Wednesday, July 25, 2018

የሲኖዶሳዊ ዕርቀ ሰላም ስምምነቱ: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገኙበት በዋሽንግተን ዲሲ ይፋ ይኾናል፤ ቋሚ ሲኖዶስ የአቀባበል ዐቢይ ኮሚቴ እንዲቋቋም አዘዘ

his holiness abune merqorewos and his holiness abune mathias
  • ኹለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ በመንፈሳዊና አስተዳደራዊ ተግባር በየድርሻቸው የሚያገለግሉበት ታላቅ ስምምነት ነው፤
  • የኹለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ በዓለ ሢመተ ፕትርክና፣ የቤተ ክርስቲያን በዓል ኾኖ ይከበራል፤
  • በኹለቱም በኩል የተላለፈው ቃለ ውግዘት ይነሣል፤ የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳትም ለአንዱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተጠሪ ኾነው ሓላፊነታቸውን ይወጣሉ፤
  • በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የተሾሙ አባቶች፣ በፍላጎታቸው መሠረት በውጭም በውስጥም አህጉረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው ይሠራሉ፤
  • የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታዊ ድጋፍ፣ የቤተ ክርስቲያንን የዓመታት የሰላም ጥረት ፍሬያማ እንዲኾን አድርጓል – “በእግዚአብሔር ቀን”
†††


በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በተካሔደው ሲኖዶሳዊ የዕርቀ ሰላም ውይይት፣ ፍጹም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የተመለሰበት የልኡካን አባቶች ስምምነት ዝርዝር ይዘት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሚገኙበት በይፋ የሚገለጽ ሲኾን፤ ወደ አገር ቤት የሚገቡትን አባቶች ለመቀበልም ዐቢይ ኮሚቴ እንዲቋቋም ቋሚ ሲኖዶስ ትእዛዝ ሰጠ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በአሜሪካ ሦስት ከተሞች ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውንን ጋራ ከሚወያዩበት የሥራ ጉብኝት ጋራ በተያያዘ፣ ከነገ በስቲያ ኀሙስ፣ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚገኙበት በዋሽንግተን ዲሲ፣ልኡካን አባቶች የደረሱበት ሲኖዶሳዊው የዕርቀ ሰላምና አንድነት ስምምነት ዝርዝር ይዘት በይፋ ይገለጻል፡፡
4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በ1984 ዓ.ም. በመንግሥታዊ ግፊትና ጫና መንበራቸውን ለቀው ከተወሰኑ አባቶች ጋራ ከአገር መውጣታቸውን ተከትሎ፣ ላለፉት 26 ዓመታት ተፈጥሮ የቆየው አስተዳደራዊ ልዩነት እልባት አግኝቶ ቤተ ክርስቲያናችን በአንድ ሲኖዶስ እንድትመራ ልኡካን አባቶች ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ትላንት ሰኞ ተበሥሯል፤ ዝርዝር ይዘቱም፣ የዕርቀ ሰላም ሒደቱ ሳይራዘም እንዲፈጸም፣ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን፣ ልኡካን አባቶችንና የሰላም ኮሚቴውን እያነጋገሩ ሲያበረታቱ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት መገለጹ፣ ለጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ድጋፋቸውን የበለጠ በማረጋገጥ በቀደመው ጣልቃ ገብነት ለተፈጸመባት ታሪካዊ በደል ዕውቅና የሚሰጥ ነው፡፡
በአሜሪካ ያሉት አባቶች፣ ከአዲስ አበባ የሔዱት ልኡካን፣ ኀሙስ፣ ሐምሌ 12 ቀን በአየር ማረፊያ ሲደርሱ ያደረጉላቸው አቀባበል በተመሳሳይም በመክፈቻው ሐምሌ 15 ቀን ያካሔዱት የጋራ ጸሎትና መርሐ ግብር፣ ከወትሮው የተለየና የመግባባቱን ደረጃ የጠቆመ ነበር፡፡ የአጀንዳ ነጥቦቹ በኹለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት ኮሚቴ አባላት ተዘጋጅቶ ቢቀርብላቸውም፣ ያለሦስተኛ ወገን አነጋጋሪነት ለብቻቸው በቀጥታ ለመወያየት ከኹለቱም ወገን የተወከሉት ስድስቱም ልኡካን አባቶች መወሰናቸው የመግባባታቸውን ጥልቀት ያረጋገጠ ነበር፡፡ ይኸውም ፍጹም ሊኾን፣ ውይይቱ በተጀመረበት ዕለት ከእኩለ ቀን በፊት የእርቁን እውንነት ለሰላምና አንድነት ኮሚቴው አብሥረዋል፤“ሦስት ሰዓት በወሰደ ስብሰባ ነው የተስማሙት፤ በኹለቱም አቅጣጫ ምንም ዐይነት ችግር አልታየም፤” ብለዋል የጉባኤው ምንጮች፡፡ ከልኡካን አባቶች አንዱ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣“ቤተ ክርስቲያንን አንድ አድርገን መሞት እንደገና መፈጠር ነው፤” ያሉትም፣የዕርቁ ብሥራት በብዙዎች ዘንድ ባሳደረው መንፈሳዊ ሐሤትና በሰነቀው ተስፋ ተመስክሯል፡፡
FB_IMG_1532343716630
የአባቶች ዕርቀ ሰላም ሒደት፣ ፍጻሜ ባገኘበት ይህ ስምምነት፣ ኹለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ በአንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አመራር፣ የማዕርግ ስምና መንበር ዕውቅና አግኝተው የድርሻቸውን እየፈጸሙ የሚቀመጡበት ነው፡፡ ይኸውም፣ 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፥ በጸሎት ተወስነው መንፈሳዊውን አገልግሎት እየፈጸሙ ቡራኬ ይሰጣሉ፤ 6ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ደግሞ፣ አስተዳደራዊውን የቢሮ ሥራ ያከናውናሉ፡፡
የኹለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ በዓለ ሢመተ ፕትርክና፣ በየተሾሙበት ቀን የቤተ ክርስቲያን በዓል ኾኖ ይከበራል፡፡ የተላለፈው ቃለ ውግዘት የሚነሣ ሲኾን፤ በ4ኛው ፓትርያርክ፣ በውጭ የተሾሙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገር ገብተው በአንድነት በሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በፍላጎታቸው መሠረት በውጭም በሀገር ውስጥም አህጉረ ስብከት ተመድበው እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ ቀኖናዊ እይታና ውይይት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች፣ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ብቻ እንደሚታይ ተገልጿል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ በዕርቀ ሰላም ስምምነቱ መሠረት ወደ ሀገር ለሚመለሱት 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለሚደረገው አቀባበል፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዐቢይ ኮሚቴ እንዲያቋቁም በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ መታዘዙ ታውቋል፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ውሳኔው፣ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ ያሉት ማረፊያዎች ምቹ ኾነው ይዘጋጃሉ፤ አቀባበሉን የሚያስተባብርና በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡ ዛሬ ማክሰኞ፣ ሐምሌ 17 ቀን በተካሔደው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሳምንታዊ የአስተዳደር ጉባኤ ስብሰባ ላይ ጉዳዩ የተነሣ ሲኾን፣ ከሰባት ባላነሱ አስተባባሪዎች የሚመሩ የመድረክ ዝግጅት፣ የጸጥታና ሥነ ሥርዐት፣ የሚዲያና ኅትመት፣ የመስተንግዶ…ወዘተ ንኡሳን ኮሚቴዎች በነገው ዕለት ይዋቀራሉ፤ ተብሏል፡፡
4ኛው ፓትርያርክና አብረዋቸው የሚመጡ ብፁዓን አባቶች፣ ከ26 ዓመታት ስደት በኋላ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱትነና አቀባበሉ የሚደረግበት ቀን፣ ከነገ በስቲያ ኀሙስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሚገኙበት በዋሽንግተን ዲሲ ከሚሰጠው መግለጫ በኋላ እንደሚታወቅ ይጠበቃል፤ በቤተ ክርስቲያን ደረጃ የተዘጋጀው የአቀባበል መርሐ ግብርም፣ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ አልያም በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ልኡካን አባቶችንና የሰላምና አንድነት ኮሚቴ የአዲስ አበባ አባላትን ከጉዟቸው በፊት በጽ/ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት፣ ሒደቱን ከፍጻሜ አድርሰው ከተመለሱ፣ በሚሌኒየም አዳራሽ ብዙ ሺሕ ታዳሚ በተገኘበት፣ የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር እንደሚያደርጉ ልዩ ስጦታም እንደሚያበረክቱ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤