  
Source: hare zetewahedo 
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤