Tuesday, August 7, 2018

በጅግጅጋ እና አካባቢው ዞኖች: 7 አብያተ ክርስቲያን ሲቃጠሉና ሲዘረፉ 8 ካህናት ተገደሉ

FB_IMG_1533473836775
  • ይቅርታ አድርጉልን፤ ጥፋት አጥፍተናል፤ እንክሳለን፤ ከእኛ 30 ሰው፣ ከእናንተ 8 ሰው ሞቷል፤
/የሀገረ ስብከቱን ተወካዮች ለማነጋገር የሞከረው ፕሬዝዳንቱ አብዲ ዑመር/

†††
(የከተማው የዐይን እማኞች እንዳስረዱት)
አሁን ትንሽ ተረጋግቷል፡፡ መከላከያ ሊገባ ነው፣ እየተባለ ቅስቀሳ እየተደረገ ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱ፣ ማምሻውን በማዘጋጃ ቤት የቤተ ክርስቲያን ተወካዮችን ሰብስቦ ሊያናግር ነው፤ ተብሏል፡፡
ባለፈው ኀሙስ በጅግጅጋ ዜድ ኤም ኢንተርናሽናል ሆቴል የክልሉ ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች ተስብስበው በከፍተኛ ደረጃ ሲመክሩ ውለዋል፡፡ በበነጋው ዓርብ ምሳ ሰዓት ላይ፣ “እስከ መንገጠል እናካሒዳለን፤” እያሉ ሲያውጁ ተሰምተዋል፤ በየሆቴሉም የሚያውቋቸውንና ተናጋሪ የሚሏቸውን እየሰበሰቡ፣“እኛም ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን” እያሉ ሲቀሰቅሱ ውለዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱም፣ “ኦሮሞና አማራ ነዳጁን ወስዷል፤ የሚያስተዳድረው ኦሮሞና አማራ ነው፤ እኔ አያገባኝም፤ የነዳጅ ገቢው 5 ፐርሰንት ነው የሚደርሳችሁ ተብሏል፤ ከአሁን በኋላ ራሳችሁን ነፃ የምታውጡ ከኾነ አውጡ፤ እኔ አላውቅም፤” በማለት ለተወሰኑ ሰዎች
ተናግሯል፡፡

ከዚያ በኋላ የሚያደራጁትን አደራጅተው፣ ቅዳሜ ጠዋት ወደ 2 ሰዓት ገደማ፣ ትራፊክ መብራቱ ጋራ ለጥምቀት በዓል መጥተን በምናስረግጥበት ዐደባባይ፣ የከተማው አዳራሽ አለ፡፡ ፖሊሱ እዚያ ጋራ መጥቶ፣ ቀኝ እጁን እያነሣ፥“አይዟችሁ! በርቱ!” ብሎ ሔደ፡፡ ወዲያው ረብሻው ተነሣ፡፡
እዚያው አጠገብ ትልቅ የገበያ አዳራሽ(ቢዝነስ ሴንተር) አለ፤ ያገኙትን ሰው ሁሉ መደብደብ፣ ንብረት መዝረፍ ጀመሩ፤ “ዐቢይ ዳወን”፣ “ሎንግ ሊቭ አብዲ ዑመር” ይላሉ፡፡ የዲኤምሲ ተሳቢ መኪኖች፣ የግልና የመንግሥት ተሽከርካሪዎች አሉ፤ ባጃጅ ይነጥቃሉ፤ የሚንቀሳቀስላቸው ከኾነ ይነዳሉ፡፡ አረንጓዴ መደብ ያለውን የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ዱቄት ነው ያደረጉት፤ገንዘቡን ዘረፉ፤ ሰነዶችን አወጥተው አስፋልት መንገዱ ላይ ዘሩት፤ የቡና ባንክንም እንደዚያው ዘረገፉት፡፡
FB_IMG_1533386299776
ከዚያ በኋላ ነው፣ አብያተ ክርስቲያኑን ወደ ማቃጠል የዘመቱት፡፡ ረፋድ አራት ሰዓት ጀምረው፣መንበረ ጵጵስናው የሚገኝባትንና በብፁዕ አቡነ ያሬድ ቅዳሴ ቤቷ የተመረቀውን የምሥራቀ ፀሐይ ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ ልሔም፣ ግብር ቤትና ጠቅላላ ንብረቷን አቃጠሉ፤ ተቋሞቿን አፈራረሱ፤ መንበረ ጵጵስናውን ሰባበሩ፡፡12 መኖርያ ቤቶች፣ 8 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት የቅዱስ ያሬድ ት/ቤት፣ አንድ የዕንጨት ሥራ ቤት፣ የካቴድራሉ ቢሮዎች የቻሉትን ያህል ንብረት ዘርፈው የቀረውን ገነጣጥለውና አጋይተው ሜዳ ነው ያደረጉት፡፡
በቅጽሯ የሚኖሩትን አባ ገብረ ማርያም አስፋው የተባሉትን መነኮስ ገድለው አስከሬናቸውን አቃጠሉ፤ የቀብር ሥነ ሥርዐታቸውን እሑድ ዕለት ፈጽመናል፤ ከእርሳቸው ጋራ ቄስ ጌጡ እና አንድ ምእመን የደረሱበትን ስላላወቅን ከተገደሉት ይኾናሉ ብለን እየሰጋን ነው፡፡ በተጨማሪም አስተዳዳሪው፣ አንድ ካህን፣ ዐቃቢቷና ሌሎቹም ተደብድበው አልጋ ላይ ናቸው ያሉት፤ ግቢው ምንም ሰው የለበትም፡፡
FB_IMG_1533387566480
አምና የተመሠረተች የደብረ ሰዋስው ቅድስት አርሴማ ገዳም መቃኞ ቤተ ክርስቲያን አለች፤ዋናው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ጎን ለጎን እየተሠራ ነው፤ በራሱ በፕሬዝዳንቱ፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ተብሎ ለመካነ መቃብር የተሰጠንና የይዞታ ማረጋገጫ ባለው ቦታ ላይ የተሠራች ናት፤ በማኅበረ ቅዱሳን፣ የአብነት ት/ቤት ለመገንባትም የታቀደባት ነበረች፤ መቃኞዋን አቃጠሉት፤ ምንም የተረፈላት ነገር የለም፤ መሪጌታ አብርሃም ጥጋቡ የሚባሉ ሠራተኛን ገደሏቸው፤ መሪጌትነታቸው ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲኾን፣ ለደብረ ሰዋስው ቅድስት አርሴማ ገዳም በተቆጣጣሪነት ተመድበው እየሠሩ ነበር፡፡
በከተማው የሕዝቡ ንብረት፣ በተወላጅነት እየተመረጠ አንድም ሳይተርፍ ዘርፈዋል፤ አቃጥለዋል፡፡ ሕዝቡም ወደ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ገብቶ ተጠልሏል፡፡ መጥተው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን እናቃጥላለን ሲሉ ሕዝቡ ተቃወመ፤ ደወል ተደወለ፤ በዙሪያው በላሜራ የተሠሩ የተከራዩ 3 ሱቆች ነበሩ፤ እነርሱን አነደዷቸው፡፡ ለመከላከል ከሞከሩ ሰዎች ሦስቱን የልዩ ኃይሉ ፖሊስ በጥይት መቷል፤ ሪፈራል ገብተዋል፤ የሊቀ ሥዩማን ጥበቡ ልጅ፣ ዲያቆን ሢራክ ጥበቡና ቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ የምትኖር ፍሬ የምትባል ፕሮቴስታንት በሪፈራል ሕክምና እየተደረገላቸው ነው፡፡ዲያቆን የሺዋስ የሚባል የምንመካበት ቅኔ ዐዋቂና ቀዳሽ ዲያቆን ተፈንክቶ ካራማራ ሆስፒታል ተኝቷል፤ ከእርሱ ጋራ የተጎዱ ሌሎቹም ቁስላቸው ዛሬ ሲተጣጠብላቸው ታይተዋል፡፡
እሑድ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ፣ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል አስተዳዳሪ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ተወካይ፣ የስብከተ ወንጌል ሓላፊው፣ መጋቤ ካህናቱና ከወጣት ማኅበሩ የተውጣጡ ወደ ፕሬዝዳንቱ ጋራ ሔደው ተወያይተዋል፡፡ “ይቅርታ አድርጉልን፤ ጥፋት አጥፍተናል፤ እንክሳለን፤ ሰው የሞተው ከእናንተ ብቻ አይደለም፤ ከእኛም 30 ሰው፣ ከእናንተ 8 ሰው ሞቷል፤ አብላጫው የኛ ነው፤ መከላከያ ገድሎብናል፤” በማለት ሕዝቡን አንድ ጊዜ አዳራሽ ሰብስቡና ላናግር ብሎ ጠይቋል፡፡ ነገር ግን፣ ሕዝቡን አዳራሽ ሰብስቦ ሰላም ነው ለማለት አልያም ልዩ ኃይሉን ልኮ ለማስፈጀት ነው፤ መከላከያም ቦታውን ሊቆጣጠር ነው፤ ጦርነት አይቀሬ ነው፤ የሚል ጥርጣሬና መረጃ ስለነበር ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም፤ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የገባም ሰው ወደ ውጭ እንዳይወጣ የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች በድምፅ ማጉያ አስጠንቅቀዋል፡፡
FB_IMG_1533386308673
ከጅግጅጋ ከተማ ውጭ፣ የደጋሃቡር መካነ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተቃጥሏል፡፡ ቄስ ኪዳነ ማርያም ንብረቱ የተባሉ ተገድለዋል፡፡
ዋርዴር ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል፤ሦስት ቀዳሽ ካህናት የነበሩት ሲኾን፣ ቄስ ያሬድ ኅቡእ የተባሉት ተገድለዋል፤ ከከተማ ውጭ ጎትተው አውጥተው ደብድበው የጣሏቸው አንድ መነኮስ ተገኝተዋል፤በነፍስ ያሉ ቢኾንም ጉዳታቸው ያሰጋል፤ ዲያቆኑ አምልጦ ጫካ ገብቷልም፣ ሞቷልም የሚል መረጃ አለ፤ የእርሱ አልተረጋገጠም፡፡
የቀብሪደኃር ደብረ መድኃኒት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አቃጥለዋታል፤ ሁለት ካህናት ወደ ጅግጅጋ ከተማ አምልጠው መጥተዋል፤ የቀሩት መከላከያ ሠራዊት ደርሶ ተርፈዋል፡፡
የጎዴ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያኑ፣ አጥሩና የተከራየ መጋዘኑ ቢቃጠልም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ተርፏል፡፡ ሽላቦ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም እና ቶጎ ውጫሌ መንበረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ አብያተ ክርስቲያናት ደኅና ናቸው፡፡
ከድሬዳዋ ወደ ጅቡቲ በሚወስደው መንገድ የሚገኙት የአይሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የደወሌ ቅዱስ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያናት፣ በሶማሌ ሕዝብ ጠባቂነትና ተከላካይነት ጭምር እስከ ዛሬ ምሽት ድረስ ደኅና እንደነበሩ ቢታወቅም፣ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች በብዛት እየገቡ ከመቆማቸው ጋራ ተያይዞ በተሰነዘሩ ማስፈራሪያዎች የምእመናኑ ስጋት አይሏል፡፡
እሑድ ዕለት፣ ጅግጅጋ ከተማው ላይ የሚገኘውን የደብረ ሰዋስው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን አቃጥለዋል፡፡
source: hara zetewahedo


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤