Wednesday, March 21, 2018

የሕዝበ ክርስቲያኑን ጩኸት እግዚአብሔር ከሰማያዊት ኢየሩሳሌም ይሰማል ! እናምናለን


ሃገራችን ኢትዮጵያ ከዛሬ ፳፮ ዓመት ከ፱ ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ ለውጥ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከ፳፮ ዓመት ከ፱ ወር ድረስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ የደረሱ ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች የሰው ልጅ በሕሊናው ከሚያስበው በላይ እንደሆን ማንም ሰው ሊያጤነው የሚገባ እንደሆነ እንገምታለን፤ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች በቁጭት እንደሚመለከቱት እናምናለን።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ዋነኞቹ የቤተክርስቲያን እሴቶች ጠፍተዋል፣ የቤተክርስቲያኒቱ የእምነት መገለጫዎች ተመዝብረዋል፣ የማምለኪያ ቦታዎች በልማት ስም ተወስደዋል ፣ የቤተክርስቲያን አባቶች ተዋርደዋል፥ ክቡር የሆነውን ሕይወታቸውን ሰውተዋል፣ ቤተክርስቲያኒቱ ባለቤት እንደሌለው ለማንም መሳቂያ መሳለቂያ እስከመሆን ደርሰዋል፣ ታላላቅ ለቤተክርስቲያን ሊጸልዩ፣ ለሃገር ምሕረትን ሊያመጡ የሚችሉ አባቶች በግፍ ከትውልድ ሃገራቸው፣ ከሚወዷት ሃገራቸው ተገፍተው ተባረዋል፣ ብቻ ሌላም ሌላም ሊባል ይችላል፥ ታዲያ ይሄ ሁሉ ሲሆን ከልካይ፣ ጠያቂ፣ ኸረ የመድኅኒዓለም ያለህ ያለ ማንም አለመኖሩ እጅግ የሚያሳዝን የሚያስገርምም ነገር ነው።ባለፉት ዓመታት ፳፮ ዓመታት ውስጥ ከሆኑት ዓበይት ተግዳሮቶች ለማስታወስ ያህል ፦
፩) ፬ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ በግፍ ከመንበራቸው ተባረዋል፤

፪)  የዝቋላ አቦ ከአንዴም ሦስት ጊዜ በእሳት ዙሪያውን ተቃጥሏል፥ የሰው ክቡር ሕይውትም አልፏል፤

፫) የአሰቦት ገዳም እንዲሁ በተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ደርሶበታል የሰው ሕይወትም አልፏል፤

፬) በጅማ ካህናትና ምዕመናን በአገልግሎት ላይ እያሉ በሰይፍ ተሰይፈዋል፣ ክቡር ነፍሳቸውን ዕለት ዕለት በሚያገለግሉበት በቅድስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰጥተዋል በግፈኞች እጅ፤

፭) በጅማ ሻሾ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን ተቃጥሎ ካሕናት እና ምዕመናን አብረው ተቃጥለዋል፤

፮) በጎንደር ለዘመናት የኖረ የአቋቋምና የቅኔ ማስመስከሪያ የአብነት ት/ቤት በአንድ ሌሌት ከነሙሉ ቅርሶቹና ድንቅ መጻሕፍቶቹ ተቃጥሏል፤

፯) በባሕር ዳር ጣና ገዳማት ውስጥ ከሚገኙት ገዳማት ውስጥ ደቃ እስጢፋኖስ እንዲሁ በእሳት ተቃጥሏል፤

፰) በተለያዩ የኢትዮጵያ ገዳማት እና አድባራት የሚገኙ በርካታ ጽላቶች፣ የወርቅ መስቀሎች፣ ድንቅ እና ብርቅ ቅርሶች ተሸጠዋል በመንግስት ካድሬዎች፤

፱) ገዳመ ዋልድባ (ዋሊ) በልማት ሰበብ ሸንኮራ እናለማለን በሚል ሰበብ ገዳማውያን ተሰደዋል፣ ተደብድበዋል፣ መነኮሳይት ተደፍረው እራሳቸውን ከገደል በመወርወር ክቡር ሕይወታቸውን ሰውተዋል፤

፲) በዋልድባ አበረንታንት ገዳም በዚሁ በልማት ሰበብ ከ፬ - ፯ የሚሆኑ ዓብያተ ክርስቲያናት በዶዘር ታርሰዋል፤


፲፩) በደብረ ሊባኖስ ለዘመናት በርካቶችን ሊቃውንት ሲያፈራ የነበረው የሐዲስ እና የብሉይ አብነት ት/ቤት በበጀት እጦት በሚል ሰበብ ቤተክህነት ዘግቶት፣ ደቀ መዛሙርቱም ተሰደዋል፤ (አቡነ ጳውሎስ)

፲፪) በወልቂጤ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቤተክርስቲያን በጠራራ ጸሐይ እንዲቃጠል ታዞ፥ ጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች ሳይቀሩ ተባባሪ ሆነው የቅድስት አርሴማን ቤተክርስቲያን በቀን አቃጥለዋል፤

፲፫) በትግራይ የፍሬምናጦስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመናፍቃን ሲዋጥ እና ለመዘጋት በተቃረበበት ወቅት ቤተክህነት ምንም ማድረግ አልቻለም እንዲያው በዝምታ ምንቸገረኝ በሚል ፈሊጥ ዝም ጭጭ ብሏል፤

፲፬) ጳጳሳት የመኖሪያ በራቸው ተሰብሮ በአጉራ ዘለል በጎረምሶች ሲደበደቡ፣ ሰባ ደረጃ ወስደው ኸረ የሰው ያለህ በእጃችሁ እንዳንሞትባችሁ እያሏቸው ደካማ መነኮሳት እና ጳጳሳትን ሲለምኑ እና ሲማጸኑ እነርሱ ግን ይበልጡኑ ደካሞቹ አባቶችን በርግጫ ፣ በጡጫ በመደብደብ ለሕልፈት አብቅተዋል፤ 

፲፭) በጎንደር ሱዳን ጠረፍ አቅራቢያ የሚገኘው የሥላሴ ገዳም፣ በድንበር መካለል ወቅት ጓዛችሁን፥ እና እቃችሁን ይዛችሁ ውጡ ተብለው በርካታ መነኮሳት ለስደት ለእርዛት እና ለእንግልት ተዳርገዋል፤

፲፮) የሰቋር ዋልድባ የእናቶች ገዳም በረሃብ ምክንያት በርካታ አቅመ ደካሞችን መደገፍ አልቻልንም በማለት ወደ ቤተክህነት ሦስት መነኮሳይትን በላከ ጊዜ፥ በስድብ ውርጂብኝ ካከናነቧቸው በኋላ ወደ ቦታችሁ ተመለሱ ተብለው ለመመከሻቸው እንኳን ለመጓጓዣ አጥተው ተጉላልተው ያለምንም ተመልሰዋል፥ የቤተክርስቲያኒቱን ምዕመን እግዚአብሔር ይጠብቅልንና እነሱ በሰጧቸው ጥቂት ገንዘብ በሰላም ወደ ባዕታቸው ከትንሽ የነፍስ ማቆያ ጋር ሊመለሱ ችለዋል፤

፲፯) የዋልድባ አበረንታንት ዘቤተ ሚናስ መነኮሳት በሦስቱም የዋልድባ ማኅበራት ተወክለው “ገዳማችን አይፈርስም” በማለት አቤቱታ ይዘው በመጀመሪያ በቤተክህነት፥ ቀጥሎም በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ቢሄዱ እጅግ ጸያፍ ስደብ እና እንግልት ደርሶባቸው፣ “እናንተ ደፋሮች የሃገር መሪ ለማነጋገር ትመጣላችሁ? መንግሥት ቦታውን ከፈለገው ምትክ ይሰጣችኃል እንጂ መከልከል አትችሉም” ተብለው ተባረዋል፤

፲፰) በመቀጠል እነዚህ የዋልድባ ልዑካን ተቀባይ በማጣታቸው ለአሜሪካው የሬደዮ ጣቢያ አማርኛው ክፍል መግለጫ በመስጠታቸው እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደ ወንጀለኛ ሲሳደዱ ቆይተው ከጸሎታቸው ተጓጉለው፥ ሱባዔ አቋርጠው ፍርክታ ለፍርክታ፥ ጫካ ለጫካ ሲንገላቱ ቆይተው፤ በመጨረሻ ከ፮ ዓመታት እንግልት በኃላ በመንግሥት ጆሮ ጠቢዎች ተጠቁሞባቸው ለእሥር ተዳርገዋል፤

፲፱) ለእሥር የተዳረጉት መነኮሳት እና ረድዕ እንሁም ዲያቆናት በጠቅላላው ወደ ፴፱ እንሚሆኑ በዕለቱ የዓይን ምስክሮች ሲገልጹ፥ ነገር ግን ከአባ ገብረ ሥላሴ እና አባ ገብረ ኢየሱስ በስተቀር ወደ ፴፭ የሚጠጉት በአካባቢው የተለያዩ  በጸለምት አውራጃዎች በእሥር እንደሚገኙ ይታወቃል፤

፳) ሁለቱ መነኮሳት ግን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ለ፭ ወራት በማዕከላዊ የማሰቃያ እሥር ቤት የሽብር ተሳታፊዎች ናችሁ በማለት ምድራዊ ስቃይ ሲያሰቃዩዋቸው ከቆዩ በኃላ በ፮ኛ ወራቸው ወደ ቅሊንጦ እሥር ቤት በማሸጋገር በመጀመሪያ ከሌሎች ፴፭ ሰዎች ጋር በአንድ መዝገብ አሸባሪ ተብለው ተከሰሱ፣ በመቀጠል የምንኩስና ልብሳችሁን ካላወለቃችሁ በሚል ሰበብ ዕለት ዕለት ድብደባ እና እንግልት ብሎም በጨለማ ቤት መጣል የመሳሰሉ እንግልቶች የዕለት ግብራቸው እስኪመስል ድረስ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፤ ዛሬ ዛሬማ ጭራሽ የአባቶቻችንን በአደባባይ እንደ ወንጀለኛ እጃቸውን በእግር ብረት ታሥረው ሲጎተቱ ባየት እጅግ ልብ የሚነካ ከመሆኑም ባሻገር፥ ይሄ በደል መንግሥት ላለፉት ፳፮ ዓመታት ርትዕይት ቅድስት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለማሸማቀቅ፣ አንገት ለማስደፋት የተደረገ ደባ እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል፥ በተለይ በቤተክርስቲያን ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን ጥፋት እና በደል ስንመለከት በቀጥታ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በበረሃ እያለ በማኒፌስቶው ገልጾ ሲሰራበት እንደነበረው ሁሉ ቤተክርስቲያንን ለማሸማቀቅ እና ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ የሚሆን ትውልድ እንዳይኖር የማድረግ ጥረታቸው እንደሆን ግልጽ ነው፤

፳፩) በባሕር ዳር የጥምቀተ ባሕር ታቦት ማደሪያ ቦታ በልማት ሰበብ ተወሰደ፤

፳፪) በፍሠሃ ገነት የቅድስተ ማርያም ቤተክርስቲያን ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ መንገድ ልንሠራ ነው በሚል ሰበበ በቀን በግሬደር አፈረሱ፤

፳፫)  የብሔረ ፅጌ ቅድስተ ማርያም ቤተክርስቲያን ቦታ ተወስዶ ለመንግሥት ሰዎች ለባለጊዜዎች ተሰጥቶ በሁለት እና ሦስት ብር ኪራይ በወር እየከፈሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ የሚያስገኝ ገራዦች ተከፍተውበታል፤

፳፬) ጠቅላይ ቤተክህነት ካሏት ፳፪ መምሪያዎች ውስጥ ከ፲፱ በላይ የሚሆኑት በኃላፊነት የሚመሩት በመንግሥት ካድሬዎች (የመንግሥትን ጉዳይ አስፈጻሚዎች ወይም የአንድ ጎጥ ቋንቋ ተናጋሪዎች) ናቸው፤

፳፭) የየረር በዓታ ለማርያም ቤተክርስቲያን ሆን ተብሎ እሳት ተለኩሶበት ከባድ የሆነ የእሳት አደጋ ሊያደርስ ችሏል፤

ሌላም ሌላም ሊባል ይችላል፥ ታዲያ ይሄ ሁሉ ነገር ምን ያሳየናል? ቤተክርስቲያኒቱ ተቋርቋሪ ትውልድ እንድታጣ፣ አባቶችም ከራሳቸው እና በዙሪያቸው ካሉ ነገሮች ችግር እስከሌለባቸው ድረስ በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰው መዓት በመካድ፣ ሰምተንም ዓይተንም አናውቅም በማለት ዛሬ ላይ ለደረስንበት ወይንም በሥልጣን ላይ ያለውም መንግሥትም ያለከልካይ የቤተክርስቲያኒቱን ማዕከላዊ አመራር በመያዝ በምዕመናን ላይ ሞትን፣ መከራን፣ እንዲሁም በቤተክርስቲያን ላይ መታመንን እንድታጣ እና ማዕከላዊ አስተዳደሯ እንዲላላ ምዕመናን በአባቶቹ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው፣ ማድረግ ዋነኛ ዓላማቸው ነው።

ዛሬ ላይ የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን በሁለት እና ከዚያም በላይ ጎራ ለይተው አንዱ አንዱን እንዲያወግዝ፥ ሌላው ሌላውን ይሄ ወፈ ግዝት ነው በማለት ምዕመኑ እምነቱን በሙሉ በማጣቱ ብሎም ወደ ሌላ እምነት እንዲኮበልል እና፥ ቅድስት ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ላይ የነበራትን ተደማጭነት እንዲሁ ደሃ እንዳይበደል ፍርድ እንዳይጓደል የማድረግ ሥራዋን በትክክል እንዳትወጣ በዚህም ምክንያት ምዕመናን እምነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ ግልጽ ነው ለዚህም ደግሞ ማሳያው ላለፉት አንድ ዓመት ከስድስት ወራት የዋልድባን አባቶች በእሥር አሥሮ በሽብርተኛ ስም መክሰስ፣ በአንድ መዝገብ ከተከሰሱት ፴፭ ሰዎች ውስጥ በሙሉ በነጻ ሲለቀቁ፥ የዋልድባ አባቶች ብቻ እስከ ዛሬ ድረስ በእሥር እንዲሰቃዩ አሁንም ድረስ በድብደባ በስድብ እና የምንኩስና ልብሳቸውን እንዲያወልቁ በሚል ሰበብ ግፍ ሲፈጸምባቸው፣ ብሎም እጃቸውን እንደ ወንጀለኛ አሥሮ ማንገላታት እና ዓለም እንዲያየው ማድረጋቸው በሙሉ ለዚህ ለምንለው ቤተክርቲያኒቱን ከመናቅ እና ምዕመናኗንም ምንም ሊያደርጉ አይችሉ ብለው ከመናቅ እና ተቆርቋሪ ትውልድ እንደሌላት “ባለቤቱን ካልፈሩ፥ አጥሩን አይነቀንቁ . . .” እንደሚባለው መሆኑ ነው፥ ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ሸፍጥ እስከ መቼ መቀጠል አለበት????
እንግዲህ ምዕመናን ቀደም ብለን እንዳልነው በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ካሕናትን በቤተመቅደስ ገሏል፣ ቤተክርስቲያንን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ የሚፈተትበትን ቤተመቅደስ ያለምን ማስጠንቀቂያ አፍርሷል፣ ምዕመናን በአደባባይ በጥይት ተደብድበው ተገለዋል፣ ጽላቶቻችን፣ ቅዱሳት እና ብርቅዬ የቤተክርስቲያናችን ቅርሶች ተመዝብረው በአውሮፓ እና በአሜሪካ ገበያ ላይ ውለዋል፣ ምዕመናን የሚያምኑት እና የሚፈሩት አባት እስዲያጡ ድረስ አባቶችን እምነተ ቢስ እና ለበጎቹ የማይራራ እረኛ አድርገውታል፣ የቤተክርስቲያኒቱን የሥነ-ምግባር እና የእምነት መሠረቶች በሚያናጋ መልኩ በየመምሪያው የሰገሰጓቸው ዋልጌ እና አግድም አደግ ካድሬዎች በሚያደርጉት ሙስና እና የሥነ-ምግባር ጉድለት ምዕመኑ በሙሉ በአጠቃላይ በእምነቱ ተስፋ እየቆረጠ ሄዷል፣ ጥብዓት የሞላቸውን ብርቱዎን አባቶች በእሥር በማስገባት እና በማንገላታት፣ እጃቸውን እንደ ወንጀለኛ በካቴና አሥሮ በአደባባይ ማንገላታት ኸረ ምኑ በቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘርዝሮ ለማቅረብ ብዙ ጊዜ እና በርካታ የተለያዩ ማሳያዎችን ማቅረብ ቢቻልም ለዛሬ ያቀረብነው በቂም ባይሆን መነሻ እንደሚሆን እናምናለን።

ለዛሬ በዚህ ይቆየን፥ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ከመቼውም በበለጠ ልጆቿን የምትሻበት እና እንባዋን የሚያብስ ልጅ የምትፈልግበት ጊዜ እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል በማለት ለዛሬ በዚሁ እንቋጫለን። በቀጣይነት ተከታዩን ይዘን እስክንመለስ ቸር ይግጠመን በማለት።

በሃገራችን ኢትዮጵያ በተለየዩ ጊዜያት በመንግሥት ታጣቂዎች ሕይወታቸውን ላጡት ነፍሳቸውን በገነት እንዲያኖርልን፥ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲያድልልን እንመኛለን።

ኢትዮጵያ ሃገራችንን እና ሕዝቦቿን በረደኤት ይጠብቅልን አሜን።  

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤