Monday, July 2, 2018

የአ/አበባ ካህናት:በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር ፓትርያርኩ እንዲያወያዩዋቸው ጠየቁ፤ ለሥራ አስኪያጁ አቀባበል ያደርጋሉ

aa dio parishes plea2
  • የዘረኝነት ምደባ የሚታረምበትን የመዋቅርና አሠራር ማሻሻያ ይጠይቃሉ፤
  • የብልሹ አገልጋዮች ሥነ ምግባርንና የሰብአዊ መብቶች መጠበቅን ያነሣሉ፤
  • የምእመናን ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የሚያገኙበት አያያዝ አጀንዳቸው ነው
  • የተሟሟተው ስብከተ ወንጌል በትሩፋት ሰባክያን እንዲነቃቃ ያመለክታሉ፤
  • ሥራ አስኪያጁ፣ በ7ቱም ክፍላተ ከተማ ተከታታይ ውይይቶችን ያደርጋሉ
†††


ባለፈው ረቡዕ፣ ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ረፋድ፤ በመንበረ ፓትርያርኩ ቅጽር የታየው የአቤቱታ አቅራቢዎች አሰላለፍ ከወትሮው የተለየ ድራማዊ መልክ ነበረው፡፡ የቋሚ ሲኖዶሱን ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ ታሳቢ አድርገው ጥያቄያቸውን ለማቅረብ በኹለት ተቃራኒ ቡድኖች የተሰባሰቡ ተሰላፊዎች በትይዩ ቆመው ተፋጠዋል፡፡ ኹሉም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አጥቢያዎች በሓላፊነትና በሠራተኝነት ያሉም የነበሩም ቢኾኑም፤ ጎይትኦም ያይኑ ከሥራ አስኪያጅነት መታገዱንና መነሣቱን ተከትሎ ሊወሰዱ ይገባሉ በሚሏቸው ርምጃዎች ዙሪያ ልዩነት እንዳላቸው ተነግሯል፡፡
በቅኔ ዘራፊ የታገዘውና የሥራ አስኪያጁን መባረር የሚደግፈው አንደኛው ቡድን ሌላኛውን፣ ጥቅም አስጠባቂ አድመኞች የተሰበሰቡበት እንደኾነ ሲተች ተሰምቷል፡፡ ርምጃው፣ ጎይትኦምን በማንሣት ሳይገታ፣በጥቅም የተሳሰሩት የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍሎች ሓላፊዎች በሙሉ ተጠርገው በአዲስ እንዲተኩ ቡድኑ ጠይቋል፡፡ ሌላኛው ቡድን በአንጻሩ፣ ጎይትኦምን የመከላከል ዓላማ እንዳለውና የግል ጥቅም አስጠባቂ እንደኾነ የተሰነዘረበትን ትችት አስተባብሏል፡፡ ይልቁንም ጥያቄው፣ የግለሰቦች ብቻ ሳይኾን፣ ሥር ነቀል የመዋቅርና የአሠራር ለውጥ ማምጣት እንደኾነ ገልጿል፡፡
በአ/አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤትና በታላላቅ ገዳማትና አድባራት ያለው ሹመትና ዕድገት፣“ለአንድ ወገን ያደላና በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፤” የሚለው ቡድኑ፣“የዋና ክፍሎች ሓላፊዎች በሙሉ ይነሡ” የሚለውን ባይቃወምም፣ ርምጃው፣ ዕውቀትንና አገልግሎትን ማእከል ባደረገ የመዋቅርና የአሠራር ለውጦች ሊደገፍ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ድንጋጌ መሠረትም፣ከልዩ ሀገረ ስብከቱ ነባራዊ ኹኔታ ጋራ የተገናዘበ የቃለ ዐዋዲ ማሻሻያ እንዲደረግና በዚህም ጉዳይ ገዳማቱንና አድባራቱን ያሳተፈ ሰፊ ውይይት ማካሔድ እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል፡፡
ይኸው ቡድን ጥያቄዎቹ እንዲመለስለት ያመለከተው፣“ለሀገረ ስብከቱ አዲስ ሥራ አስኪያጅ ከመሾሙ በፊት” ቢኾንም፤ ጎይትኦም ያይኑ ተነሥቶ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ መመደባቸው የተገለጸው፣ በዕለቱ የተካሔደው የቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ እንዳለቀ ነበር፡፡ ከቋሚ ሲኖዶሱ የወቅቱ አባላት አንዱ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ከስብሰባው እንደወጡ ከአዳራሹ ፊት ለፊት በትይዩ ለቆሙት ሰልፈኞች፣“ጥያቄያችሁ ተመልሶላችኋል” በማለት ምደባውን ሲያስታውቁ፣ድጋፉን በጭብጨባና በውዳሴ የገለጸው አንዱ ቡድን ብቻ ነበር፡፡ ጎይትኦም እንዲነሣና በሕግ እንዲጠየቅ የወተወተው ይኸው ቡድን፣“የዋና ክፍሎች ሓላፊዎችም በአዲስ ይተኩ!” የሚለው ጥያቄው ገና ምላሽ ይጠብቃል፡፡
የመዋቅርና የአሠራር ለውጥ አቀንቃኙ ቡድን በበኩሉ፣ አዲሱን ሥራ አስኪያጅ ተቀብሎ አብሮ እንደሚሠራ እየገለጸ ቢኾንም፤ ከወር በፊት እየተሰበሰብኩ ስመክርበት ቆይቻለሁ፤ በሚለው እንቅስቃሴው እንደሚገፋበት ገልጿል፡፡ከተሿሚው ሥራ አስኪያጅ ጋራ እንደሚነጋገርበትና ዓላማውም፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፉ ተግባራት የሚታረሙበትና የአገልጋዩ መብቶች የሚጠበቁበት፣ በምእመናን የሚነሡ ጥያቄዎችም ፈጣን ምላሽ የሚያገኙበትን ኹኔታ መፍጠር እንደኾነ አስታውቋል፡፡ አዲስ አድማስ እንደዘገበውም፣ የውይይት መርሐ ግብሩ፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ እንዲጠራ ነው የጠየቀው፡፡
የኹለቱም ቡድኖች ጥያቄዎች መግፍኤ፣ ከግለሰብ ተሳታፊዎቻቸው ሥነ ምግባራዊ አቋምና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በሰፈነው የጎሠኝነትና ጥቅመኝነት ትስስር ያላቸው የኋላ ታሪክ እየተጠቀሰ የተለያዩ ትችቶች እየተሰነዘረበት ይገኛል፤ በጥርጣሬ ከመታየትም አልዳነም፡፡ ኾኖም፣ በመደመር ሲታይ፣ ነገ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. አቀባበል የሚደረግላቸው ሥራ አስኪያጁና ምክትላቸው የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ዕቅድና ተግባር የሚጠቁመው ነገር እንዳለው አጠያያቂ አይኾንም፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ካህናትና ሠራተኞች፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በሀገረ ስብከቱ አሠራሮች እና የምእመናን አቤቱታዎች ጉዳይ ላይ ሰብስበው እንዲያነጋግሯቸው ጠየቁ፡፡
ከሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት የተውጣጡት ካህናቱና ሠራተኞቹ ባለፈው ረቡዕ፣ ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በራሷ የውስጥ አስተዳደራዊ ችግር ምክንያት፣ ክብሯና ልዕልናዋ እየተዳከመ፣ ተደማጭነቷና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እየቀነሰ ነው፤ ብለዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን የቀደመ ስም ለመመለስና ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በአግባቡ እንድትወጣ ለማስቻል፣ የአስተዳደር ችግሮቿን መፍታት ወሳኝ እንደኾነ የጠቀሱት ካህናቱ፣በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ችግሮች ላይ፣ ከቅዱስ ፓትርያርኩ እና ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋራ መወያየት እንፈልጋለን፤ ብለዋል፡፡
aa dio parish heads and clergies
ከ14 ያላነሱ ዐበይት ነጥቦችን ባካተተው ማመልከቻቸው፥ምዝበራን እያስፋፋ በሚገኘው የጎሠኝነት አደረጃጀት፣ በአገልጋዮች ሥነ ምግባርና የሥራ ላይ መብቶች እንዲሁም በሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ አመልክተዋል – ካህናቱ፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ሌብነትንና ግብረ ሰዶማዊነትን ጨምሮ በአገልጋዮች አስከፊ የሥነ ምግባር ብልሽት ምክንያት ክብሯን አያጣች ነው፤ ያሉት ካህናቱ፤ እነኚህን ችግሮች ለማረም ሰፊና ጥልቅ ውይይት እንሻለን፤ ብለዋል፡፡ በመወያየት የሚደረስበት የጋራ መግባባትና እርሱንም ተከትሎ የሚወሰዱ የማሻሻያ ርምጃዎች፥ በጎሠኝነትና ጥቅመኝነት ላይ የተመሠረተ ዓምባገነናዊና አድሏዊ አስተዳደር፣መንፈሳዊ ታማኝነትንና ዕውቀትን ማእከል ባደረገ የመዋቅርና የአደረጃጀት ማሻሻያዎች የሚታረምበትን፤ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚሰፍንበትን፣ በአጠቃላይ ክህነትንና ሞያን የሚያስከብር የሕግ የበላይነት ለማስፈን እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍሎች ሓላፊዎች በሙሉ እንዲነሡና የጥቅም መረቦቻቸው ተለይተው በሕግ እንዲፈተሽ አክለው የጠየቁት ካህናቱ፤ ግለሰቦችን ከማይገባቸው ሓላፊነት ከማንሣት ባሻገር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክና ሐዋርያዊ ተልእኮ በሚመጥን ደረጃ ከጎጠኝነትና ጥቅመኝነት የጸዳ የአስተዳደር መዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር እንደ አዲስ እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡
በአሠሪ እና ሠራተኛ ድርሻችን፣ በሠራተኛ ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅና ከምእመናን በሚመጡ አስተያየቶች ዙሪያ በአጠቃላይ፣ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር ላይ ከቅዱስነትዎ እና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋራ ለመነጋገር መርሐ ግብር እንዲያዝልን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ከ150 ባላነሱ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ፊርማ የተደገፈው ይኸው ጥያቄ፣ ባለፈው ረቡዕ በተካሔደው የቋሚ ሲኖዶስ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ ወቅት በንባብ እንደተሰማና ሀገረ ስብከቱን በበላይነት በሚመሩት በቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል ምላሽ እንደሚሰጥበት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሠራተኞች በኩል ተገልጾልናል፤ ብለዋል ካህናቱ፡፡
በተደጋጋሚ ከሀገረ ስብከቱ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች፣ አቤቱታ የቀረበባቸውና ከሥራ አስኪጅነታቸው ባለፈው ሳምንት ዐርብ በቅዱስ ፓትርያርኩ የታገዱት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው በምትካቸው መ/ር ይቅርባይ እንዳለ ባለፈው ረቡዕ መመደባቸው ታውቋል፡፡
Mmr Yikerbay Endale2
አዲስ የተመደቡት ዋና ሥራ አስኪያጁ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ እና ምክትላቸው መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሐና፣ ከነገ በስቲያ ሰኞ፣ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ተጠቁሟል፡፡ይህንም ተከትሎ፣ የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት ጨምሮ የ7ቱ ክፍላተ ከተማ አብያተ ክህነትንና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሓላፊዎችን፣ ካህናትና ሠራተኞችን በየደረጃው ያሳተፈ ተከታታይ ውይይትይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
source: ሐራ ዘተዋሕዶ


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤