Wednesday, March 28, 2018

የታሰሩት የዋልድባ መነኰሳት: በሕግ ፊት እኩል ኾኖ የመታየት መብታቸው ተጥሷል – ጠበቃው

FB_IMG_1522057967519
  • የ32ቱ ክሥ የተቋረጠበትና የ3ቱ ተከሣሾች ሳቋርጥ የቀረበት የሕግ ምክንያት አልተገለጸም፤
  • የሥነ ሥርዓት ሕጎች ተለጥጠው ከተተረጎሙ በተከሠሡት ላይ የማይመለስ ጉዳት ያስከትላል፤
  • በተለይም በታሰሩ ሰዎች ላይ፣ አለ የተባለ ማስረጃ በሰዓቱ ቀርቦ የተፋጠነ ፍትሕ ይሰጣቸው፤
  • በፍርድ ሒደት ነጻ ቢባሉም እንኳን፣ ጉዳታቸው የበዛ እንዳይኾን ዐቃቤ ሕግ ሓላፊነቱን ይወጣ
  • በቂ ማስረጃ ባልቀረበበት ኹኔታ ፍ/ቤቱ፥“ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ”ያለው ሊያነጋግር ይችላል፤
  • ከሣሹ አካል፥ በሕግ ፊት የተከሠሡ ሰዎች እኩል መኾናቸውን ለማረጋገጥ፣ ትልቅ ዋጋ በመስጠት ከተለዋጩ ቀጠሮ በፊት የሚወስነው ውሳኔ ካለ እንጠብቃለን፡፡
†††

(የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ፤ መለስካቸው አምኃ፣ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም.)
እነተሻገር ወልደ ሚካኤል በሚል የክሥ መዝገብ የ”ሽብር ወንጀል” ክሥ የተመሠረተባቸው የዋልድባ ገዳም መነኰሳት አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም እና አባ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት እንዲሁም አቶ ነጋ ዘላለም ላይ ዐቃቤ ሕግ ቆጥሬአቸዋለኹ ያላቸውን ምስክሮች ዛሬ ሳያቀርብ ቀረ፡፡
መዝገቡ ቀደም ሲል የተቀጠረው፣ ምስክሮቹን በዛሬ ዕለት አቅርቦ እንዲያሰማ የነበረ ቢኾንም፣ ዐቃቤ ሕግ ሊያስረዳ ባልቻለው ምክንያት የቆጠራቸው ሦስቱ ምስክሮች አልቀረቡም፤ ብሏል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ከወትሮው በተለየ ኹኔታ ፖሊስ እነዚኽን ምስክሮች እንዴት ሊያቀርባቸው እንዳልቻለ እንኳ ለፍ/ቤቱ ለማስረዳት አልኾነለትም፡፡
ፍ/ቤቱ ቀደም ሲል በነበሩ ቀጠሮዎች፣ ዐቃቤ ሕግ በጥንቃቄና ሳይዘነጋ ምስክሮቹን በቀነ ቀጠሮው እንዲያቀርብ ሲያስጠነቅቀው ቆይቶ የነበረ ቢኾንም፣ እንደ ትእዛዙ አልተፈጸመም፡፡ ይኹንና ዐቃቤ ሕግ፣ አንድ ተጨማሪ ቀጠሮ ተሰጥቶት ምስክሮቹን እንዲያቀርብ ፍ/ቤቱን ጠይቋል፡፡
የተከሣሽ ጠበቆች፣ የዐቃቤ ሕግን ጥያቄ ተቃውመዋል፡፡ ደንበኞቻችን ከታሰሩ አንድ ዓመት ከሦስት ወር አልፏቸዋል፡፡ ስለኾነም ዐቃቤ ሕግ በማናቸውም በከሠሣቸው ሰዎች በተለይም በታሰሩ ሰዎች ላይ አለኝ ያለውን ማስረጃ በሰዓቱ በማቅረብ የታሰሩ ሰዎች የተፋጠነ ፍትሕ እንዲያገኙ፣ ምናልባት በፍርድ ሒደት ነጻ ቢባሉም እንኳ የሚደርስባቸው ጉዳት የበዛ እንዳይኾን ሓላፊነቱን መወጣት ሲኖርበት ይህን አላደረገም፤” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
አክለውም፣ ፍ/ቤቱ ያልተቀበለው ቢኾንም እኒህ ሰዎች ተከሣሾች፣ ክሣቸው ተቋርጦ ከተፈቱት 32 ተከሣሾች ጋራ በአንድ መዝገብ የተከሠሡ መኾናቸውን ለፍ/ቤቱ አስታውሰዋል፡፡ ከጠበቆች መካከል አቶ አምኃ መኰንን ይህን ነጥብ ለአድማጮች ይበልጥ እንዲያብራሩ ጠይቀናቸው ነበር፡-
በእኛ በኩል እስከ አኹንም ድረስ፣ የ32ቱን ክሥ ያቋረጠበትን መስፈርት(ምክንያት) እና የእኒህን የሦስት ተከሣሾች ሳያቋርጥ የቀረበት ግልጽ የሕግ ምክንያት የተነገረ ነገር የለም፤ እኛም የምናየው ነገር የለም፡፡ ከዚህ አንጻር ተከሣሾቹ በሕግ ፊት እኩል ኾኖ የመታየት መብታቸው ተጥሷል፤ የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ይህንንም ለፍ/ቤቱ ገልጸናል፡፡ በርግጥ ፍ/ቤቱ፣ ይህ ነጥብ ፍ/ቤቱን የሚመለከት አይደለም፤ በሚል አልተቀበለውም፡፡

Lawyer Amha Mekonen
ከተከሣሽ ጠበቆች አንዱ አቶ አምኃ መኰንን (ፎቶ: ጌታቸው ሺፈራው)


ከዚህም በተረፈ ዐቃቤ ሕግ በተደጋጋሚ ምስክሮቹን በታዘዘበት ጊዜ እንዲያቀርብ ተነግሮት ያልፈጸመ ስለኾነ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ታልፈው በሰነድ ማስረጃዎች ለደንበኞቻቸው ብይን እንዲሰጥ የተከሣሽ ጠበቆች ጠይቀዋል፡፡ ፍ/ቤቱ የኹለቱን ወገን ክርክር ካዳመጠ በኋላ የዐቃቤ ሕግን ክርክር ውድቅ ማድረጉን ለችሎት ገልጿል፡፡ የተከሣሽ ጠበቆችን ክርክር ሕጋዊነት እንደተቀበለ ገልጾ፣ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ሲባል ለዐቃቤ ሕግ አንድ ተጨማሪ ዕድል በመስጠት፣ ሚያዝያ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ምስክሮቹን እንዲያሰማ ቀጠሮ ቆርጧል፡፡
አቶ አምኃ መኰንን በፍ/ቤቱ ውሳኔም ያላቸውን አስተያየት አካፍለውናል፡-
በእኔ በኩል የሥነ ሥርዐት ሕጉ ግልጽ ነው፡፡ በተለይም በወንጀል ጉዳይ የሥነ ሥርዐት ሕጎች በጣም በጥንቃቄና በጠባቡ መተርጎም አለባቸው፡፡ ተለጥጠው የሚተረጎሙበት ኹኔታ ካለ በተከሠሡና በተለይ በታሰሩ ሰዎች ላይ የማይመለስ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ዐቃቤ ሕግ በቂ ምክንያት አላቀረበም፡፡ ፍ/ቤቱም ይህን አረጋግጧል፤ ተቀብሏል፡፡ እንግዲህ ከዚያ በኋላ ደግሞ ፍ/ቤቱ በራሱ መንገድ ለትክክለኛ ፍትሕ ሲባል ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በቂ ማስረጃ ባልቀረበበት ኹኔታ ትክክለኛ ፍትሕ ምን ማለት ነው የሚለው ሊያነጋግር ይችላል፡፡ ይኼ የፍ/ቤቱ አቋም ስለኾነ በጸጋ ተቀብለን የሚቀጥለው ቀጠሮ ላይ ምስክሮች የሚቀርቡ ካሉ ወይም ከዚያ በፊት በከሣሹ አካል፣ በሕግ ፊት የተከሠሡ ሰዎች እኩል መኾናቸውን ለማረጋገጥ፣ ትልቅ ዋጋ በመስጠት ከዚያ በፊት የሚወስነው ውሳኔ ካለ እንጠብቃለን፡፡

ዐቃቤ ሕግ፣ ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ እነተሻገር ወልደ ሚካኤል በሚል መዝገብ፣ አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያምን፣ አባ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖትንና አቶ ነጋ ዘላለምን ጨምሮ በ35 ሰዎች ላይ በሽብር ወንጀል ክሥ እንደመሠረተባቸው አይዘነጋም፡፡ በአኹኑ ወቅት ከሦስቱ ተከሣሾች በስተቀር የ32ቱ ተከሣሾች ክሥ ተቋርጦ መፈታታቸው ታውቋል፡፡


source: haratewahido
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤