Wednesday, October 25, 2017

! ሰበር ዜና – ቅዱስ ሲኖዶስ: የተሐድሶ ኑፋቄ ተላላኪውን በጋሻው ደሳለኝን አውግዞ ለየ !

  • በደሉ፥ በበርካታ የምስል፣ የድምፅና የሰነድ ማስረጃዎች ተረጋግጧል
  • በደርዘን ለሚቆጠሩ ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲላገድ ቆይቷል
  • ከሐዋሳ የመጡ ልኡካን፣ በደሉንና ድፍረቱን በማስረጃ አብራርተዋል
  • የይቅርታ ዕድሎች በቂ በመኾናቸው፣ ጠርቶ መጠየቁ አላስፈለገም
  • ውግዘቱ የተላለፈው ልዩነት በሌለበት የምልአተ ጉባኤ ድምፅ ነው፤
†††

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በተደጋጋሚ የሰጠችውን የንስሐና የይቅርታ ዕድል ተጠቅሞ ከመታረም ይልቅ፣ ለማንነቷና ማዕከላዊ አንድነቷ ስጋት የኾነውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ማስተጋባት የመረጠውና በቅርቡም ክብሯን እያንኳሰሰ ለመገዳደር የዛተው በጋሻው ደሳለኝ፤ የማይታረም የጥፋት መሣሪያ እንደኾነ ያረጋገጠው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አውግዞ ለየው፡፡
ውግዘቱ የተላለፈው፣ የበጋሻው በደሎች በስፋትና በተደጋጋሚ በተፈጸሙበት የሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ቀደም ሲል ለቋሚ ሲኖዶስ በደብዳቤ ባስታወቁት መሠረት፣ በምልአተ ጉባኤ ተ.ቁ(10) የተያዘው አጀንዳ፣ በዛሬው፣ ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ የቀትር በኋላ ውሎ በታየበት ወቅት ነው፡፡
ከ1997 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ፣ ላለፉት ከደርዘን በላይ ዓመታት በጋሻው በንግግርም በድርጊትም በቤተ ክርስቲያን ላይ የፈጸማቸውን በደሎች የሚያስረዱ በርካታ የድምፅ፣ የምስልና የሰነድ ማስረጃዎች እየቀረቡ ተነጻጻሪ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ከሐዋሳ የመጡ ዐሥር ያህል ልኡካን በአስረጅነት ያቀረቡና ያብራሩ ሲኾን፤ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ሥርዓተ እምነትን፣ ክርስቲያናዊ ትውፊትንና ታሪክ በንግግርም በድርጊትም በመናቅና በማቃለል የፈጸማቸውን በደሎች የሚያስረዱ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን፣ በዘመናት ብሔራዊ አስተዋፅኦዋ የገነባችውን መልካም ስም በዐደባባይ እያንኳሰሰ “ትከሻ ለመለካካት” የዛተባቸውና የተገዳደረባቸውም ናቸው፡፡
ከተጠቀሱት ውስጥ፡- “ጋለሞታዪቱ ቤተ ክርስቲያን”፣ “ክርስቶስን ሰብካ የማታውቅ ቤተ ክርስቲያን”፣ “ከፖሊቲካ ጋራ የተጋባች ቤተ ክርስቲያን”፣ “ውሸት ሰብስባ ውሸት ስታስተምር የኖረች ቤተ ክርስቲያን”፣ “ምእመናኗን በትና ገንዘብ የምትሰበስብ ቤተ ክርስቲያን”፣… ወዘተ የሚሉት እንደሚገኙበትና እነኚህን የመሳሰሉ ሌሎችም በርካታ ነገሮች ከነማብራሪያቸው መቅረባቸው ተገልጿል፡፡


ማስረጃዎቹ ከታዩና ከተሰሙ በኋላ፣ ርእሰ መንበሩ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ “ለምንድን ነው ጠርተን የማንጠይቀው?” የሚል ሐሳብ አንሥተዋል፡፡ “አባታዊ መንፈስ ያለው ንግግር አደረጉ፤” ያሉ ምንጮች፣ በጋሻው በተደጋጋሚ እንደተመከረ፣ በቋሚ ሲኖዶስም ይቅርታ ጠይቆ ዕድል እንደተሰጠው፣ ቢሰጠውም ኾነ ብሎ እየበደለ እንዳለና እንዳልተጠቀመበት በማውሳት ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ ይህም በቂ እንደኾነና ጠርቶ መጠየቅ ሳያስፈልግ ተገቢው ውሳኔ እንዲሰጥ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
በተያዘው አቋምም፥ በጋሻው፣ ለይቅርታ የተሰጠውን የተነሣሒነት ዕድል ተጠቅሞ ከመታረም ይልቅ የተሐድሶ ኑፋቄን በዐደባባይ ማስተጋባት በመቀጠሉ፤ ቤተ ክርስቲያንን ለማንኳሰስ መዛቱና መገዳደሩ በማስረጃ በመረጋገጡ፣ ተወግዞ ከቤተ ክርስቲያን እንዲለይ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው ልዩነት በሌለበት ድምፅ ወስኗል፡፡
በጋሻው ደሳለኝ፣ እንደ ያሬድ ዮሐንስ እና በሪሁን ወንደወሰን ካሉት የኑፋቄ ግብረ አበሮቹ ጋራ፣ በልደታ ኮንዶሚኒየም ከሚገኘው የውግዙ ግርማ በቀለ “የእውነት ቃል አገልግሎት” የተወገዘ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ ድርጅት፣ ለሦስት ወራት በኑፋቄ ‘ሠልጥኖ’ መውጣቱ ተጠቁሟል፡፡
በሮሜ፣ ገላትያና ዕብራውያን መልእክታት ‘የመዳን እውነት ቃል’ ላይ ያተኩራል የተባለው ‘ሥልጠናው’፤ “ሺው መንግሥት”፣ “አስቀድሞ መወሰን” እና “መነጠቅ” በሚሉ ማደናገሪያዎች እነበጋሻውን እንዳጦዛቸው ታውቋል፡፡ “አኹን ትምህርት ያገኘነው፤ አኹን ነው የዳንነው፤ አኹን ነው የበራልን” በማለትም ሲናገር ይሰማል፡፡ ወደ ሐዋሳ አምርቶ፣ “የጥንቷ ኦርቶዶክስ ሚሽን” በማለት “ልሳንና የዘይት ፈውስ” እንደጀመረም ተጠቅሷል፡፡
ለበጋሻው መጥፋት ዋናው ምክንያት፣ “ድነናል፤ ሌላ አያስፈልግም” የሚለው ጥራዝ ነጠቅነ ነው፤ የሚሉ ታዛቢዎች፣ ዐዋቂነት የሌለበት በርካሽ የተገኘ ታዋቂነት የተነሣሒነት ዕድሉን እንዳይጠቀምበት እንዳደረገው ያስረዳሉ፡፡ በ“ልሳንና የዘይት ፈውስ” ግልጥ ኑፋቄውን ከጀመረ በኋላ አንዳንድ የቡድኑ አባላት መለየት መጀመራቸውን ተጠቅሞ፣ ባለፈው ግንቦት የተላለፈውን ሲኖዶሳዊ ጥሪ የበለጠ ማስተጋባት እንደሚያስፈልግም ያሳስባሉ፡፡
በሌላ በኩል፣ ስለ አባ መዓዛ በየነ ከዋሽንግተንና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት በተጻፈ ደብዳቤ፤ “ወልደ አብ” ስለተባለ የክሕደት መጽሐፍ ከሊቃውንት ጉባኤ በቀረበ ማጣራት የተያዙ አጀንዳዎችን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በምልአተ ጉባኤ ስብሰባው አይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍባቸው ይጠበቃል፡፡
source: Hara Tewahedo 

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

1 comment:

  1. ጥሩ ጅምር ነው ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲህ አይነት ጅምር ከጀመረ በጣም ጥሩ አካሄድ ነው፣ ምናልባት በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥም ያሉትን መናፍቃን ጠራርቶ ማውጣት ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቅ ሥራ ነው እና አባቶቻችን በርቱልን እንላለን፥ ለሠራችሁት በርካታ እና ትላልቅ ሥራዎች ላለፉት ሁለት ተከታታይ ምልዓተ ጉባኤ ለማናችንም ክርስቲያኖች ብርታት እና የመንፈሥ ጥንካሬ ይሆነናል እና አሁንም "የነብርን ጅራት ከያዙ አይለቁ" ነውና የጀመራችሁትን መልካም የምንጠራ ሥራ እስከነ ሰንኮፉ ሳታወጡ ብትቀሩ በኃላ ማመርቀዙ እና እውስጥ ሆነ እንደገና መንፈራገጡ ስለማይቀር እውስጥ ያሉትን መንግላችሁ አውጡልን እንላለን።
    መልካም ሥራ በርቱልን

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤