Friday, April 19, 2019

በቤተ ክርስቲያን ላይ የቀጠለውን ጥቃት በጥናትና በቅንጅት የሚመክት የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች አደረጃጀት በየከባቢው እንዲጠናከር የሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት ጥሪ አቀረበ

49343002_1949418621774027_5310064051697483776_n
 • ለለውጡ ጊዜ በመስጠት ትዕግሥት ብናደርግም፣ግድያና ጥፋቱ በጠራራ ፀሐይ ቀጥሏል

 • ሥልጣንን፣ ፖለቲካን፣ ቋንቋንና ወቅትን ተገን ያደረገ ትንኮሳና ጥቃት ዛሬም ቀጥሏል፤

 • የጎሠኝነትና አክራሪነት ግጭቶች፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በተለየ መንገድ ጎድተዋል፤

 • ከሌሎች አብያተ እምነት ይልቅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያነጣጠሩ ናቸው፤

 • ግጭት በተነሣ ቁጥር የበቀል እና የጥላቻ መወጣጫ የምትደረገው ቤተ ክርስቲያን ናት

                                                                              ***

 • ቅዱስ ሲኖዶስ፣ አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ክትትል ያድርግ፤ መንግሥትንም ያሳስብ

 • ለልዕልናዋ በምልዓተ ጉባኤ በአጽንዖት ይምከር፤ ለደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ምላሽ ይስጥ፤

 • አገር ናትና መንግሥት አደጋ ከመድረሱ በፊት ይጠብቃት፤ ስትጎዳም ፈጥኖ ይጠግናት

 • የደረሰባትን በደልና አደጋ ያጣራልን፤በሚዲያ የታገዘ የጥላቻ ዲስኩር በዐዋጅ ይከልክል፤

 • የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን አደረጃጀት በየከባቢው አጠናክረን በቅንጅት እንከላከል!
***


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።
ከሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት በአገራችን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
አንተ የምትተኛ ንቃ!” (ኤፌ.515)
በአገራችን በኢትዮጵያ የመጣውን አስተዳደራዊ ለውጥ ተከትሎ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና መሰል በኾኑ ዘርፎች አዎንታዊ እንዲሁም አሉታዊ የኾኑ ክሥተቶችን እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ በተለይም ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ እንዲህ ዓይነቱ መስተቃርን የሞላባቸውኔታዎች እየተበራከቱ መጥተዋል።
ለውጡን ተከትሎ፥ የእስረኞች መፈታት፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ መዋሐድና ሌሎች ይበል የሚያሰኙ በጎ ተግባራት የተፈጸሙ ቢኾንም፣ አሳዛኝና ልብ የሚሰብሩ ድርጊቶችም እንዲሁ በርካታ ናቸው፡፡ በተለይም ከጎሠኝነትና አክራሪነት ጋራ በተያያዘ የሚነሡ ግጭቶች የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፉ፣ የብዙዎችን ንብረት ያወደሙ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን መጠለያ አልባ ያደረጉ አሳፋሪ ተግባራት በስፋት ታይተዋል፡፡
እነዚህ ግጭቶችሉ፣ በተለየ መንገድእጅግ የተከበረችውንና የአገሪቱን ቀዳሚ ቁጥር የያዘችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ጎድተዋል፡፡ የካህናቱንና የምእመናንን ሕይወት ቀጥፈዋል፤ ንዋያተ ቅድሳቷንና አንጡራ ሀብቶቿን አሳጥተዋል፡፡ እጅግ የሚገርመውና ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ደግሞ፣ የተነሡት ግጭቶች ኹሉ ከሌሎች አብያተ እምነቶች ይልቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያነጣጠሩ መኾናቸው ነው፡፡
ኹላችንም እንደምንገነዘበው፣ ላለፉት 40 ዓመታት፣ በመንግሥት ደረጃ ከሚሾሙ ሹማምንት አብዛኞቹ ኦርቶዶክስ ጠል የኾኑና በዋናነት ቤተ ክርስቲያንን በአገኙት አጋጣሚ የማዳከምና የመበደል ብሎም በቀጥታ ሥልጣንን፣ ፖለቲካን፣ ቋንቋን፣ አካባቢንና ወቅትን ተገን በማድረግ ሲያሳድዷት ኑረዋል፡፡ ዛሬም ከትላንቱ የተሻለ ዘመን ይመጣል ብለን ተስፋ ብናደርግም፣ በስውርም ይኹን በዐደባባይ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደረገው ጥቃትና ትንኮሳ እንደ ቀጠለ ነው፡፡
በተለይም፦

 • በተቀናጀና በተሰናሰለ መልኩ አስተዳደሯን ከማዳከም ጀምሮ መሠረተ እምነቷን እሰከ መበከል፤

 • ሀብት ንብረቷን ከመውረስ አድባራትና ገዳማቷን እስከ ማቃጠል፣ ካህናትና ምእመናኗን በግፍ እሰከ መግደል፤

 • ከሹክሹኩታ ምክር እስከ ሚዲያ ዘለፋ፤

 • ከግል ዘረኝነት እስከ ተደራጀ ዘረኝነት ወዘተ ጥቃት እየተፈጸመባት ይገኛል።

ቤተ ክርስቲያናችን በተለይም ባለፉት ኻያ ሰባት ዓመታት፣ በፕሮግራም ደረጃ መሠረታዊ ጥላቻ በሚታይበት መልኩ ግፍ ስታስተናግድ መኖሯ ይታወቃል። ከለውጡ በኋላ በመንግሥት ደረጃ የታየውን መልካም ጅማሮ በተለይም፣ ተራርቀው የነበሩ አባቶች በዕርቀ ሰላም አንድነታቸውን አግኝተው የሰላሙን በረከት አጣጥመን ሳንጨርስና የምሥራቹ ዐዋጅ ተግባራዊ ኾኖ ሳይጠናቀቅ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የአገራችን ክፍሎች በምንም ይኹን በምን በወገኖቻችን መካከል ትንሽ አለመግባባት በተነሣ ቁጥር የበቀልና የጥላቻ መወጣጫ እየተደረገች ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት።
በያዝነው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ እንኳን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተቃጣው መከራና ሥቃይ ቢዘረዘር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ብሎ ለማመን ይከብዳል። ከእነዚህም መካከል፦

 • ካህናትና ምእመናን በድንጋይ ተወግረው፣ በጥይት ተደብደበው ተገድለዋል፤ በእሳት ጋይተዋል፤

 • በርካታ ሕንፃ አብያተ ክርስቲያን በድጅኖ ፈርሰዋል፤ በቦንብ ጋይተዋል፤ እንደ ጧፍ በእሳት ነደዋል፤

 • ካህናትና ምእመናን ንብረት ካፈሩበት፣ ተወልደው ካደጉበት፣ ወልደው ከዳሩበት እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፤

 • የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ በመኾናቸው ብቻ ትዳራቸውን እንዲፈቱ፣ የሥራ ሓላፊነታቸውን እንዲያጡ ተደርገዋል፤

 • ለኹለት ሺሕ ዘመናት ዘር፣ ቋንቋ ሳትለይ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ በትምህርት፣ በጤና፣ በልማት፣ በአስተዳደር፣ በሥነ ምግባር… ወዘተ ስትረዳ ስታገለግል የኖረችውንና ያለችውን ቤተ ክርስቲያን የአንድ ብሔር መገለጫ አድርጎ በጥላቻ ፖለቲካ በሰከሩ ግለሰቦች ቀስቃሽነት ሰለባ ኾናለች፤

 • በሱማሌ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች ዛሬም መከራዋ የበረታ ኾኗል፤

እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ ማኅበረ ካህናት፣ ነገሮችን በማስተዋልና የመጣውን ለውጥ ጊዜ ከመስጠት አንጻር በትዕግሥት ስንከታተል ቆይተናል፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ የታጠቀና ጥላቻን አንግቦ ቤተ ክርስቲያናችንን ለማጥቃት ያለመ ኃይል መኖሩንና በተለይም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በከሚሴ፣ አጣዬና ኤፍራታና ግድም አካባቢዎች በተከሠተው ግጭት፣ በጠራራ ፀሐይ የቤተ ክርስቲያናችን ቅጥር ተደፍሮ፣ ሀብት ተዘርፎ፣ መቅደሷ ተቃጥሎ፣ ምእመኖቿ ተገድለው መታየቱ ሕዝበ ክርስቲያንን ያስቆጣ፣ ካህናቱን እጅግ ያሳዘነ ተግባር ኾኖ አግኝተነዋል።
በመኾኑም የሚከተሉትን መልእክቶች ለሚመለከታቸው አካላት እናቀርባለን፤
/ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፡-

 • ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በአገራችን በኢትዮጵያ የመጣውን አስተዳደራዊ ለውጥና ወደፊትም ምርጫውን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን አገራዊና መሰል ጉዳዮችን እየተከታተለና እየገመገመ የቤተ ክርስቲያናችንን ኹለንተናዊ ልዕልና እና ክብር እንዲያስጠብቅ እንጠይቃለን፤

 • ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በአገራችን በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ምክንያት በተከሠቱ ግጭቶች ምክንያት በደረሰብን የሞት፣ የስደት፣ የመቁሰልና መሰል በደልና ተያያዥ ጉዳዮች፣ ከክልል እስከ ፌዴራል፣ ከግለሰብ እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች ድረስ ተጠያቂ የኾኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርግ፣ በኹኔታዎቹም ዙርያ ሙሉ መረጃ መስጠትና ከቀጣይ አደጋም ቤተ ክርስቲያናችንን ለመጠበቅ መንግሥት ሓላፊነቱን እንዲወጣ እንዲያሳስብ እንጠይቃለን።

 • በአባቶች መካከል የአስተዳደር ልዩነቶችን በማጉላትና በማሰራጨት፣ ትኩረትን በማሳጣትና ሚዛን በማዛባት በአገራዊ ኹኔታ ላይ ትኩረት እንዳይኖረን ከሚያደርጉ ግርዶሾች በመላቀቅ ለአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን ልዕልና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በአጽንዖት እንዲመከርበት እንጠይቃለን፤

 • ሰሞኑን በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰውን አሳዛኝ ድርጊት ተከትሎ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ደቀ መዛሙርት፣ ወደ ዐደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን ማሰማታቸው ይበል የሚያሰኝና የሚደነቅ ተግባር ሲኾን፣ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት እና ሌሎች አባቶች ግን ለጩኸታቸው መልስ አለመስጠታቸው አሳዝኖናል፤ ደቀ መዛሙርቱ የጠየቁት ጥያቄ አግባብነት ያለው በመኾኑ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ መልስ እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን፡፡

/ የኢትዮጵያ መንግሥት፡-

 • በተደጋጋሚ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚደርሰውን አደጋ መንግሥት እየተመለከተ ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሠቱ ማድረግ ሲገባው በቸልተኝነት መመልከቱ እጅግ ልብን የሚነካ ተግባር ነው፡፡ አገር የኾነችውንና ለአገር መከታ በኾነችው ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያናችን አደጋ ከመድረሱ በፊት ሊጠብቃት፣ አደጋም ከደረሰ በኋላ የጠፋባትን ፈልጎ፣ የተጎዳባትን ጠግኖ፣ የተቃጠለባትንና የፈረሰባትን አድሶ በአጠቃላይ የሚቻለውን ኹሉ የማድረግ ሓላፊነት ስላለበት ይህን ሓላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን፤

 • በአገራችን በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ክልሎችና ዞኖች ውስጥ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰው በደልና አደጋ እንዲጣራልን፣ አጥፊዎች ተለይተው በሕግ እንዲጠየቁ፣ በቀጣይም ገዳማትና አድባራት መሰል ጥቃት እንዳይደርስባቸው የሕግና የጥበቃ ከለላ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፤

 • በአገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ አገር ወስጥ የነበሩና ከአገር ውጪ ወደ አገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከፊሎቹ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ባላቸው ጥላቻ የተመሠረተ ዲስኩር በሚዲያ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም በጽሑፎቻቸውና በብዙኃን መገናኛ ጭምር ታግዘው የሚደረጉ ዘመቻዎች በዐዋጅ እንዲከለከሉ እንጠይቃለን፤

/ ምእመናን በተለይም ወጣቶች፡-

 • የቤተ ክርስቲያናችንን ኹለንተናዊ ክብር ለማስጠበቅ ከጥላቻና ከጠብ በጸዳ መልኩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ቅርሶችን፣ ክብረ በዓሎቻችንን፣ ከጸጥታ ኀይሎችና ከካህናት ጋራ በመቀናጀት መጠበቅ፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በየአካባቢው የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ጠንካራ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ከዚህ በኋላ የሚደርሰውን ጥቃት በጥንቃቄና በንቃት በመከታተል ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ከዳግም ጥቃት እንድንከላከል እንጠይቃለን፤

 • እነዚህ የወጣት ኦርቶዶክሳውያን አደረጃጀቶች፣ በዕለትና በሳምንት መደብ ወይም ተራ በማውጣት አካባቢንና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን መጠበቅ፤

 • ውድና ቅርስ የኾኑ ንዋያተ ቅድሳትን በተቀናጀና በተጠና መልኩ ከአደጋ በፊት መከላከልና መጠበቅ ስለሚቻልበት ኹኔታ መምከር፤

 • ሊከሠቱ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ፣ የተሰሙ የትኛውንም መረጃ ቅድሚያ ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ ከዚህ በኋላ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንዳይከሠት ከእግዚአብሔር ጋራ በመኾን የምትችሉትን ኹሉ ጥረት እንድታደርጉ እንጠይቃለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ አገራችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፡፡
የሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት
ሚያዝያ 5/2011 .ም.

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤