Saturday, October 27, 2018

የዋልድባ ዳልሻህ እናቶች የድረሱልን እርዳታ ጥሪ አቀረቡ


  • የዳልሻህ ዋልድባ እናቶች ቤተክህነት በመሄድ ድረሱልን ጥሪ አቅርበዋል፥ ነገር ግን መልካም ምላሽ አላገኙም
  • ደካማ እናቶች አረጋውያን እናቶች ያሉበት ቦታ በመሆኑ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል
  • ገዳማውያን እናቶች በአካባቢው ከሚደርስባቸው ችግር በተጨማሪ በረሃብ፣ በጥም እና በእርዛት እየተሰቃዩ ነው
  • ሕዝበ ክርስቲያኑ በሚችለው እንዲረዳቸው ጥሪ አቅርበዋል


በዳልሻህ ዋልድባ የሚኖሩ መነኮሳይት እናቶች በዚህ በያዝነው የመከር ዘመን ከወትሮው የተለየ ከበድ ያለ የረሃብ ዘመን መሆኑን እና በሚኖሩበት በዳልሻህ የእናቶች ገዳም በርካታ እናቶች ለረሃብ እና ለእርዛት የተጋለጡበት ሁኔታ እንዳለ፥ ከዋልድባ ዳልሻህ ተወክለው የመጡት እናቶች ገልጸውልናል።


ባለፉት ዓመታት እነዚህ እናቶቻችን በረሃብ በእርዛት ብሎም በጥም በሚሰቃዩበት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ረጅም ጉዞ በማድረግ ለጠቅላይ ቤተክህነት ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል፥ መልሱ ግን እንደ ሁልጊዜው በቦታችሁ ተመለሱ እዛው ባላችሁበት ችግራችሁን እንመለከታለን በሚል ወደ ቦታቸው ባዶ እጃቸውን ለብዙ ጊዜ እንደተመለሱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ነገር ግን ዛሬ ባለው የለውጥ እና የአንድነት መንፈሥ በመምጣቱ ዛሬም እንደ ትናንቱ መልዕክተኞች ሆነው የመጡት እናቶች የማኅበራቸውን ችግር ለማስረዳት በጠቅላይ ቤተክህነት ተገኝተው የችግራቸውን ጥልቀት እና የረሃቡን አሳሳቢነት በአጽንዖት ለማስረዳት ሞክረው ነበር፥ ነገር ግን አጥጋቢ ውጤት ሊያገኙ አለመቻላቸውን በኀዘን ገልጸውልናል።


በቀደሙት ዓመታት በሰቋር ዋልድባ የእናቶች ገዳም እንዲሁም በዳልሻህ ዋልድባ የእናቶች ገዳም በርካታ ችግሮች እና ብዙ ሰቆቃ ሲደርስ እንደነበረም ይታወሳል፥ ከሚገጥማቸው ችግሮች ከብዙ በጥቂቱ። በተለያየ ጊዜ የአካባቢው ሚሊሻዎች በእናቶች ላይ በርካታ አካላዊ እና የሥነ ልቡና ጥቃቶችን ፈጽመዋል፣ በተለያየ ጊዜ የሚደርስባቸውን የረሃብ እና እርዛት ችግር ለማሳወቅ ለማስታወስ ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በሄዱበት ወቅት ተመለሱ እና እዛው ባላችሁት እንረዳችኃለን ተብለው መልዕክተኞቹ የመመለሻ ገብዘብ እስከሚያጡ ድረስ በብዙ ችግር ወደ ገዳማቸው መመለሳቸው፣ የሚደርስባቸውን ችግር በውጪ ለሚገኙ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በሚናገሩበት ጊዜ የሚደርስባቸው እንግልት እና ስቃይ ፣ እና እናቶቻችን የሚኖሩበት ገዳም እጅግ በረሃማ እንደመሆኑ መጠን እንኳን ለእናቶች ለወንዶችም እጅግ አስቸጋሪ ቦታ መሆኑ ግልጽ ነው፥ ነገር ግን እነዚህ እናቶች በመንፈሣቸው ጠንካሮች በፈጣሪያችን መንገድ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንጦስ ኖሮ ያሳየንን ሕይወት እነርሱም ሊኖሩበት በእንዲህ አይነት ቦታ ይኖራሉ፥ ጠዋት በኪዳን ጸሎት ማታ በሰርክ ጸሎት እንዲሁም ለሊቱን በጾም ጸሎት ጽሙድ ሆነው ለሃገር፣ ለወገን፣ ለመሪዎች፣ ለዓለም ሰላም እና ለሃገራችን መልካም ዘመን እንዲመጣ ወደ ፈጣሪያቸው እለት እለት የሚያሳስቡ እናቶቻችን በረሃብ አለንጋ ሲገረፉ እንዴት ሰው ማስቻል ሰጠው እንዴትስ አስችሎን ዝም ማለት ቻልን ሕዝበ ክርስቲያኑም ሃላፊነታችንን እንዳንረሳ እንዳንዘነጋ አደራ ለማለት እንወዳለን።


በዘንድሮው ዓመት የጠቅላይ ቤተክህነት 366 250ሺሕ 448 ብር 05 ሳንቲም በጀት ሲያጸድቅ ምናልባት ከዚህ በጀት ውስጥ የተወሰነው በተለይ እራሳቸውን መርዳት እና በምዕመናን የማይደገፉትን ገዳማት እና መካናት መርጃ የሚል በጀት እንደሚኖር ይታመናል ነገር ግን እነዚህ እናቶች ከዋልድባ እስከ አዲስ አበባ ድረስ እርዳታችሁን ፍለጋ መጥተናል በጣም በርካታ እናቶች በችግር ላይ ይገኛሉ እና በምትችሉት ለእለት ጉርስ የሚሆን እና ለጥቂት ለባሰባቸው እናቶች አቡጀዲ መግዣ የሚሆን እርዳታ አድርጉልን በማለት ሃገር አቋርጠው መጥተው እርዳታ ለመጠየቅ ሞክረው ነበር፥ ነገር ግን መልካም ምላሽ ከማግኘት እንደ ወትሮው በዛው በቦታችሁ ተመለሱ እና እንመለከታለን ችግሩን ለመቅረፍ እንሞክራለን በማለት እንዲመለሱ መደረጋቸው በእጅጉ የሚያሳዝን እና የሚያስቆጭ እንደሆነ ማንም የሰው ልጅ ይረዳዋል ብለን እናምናለን።


ጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ የገዳማት እና የልማት ተራድዖ ተብሎ የሚታወቀው ተቋም ዋናው ሥራው እነዚህን የተቸገሩ ገዳማት እና መካናትን መደገፍ እና በተለይ ሁለንተናዊ የሆነ ሥልጠና ሰጥቶ በገዳሙ የሚኖሩትን እናቶች እና አባቶች ሥራ ሰርተው ገዳማቸውንም ሆነ እራሳሣቸውን እየደገፉ የሚኖሩበት መንገድ ማመቻቸት እና መፈለግ እንደሆነ ይታመናል። ነገር ግን እነዚህ እናቶቻችን እና አባቶች በተለያየ ጊዜ ችግር በገጠማቸው ቁጥር መጥተው መልካም መልስ የማየገኙ ከሆነ ግን፥ ወደ ግለሰቦች ወይም በጎ አድራጊዎች መሄዳቸው አይቀሬ ነው ምክንያቱም ረሃብና ጥም ጊዜ ስለማይሰጥ የሚቻለውን ሁሉ አድርገው ለተራቡት እና ለተራቆቱን አናቶቻቸው እና አባቶቻቸው መድረስ ተቀዳሚ ተግባራቸው እንደሚሆን የታመነ ነው፥ በዚህ በተቸገሩ እና ዙሪያው ገደል በሆነበት ወቅት ግን የሰዎችን እጅ ወይም የተለያዩ ድርጅቶችን ድጋፍ ሲፈልጉ፥ ተያይዞ ሌሎች ችግሮች አብረው እንደማይመጡ ዋስትና የለንም፥ ሁሉ በጎ አድራጊ ምዕመን ወይም ሁሉ በጎ አድራጊ ድርጅት መልካም ቢያደርግም፥ በሰጠው ልክ ደግሞ ወረታ የሚፈልግ ወይም የሚጠብቅ ቢሆን እና ወደ ገዳሙ አላስፈላጊ ነገሮችን ለምሳሌ የተበረዙ መጻህፍትን በእርዳታ ስም ሊያመጣ እና ሊያስገባ እንደማይችል ማን ዋስትና ሊሰጥ ይችላል ለምሣሌ በጎ አድራጊ መስሎ ጠላት የተለያዩ ነገሮችን ወደ ገዳሙ ሊያስገባ ሊያመጣ እንደሚችል የታወቀ ነው ድርጅቶችም ቢሆኑ እኛ እንዲህ አይነት እርዳታ እናረጋለን እንዲህ አይነት ምግብ እናቀርባለብ በማለት በርካቶችን ከሃይማኖታቸው እንዳስኮበለሉ እና እንዳስወጡ ብዙዎቻችን የምናውቀው እውነታ ነው። ለዚህም ነው የዋልድባን እንታደግ ማኅበር ዛሬም ለጠቅላይ ቤተክህነት ይሄንን ጉዳይ በቸልታ ባይመለከተው እና በተለያዩ ጊዜያት ተቸግረው መፍትሄ ፈልገው የሚመጡ ገዳማውያን እናቶችን እና አባቶችን ቤተክህነቱ ተቀብሎ በሥርዓት ችግራቸውን ቢሰማ፥ በመቀጠል በልማትና ተዳድዖ ኮምሽን በኩል አስፈላጊው ክትትል ቢደረግ እና በሰው ሃይል እና በማቴርያል እርዳታም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመን በማንኛውም ጊዜ የሚራዳ ምዕመን እንደሆነ እየታወቀ ነገሮችን በቸልታ መመልከቱ ሊመጣ ከሚችለው አደጋ አይብስም በማለት ስጋታችንን እናቀርባለን።


በመጨረሻ የዋልድባን እንታደንግ ማኅበር እንደ ተቋም የኢትዮጵያ ገዳማት በሚደርስባቸው ችግሮች በሙሉ ችግሮችን በመስማት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው፣ ወደፊትም ይሄንን ጥረት በቅርብ በመከታተል ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንዲሁም ከምዕመናን ጋር በመነጋገር የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ እና ለመራዳት ባለው አቅም ለመሥራት ጥረት ያደርጋል፥ እስከ አሁንም በተለያየ ጊዜ በተለይ በዋልድባ ገዳም ላይ የሥኳር ፋብሪካ ሊገነባ ከታሰበበት ጊዜ ጀምሮ በሚደርሰው ችግር በአጠገብ በመሆን በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል በመቀጠልም አምላከ ቅዱሳንን አጋዥ አድርገን ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት በዝግጅት ላይ እንገኛለን።


አምላከ አበው ሃገራችንን እና ሕዝቧን በረደኤት ይጠብቅልን አሜን።


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤