Monday, October 23, 2017

ፓትርያርኩ የጠሩት የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ስብሰባ ሳይካሔድ ቀረ

  • በቦታው የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ብቻ ናቸው
  • ብዙዎቹ ዕለቱኑ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሲመለሱ እያሉም ያልተገኙ አሉ
  • እንዳይገኙ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጥብቅ አዘዋል፤እስከ አየር ማረፊያ የሸኙም አሉ
  • “ፓትርያርኩ ከቤተ ክህነቱ መዋቅር ላጡት ተቀባይነት ማሳያ ነው፤” 
†††
ትላንት በተጠናቀቀው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 36ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ፍጻሜ ማግሥት፣ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በልዩ ጽ/ቤታቸው በኩል በድብቅ ጠርተውታል የተባለው የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ስብሰባ ሳይካሔድ መቅረቱ ተገለጸ፡፡
ስብሰባው፣ ለዛሬ፣ ጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ጠዋት 3፡00 ላይ በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ተጠርቶ የነበረ ቢኾንም፣ ከአንድ ሀገረ ስብከት በቀር ብዙዎቹ ሥራ አስኪያጆች ወደ የአህጉረ ስብከታቸው በመመለሳቸው፣ አንዳንዶቹም በከተማው እያሉ ባለመገኘታቸው ሳይካሔድ እንቀደረ ተገልጿል፡፡
የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች በበኩላቸው፣ አጠቃላይ ጉባኤው የተጠናቀቀበትን መንፈስ ይዞ ስብሰባውን ማካሔዱ ፋይዳ እንደሌለው በመታመኑ፣ ትላንት ማምሻውን በተካሔደ ምክር እንዲሰረዝ መወሰኑን ነው የተናገሩት፡፡
በሥፍራው ተገኝተዋል የተባሉት፣ በብፁዕ አባ ማርቆስ የሚመራው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ዕንባቆም ጫኔ ሲኾኑ፤ ስለሚናገሩበት ጉዳይ ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ መክረው በስፋት ተዘጋጅተውበት እንደነበር ተነግሯል፡፡
ከእርሳቸው በቀር ሌሎች ተሰብሳቢዎች ባልተገኙበት ጧት፣ በመንበረ ፕትርክናው አካባቢ ለብቻቸው ሲዟዟሩ ታይተዋል፡፡ ምን እንደሚፈልጉና ምን ሊሠሩ እንደመጡ የፓትርያርኩ ረድእ መላልሰው ሲጠይቋቸውም ነበር፣ ተብሏል፡፡


የደብረ ማርቆሱ ሥራ አስኪያጅ ለአጠቃላይ ጉባኤው ባቀረቡት ሪፖርት፣ በሀገረ ስብከቱ የማኅበረ ቅዱሳንና የሰንበት ት/ቤቶች አባላት ላይ በርካታ ሐሰተኛ ውንጀላዎችን ያሰሙ በመኾኑ፤ ፓትርያርኩ ለዛሬ ጠርተውት የነበረው ስብሰባ ቢካሔድም ከዚሁ የተለየ እንደማያስረዱ ነው የተመለከተው፡፡
ፓትርያርኩ፣ “ጥብቅ መመሪያ” እያሉ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በጻፏቸው ደብዳቤዎች፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ “የሕግ አግባብነትና ድጋፍ እንደሌለውና ዛሬም ኾነ ለወደፊት በቤተ ክርስቲያን ስም እንዳይጠቀም የሚያስችል መመሪያ ተፋጥኖ ሥራ ላይ እንዲውል” አዝዘዋል፡፡
መመሪያው፣ የማኅበሩን አገልግሎት የሚያውቀውን የቅዱስ ሲኖዶስ(ቋሚ ሲኖዶስና ምልአተ ጉባኤ) ውሳኔ ያላገኘ ሕገ ወጥ በመኾኑ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ውድቅ ተደርጓል፤ ከአጠቃላይ ጉባኤው ሒደት ጋራ በተያያዘም የነበረው ተፈጻሚነት የተሸራረፈ ነበር፤ እንዲያውም፣ ጥቅሙ ለማኅበሩ አመዝኖ ፓትርያርኩ ማየትና መስማት የማይፈልጉትን ትርፍ ነው ያስገኘለት፡፡
ፓትርያርኩ፣ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችን ስብሰባ የጠሩት፣ ማኅበሩንና አባላቱን ከአህጉረ ስብከቱ ጋራ ተቀናጅተው እንዳይሠሩ በማራራቅ፣ ዳግመኛ እንዲህ ዓይነት ሪፖርት እንዳያቀርቡ መመሪያ ለመስጠት ነበር፡፡
36ኛው ዓመታዊ ስብሰባ ትላንት ቀትር ላይ ሲጠናቀቅ፣ ከዚህ በኋላ የሚኖረው ስብሰባ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ብቻ እንደኾነ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ በአጽንዖት ማሳወቃቸውና ጉባኤተኞችም ወደየሀገረ ስብከታቸው እንዲመለሱ ማሳሰባቸው፣ ፓትርያርኩ ስለጠሩት ስብሰባ እንደሚያውቁና አግባብነት ስለሌለውም እንዳይሳተፉ ለማስጠንቀቅ እንደኾነ ታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት፣ ሰኞ ለሚመጀረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ዐዲስ አበባ የሚሰነብቱት ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ሥራ አስኪያጆቻቸው በስብሰባው እንዳይገኙና ወደ የሀገረ ስብከታቸው እንዲመለሱ በጥብቅ አሳስበዋል፡፡ በተለይም፣ ፓትርያርኩ፣ በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ላይ በሰነዘሩት ዘለፋ ከተቆጡ አባቶች፣ ሥራ አስኪያጆቻቸውን እስከ አየር ማረፊያ ድረስ ሔደው የሸኙ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
“ሀገረ ስብከት” ማለት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተለይቶ የተከለለና በሊቀ ጳጳስ ወይም በኤጲስ ቆጶስ የሚመራ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ክልል ነው፡፡ በክፍሉ/በዞኑ/ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ አጠቃላይ አመራርና አስተዳደር የሚሰጥ የሥራ አስፈጻሚ አካል በመኾኑ፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ተጠሪነት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ነው፡፡ የሥራ አስኪያጁ ተጠሪነት ለሊቀ ጳጳሱ፣ የሊቀ ጳጳሱም ተጠሪነት ለቅዱስ ሲኖዶስ በመኾኑ፣ ፓትርያርኩ በራሳቸውና በቀጥታ ሥራ አስኪያጆችን ጠርተው መሰል ሕገ ወጥ መመሪያ ሊያስተላልፉ የሚችሉበት አግባብ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑም ይኹን በሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ደንቡ(ቃለ ዐዋዲው) የለም፡፡
ከሥራ አስፈጻሚው አካል በውል የተዘጋጀ የጥሪ ደብዳቤ ሳይኖር፣ ለሥራ አስኪያጆቹ በግል በመንገር ስብሰባውን የጠራው የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለፓትርያርኩ የአስተዳደር አገልግሎት ድጋፍና ለጽሕፈት ነክ ሥራዎች ብቻ የታሰበ ቢኾንም፣ ያለአግባብ ራሱን ከፍተኛ የመዋቅርና የሥልጣን አካል አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህም፣ ለሕግና ሥርዓት መዛባት፣ ለመልካም አስተዳደር ዕጦትና ለመሳሰሉት ችግሮች ቀዳዳ የከፈተ አሠራር ኾኖ እንደሚታይ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ዛሬም፣ ካለአንዱ በቀር ከ48 ያላነሱ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ‘ቦይኮት’ የተደረገው ስብሰባው፣ ከአሠራር ብልሽቱ ጋራ ተያይዞ የፓትርያርኩ ተቀባይነትና ተደማጭነት ማጣት፣ በመካከለኛው የቤተ ክህነቱ መዋቅርም በግልጽ የታየበት ተደርጎ ተወስዷል፡፡
Source: Hare Zetewahedo 

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤