Wednesday, March 21, 2018

የታሰሩት አባቶች ልብሰ ምንኵስናቸው ከመልበስ እንዳይከለከሉ ፍ/ቤት አዘዘ፤ “ክሡ የማይቋረጥበት ሕጋዊ ምክንያት አይታየኝም”/ጠበቃው/

waldiba menekosat

  • ምስክሮችን ለማቅረብ ዳተኝነት የታየበት ዐቃቤ ሕግ፣ በቂ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ምስክሮቹን በዕለቱ እንዲያቀርብ ፍ/ቤቱ አስጠነቀቀ
  • አባ ገብረ ኢየሱስ ከ“ቅጣት ቤት” ወጥተዋል፤ ኹለቱም በዞን አንድ ይገኛሉ፤ አጠቃላይ ኹኔታው የተሻሻለ መኾኑን ገልጸዋል፤
†††


(የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ፤ መለስካቸው አምኃ፤ መጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ.ም.)
በእስር ላይ የሚገኙት ኹለቱ የዋልድባ መነኰሳት፣ ሃይማኖታዊ ልብሳቸውን ከመልበስ እንዳይከለከሉ ፍ/ቤት ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በቅጣት ተገልለው የቆዩት አባ ገብረ ኢየሱስ ከቅጣት ቤት መውጣታቸው ተገልጿል፡፡ ፍ/ቤቱ፣ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዲያቀርብ ቀጠሮ ይዟል፡፡
በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት አባ ገብረ ኢየሱስ ገብረ ማርያም እና አባ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት፣ በእስር ቤቱ አስተዳደር እንዳይለብሱ ተከልክለውት የነበሩትን ሃይማኖታዊ ልብሶቻቸውን እንዲለብሱ፣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት አዘዘ፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት፣ ኹለቱ መነኰሳት በቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር የሚፈጸሙባቸውን በደሎች በዝርዝር ለፍ/ቤቱ አቤት ብለው ነበር፡፡ አስተዳደሩ፣ ኹለቱ አባቶች፣ በሥርዐተ ምንኵስናቸው የተቀበሉትን አለባበስ እንዲያወልቁ መገደዳቸውን፤ ከዚኹ ጋራ ተያይዞም የተለያዩ እንግልቶች እንደደረሱባቸው አመልክተዋል፡፡
27858893_775691875950725_6070209914328406221_nበተለይ አባ ገብረ ኢየሱስ ገብረ ማርያም፣ በቂሊንጦ እስር ቤት ዞን አምስት ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ፣ በማያውቁትና ተለይቶ ባልተነገራቸው ጥፋት ምክንያት፣ በልዩ ቅጣት ተገልለው እንደሚገኙ ለፍ/ቤቱ አቤቱታቸውን አመልክተው ነበር፡፡ ፍ//ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፣ የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር መልስ ተመልክቶ ትእዛዝ ለመስጠት እንደነበር ያስወሱት የተከሣሾቹ ጠበቃ አቶ አምኃ መኰንንየታሳሪዎች አያያዝ የተሻሻለ መኾኑን ይናገራሉ፡፡
እንግዲህ ዛሬ በችሎት ስንቀርብ፣ በእነአባ ገብረ ኢየሱስ በኩልም የተነገረኝና ያወቅነው፣ በርግጥ ከዚያም በፊት መረጃው ደርሶናል፤ ከአልባሳት ጋራ በተያያዘ የነበረባቸው ችግር እንደተፈታና መቀየሪያ የሃይማኖት ልብሳቸውም እንደገባላቸው፣ አውልቁ የሚለውም ጥያቄ እንደቆመ፤ አባ ገብረ ኢየሱስም ከዞን 5 ወጥተው ኹለቱ መነኰሳት በአኹኑ ጊዜ አንድ ላይ ዞን አንድ እንደሚገኙና አጠቃላይ ኹኔታው የተሻሻለ መኾኑን ገልጸውልናል፡፡
ፍ/ቤቱም በችሎት ላይ እንዳስታወቀው፣ የሰጠው ትእዛዝ የመነኰሳቱን መብት የሚያስጠብቅ እንደኾነ አቶ አምኃ አስረድተዋል፡፡
“ፍ/ቤቱ በኋላ ላይ የገለጸልን፣ በፍ/ቤቱም በኩል ሊነገር የነበረው ትእዛዝ ይህንኑ የመነኰሳቱን መብት የሚያስጠብቅ እንደኾነ፣ በተለይ ከአልባሳት ጋራ በተያያዘ እንዲያወልቁ ሊገደዱ እንደማይገባ የሚገልጽ ትእዛዝ እንደነበረ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንኑ ከእኛ የተነገረውን መረጃ ከሰማ በኋላ ትእዛዙ ለማረሚያ ቤቱ እንዲተላለፍ ፍ/ቤቱ አዝዟል፡፡”
ክሡ ይቋረጣል፤ የሚል ግምት በብዙዎቹ ዘንድ አለ፡፡ እንደ አንድ የሕግ ባለሞያ በዚህ ረገድ ምን እንደሚታያቸው ለአቶ አምኃ ጥያቄ አቅርቤላቸው ነበር፡፡
በክሡ መቋረጥ በኩል፣ ኹላችንም በየጊዜው በየቀጠሮው በየቀኑ የምንጠብቀው ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ ክሥ ላይቋረጥ የሚችልበት በእኔ በኩል ምንም ዐይነት የሕግ ምክንያት የለም ብዬ ነው የማምነው፡፡ በዚህ መዝገብ ላይ እንደሚታወቀው 35 ተከሣሾች ነበሩ፤ የ32ቱ ክሥ ተቋርጧል፤ የኹለቱ መነኰሳትና የአንድ ተከሣሽ ክሥ ነው ያልተቋረጠው፡፡ከክሥ ዝርዝሩ ይዘት አንጻር ሲታይ የመነኰሳቱ ክሥ ላይቋረጥ ይችላል የሚያስብል ሕጋዊ ምክንያት አይታየኝም፡፡ በርግጥ ክሡን የማቋረጥ ሓላፊነቱ የከሣሹ የዐቃቤ ሕግ ነው፡፡ እስከ አኹን ድረስ እንግዲህ ክሡን አላቋረጠም፡፡ ስለዚህ በእኛም በኩል እንደማንኛውም ኅብረተሰብ ክሡ በማንኛውም ጊዜ ይቋረጣል፤ የሚል ነው፡፡
ፍ/ቤቱ በመጨረሻም፣ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዲያቀርብ ለመጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡ አክሎም፣ የቆጠራቸውን ምስክሮች በቀጠሮ ለማቅረብ ዳተኝነት ያለበት መኾኑን ተደጋግሞ የታየ መኾኑን በማስታወስ፣ በቂ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ምስክሮቹን በዕለቱ እንዲያቀርብ ፍ/ቤቱ አስጠንቅቋል፡፡
ዐቃቤ ሕግ፣ ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ እነተሻገር ወልደ ሚካኤል በሚል መዝገብ አባ ገብረ ኢየሱስ ገብረ ማርያምንና አባ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖትን ጨምሮ በ35 ሰዎች ላይ በሽብር ወንጀል ክሥ እንደመሠረተባቸው አይዘነጋም፡፡ በአኹኑ ወቅት ከሦስቱ ተከሣሾች በስተቀር የ32ቱ ተከሣሾች ክሥ ተቋርጦ መፈታታቸው ታውቋል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤