Tuesday, March 27, 2018

በሁለቱ የዋልድባ መነኰሳት ላይ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ባለማቅረቡ ፍ/ቤቱ ለሚያዝያ ፲፰ ቀን ፳፻፲ ቀን በድጋሚ ቀጠረ

FB_IMG_1522058589440
  • ዐቃቤ ሕግ እና ፖሊስ፣ “ምስክሮቹ ያልቀረቡበትን ምክንያት አናውቅም፤” አሉ
  • አብረውን ተከሠው ከነበሩት የምንለየውና የማንፈታው ለምንድን ነው? ያሰረንስ አካል ማን ነው?/መነኰሳቱ/
  • እግዚአብሔር አለ፤ እመቤታችን አለች፣ አትፍሩ፤ እግዚአብሔር ዐዋቂ ነው፤”/አብሯቸው የተከሠሠው ነጋ ዘላለም/
†††

በእነተሻገር ወልደ ሚካኤል ላቀው የክሥ መዝገብ “በሽብር ወንጀል” በተከሠሡት ኹለቱ የዋልድባ መነኰሳት፥ አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም(4ኛ ተከሣሽ) እና አባ ገብረ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት(5ኛ ተከሣሽ) እንዲሁም በ2ኛ ተከሣሽ ነጋ ዘላለም ላይ ምስክሮችን ለማሰማት ዛሬ ቀጠሮ የተያዘለት የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ፣ ምስክሮቹን ማቅረብ ሳይችል የቀረ ሲኾን፤ ከተከሣሾቹ አንዱ አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም በበኩላቸው፣ “አብረውን ከተከሠሡትና ክሣቸው ተቋርጦ ከተፈቱት ከ32ቱ የተለየነውና የማንፈታው ለምንድን ነው? ያሰረንስ አካል ማን ነው?” ሲሉ ችሎቱን ጠየቁ፡፡
ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማቅረብ ዳተኝነት እየታየበት እንደኾነ ባለፈው ቀጠሮ የጠቀሰው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት፣ ከአቅም በላይ የኾነ ችግር ካላጋጠመ በቀር ለዛሬ መጋቢት 18 ቀን አሟልቶ እንዲያቀርብ አስጠንቅቆት የነበረ ቢኾንም፣ አቅርቦ ሳያስደምጥ ቀርቷል፡፡
FB_IMG_1522058263409
ካህናትንና መነኰሳትን ጨምሮ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር በታደመበት የዛሬው ችሎት፣ ምስክሮቹ በምን ምክንያት እንደቀሩበት በፍ/ቤቱ የተጠየቀው ዐቃቤ ሕግ፣ ለምን እንዳልመጡ አላውቅም፤ ምንም የማውቀው ጉዳይ የለም፤ የሚል ምላሽ ነው የሰጠው፡፡
ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎቹን በጊዜው የማቅረብ ግዴታ ቢኖርበትም በተደጋጋሚ ምስክሮቹ መቅረታቸውን ያወሱት የተከሣሽ ጠበቆች፣ ፍትሕን እንደሚያጓድልና የፍ/ቤቱንም የሥራ ሒደት እንደሚያስተጓጉል አስረድተዋል፤ የዐቃቤ ሕግ፣ ምስክር የማስደመጡ ሒደት ታልፎ አለ በተባለው የሰነድ ማስረጃ ለብይን እንዲቀጠርላቸው ጠይቀዋል፡፡ የማዕከላዊ መርማሪ የኾኑት አቶ አብዲ፣ የፌዴራል ፖሊስን ወክለው ለችሎቱ መልስ እንዲሰጡ ሲታዘዙ፣ ምስክሮቹ በመቅረታቸው ዙሪያ ምንም የሚያውቁት ጉዳይ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
ፍ/ቤቱም፣ ዐቃቤ ሕግ ይኹን ፌዴራል ፖሊስ፣ ምስክሮቹ የቀሩበትን ምክንያት ባልገለጹበትና ምንም እንደማያውቁ በተናገሩበት ኹኔታ፣ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል በማለት ለሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተከሣሾች ወደ ችሎት ሲገቡ ከመቀመጫው በመነሣት አክብሮቱን የገለጸው በመቶዎች የሚቆጠር ተመልካች፣ የፍ/ቤቱን ውሳኔ በመቃወም በችሎቱ የማጉረምረም ድምፅ ማሰማቱ ታውቋል፤ የሚያለቅሱም ነበሩ፡፡
በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 32/1/(ሀ)(ለ)(38) እና በፀረ ሽብር ዐዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 ሥር የተደነገገውን ተላልፈዋል ተብለው የተከሠሡት ኹለቱ መነኰሳት፣ ዋስትና ተከልክለው በእስር አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ማስቆጠራቸውን የተከሣሽ ጠበቆች ገልጸዋል፡፡
የፍ/ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ እንደተሰማ እጃቸውን በመስቀል አምሳያ አንሥተው ለመናገር እንዲፈቀድላቸው አጥብቀው የጠየቁት 4ኛ ተከሣሽ አባ ገብረ ኢየሱስ፣ ከእኛ ጋራ በተመሳሳይ መዝገብ ተከሠው የነበሩ 32 ሰዎች በመንግሥት ዐዋጅ ተፈተዋል፤ እኛ ተለይተን የማንፈበት ምክንያት ምንድን ነው? ያሰረንስ አካል ማነው? በማለት ጠይቀዋል፡፡ የመሀል ዳኛው፣ “ስለ እርሱ እኛ የምናውቀው ጉዳይ የለም፤ እኛን አይመለከተንም፤ የበላይ አካል ያደረገው ነው፤” ብለው ሲመልሱላቸው፣ “መንግሥት እና ፍ/ቤት አንድ አይደለም ወይ?” በማለት መልሰው ጠይቀዋል፤ ዳኛውም፣ የሦስቱን የሕግ አካላት ሚና እና ልዩነት በማስረዳት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከችሎት ሲወጣ፡- “ፎቶ አንሥተሃል” የተባለ አንድ ዘማሪ፣ በፖሊስ ተይዞ ሕዝቡ እየተከተለው ነበር፡፡ ፎቶ ማንሣቱን አልካደም፤ ነገር ግን ሌሎችም ሰዎች ሲያነሡ እንደነበር ተናግሯል፡፡ ሞባይል ስልኩን ፖሊስ ተቀብሎታል፡፡ የችሎቱ ተመልካች ፎቶ እንዳያነሣ ፖሊስ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ተሰምቷል፡፡
በኹለቱ መነኰሳት ላይ መረጋጋት፣ ደስታና መጽናናት በጉልሕ ይነበብባቸዋል፡፡ ፖሊስ ለማከላከል ቢሞክርም ሕዝቡ ተሰልፎ ሰላምታ እየሰጣቸው ሳለ፣ፎቶ ሲያነሣ በተያዘው ልጅ ምክንያት የተፈጠረውን ግርግር እያዩ ሲጨነቁ ተስተውለዋል፡፡ አብሯቸው የተከሠሠው ነጋ ዘላለም ድምፁን ከፍ አድርጎ፡-እግዚአብሔር አለ፤ እመቤታችን አለች፣ አትፍሩ፤ እግዚአብሔር ዐዋቂ ነው፤ እያለ ለሕዝቡ ይናገር ነበር፡፡
source: haratewahido
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

1 comment:

  1. tmsgan egzabher amlak yaddis ababan hzb asabaw!! abat ydengl legoth bzatachow !!ahunem gan bzew tamer ytyal eser batowech bmulew yzagalew abatochachren bdel wdgandmachew bsalam ymlasalew kalech dengle maryame menem ayhonwe atasebew mchame lemanbbeb tchagrew yhanale lmanber mtsaf slmalchilebet ykeret agattmache anebewet ydengel yasreat lg

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤