Monday, October 23, 2017

ፓትርያርኩ: በመክፈቻ ቃለ ምዕዳናቸው የተነሣሒነት ጥሪ ቢያቀርቡም፣ በግትርነትና ቡድንተኝነት አፈረሱት፤ ትውልዱን በጅምላ ነቀፉ

 • የምልአተ ጉባኤውን የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ አሠያየም፣ በግትርነትና ቡድንተኝነት አወኩ
 • “ስለማኅበረ ቅዱሳን አታንሡብኝ፤ በአባ ማርቆስ ጉዳይ የሚቀርብ አጀንዳ አልቀበልም፤” አሉ
 • ብፁዕ አባ ማርቆስን በኮሚቴነት ለማስመረጥ ሲሟገቱ የተመረጡት አባቶች ራሳቸውን አገለሉ
 • ከምሥራቅ ጎጃም እንዲነሡ የተጠየቀውን በመቃወም የመጡ ደጋፊዎችን ተቀብለው አነጋገሩ
 • ኮሚቴው ሊሠየም ባለመቻሉ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ባቀረባቸው 16 አጀንዳዎች ውይይቱ ይቀጥላል፤
†††
 • በበጋሻው ደሳለኝ፣በ“ወልደ አብ መጽሐፍ” እና በአባ መዓዛ በየነ ላይ የቀረቡ ጉዳዮች ተካተዋል፤
 • የጅቡቲ ሀገረ ስብከት፣ በድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሥር እንዲተዳደር ጥያቄ መቅረቡ ተገልጿል፤
 • ከግንቦት በኋላ ወደ ሀገረ ስብከታቸው ያልተመለሱት ብፁዕ አቡነ ሙሴ ጉዳይም ይታያል፤
 • ወደ ሀገር እንዲመለሱ የመጨረሻ ጥሪ የተላለፈላቸው ብፁዕ አባ ኤዎስጣቴዎስም አሉበት፤
 • በሶማሌና በኦሮሚያ ድንበር በተፈጠረው ግጭት ስለሞቱና ስለተፈናቀሉ ዜጎችም ይወያያል፤
†††
 • የ36ኛውን አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ የጋራ መግለጫ እና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ያጸድቃል፤
 • የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ ስለ መንፈሳዊ ኮሌጅ ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ይመለከታል፤
 • በገዳማት መተዳደርያ ደንብ ረቂቅ በግንቦት የሰጠውን ማሻሻያ ተመልክቶ ደንቡን ያጸድቃል፤
 • በውጭ በስደት ከሚገኙ ብፁዓን አባቶች ጋራ ተጀምሮ ስለተቋረጠው ዕርቀ ሰላም ይነጋገራል፤
 • ለ2010 ዓ.ም. የቀረበውን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በጀት ረቂቅ ያጸድቃል፤
†††


ትውልዱን፥ በራስ ወዳድነት፣ ባለመታዘዝና በተሳዳቢነት በጅምላ የወቀሱት ፓትርያርክ አባ ማትያስ፤ “ራስን በመካድ የጌታ ትምህርት በንሥሓ የመመለስ ጥሪ” ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቢያቀርቡም፣ ለሥልጣኑና ለአሠራሩ ባለመገዛት፣ የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ እንዳይሠየም ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡
በምልአተ ጉባኤው መክፈቻ ቃለ ምዕዳናቸው፥ ግልጽነትንና ታማኝነትን በማረጋገጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ “ለነገ የማይባል የቤተ ክርስቲያናችን ዓቢይ አጀንዳ ነው፤” ቢሉም፣ በብፁዕ አባ ማርቆስ ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ በደሎች እየታወከ ስለሚገኘው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የካህናትና ምእመናን አቤቱታ፤ ሕገ ወጥ ትእዛዞችን በማስተላለፍ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋራ የፈጠሩት ውዝግብ፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ተያያዥ ጉዳዮች፣ በአጀንዳነት እንዳይያዙ ግትር አቋም በማራመድ ግብዝነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ ዛሬ ሰኞ፣ ጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲከፈት ርእሰ መንበሩ ፓትርያርክ አባ ማትያስ ባሰሙት የመክፈቻ ቃለ ምዕዳን፦ “ራስን የመውደድና የእኔ አውቅልሃለሁ ዝንባሌ” የዘመናችን ባሕርየ ሰብእ መታወቂያ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
ትውልዱ፣ እንደ ትላንቱ፣ አበው ባሉት እንመራ፤ እንታዘዝ፤ አበውን እናዳምጥ፤ የሚል ሳይኾን፣ ከእናንተ ይልቅ እኛ እናውቃለንና እኛ የምንላችሁን ተቀበሉ በማለት ወደ ላይ አንጋጦ የሚናገር፤ ራስ ወዳድ የኾነ፤ መታዘዝን የሚጠላ፤ ከሃይማኖታዊነት ይልቅ አመክንዮዋዊነትን የሚያመልክ ነው፤ ሲሉ በጅምላ ወቅሰዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስትጠበቅ የኖረችውና ወደፊትም የምትጠበቀው፣ በመንፈሰ እግዚአብሔር በታጀበ ጥበብና ስልት እንጂ “ከፍልስፍና ብቻ በተገኘ የተውሶ ዕውቀት” እንዳልኾነ የጠቀሱት ፓትርያርኩ፣ “ኹሉም ሊያስብበት ይገባል፤” ብለዋል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ ስላቆየው ጥበብና ስልት ሲያብራሩም፣ “ኦርቶዶክሳዊና ሲኖዶሳዊ የኾነ የውሉደ ክህነት አመራር” እንጅ፣“የምዕራባውያንና የሉተራውያን ምክር ቤታዊና ዘመን አመጣሽ ፍልስፍና አይደለም፤” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ካህናቱ – መሪ፣ ሕዝቡ – ተመሪ የኾነበት የእዝ ሰንሰለት፤ “ካህኑ ተናገረ ማለት እግዚአብሔር ተናገረ ማለት ነው፤” ተብሎ የሚታመንበት ቅንነትና ታዛዥነት፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ጠብቆ እንዳቆየ አስገንዝበዋል፡፡
“… እንደዚያ ቢኾን ኑሮ፣ የምናያት፥ አንዲት፣ ሐዋርያዊትና ኃያል ቤተ ክርስቲያን ሳትኾን፣ የተበታተነች፣ የደከመችና መዓዛ ሐዋርያት የሌላትና የተለያት ቤተ ክርስቲያን ነበር የምናየው፤” በማለት አመልክተዋል፡፡
ጅምላ ወቀሳቸውን በመቀጠልም፣ “ራስ ወዳዱ ትውልድ” በአባቶች ላይ ተደራቢ አመራር ሰጪ፤ በአባቶች ላይ የስድብ ናዳ አውራጅ ከኾነ ውሎ ማደሩን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፣ “ከጎናችን ሳይኾኑ ከጎናችሁ አለን፤” ይላሉ ያሏቸውን በስም ያልጠቀሷቸውን ወገኖች ኮንነዋል – “ስለ ድርጊቱ አፍራሽነት አንድ ቀን ስንኳ የተቃውሞ ሐሳብ አለመሰንዘራቸው በስተጀርባው እነርሱ ራሳቸው ያሉበት እንደኾነ የሚያመላክት መስሎ አሳይቶባቸዋል፤” ብለዋል፡፡
በቃለ ምዕዳናቸው መጨረሻም፣ “የራስ ወዳድነት አመላከከት ከሚያመጣው ጥፋት መጠበቅ” የወቅቱ ዋና ጥያቄ እንደኾነ ጠቅሰው፣ መፍትሔ ያሉትን ለምልአተ ጉባኤው በአማራጭ አቅርበዋል – አኹን ዋናው ጥያቄ፣ ይህ ራስ ወዳድ የኾነውን አመለካከት ተቀብሎ የሚመጣውን ጥፋት ማስተናገድ ይሻላል? ወይስ ራስን መካድ የሚለውን የጌታ ትምህርት አሥርፆ ነገሮች ኹሉ በንሥሓ ወደነበሩበት መመለስ፤ ምርጫውን ለዚህ ዓቢይ ጉባኤ አቅርበነዋል፡፡”
የዘመኑን ትውልድና ዕውቀቱን በደፈናው ቢያጣጥሉም፣ የቤተ ክርስቲያንን ዙሪያ መለስ ምጣኔ ሀብት በሚገባ ለመያዝ እንዲሁም፣ የሰው ኃይሏን በአግባቡ ለመጠቀም “የዘመኑን አሠራር መከተል የግድ ያስፈልገናል፤” ብለዋል፡፡ በየቃለ ምዕዳናቸው እንዳስለመዱትም፣ ግልጽነትንና ታማኝነትን ማረጋገጥ የተሰኘ ተግባር የራቀውና ቁርጠኝነት የሌለበት ዐዋጃቸውም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
ቤተ ክርስቲያን ያላትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልእኮ በሚገባ ለማከናወን፣ ግልጽነትንና ታማኝነትን በማረጋገጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ለነገ የማይባል የቤተ ክርስቲያናችን ዓቢይ አጀንዳ ኾኖ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ አኳያም፣ የቤተ ክርስቲያንን ዙሪያ መለስ ምጣኔ ሀብት በሚገባ ለመያዝና ለማሳደግ እንዲሁም፣ የሰው ኃይሏን በአግባቡ ለመጠቀም የዘመኑን አሠራር መከተል የግድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ይኹንና የመክፈቻ ቃለ ምዕዳኑ፣ ግብዝነት የተመላበትና ፓትርያርኩ ራሳቸውን የሚፃረሩበት እንደኾነ ብዙዎች ታዝበዋል፡፡ ሲኖዶሳዊውን ኦርቶዶክሳዊ የአመራር ጥበብ መከተልና ለአበው መታዘዝ ከትውልዱ ጠፍቷል፤ ካሉ ግንባር ቀደሙ ተጠያቂ፣ ሌላ ማንም ሳይኾን ፓትርያርኩ ራሳቸው ናቸው፤” ይላሉ ታዛቢዎቹ፡፡ ይህም፣ ለቤተ ክርስቲያንን ለውጥና መሻሻል ታላላቅ ተስፋዎችን የፈነጠቁ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች እንዳይፈጸሙ ካመከነው አመራራቸው ብቻ ሳይኾን፣ ዛሬም በምልአተ ጉባኤው ጅማሬና ውሎ በግልጽ የታየ ነበር፡፡
Source: Hara Tewahedo


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤