Sunday, November 26, 2017

የዋልድባ አባቶች የችሎት ውሎ ከቅሊንጦ መልስ

  •   በችሎት እለት ከፍተኛ መታወክ በፍርድ ቤት ተከስቷል
  •     በኢትዮጵያ የፍርድ ቤት ታሪክ እንዲህ አይነት ረብሻ አይተን አናውቅም ብለዋል የዓይን ምስክሮች
  •     አባ ገብረ ኢየሱስ እና አባ ገብረ ሥላሴ ዘዋልድባ ወደ ዞን ፭ (የጨለማ ማሰቃያ) ተዛውረዋል
  •     አባቶች አሰቃዮቻቸውን (ደብዳቢዎቻቸውን) ኦፊሰር ካሱን ዘራችሁ አይባረክ ጥቁር ውሻ ውለዱ በማለት     ተራግመዋል ገዝተዋል
  •  ስቃያቸው እስከ መቼ ይቀጥል ይሆን 

  • አባ ገብረ ኢየሱስ


የጠዋቱ ቀዝቀዝ ያለ አየር ይነፍስ ነበር እለቱ ሐሙስ ኅዳር ፲፬ ቀን በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፪ኛ ምድብ ችሎት እንደተለመደው የተለያዩ ክስ የተመሠረተባቸው የክስ ሂደታቸው የሚታይበት ቦታ ነው፥ በዚህ ቀን ግን ከእለቱ ለየት ባለ ሁኔታ ከቅሊንጦ  በመጡ ታራሚዎች የክስ ሂደታቸው የሚታይበት ቀን በመሆኑ ሊሆን ይችላል ወይም ሁለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መነኮሳት የክስ ሂደታቸው የሚታይበት ቀን በመሆኑ ሊሆን ይችላል፥ ከሌሎች ቀናት ለየት ባለ ሁኔታ ችሎት ከአፍ እስከ ገደፉ የክሱን ሂደት የሚከታተሉ ተከታታዮች፣ የተከሳሾች ዘመድ አዝማድ እንዲሁም የፍርድ ቤቱ የህግ ሂደቱን የሚቆጣጠሩ የጸጥታ ሃይሎችን ጨምሮ በርከት ያሉ ሰዎች የሚገኝበት ፪ኛ ምድብ ችሎት የፍርድ ሂደት ሊከታተሉ የተመደቡ ሦስት የፍርድ ቤቱ ዳኞች ቦታቸውን ይዘዋል። የመሃል ዳኛው “ጸጥታ ይከበር” በማለት የችሎቱን የፍርድ ሂደት ለመጀመር ደጋግመው  በያዙትን የዳኞች መዶሻ መሰል በጠረጴዛው ላይ ያንኳኳሉ፣ የመጀመሪያዎችን ታራሚዎችን የጸጥታ ሃይሎች ወደ ችሎት እንዲያስገቡም ሊሆን ይችላል ሂደቱ በእንዲህ ያለ ቀጥሎ።


የመጀመሪያዎቹ ታራሚዎች ከወልቃይት አካባቢ ተከሰው የመጡ ታራሚዎች ሲሆኑ፤ የመሃል ዳኛው ለተከሳሾች ከባለፈው ችሎት መልስ በጽሁፍ የእምነት ቃላቸውን እንዲሰጡ በተጠየቁት መሠረት እንደተዘጋጁ ይጠይቃሉ፥ ነገር ግን የግራው ዳኛ በተቃራኒው የተለያዩ ነገሮችን ይናገራሉ በችሎቱ ውስጥ መረጋጋት አይታይም፥ የሆነ የጎደለ ወይም የተረበሸ ነገር እንዳለ የዓይን ምስክሮች ይናገራሉ፥ የሆነ ሆኖ የወልቃይት ታራሚዎች ለፍርድ ቤቱ ችግራቸውን ለፍርድ ቤቱ ደጋግመው ለማብራራት ዘግ ባለ ድምጽ ይናገራሉ ታዳሚዎች ድምጻቸው እንደማይሰማ ለማስገንዘብ ይመስላል ጉምጉታ ይሰማል፤ ታራሚው በጣም መማረር እና ተስፋ መቁረት ይታይበታል በመጨረሻ ሱሪውን በመፍታት የደረሰበትን ለፍርድ ቤቱ ለማሳየት ፈትቶ ያሳያል ፥ በመቀጠል ታራሚው "እናተው አሳሪዎች፣ እናንተው ገራፊዎች፣ እንደገና እናንተው ፈራጆች" እንዴት እንሁን እኛ በማለት በምሬት ይናገራል፥ ልቅሶ ይተናነቀዋል ያነባልም ነገርግን ሰሚው ፍርድ ቤቱ ሳይሆን ታዳሚው ብቻ ነበር ፤ በዚህ ጊዜ ነበር ፪ኛ ምድብ ችሎት ታዳሚ መቆጠር እስኪያቅተው ድረስ ከፍተኛ ጩኽት እና ጉምጉምታ የፍርዱን ሂደት እስኪቋረጥ ድረስ ሁከት ሆነ፣ ጩኽት ሆነ፣ ልቅሶ እና ጫጫታ በዛ ታራሚው ሰውነቱ ተተልትሏል፣ በብልቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ቆስሏል፣ በአጠቃላይ ሰውነቱ ከሰውነት ጎዳና ውጪ በመሆኑ የክስ ሂደቱን የሚከታተሉት ታዳሚዎች በሙሉ ይጮኻሉ፣ ያለቅሳሉ፣ እረ ምን ጉድነው የመጣብን በማለት ድምጻቸውን ያሰማሉ፤ የፍርድ ቤቱ ጸጥታ ሰራተኞች መቆጣጠር እስኪያቅታቸው ድረስ ሁከት ሆነ፥ በመጨረሻም የጸትታ ሃይሎች ታዳሚውን በሙሉ ከችሎት እስኪያስወጡት ድረስ እና የፍርዱ ሂደት እስኪቋረጥ ድረስ ከወትሮው ለየት ያለ ከበድ ያለ ብጥብጥ ተፈጠረ በመጨረሻም የክሱ ሂደት ተቋረጠ። በርከት ያሉ የዓይን ምስክሮችም እንዲህ አይነት ሁኔታ አይተን አናውቅም፥ ተከስቶም አያውቅም ይላሉ እነዚሁ የዓይን ምስክሮች።
በችሎቱ ውስጥ ሦስቱ ከወልቃይት የመጡ ታራሚዎች፣ ሁለቱ የዋልድባ ገዳም አባቶች አባ ገብረ ኢየሱስ እና አባ ገብረ ሥላሴ እንዲሁም የሕግ ጠበቆቻቸውን ጨምሮ በችሎቱ ውስጥ ሲቀሩ፥ የፍርዱን ሂደት ሊከታተሉ የመጡትን ሰዎች ግን በሙሉ በማስወጣት የፍርዱን ሂደት ለመቀጠል ይሁን ወይም ሌላ ችሎቱ በዝግ ከተከላካይ ጠበቆች ጋር ዘለግ ላለ ሰዓታት ቀጥሎ ነበር፥ በመጨረሻ ሁለቱ የዋልድባ አባቶች በጸጥታ ሃላፊዎች እየተመሩ ወደ ቅሊንጦ ወደሚወስዳቸው መኪና ይመሯቸዋል፣ ጥቂት ምዕመናን ለአባቶች የሚቀመስ ለማቀበል ሲሞክሩ መጉላላት እና ጉሸማ ደርሶባቸዋል፤ በመጨረሻም የወልቃይት ታራሚዎችም ወደመኪናቸው በመምጣታቸው ወደ ቅሊንጦ ጉዞ ሊጀምሩ በዝግጅት ላይ እያሉ፥ በድጋሚ ሁከት ሆነ ሰው ይጮኻል፣ ጉምጉምታ በዝቷል፣ የጸጥታ ሃላፊዎች ሰዉን ለማስወጣትና ጉዟቸውን ለመጀመር የተቻኮሉ ይመስላሉ በአጠቃላይ ሁኔታው በሙሉ ከወትሮው የተለየ ነበር፥ የሆነ ሆኖ የእለቱ የፍርድ ሂደት ያለምንም ቀጠሮ፥ ያለምንም መፍትሄ፥ እንዲሁ ያለምንም በቂ መልስ የታሳሪዎች ጉዞ ወደ ቅሊንጦ ይሆናል፥ የህግ ሂደታቸው ወይንም ብይን የሚታይበት ቀን ግን አይታወቅም ምን ሊሆን እንደሚችልም የገመተ ሰው ሳይኖር እንደው እንደ ዋዛ የሰው ልጅ ያለ ፍርድ ሂደት በንህዝላልነት አለፈ። የነገውስ የሚቀጥለውስ የቤተክርስቲያን አባቶች ያለፍርድ ሲጉላሉ ተመልካችም አቤት ባይም የለም ቤተክርስቲያንም ዝም፣ ምዕመንም ዝም፥ ነገር ግን አምላከ አበው አንድ ቀን እንደሚያስባቸው እሙን ነው።
አባ ገብረ ኢየሱስ እና አባ ገብረ ሥላሴ በቅሊንጦ እንደተመለሱ በቀጥታ ወደ ዞን ፭ ወደሚባለው የጨለማ እና የሥቃይ ቦታ ይዛወራሉ፥ ለምን ብለው ቢጠይቁ መልስ የለም በየእለቱ ማታ ማታ ኦፊሰር ካሱ የሚባል የጨለማ፣ የጽልመት መልዕክተኛ እለት እለት አባቶችን በመደብደብ፣ በመዝለፍ፣ በማንቋሸሽ ይህ ነው የማይባል ስቃይ እያደረሰባቸው እንደሆነ ለመረዳት ችለናል፥ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ይዞ የመጣው የእስረኛ ልብስ መልበስ አለባችሁ፣ አባቶቻችን ደግሞ በቁማችን ልብሰ ተክህኖአችንን አናወልቅም ሞትም ብታመጡብን አናወልቅም ብለው እለት ተእለት ስቃይ እያደረሱባቸው ይገኛሉ፥ ከሁሉ በተለየ ኦፊሰር ካሣሁን የሚባለው ከበድ ያለ ስቃይ እያደረሰባቸው ይገኛል፥ አባቶችም “ትውልድህ ሁሉ የተረገመ ይሁን፥ ሰባት ትውልድህ ትቁር ውሻ ውለድ” በማለት ረግመው እና ገዝተው ቢናገሩም ሰውየው ግን የሥቃይ ዱላውን እያወረደባቸው ይገኛል። “የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” ማቴዎስ ፲፮ ፥ ፲፱ እግዚአብሔርም ለቅዱሳን አባቶች በምድር ያሰሩትን በሰማይም ይታሰር ዘንድ ቃል ኪዳን አድርጎላቸዋል፥ እነዚህ ተረፈ አርዮሳውያን ይህንን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብንልም ዛሬም ድረስ በተለያየ ዘዴ እርስ በእርስ ለማጋጨት እና ወንድማማቾችን ለመለያየት ሁለቱን አባቶችም ለማጋጨት በማሰብ ይመስላል በምርመራ ጊዜ ለአባ ገብረ ሥላሴ “አባ ገብረ ኢየሱስ ተቀብለው የእስረኛ ልብሳቸውን ለብሰዋል” ስለዚህ እርሶ ነው እምቢ ያሉት እና በውድም በግድም ይለብሳሉ በማለት፥ ለአባ ገብረ ኢየሲስም “አባ ገብረ ሥላሴ ፈቃደኛ ሆነው ለብሰዋል” በማለት ሁለቱን አባቶች ለማጋጨት እና ለመለያየት እየተጠቀሙበት ያለው ዘዴ እንደሆነ አባቶቹ ሳይረዱት የቀሩ አይመስልም፤ አባቶችም በመንፈሣዊ ጥንካሬያቸው ቀጥለው በሕይወት ቆመን ልብሳችንን አናወልቅም፣ እሬሳችን ላይ ልታለብሱ ትችሉ እንደሆነ እንጂ በፍጹም ሊሆን እንደማይችል ደጋግመው ተናግረዋል። ለዚህም ይመስላል ሁለቱም አባቶች በሃሳባቸው እንደጸኑ እና የእስረኛ ልብሱን አንለብስም ልብሰ ተክህኖአችንን ወይም ቆባችንን አናወልቅም በማለታቸው፥ የየእለት ሁኔታቸው ድብደባ እና ስቃይ ሆኗል፥ የዓይን ምስክሮችም ለአባቶቻችን እንድረስላቸው፥ አለበለዚያ ግን አባቶቻችንን ከድብደባ ብዛት በሕይወት ልናገኛቸው የምንችል አይመስለንም ብለውናል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅም ታሪኳ የጥቃት ነፋሳት ሲነፍሱባት፥ የአፍራሽ ዝናማት ሲዘንሙባት፥ ምንም ነገር እንዳልደረሰባት ሆና እኛ ዘመን የደረሰችው፥ መሠረቷ በዐለት የሚመሰሉ ጠንካራ ቅዱሳን ገዳማት ስለሆኑ ነው። ከዋናዎቹ ገዳማት አንዷ የግሑሣንና የግሑሣት እናት ቅድስት ዋልድባ ናት። ኢትዮጵያ ካሏት ጥንታዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቦታዎች ዋልድባ አንዱ ብቻ ሳይሆን ዋነኛው ነው፡፡ በሰሜን ጎንደር እና በምዕራብ ትግራይ ተንጣልሎ፣ ከሰሜን ተራራዎች ሠንሠለት ግርጌ ተዘርግቶ የሚገኘው ይህ ገዳም፣ በብዙ ወጣ ገባ መልክዐ ምድሮች እና ኮረብታዎች የተሞላ፣ አብዛኛውም በደን የተሸፈነ ነው፡፡ እንደ ኤዶም ገነት አራት ጅረቶች የሚያጠጡት ሲሆን 
እንስያ በሰሜን፣ ተከዜ በምሥራቅ፣ ዛሬማ በምዕራብ፣ ዜዋ ደግሞ በደቡብ ያረሰርሱታል፡፡ የዋልድባ ገዳም ታሪክ ሳብ ብሎ ወደ መጀመርያው የክርስትና ዘመናት ይጓዛል፡፡ በ5ኛው መ/ክ/ዘ በአካባቢው በተባሕትዎ ይኖሩ የነበሩ መናንያን እንደነበሩበት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡መሥራቿ ኮከበ ገዳም ከተባሉት ሰባት ሳሙኤሎች አንዱ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሳሙኤል ከቅድስናቸው የተነሣ የዱር አራዊት ይታዘዟቸው ነበር። ጾም ጸሎት ስግደት ስላደከማቸው፥ መንፈሳዊ ተልእኳቸውን የሚያደርሱት አናብስትን ፈረሳቸው አድርገው ነበር። አቡነ ሳሙኤል ሲጸልዩ እመቤታችን ትገለጽላቸው እንደነበረ በተአምረ ማርያም ተመዝግቧል። በዚሁ ልምድ ከዕለታት አንድ ቀን ተገልጻላቸው እንዲህ ብላቸዋለች፤”ወዛቲ፡ ጸሎት፡ ዘትጼሊ፡ ወቅዳሴየ፡ ኢትኅድግ፡ በመዋዕለ፡ ሕይወትከ፡ ወለደቂቅከኒ፡ እምድኅሬከ፡ አዝዝ፡ ከመ፡ ኢይኅድጉ፡ እስመ፡ ዘይጼውዓኒ፡ በዝንቱ፡ ቅዳሴ፡ አፈቅሮ፡ በኲሉ፡ ልብየ” (“ይቺን የምትጸልያትን ጸሎትና ቅዳሴየን በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምንጊዜም እንዳትተዋቸው። የመንፈስ ልጆችህም እንዳይተዋቸው እዘዛቸው። በዚህ ቅዳሴ ስሜን የሚጠራውን በሙሉ ልቤ እወደዋለሁ”) ብላቸዋለች። “ይኸውም ሊታወቅ ዛሬ በዋልድባ በቃሉ ያጠና፥ በቃሉ ያላጠና በመጽሐፍ ቅዳሴ ማርያም ሳይደግም የሚውል የለም” ይላል የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ መቅድም። የዋልድባ ገዳም መንፈሳዊ ጥንካሬ የተመሠረተችበት ቦታ ነው። እንደሚታመነው፥ ቅድስት ማርያም፥ ቅዱስ ዮሴፍና ሰሎሜ ሕፃኑን ክርስቶስን ከንጉሥ ሄሮድስ ቁጣ ወደግብፅ ያሸሹ ጊዜ ወደኢትዮጵያም መጥተው ነበር፤ ያረፉትም ዋልድባ ነበር ።
እንግዲህ እነዚህ መነኮሳት ድምጸ አራዊቱን፣ ግርማ ሌሊቱን ታግሰው ከሰው ርቀው እራፊ ለብሰው ፍቅረ ክርስቶስ ይዟቸው በዋልድባ ገዳም ተወስነው ጤዛ ልሰው፣ ቅጠል በልተው፣ድንጋይ ተንተርሰው በገዳም ሲኖሩ ዕለት ዕለት ከፈጣሪያቸው ለፈጣሪያችን ስብሃት እያደረሱ ሲኖሩ የዘመኑ መሳፍንት ዋልድባ ገዳም ለሃገራችን ኢትዮጵያ ያበረከተው አስተዋጸዖ ተረስቶ ገዳማውያኑን በዘር በጎጥ እየለዩ፥ ከፊሉን በእስር ቤት በማጋዝ ዛሬ ድረስ ስቃይ እያደረሱባቸው እና ቤተክርስቲያኒቱን እየገደሏት ይገኛሉ። በቀደሙት ነገሥታት ዘመን የመንግሥቱና የቤተክርስቲያኒቱ ባለሥልጣኖች ሀገር የሚመሩት አብረው በመመካከርና በመተሳሰብ ነበረ። በዚያ ሰላማዊ ግንኙነት ዘመን የመኳንንቱ ታላቁ ትሩፋታቸው ለገዳማቱ ጉልት መጎለትና በቅዱሳኑ መነኮሳት መባረክና በጸሎታቸው መተማመን ነበር። ገዳማቱ ርስቱን ከሁለት ጥቅም ላይ ያውሉታል። አርሰው አምርተው የምርቱን አንዱን ክፍል ለኑሯቸው ያደርጉታል፤ ሁለተኛውን ክፍል ደግም ቊጥራቸው ከፍ ያለ ድኩማን ይረዱበታል። የዛሬዎቹ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የቤተክህነቱ ሃላፊዎች ለገዳማቱ ርስት ጎልተው በቅዱሳን አበው መባረክ ባይፈልጉም፥ ዘመናዊውን የምርት አመራረት አስተምረዋቸው የተለመደውን የድኩማን እርዳታቸውም በይበልጥ እንዲያስፋፉት ማድረግ ብሔራዊ ግዴታቸው ነበር። እነሱ ግን ይኸን በማድረግ ፈንታ ጉልታቸውን ቀምተው ለራሳቸው መበልጸጊያ አደረጉት፤ ሌላውን የሕዝብ መሬት እየቀሙ ለውጪ ሀገር ቱጃሮች ርስተ ጉልት አደረጉት። ይህ መቅሠፍትን በራስ ላይ ማምጣት ነው። ይኽ መዓት ደግሞ ጀምሯል እግዚአብሔር ሁልጊዜም ከደካሞች ጋር፥ ከተገፉት ጋር ነው አባቶቻችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ አደባባይ እንደሆነበት ጺህሙ ተነጭቷል፣ ተተፍቶበታል፣ ተገርፏል፣ ጭንቅላቱ በዘንግ ተደብድቧል ብዙ ስቃይ በዕለተ አርብ ደርሶበታል፥ ዛሬም በእነ አባ ገብረ ኢየሱስና አባ ገብረ ሥላሴ ላይ እየደረሰው ያለው ትላንት በጌታቸው በጌታችን የደረሰውን ዛሬም በእነሱ ላይ እየደረሰ ነው፣ ለእነሱ በረከት ነው ለአድራጊዎቹ ግን ወዮላቸው . . . በኤፌሶን ፮ ፥ ፲ - ፲፩ በሰፈረው ቃል መሠረት “በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ። የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።” አባቶቻችን ምንም መከራ ቢበዛባቸው የፈጣሪያቸውን የጦር ልብስ በመልበሳቸው የሚደርስባቸውን ከመጤፍ ሳይቆጥሩት ዛሬ ድረስ አሉ፥ የነገውን ግን እርሱ የሠራዊት አምላከ ሳሙኤል ያውቃል . . .
ይቆየን
የአባቶቻችን በረከት ረደኤት አይለየን አሜን

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

1 comment:

  1. አባቶቻችን እግዚአብሔር ይህን ስቃይ የምትችሉበት አጽንኦት መድኃኒአለም አይንፈጋችሁ።ለቤተክህነት እና ለኦፊሰር ካሱ ቆም ብለው የሚያስተውሉበት መድኃኔአለም ልቦና ይስጣቸው ።

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤