
- ከወንጀል ክሡ በመለስ፣ ሃይማኖታዊ ክብሯ በዐደባባይ ሲዋረድ ዝምታን መምረጧ ምነዋ ያሰኛል፤
- በፓትርያርኩ አማካይነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ስጦታ ማበርከቱ፣“ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምፀት ነው፤”
- ጉዳዩ በምእመኑና በሌሎችም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ትኩረት እያገኘ ነው፤ የቤተ ክህነቱ ዝምታ አነጋጋሪ ኾኗል፤
†††
በእነተሻገር ወልደ ሚካኤል ክሥ መዝገብ በሽብር ወንጀል ተከሠው በቂሊንጦ እስር ቤት በሚገኙት ኹለቱ የዋልድባ ገዳም መነኰሳት ጉዳይ፣ ቤተ ክርስቲያን ድምፅዋን አለማሰማቷ አነጋጋሪ መኾኑን ብዙኃን መገናኛዎች እየዘገቡ ነው፡፡
ዛሬ ቅዳሜ፣ መጋቢት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ታትመው የወጡት ቁም ነገር እና ግዮን መጽሔቶች፥ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት፣ ኹለቱ አባቶች ልብሰ ምንኵስናቸውን ከመልበስ እንዳይከለከሉ ትእዛዝ መስጠቱን በመጥቀስ፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታት ቤተ ክርስቲያን ዝምታን መምረጧ እያነጋገረ መኾኑን ዘግበዋል፡፡

ኹለቱን መነኰሳት ለእስር የዳረጋቸው፣ መንግሥት በዋልድባ ገዳም አካባቢ የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ሲጀምር፣ “ይዞታችን አይነካብን” በማለታቸው እየከረረ በሔደው ውዝግብ ሳቢያ መኾኑን ያወሳው ቁም ነገር መጽሔት፤ ከተመሠረተባቸው የሽብር ወንጀል ክሥ በመለስ፣ ሃይማኖታዊ ክብራቸው በዐደባባይ ሲዋረድ ከቀኖናው አንጻር ቤተ ክርስቲያን ዝምታን መምረጧ ምነው ያሰኛል፤ ብሏል፡፡
“ቤተ ክርስቲያን የእምነት አባቶቹን አቤቱታ አልሰማችም ለማለት ያስቸግራል፤ በሃይማኖት ቀኖናዋ መሠረት ከተከሠሡበት የወንጀል ክሥ በመለስ ሃይማኖታዊ ክብሯ በዐደባባይ ሲዋረድ ዝምታን መምረጧ ምነው ያሰኛል፡፡መነኰሳቱ ቢያንስ ልብሳቸውን እንደለበሱ በማረሚያ ቤት እንዳይቀመጡ የተፈጸመባቸው በደል፣ “የሃይማኖቶችና እምነቶች ነጻነት ተከብሮባታል” በምትባለዋ አገራችን መደረጉ አነጋጋሪ ነው፡፡ ጉዳዩን የሠሙ የመንግሥት ባለሥልጣናትም፣ ሕግ የማስከበር ሓላፊነታቸው እንደተጠበቀ ኾኖ ዜጎች ሃይማኖታዊ ሥርዐታቸውን እንዳይፈጽሙ የሚከለከሉበት አግባብ ምን እንደኾነ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይገባል፡፡ይህ በእንዲህ እያለ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ “ለሃይማኖቶች እኩልነት ለሠሩት አስተዋፅኦ” በሚል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ስጦታ በቅዱስ ፓትርያርኩ አማካይነት መስጠቱ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምፀት ነው፡፡የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፣ በፖሊቲካዊና ተያያዥ ጉዳዮች ለእስር የተዳረጉ ግለሰቦች ክሣቸው ተቋርጦ እንዲለቀቁ ኾኗል፡፡ በርካታ ፖሊቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ከእስር ተለቀዋል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ደግሞ በእነተሻገር ወልደ ሚካኤል ክሥ መዝገብ ተከሠው ከነበሩት 35 ተከሣሾች መካከል 32ቱ ክሣቸው ተቋርጦ ተፈተዋል፡፡ ይኹን እንጅ 2ኛ ተከሣሽ ነጋ ዘላለም መንግሥቴ፣ 4ኛ ተከሣሽ አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም እና 5ኛ ተከሣሽ አባ ገብረ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት ብቻ ክሣቸው ሳይቋረጥ ቀጥሏል፡፡ ክሣቸው ለመን አልተቋረጠም? አጥጋቢ መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ነው፡፡መነኰሳቱ እንደሚለቀቁ የብዙዎች እምነት ነበር፡፡ አንዳንድ ብዙኃን መገናኛም፣ ኹለቱ የዋልድባ መነኰሳት ሊለቀቁ እንደሚችሉ የሚገልጽ ዘገባ ሠርተው ነበር፡፡ ይኹን እንጅ እንደተባለው ሳይኾን ቀርቷል፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝበ ክርስቲያኑን ጨምሮ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡”
ግዮን መጽሔት በበኩሉ፣ የኹለቱ የዋልድባ ገዳም አባቶች ጉዳይ በሕዝበ ክርስቲያኑና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ ትኩረት እያገኘ መኾኑን ጠቅሶ፣ “የደረሰባቸውን ግፍና ሠቆቃ በተመለከተ በሀገር ቤት የሚገኘው ቤተ ክህነት ዝምታ አነጋጋሪ ኾኗል፤” ሲል ዘግቧል፡፡
source: haratewahidoመነኰሳቱ በማዕከላዊ በነበሩ ጊዜ በጨለማ ቤት ውስጥ ለቀናትና ለሳምንታት በማቆየትና ቶርች በማድረግ፣ የምንኵስና ልብሳችሁን አውልቁ፤ እየተባሉ ከፍተኛ ድብደባ ሲፈጸምባቸው እንደቆዩ ለችሎት ሲገልጹ ቆይተዋል፤ ፍ/ቤቱም፣ መነኰሳቱ ሃይማኖታዊ ልብሳቸውን ከመልበስ እንዳይከለከሉ ወስኖላቸዋል፡፡መጋቢት 10 ቀን በዋለው ችሎት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ድጋፋቸውን አሳይተዋቸዋል፡፡ አንድ ሰዓት ዘግይተው የተሠየሙት ዳኞች፣ የመነኰሳቱን ጉዳይ በሦስተኛ መዝገብ የተመለከቱት ሲኾን፤ ቅያሪ ልብሰ ምንኵስናቸው እንዲገባላቸው፤ ተለያይተው መታሰራቸው ቀርቶ በአንድ ላይ እንዲኾኑ በቀደመው ችሎት የሰጡት ትእዛዝ ተፈጻሚ መኾኑን ካረጋገጡ በኋላ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለመጋቢት 18 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡የዋልድባ መነኰሳት እየደረሰባቸው ያለውን ግፍና ሠቆቃ በተመለከተ፣ በሀገር ቤት የሚገኘው ቤተ ክህነት ዝምታ አነጋጋሪ ኾኗል፡፡
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!
No comments:
Post a Comment
እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤