Monday, July 2, 2018

ሥራ አስኪያጁ መ/ር ይቅርባይ:“ደላሎች ይውጡ፤ የክህነት ልዕልና ይመለስ፤መናፍቅ የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ አይብላ!”ሲሉ የጋራ ተጋድሎ ጥሪ አቀረቡ

mmr yikirbay endale sene2010a
 • ሓላፊነታቸውን በስኬት እንዲወጡ፣ለየአጥቢያ አሳራጊዎች የ3 ቀን ጸሎት ታዘዛላቸው፤
 • በደማቅ ጭብጨባ የተደገፈው ንግግራቸው፣ በቅኔም፣ ኹለተኛው ዐቢይ” አሰኛቸው፤
 • የፈረጅያ ሥር ኑፋቄ፣በልማት ስም መነገድና ክህነትን ማዋረድ ይቁም፤ሲሉ አስጠነቀቁ
 • ሓላፊዎች ከድላላ ተግባራት እንዲታቀቡና የሥራ ሰዓትን አክብረው እንዲሠሩ አሳሰቡ፤
 • ጊዜው ይናገራል፤በሩን ለባለጉዳዮች ክፈቱ፤ መዋቅር ጠብቁ/ብፁዕ ዋና ሥ/አስኪያጁ/
†††
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ውድቀት፣ “ከግለሰቦች ብልሹ ጠባይዕና ሥነ ምግባር” የተነሣ መኾኑን ያስገነዘቡት አዲሱ ተሿሚ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ፣“ደላሎች ይውጡ፤ የክህነት ልዕልና ይመለስ፤ መናፍቅ የቤተ ክርስቲያንን እንጀላ አይብላ!” ሲሉ የጋራ ተጋድሎ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ዛሬ ሰኞ፣ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ረፋድ፣በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ በተከናወነው ደማቅ የአቀባበል መርሐ ግብር ላይ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዐደባባይ እየተሰደበች ያለችው በአገልጋዮቿ ብልሹ ሥነ ምግባር ምክንያት እንደኾነ በአጽንዖት የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ ስሕተቱን በማረም ስድቧን ለማራቅና ክብሯን ለማስመለስ፣ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያሉ መላ ሓላፊዎች፣ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች፤ዘርንና ጎሣን ሳይቆጥሩ በጋራ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስቸጋሪ አድርገውታል፤ለብዙ ውድቀትም ዳርገውታል፤ ያሏቸውን “የግለሰቦች ብልሹ ተግባራት” የዘረዘሩት ሥራ አስኪያጁ፣ “ከሰብኣ ዓለም እንኳ የማይጠበቅ” በማለት ነው አስከፊነታቸውን የገለጹት፡፡ በኑፋቄ ተወናብደው ካጣናቸው ይልቅ፣በአገልጋዮች ብልሹ ሥነ ምግባር ሳቢያ ከእናት ቤተ ክርስቲያን የራቁትና የኮበለሉት እንደሚበዙም አስረድተዋል፡፡
ሐቀኞችና የተማሩት የሚገባቸውን ቦታና ዋጋ እንዳያገኙና እንዲንገላቱ ያደረገው “የደላሎች ሰንሰለት” መኾኑን በመጥቀስ፣ በሥራ አስኪያጆች እና በሠራተኞች መሀል ያሉት ደላሎች ይውጡ! ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ለድለላ ሲባል ከቢሮ ውጭ የሥራ ሰዓት መባከን እንደሌለበትና ሓላፊዎች፣ ቤተ ክርስቲያንን ቀን ከሌሊት ደክሞ የሚያገለግለውን ባለጉዳይ፣በጊዜ በሥራ ቦታቸው ተገኝተው ክብሩን ጠብቀው በሥርዐቱ ማስተናገድ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
Mmr Yikirbay Endale sene2010b
ጎሠኝነትና ጥቅመኝነት ባየለበት ሀገረ ስብከት፣ ዐቀብተ እምነት እንዲርቁና እንዲሸማቀቁ በማድረግ የዕቅብተ እምነት አገልግሎቱ በመዳከሙ፣ የኑፋቄው ወኪሎች በመዋቅሩ መሰግሰጋቸውን በጠቆመው ንግግራቸው፣የቀሚስ ውስጥ ኑፋቄ ይቁም፤ የፈረጅያ ሥር ኑፋቄ ከቤተ ክርስቲያን ይውጣ፤ መናፍቅ የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ አይብላ፤ ብለዋል፡፡ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሓላፊዎች፣ ለፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተጋድሎ ትኩረት በመስጠት ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡
መ/ር ይቅርባይ አያይዘውም፣ ክብረ ክህነትንና ክብረ ምንኵስናን የሚያስደፍሩ አገልጋዮች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መክረዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መገልገያና ክብር የኾነውን መስቀሏን፣ ቆቧን፣ ቀሚሷን ለብሶ በየመጠጥ ቤቱና በአልባሌ ቦታ መታየት ይቁም፤ ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ይልቁንም የቀደሙትን አበው ሥነ ምግባር በመመለስ ለክህነት ልዕልና መጠበቅ እንዲጥሩ አዘክረዋል፡፡
በልማት ስም፣የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ከአካባቢ የገበያ ዋጋ በታች በብላሽ እያከራዩ መብቷንና ጥቅሟን አሳልፈው የሚሰጡ፣ በምትኩ የግል ጥቅማቸውን የሚያካብቱ የአድባራት አስተዳዳሪዎች መኖራቸውን ያረጋገጡት መ/ር ይቅርባይ፣ “አቁሙ፤ ክብራችሁን ጠብቁ” ሲሉ አስጠንቅቀዋቸዋል፡፡ “ይቁም በሚል ቃለ አጋኖ እየታጀበ የቀረበው የሥራ አስኪያጁ ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር፣ አላግባብ በተፈጸመ ቅጥር በየአጥቢያው ተከማችተው የአገልግሎት ድርሻቸውን ግን በደጀ ጠኚ እንዲሸፈን እያደረጉ በመደበኛ የሥራ ሰዓት በመነገድና በመደለል የሚያተርፉባትን ጮሌዎችንም እንደማይታገሡ የተጠቆመበት ነው፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መልካም ስምና ዝና እንዲሁም የክህነትን ልዕልና የሚፃረሩት እኒህ ብልሹ ተግባራት፣ ከሥራ አስኪያጅ እስከ አጥቢያ ሠራተኞች ያሉት የተዘፈቁበት መዋቅራዊ መኾኑን በመግለጽ ምልዓቱን አስረድተዋል፡፡መናፍቃኑን አውግዞ መለየት ሲቻለን፣ በጉያዋ የተቀመጡ ክርስቲያን ያልኾኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ማን ያውግዝልን?”የሚያሰኝ በመኾኑ፣ “በጋራ ኾነን ብልሹ አሠራርን አርመን ወደ መልካም አስተዳደር እናምጣ፤” ሲሉ የተጋድሎ ትብብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በነባሩ ብልሹ አስተዳደር ከሥራ በመታገድና በመፈናቀል ከሞራላዊ ጉዳት አንሥቶ ግፍ የተፈጸመባቸውን አገልጋዮችና ሠራተኞች፣ በራሳቸውና በጽ/ቤታቸው ስም ይቅርታ የጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፣ የእያንዳንዳቸውን ጉዳይ አጣርተው መፍትሔ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል፡፡
Megabe Tibeb Minase Woldehana
ምክትል ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሐና
ከምክትል ሥራ አስኪያጁና በቀጣይነት ከሚመደቡ ሓላፊዎች ጋራ በመኾን ብልሽቱን ለማረምና ቤተ ክርስቲያንን ከነቀፋ ለመታደግ በጋራ የሚያደርጉት ጥረት ይሠምርላቸውም ዘንድ፣ ለመላው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አሳራጊዎች የሦስት ቀን ጸሎት እንዲታወጅላቸው፣ በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙትን፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስን ጠይቀዋል፡፡
ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ መ/ር ይቅር ባይ እንዳለ በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሐና በምክትል ሥራ አስኪያጅነት በቅዱስ ፓትርያርኩ መመደባቸውን የሚገልጸውን የሹመት ደብዳቤ፣ በመርሐ ግብሩ መግቢያ በንባብ አሰምተዋል፤ ጉባኤተኛውም በደማቅ ጭብጨባ አቀባበል አድርጓል፡፡ “አስተዋይ ልጅ ነው፤” በማለት ስለ ሥራ አስኪያጁ መስክረዋል- ብፁዕነታቸው፡፡ “የእኛው ልጅ [የጠቅላይ ጽ/ቤት ባልደረባ] ሙሽራ ስለኾነ፣ እኛ ሚዜዎች ኾነን መጥተናል፤” ሲሉም ፈገግ አሰኝተዋል፡፡
their graces the arcbishops“ጊዜው ይናገራል፤ በሩን ለባለጉዳዮች ክፈቱ፤”በማለት ያከሉት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የሀገረ ስብከቱ አካሔድ፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሚተላለፉ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን በማስፈጸም መዋቅርንና አሠራርን የሚያስከብር ሊኾን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ የቅዱስነታቸውን መልእክት ያስተላለፉት፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የውጭ ጉዳይ መመሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊም፣ተሿሚዎች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ ሓላፊዎችና ሠራተኞች በጋራ እየተመካከሩ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው በቃለ ምዕዳናቸው አሳስበዋል፡፡
በዚሁ የአቀባበል ሥነ ሥርዐት ላይ ቅኔ የሰጡ አንድ አገልጋይ፣ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር ይቅርባይ እንዳለን፣ “ዳግማዊ ዐቢይ፤ ኹለተኛው ዐቢይ ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡ ሰፊ አድናቆት የተቸረውን ንግግራቸውን ተከትሎ የቀረበ ውዳሴ እንደመኾኑ፣ “አማሳኝና ዘረኛ ተጠርጎ ይውጣ!” በሚል የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅና ለአመራራቸውም ድጋፍ የተገለጸበት ነው፡፡
36481161_632243700473859_4355139804996829184_n
ከ500 በላይ ተሰብሳቢዎችን የሚይዘው አዳራሹ ሞልቶ በመቀመጫዎች ዙሪያና በውጭም የቆሙ ታዳሚዎች በታዩበት መርሐ ግብር፣ ነባር የአስተዳደር ጉባኤ አባላት የዳር ተመልካች ኾነው አርፍደዋል፡፡ ተበዳዮች የሚሰነዝሩባቸውን ትችትና ዘለፋ በመሸሽ፣ “መሸማቀቅና ፍርሃት የታየባቸው፤ ከዚያም አልፎ በተናጠል እና በቡድን እየኾኑ ቢሯቸውን ከውስጥ ቆልፈው ያረፈዱም እንደነበሩ” ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ሥራ አስኪያጁና ምክትላቸው፣ አመራራቸው የተሳካ ይኾን ዘንድ፣ከጸሎት ጋራ ከወዲሁ እየተስተዋለ ባለው የደላላ ሓላፊዎች አሰላለፍና ሤራ ተጠልፈው እንዳይወድቁ ሊጠነቀቁ ያስፈልጋል፡፡
‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡
ከሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የአ/አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ኾነው በቅዱስ ፓትርያርኩ የተመደቡት መ/ር ይቅርባይ እንዳለ፣ በአቀባበል መርሐ ግብሩ ያሰሙት ንግግር ሙሉ ቃል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡
 • ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ
 • ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፤ የውጭ ጉዳይ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ
 • ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል፤ የጋምቤላ፣ አሶሳ እና ደቡብ ሱዳን ሊቀ ጳጳስ
 • ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ የምሥራቅ ወለጋ፣ የሆሮጉድሩ እና የቄለም ወለጋ ሊቀ ጳጳስ
 • የመንበ ረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመመሪያ ሓላፊዎችና ሠራተኞች
 • የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የክፍሎች ሓላፊዎችና ሠራተኞች
 • የገዳማት እና የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች
 • በዚህ የአቀባበል ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኛችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፤
በቅድሚያ እንዲህ አምራችሁና ተውባችሁ፣ በሙሉ ፍላጎትና በውስጣዊ ደስታ ተሞልታችሁ ይህን የአቀባበል መርሐ ግብር ለማሣመር በዚህ አዳራሽ በመገኘታችሁ፤ በዚህ አስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ በርጋታ ኾናችሁ ሰላምን ለማስፈን ላሳያችሁት መንፈሳዊ አባትነት፣ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን በልዑል እግዚአብሔር ስም አቀርባለሁ፡፡
በመቀጠልም፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በጣም በርካታ ካህናትን ያቀፈና ባለብዙ ችግርም ጭምር በመኾኑ፣ ምርጥ የሥራ ተሞክሮዎች እንዳሉት ኹሉ ብዙ የሥራ ውድቀቶችም አሉበት፡፡ ምንም እንኳ ሥራው አስቸጋሪ ባይኾንም፣ ከሥራው ጋራ ተያይዘው የሚመጡ ግለሰቦች ጠባይዕ ሥራውን አስቸጋሪ እንደሚያደርገው መገመት አያዳግትም፡፡ ይኹን እንጅ፣ በጋራ ኾነን ሳንበጣጠስ፣ ሳንለያይ፣ ሳንገፋፋ፣ ዘርና ጎሣ ሳንቆጥር አብረን በጋራ ከሠራን፣ ከተመካከርን፤ እኔ ከበላሁ ሌላው ጦሙን ይደር የሚለውን የሆዳሞችን አመለካከት ከተውን፤ እንዲሁም፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል፤ ይሉት ብሂል ከተጸየፍን ከእኛም አልፎ ለዓለም የሚበቃ ሰላም ይኖረናል፡፡
አሁን የምናየው ኹኔታ ከዚህ ፈጽሞ የተለየም ብቻ ሳይኾን፣ ፍጹም ተቃራኒና ከመንፈሳዊ አባቶችና ወንድሞች ቀርቶ ከሰብአ ዓለም እንኳ የማይጠበቅ ተግባር በመኾኑ፣ እያንዳንዳችን እንደየአቅማችን ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን፤ ቤተ ክርስቲያናችንንም ዋጋ እናስከፍላታለን፡፡
ቤተ ክርስቲያናችንን መለወጥ ከፈለግን፣የተማሩ ሊቃውንት ይከበሩ፡፡ ከውሻ ጋራ ታግለው፣ ቁራሽ ለምነው የተማሩት ትክክለኛውን ሥፍራ ይያዙ፤ ቅዳሴን በቴፕ ያጠኑ፣ ወረቡን በካሴት ቀድተው ያጠኑቱ፣ የሰው ፊት እየገረፋቸው ከተማሩት ሊቃውንት በላይ ኾነው የሚመሩበት ጊዜ ያብቃ፡፡ ሰዎች፣ በሚጠቀሙበት ቁሳቁስና በሚለብሱት ልብስ አይመዘኑ፤ በአፈ ጮሌነት አይከበሩ፡፡ መጽሐፍ እንደሚለው፦ “ያን ጠቢብ ድኃ ሰው ማንም አላሰበውም” ነውና፣ጠቢባን ወድቀዋል፤ያልተማሩት ነግሠዋል፤ ሐቀኞች ጎስቁለዋል፤ ደላሎች ከብረዋል፤ ስንዴ ከእንክርዳድ፣ ዱቄት ከአመድ ተቀላቅለዋል፤ እነዚህ ተለይተው ይታወቁ፤ በአንድ ወንበር አይደባለቁ፤ ኹሉም አቅማቸውን ይወቁ፤ ያልተማሩ ለመማር፣ የተማሩት ለማስተማር ወገባቸውን ይታጠቁ፡፡
ክቡራን ሊቃነ መናብርት፤ ዓለም አንድ በኾነችበት በዚህ ሰዓት ብንከፋፈል ራሷ ዓለም ትሥቅብናለች፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላም፣ የኢትዮጵያ ሰላም ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስትታወክም ኢትዮጵያ ትታወካለች፡፡ ስለዚህ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ስንል እንዲሁም ለራሳችን ስንል ሰላምን እናስፍን፡፡በአድባራት ላይ፣ “ትልቁ ዓሣ ትንሹን ዓሣ መብላቱን” ያቁም፤ “ውኃውን” በጋራ እንጠቀም፡፡
በሥራ አስኪያጆች እና በሠራተኞች መሀል ያሉት ደላሎች ይውጡ፡፡ በደላሎች የተነሣ ብዙዎች ተርበዋል፤ ከሥራ ተፈናቅለዋል፤ቤተሰባቸው ተበትኗል፡፡ኹሉም ሰው ጉዳዩን እኩል ያቅርብ፡፡ ኹሉም ልጅ እንጅ የእንጀራ ልጅ አይኹን፡፡ ቦታው ላይ የተመደብነው ባለሥልጣናት፣ ሰዓታችንን አክብረን ሥራውን ቢሮ ውስጥ እንሥራ፤የቢሮ ሥራ በሆቴል አይሠራ፡፡
ባለጉዳይ የሚያቀርበው አቤቱታ፣ይሳካም አይሳካም በሥርዐት ይስተናገድ፡፡ ምክንያቱም እኛ ጋራ የሚቀርበው ባለጉዳይ፣ ሌሊት ማሕሌቱን፣ ሰዓታቱን፣ ኪዳኑን፣ ቅዳሴውን ጨርሶ አገልግሎ መከራውን አይቶ የሚመግበንም ነውና እናክብረው፡፡
የተከበራችሁ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሓላፊዎች፤ እንድትመሩ የተሰጣችሁን ቤተ ክርስቲያን ከተሐድሶ መናፍቃን ጠብቁ፡፡ የቀሚስ ውስጥ ኑፋቄ ይቁም፡፡ የፈረጅያ ሥር ኑፋቄ ከቤተ ክርስቲያን ይውጣ፡፡ በአጠቃላይ፣“መናፍቅ የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ አይብላ፡፡”የቤተ ክርስቲያናችን የቀደመ ክብሯ ይመለስ፤ የክህነት ልዕልና ይመለስ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ በእኛ በአገልጋዮቿ ክብሯን አጥታለች፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መገልገያና ክብር የኾነውን መስቀሏን፣ ቆቧን፣ ቀሚሷን ለብሶ በየመጠጥ ቤቱና በአልባሌ ቦታ መታየት ይቁም፡፡የቀደመው የአበው ካህናት ሥነ ምግባር ይመለስ፡፡
በየአብያተ ክርስቲያናት የተመደቡ ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልጋዮች፣ በደጀ ጠኚዎች ብቻ እየሸፈኑ የደመወዝ ቀን ብቻ ብቅ ማለት ይቁም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አክብራ የሾመቻቸው አንዳንድ አስተዳዳሪዎች፣ ሥልጣንን መከታ በማድረግ አባቶቻችን ያቆዩልንን የቤተ ክርስቲያን ይዞታ(መሬት)፣ ያለአግባብ መሸጥና ማከራየት ይቁም፡፡ ካሬው በ40ሺሕ ብር ሊዝ በሚሸጥባት መዲናችን፣ በ2ብር እና በ7ብር ብሎም በ20ብር፣ የቤተ ክርስቲያንን መሬት ማከራየት ይቁም፡፡
መናፍቃኑስ ቢኾኑ ከዚህ በላይ ምን በደሉ? ኑፋቄአቸውን በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ድል እናደርጋለን፤ አስፈላጊ ከኾነም ከመካከላችን አውግዘን እንለያቸዋለን፡፡ ታድያ በጉያዋ የተቀመጡ፣ “ክርስቲያን ያልኾኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን” ማን ያውግዝልን? እንዲህ ዐይነቱን የመሪ ተብዬዎች ጭካኔ የሚመለከቱ ምእመናን፣ ከቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውና ከአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸው ጉያ እየኮበለሉ ወደ መናፍቃን ጎራ ይኮበልላሉ፡፡ በኑፋቄአቸው አወናብደው ከወሰዱብን ይልቅ፣ በመጥፎ ሥነ ምግባራችን ዕንቅፋት ኾነን ያባረርናቸውን ዓለም ይቁጠራቸው፡፡ ስለዚህ በጋራ ኾነን ብልሹ አሠራርን አርመን ወደ መልካም አስተዳደር እናምጣ፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው የአስተዳደር ኹኔታ በግፍ የተበደላችሁትን፣ ፍትሕ በማጣት የተሠቃያችሁትንና ልዩ ልዩ የሞራልና ከሥራ የመፈናቀል አደጋ ውስጥ የገባችሁትን ኹሉ፤ በእኔና በመላው የጽ/ቤታችን ሠራተኞች ስም ይቅርታ እየጠየቅሁ፣ የደብር አስተዳዳሪዎችም፣ በግፍ የተባረሩትን አጣርተን፣ ከቅዱስ አባታችንና ከቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ተቀብለን በምንወስደው የመፍትሔ አቅጣጫ ኹሉ ከጎናችን በመኾን እንድትደግፉን ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
በዛሬው ዕለት ለተደረገው አቀባበል ዋናው ምክንያቱ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አምነውበት የመደቡት ምደባ በመኾኑ፣ ጉባኤው፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩንና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን እንዲያመሰግንልኝ በትሕትና እጠይቃለሁ፡፡
በመጨረሻም አዲሱ የሥራ አመራር የተሳካ ውጤታማ ሥራ ይሠራ ዘንድ፣ በጋራ ኾነን በዐደባባይ የተሰደበችዋን ቤተ ክርስቲያን እንታደግ ዘንድ፣አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ኹሉ ለአሳራጊዎች አመራር እንዲያስተላልፉልን፤ ለእኔና ከእኔ ጋራ ለተመደቡት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም ወደፊት ሊመደቡ ለሚችሉ ሠራተኞች የሦስት ቀን ጸሎት፣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ እንዲያውጁልን በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ 
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤