Monday, October 30, 2017

የቤተክርስቲያን አባቶች በፍርድ ማጣት ሲሰቃዩ፥ ቅዱስ ሲኖዶስ ለምን ዝም አለ?

የቤተክርስቲያን አባቶች በፍርድ ማጣት ሲሰቃዩ፥ ቅዱስ ሲኖዶስ ለምን ዝም አለ?
     የጥቅምት ፲፬ የፍርድ ቤት ይህን ይመስል ነበር

§      የዋልድባ አባቶች በፍርድ እጦት እየተሰቃዩ ነው
§      የመነኮሳቱ ጉዳይ እንግዳ በሆኑ ሁኔታዎች የተሞላ ሆኗል
§      የጥቅምት ፲፬ የፍርድ ቤት ውሎ እንዴት ነበር
§      የመነኮሳቱን መጎሳቆል ሃላፊነት ማነው የሚወስደው
ዋልድባ ገዳም ላይ መንግሥት በዕቅድ ላይ የነበሩትን ሰባት ትላልቅ የስኳር ፋብሪካዎች ለማቋቋም በሚል ሰበብ በዋልድባ ገዳም ላይ መጠነ ሰፊ ጥፋት፣ በመነኮሳት ላይ እንግልት እንዲሁም ግድያ ሲፈጽም የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት በአካባቢው ባሉ ባለሟሎቹ ለበርካታ መነኮሳት መደብደብ፣ መሰቃየት፣ ብሎም ለህልፈት መብቃት ብቸኛ ተጠያቂው መንግሥት እና በአባቢው ያሉ ተላላኪዎች እንደ እነ አማናይ እና ሲሳይ መሬሳ የመሳሰሉት ብዙ ግፍ እና እንግልት በመነኮሳቱ ላይ ሲፈጽሙ እንዲሁም ግብረ በላ በመላክ ግፍ ሲያስፈጽሞ፥ ዛሬ ድረስ ለበርካታ መነኮሳይት መደፈር፣ መደብደብ እና እንግልት የደረጉ እነዚህ ሰዎች ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጡም የሚል እምነት አለን። ያኔ ነበር እንግልቱ በመነኮሳት ላይ ሲጨምር፣ የአበው አጽም ሲፈልስ፣ እንዲሁም የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ሥጋው እና ደሙ የሚፈተትባቸው ቤተክርስቲያናት ለመፍረስ ሲታቀዱ በዋልድባ ሦስቱም ማኅበራት ማለትም


፩) አበረንታንት መድኅኒዓለም
፪) ሰቋር ኪዳነ ምሕረት
፫) ዳልሻህ ኪዳነ ምሕረት  ባሉ የገዳሙ ሃላፊዎች ተወክለው ወደ አዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለሰ ዜናዊ ጽ/ቤት በዛም ተቀባይነት ሲያጡ፥ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በመሄድ የሦስቱም ማኅበራት ተፈርሞ እና በማኅተም ተደርጎ የመጣውን ደብዳቤ ለማድረስ የመጡት የዛሬው እስረኛ አባ ገብረ ኢየሱስ፥ ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስቴሩም ቢሮ ሆነ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ጭራሽ የሚቀበላቸው ቀርቶ በቅን የሚያናግራቸው በማጣታቸው ይዘው ይመጡትን ደብዳቤ በፖስታ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩም ቢሮ ለቤተክህነቱም በመላክ፣ ወደ ዋልድባ ገዳም ከመመለሳቸው በፊት የተሰጣቸውን ታሪካዊ ሃላፊነት ዝም ብለን አንመለስም ብለው ለመጀመሪያ ጊዜ ለአሜሪካው ሬድዮ ጣቢያ አማርኛው ክፍል አቤቱታቸውን ያቀረቡት። መነኮሳቱ በወቅቱ የተናገሩት ነገር ቢኖር “እኛ አፈር ጠባቂዎች ነን፥ ቦታው የመድኅኒዓለም ነው፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ግን እንዲያውቀው ፈልገን ነው” አጽመ ቅዱሳን እየፈለሰ ነው፣ ገዳሙ በዶዘር እየታረሰ ነው፣ መነኮሳቱ ላይ ማስፈራሪያ እና እንግልት እየደረሰብን ነው ብለው ነበር ለዓለም አቤቱታቸውን ያቀረቡት፥ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነበር እንደ አውሬ በደረሱበት ሲታደኑ፣ ለጠቆመ ወይም የእርሳቸውን መያዝ ለጠቆመ ኮኒዶሚኒየን እንሰጣለን፣ መንግሥት የተለያየ ማባበያ እንደሚሰጥ ሲለፍፍ የነበረው ነገር ግን እኝህ አባት ከገዳም ወደ ሌላ ገዳም ጸሎታቸውን እንኳን ሳይጨርሱ እንደአውሬ በጨለማ ሲንከራተቱ፣ ሌሎች መነኮሳት ገዳማቸውን ጥለው ስደቱ ቢደክማቸው፣ እንግልቱ ቢከብድባቸው ሃገር ጥለው ወደ ሱዳን የገቡም እንደነበሩ ልብ ይሏል።
አባ ገብረ ኢየሱስ ግን ላለፉት ፭ እና ፮ ዓመታት የነበረውን እንግልት እና ከቦታ ቦታ መንከራተት በዋልድባ ዳልሻ በሱባኤ በነበሩበት ጊዜ የዘመኑ አድር ባይ መነኮሳት ጠቁመውባቸው በጨካኞች፣ በአረመኔዎቹ የወልቃት አውራጃ ታጣቂዎች እጅ ወደቁ፣ ተደበደቡ፣ ተሰቃዩ ብዙ እንግልት ደረሰባቸው እዚህ ላይ አባ ገብረየሱስ ሲያዙ አብረዋቸው ፴፱ መነኮሳት አብረዋቸው ተባባሪ አባሪ ተብለው አብረው ተይዘው ነበር፣ ነገር ግን አባ ገብረየሱስን እና ሌሎች ሦስት መነኮሳት እና መናኞችን ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ እስር ቤት ጨለማ ክፍል ወስደው ከማን ጋር ነው የምትተባበሩት፣ የግንቦት ሰባት ጋር ነው ወይንስ ከማን ጋር ነው በሚል ስቃያቸውን ሲያበዙ፣ ዚገርፏቸው፣ በጨለማ ቤት ለሳምንታት ሲያሰቃዮዋቸው ቆይተው የዛሬ ፫ ወር ገደማ የሚሉት ቢያጡ የሚከሱበት መረጃ ቢያጡ “በሽብርተኛ ወንጀል” ተከሰው ወደ ቅሊምጦ ማረሚያ ቤት “የምድር ሲዖል” ወደ ሚባለው ቦታ ተወስደው ክስ ተምስርቶባቸው የጥቅምት ፲፬ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፣ አንዴ አቃቢ ህጉ መረጃ እያሰባሰብኩ ነው ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ፣ በሌላ ጊዜ ምስክሮችን ለማጣራት እየሞከርን ነው ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠን በሚል ላለፉት ሰባት ወራት በማዕከላዊ እስረኛ ማሰቃያ ድብደባ፣ ስቃቅ እና ሰቆቃ ሲደርስባቸው ከነበረበት ጨለማ እስር ቤት ወጥተው ወደ ቅሊምጦ ማረሚያ ቤት በሚባለው “የምድር ሲዖል” ከተወሰዱ ሦስት ወራት ተቆጠሩ ነገር ግን፣ ይሄ ሁሉ ሲሆን የቤተክርስቲያን የበላይ አካል ነው የምንለው ቅዱስ ሲኖዶስ ዝም፣ ጳጳሳቱም ዝም፣ ምዕመናንም ዝም . . . እውነትም የቀደሙት አባቶች ያሉት እውነት ነው “እማማ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፥
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ነበር ያሉት ዛሬም ይሄው ነው የሆነው እረ የቤተክርስቲያን አምላክ አንድ ይበለን፥ ሌላው ቢቀር በእስር እየተንገላቱ ያሉት መነኮሳት ወንድሞቻቸው ናቸው ሌላው ቢቀር “እግዚአብሔር ያስፈታችሁ” ማለት ማንን ገደለ? ወይንስ እንደ ተለመደው “ማርያምን! ስለ ዋልድባ ምንም የማውቀው ነገር የለም” ሊሉን ነው? አለበለዚያ ደግሞ “ዋልድባ ቢነካ እንዴት የትግራይ ሕዝብ ዝም ይላሉ?” ነበር ያሉን . . . የኢትዮጵያ አምላክ ፍርዱን ይስጣ
ዛሬ ዛሬ በመነኮሳቱ ላይ የተነሳባቸው ክስ ይልቁንም የመነኮሳትን ሃላፊነት የዘነጉ የእስር ቤት ሃላፊዎች ወይም በዚያው ያሉ አንጋቾች በመነኮሳቱ ላይ የተለመደውን የጭቃ ጅራፋቸውን እያደረሱ ነው፥ መንፈሣዊ አባት ሲባል ትልቁ እና ዋነኛው ምግባሩ በፈጣሪም የተሰጠው ሃላፊነት ደሃ እንዳይበደል፥ ፍርድ እንዳይጓደል ሆኖ እንኳ ቢሆን ደካሞችን ያጽናናል፣ ይመክራል፣ የጽድቅ መንገድን ያሳያል፣ ቃለ እግዚአብሔርን ላልደረው ሁሉ ያዳርሳል። ታዲያ የአባቶቻችን ዋነኛው ምግባራቸው ይሄ ሆኖ በተገኙበት “በምድር ሲዖል” ቅሊምጦ እስረኞችን ያጽናናሉ፣ ይመክራሉ፣ የጸልያሉ፣ ያላቸውን ለእስረኛ ያካፍላሉ፣ አብዝተው ወደ ፈጣሪያቸው ያመለክታሉ ይሄ ያልተመቻቸው የቅሊምጦ ሃላፊዎች ዛሬም በአባቶቻችን ላይ የተለመደውን እንግልት እና ድብደባ እያደረሱባቸው መሆኑን ነበር የሰማነው። ካህንን ጸሎት አቁም ይባላል እንዴ? ወታደርን መሣሪያህን ጥለህ ቁጭ በል እንደማለት ነው መነኮሳቱ ሃዋሪያዊ ሥራቸውን በደረሱበት በእስር ቤት ይሁን ወገዳም ይሁን ወይም እግዚአብሔር በፈቀደው ቦታ ሁሉ ማጽናናታቸውን፣ መምከራቸውን፣ ማስተማራቸውን፣ መጸለያቸውን እንዴት አቁሙ ይባላል? አልገባቸውም እንጂ ለእነሱም እንደሚጸልዩላቸው ባወቁት . . . ጌታም እኮ በመዋዕለ ስጋዌው በመስቀል ላይ በዋለ ጊዜ ያ ፈሪሣዊ ወታደር መጥቶ የክርስቶስን ጎኑን በጦር ቢወጋው የደሙ ፍንጣቂ በዓይኑ ብትገባ፣ ታውሮ የነበረውን ዓይኑን አብርቶለታል፥ እንዲህ ነው የእኛ አምላክ ያስተማረው ዛሬም የእርሱ ደቀ መዛሙርት መነኮሳት በእስር ቤት ለአሳሪዎቻቸው ለገራፊዎቻቸው ስቃይ እና መከራ ለሚያደርጉባቸው ሁሉ ዛሬም ይጸልያሉ።
ባለፈው የጥቅምት ፲፬ የፍርድ ቤት ውሏቸው ነበር አባቶቹ መነኮሣት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ያቀረቡት እንግልት፣ ግርፋት በዛብን ስቃያችንን አበዙብን፣ ጸሎት ተከለከልን፣ በጨለማ ቤት ተጣልን ተንገላታን በማለት ሰፋ ያለ አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት፣ የመነኮሳቱም የሕግ ተከላካይ ጠበቃም ይሄንን አስመልክቶ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታውን በጽሁፍ እና በቃል ለፍርድ ቤቱ አሰምቶ ነበር፥ ነገር ግን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የአባቶቹን የፍርድ ሂደት ሲከታተሉ የነበሩትን ዳኛ ባልታወቀ እና ባልታሰበ ሁኔታ በመቀየራቸው የፍርድ ቤቱ ዳኛ መዝገቡን በደንብ መመርመር ይኖርብኛል በሚል፣ አቃቤ ህጉም ምርመራዬን ለመጨረስ ተጫማሪ ምስክሮችን ማነገር አለብኝ በሚል ሰበብ በድጋሚ የፍርድ ሂደታቸው ለአንድ ወር ከ፲፫ ቀን እንደገና እንዲተላለፍ ተደርጎ ተመላሽ ቀጠሯቸው ለሕዳር ፳፮ ተቀጥሮ ነበር የፍርድ ሂደቱ የተጠቃለለው፥ አሁንም ይሄ ሁሉ ሲሆን በቤተክርስቲያን አባቶች ላይ ይሄንን ያህል ስቃይ እና እንግልት ሲደርስ ከቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ ከምዕመናን ወገን ይመለከተኛል ያለ ወገን ባለመገኘቱ በጣም በጣም ያሳዝናል እውነትም ይቺ ቤተክርስቲያን የማን ነች? ምዕመኗስ ምን ይሆን የምንጠብቀው? ምን ይመጣልን ይሆን? ከዚህ በፊት እኮ
፩) የጳጳሳት ቤት ሲሰበር ዝም
፪) ጳጳሳት በማንም ዋልጌ ሲደበደቡ ብሎም ለህልፈት ሲዳረጉ ዝም
፫) ገዳማት እና አድባራት በእሳት ሲጋዩ ዝም
፬) ታቦታት ሲሰረቁ፣ ብርቅዪ የቤተክርስቲያን ሃብት ሲመዘበር ዝም
፭) በ፴ ብር ደሞዝ ከሚሊዮን በላይ የሚገመተውን የቤተክስቲያን ቅርስ የሚጠብቁ አባቶች ሲደበደቡ ሲገደሉ                   ዝም
፮) ዛሬ ደግሞ “ገዳማችን እንዳይነጥፍ እንፈራለን” ያሉ መነኮሳት ላለፉት ሰባት ወራት ከማዕከላዊ እስከ ቅሊምጦ ሲሰቃዩ    
   ዛሬም ዝም
እውን ዛሬ ይህች ቤተክርስቲያን የማን ናት ተብሎ ቢጠየቅ መልስ ይኖረን ይሆን? እውን እነ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ የተወገረላት፣ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመንኮራኩር የተፈጨላት፣ እነ ቅዱስ ጳውሎስ ቁልቁል የተሰቀሉላት፣ እነ አቡነ ጴጥሮስ በጣሊያን ጥይት ደረታቸውን የተደበደቡላት እውን እነዚህ ቅዱሳን አባቶቻችን ቀና ብለው ቢመለከቱ ምን ይሉን ይሆን? በእውነት ከፊታቸው የመቆም ብቃቱ ይኖረን ይሆን? እንጃ
ያለ በደላቸው በእስር የሚሰቃዩ አባቶቻችን ረደኤታቸው በረከታቸው ይደርብን አሜን
ማስተዋሉን ያድለን
ዋልድባን እንታደግ!


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤