Friday, June 14, 2019

መንግሥት አደራ በል ባለሥልጣናቱን አደብ እንዲያስገዛ፣ ሕዝቡም የአገርና የቤተ ክርስቲያን ጠላትና ወራሪ ከኾኑ ሰዶማውያንና ተባባሪዎቻቸው እንዲጠነቀቅ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳሰበ!

Holy Synod Ginbot2011 closing
 • በቱሪዝም ሽፋን ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ያስታወቀው፣ አሜሪካዊ የግብረ ሰዶማውያንአስጎብኚ ድርጅት እንዳይገባ አወገዘ!
 • የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ 7ቱን አጽዋማት የመጾም እና አልባሳትን የመልበስመብትና ነፃነት እንዲከበር አሳሰበ፤
 • ምእመናን በትክክል እንዲቆጠሩ፣ ቆጠራውም በሰላም እንዲከናወን፣ በየአህጉረ ስብከቱትምህርት እንደሚሰጥና የሚከታተል ኮሚቴም መሠየሙን አስታወቀ፤
 • እኒህ የምልአተ ጉባኤው ውሳኔዎች መልካም ቢኾኑም፣ በአህጉረ ስብከት ማጣራት ሪፖርቶችውሳኔና በመሪ ዕቅድ ትግበራ አጀንዳ አሳፋሪ ይዞታዎች የታዩበት መደበኛ ስብሰባ ነው!
***


 • ብዙ የተደከመበትን የመሪ ዕቅድ ትግበራ ሒደት፣ በቀዳሚ አጀንዳነት ይዞ የምር መገምገምናተገቢውን መመሪያ መስጠት ሲገባው፣ በተሰላቸበት የመጨረሻ ቀን አንሥቶ ወደ ኋላእንዲመለስና ተንገራግጮ እንዲቆም በር ለሚከፍት ዓምባገነናዊ ውሳኔ አሳልፎ ሰጥቶቷል
 • ዋናው ተጠያቂ፣ ሐሳቡ የእኔ ነው፤ እያሉ በየመድረኩ የሚመጻደቁትና በተጨባጭ ግንአስተዳደራዊ ለውጡ እንዳይተገበር የሚፈልጉት ፓትርያርኩ ቢኾኑም፣ በሲኖዶሳዊ ሥልጣኑገሥጾ ሊገራቸውና ሒደቱን ሊያስቀጥል ይገባ ነበር
 • የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ለተመሠረተበት የካህናትና ምእመናን ኅብረትአቤቱታዎች፣ ፍትሕ ሳያይ፣ ለሊቃነ ጳጳሳቱ አድልቶ እንደወሰነ ብዙዎች ታዝበዋል፤
 • በዋና ጸሐፊ እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ምርጫ ከተያዙ አቋሞች አንጻር፣ በወሳኝ ጉዳዮች ላይበቡድን እየደገፈና እየተቃወመ በኅቡእና በገሐድ ሲሻኮት ከርሟል!!
***
ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በፍትሕ ርትዕ ይመራሉ ተብለው በተሠየሙ የወረዳና የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የቤተክርስቲያንና የምእመናን መብትና ደኅንነት እየተጣሰና ለአደጋ እየተጋለጠ እንደኾነ የጠቀሰው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የፌዴራሉ መንግሥት ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አስፈላጊውን መመሪያ እንዲሰጣቸውአሳሰበ፤ በቱሪዝም ሽፋን ተደራጅቶ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣትና የቤተ ክርስቲያንን ቅድስና የሚጎዳ ተግባር ለመፈጸም ያቀደውን አሜሪካዊ የግብረ ሰዶማውያን አስጎብኚ ድርጅት ደግሞ፣ ወደ ቅድስት አገራችን እንዳይገባ፣ ቅዱሳት መካናትንም እንዳይረግጥ አወገዘ፤ ሕዝቡም ሥነ ምግባርን ከሚያበላሹና ባህልን ከሚያጠፉ ሰዶማውያንና ተበባሪዎቻቸው እንዲጠበቅ አሳሰበ፡፡
ለ18 ቀናት ሲያካሒድ የሰነበተውን የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ፣ ዛሬ ሰኞ፣ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲያጠናቅቅ፣ ረፋድ 4፡00 ላይ ባወጣው ባለ15 ነጥቦች መግለጫ፣ ቤተ ክርስቲያን ከምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ በማኅበራዊ ዘርፍ ለአገር ዕድገትና ለሕዝቡ የኑሮ መሻሻል፣ በተለይም ለሰላምና አንድነት በመቆም ድርሻዋን እንድትወጣ መወሰኑን ቅዱስ ሲኖዶሱ አስታውቋል፡፡
አገራችን ከጥንቱ ከመሠረቱ ጀምራ፣ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው የሚለውን መርሕ ተከትላ፣ ሰላሟን፣ ፍቅሯንና አንድነቷን ጠብቃ የውጭ ባዕዳን ወራሪዎችን በመመከት ክብርዋንና ልዕልናዋን ለረጅም ዘመናት ጠብቃና አስጠብቃ እንደኖረች አስታውሶ፣ በአኹኑ ዘመን የሚታዩትን ያልተለመዱ ባሕርያት፣ ሕዝቦችዋ በሰከነ መንፈስ ቆም ብለው በመምከርና በመወያየት ወደ ጥንተ ሰላምዋ እንድትመለስ የማድረግ ሓላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ለምትፈጽመው ማኅበራዊና ልማታዊ ተግባር በጎ ፈቃድ በማያሳዩ ባለሥልጣናት፣ በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የቤተ ክርስቲያንንና የተከታዮቿ ምእመናንን መብትና ደኅንነት ለአደጋ እያጋለጡና እየጎዱ እንደሚገኙ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው አመልክቷል፡፡ ከየአህጉረ ስብከቱ በቀረበለት ሪፖርት መሠረት፡-
 • የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣
 • የክርስቲያኖች መገደልና ከቄያቸው መፈናቀል፣
 • በሃይማኖታቸውና በሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ላይ ተጽዕኖ ማድረግ፣
 • የአብያተ ክርስቲያናት ነባር የይዞታ ቦታዎችን በሕገ ወጥ መንገድ መቀማት
የሚሉትና የመሳሰሉት ጥቃቶችና ጫናዎች እየደረሰብን እንደኾነ ያስረዳው መግለጫው፣ የፌዴራሉ መንግሥት፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በፍትሕ ርትዕ ይመራሉ ብሎ ላስቀመጣቸው የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎችኹሉ አስፈላጊውን መመሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቋል፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች፣ በሥርዐተ እምነት ነፃነታቸው ላይ የሚደርስባቸው ጫና ተወግዶ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውእንዲከበር አሳስቧል፡፡ እንደ እምነታቸው ሥርዐት፣ በዓመት ባሉት ሰባት አጽዋማት፣ የመጾም መብታቸውተጠብቆ አስፈላጊው አቅርቦት እንዲደረግላቸው፣ ሃይማኖታዊ በዓላትንም በሚያከብሩባቸው ጊዜያት፣ የኖረናየቆየውን ትውፊታዊ አልባሳት የመልበስ መብታቸው እንዲጠበቅ፣ ለየኮሌጆቹና ለየዩኒቨርሲቲዎቹ ማሳሰቢያው እንዲደርሳቸው መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ለተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት፣ ለአብነት ት/ቤቶች፣ ሰው ሠራሽ አደጋ ለደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች፣ ለጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃ ማደሻ የሚኾን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል፡፡
በቅዱሳት መጻሕፍት ኹሉ የተወገዘው ግብረ ሰዶም፣ ዜጎች በቅድስናና በፈሪሃ እግዚአብሔር ተከብረው የሚታወቁባትን የአገራችንን ታሪክ የሚቀይር፣ የዜጎችን መልካም ሥነ ምግባር የሚለውጥ፣ ሕገ ተፈጥሮንና የተቀደሰውን ጋብቻ የሚያበላሽ እንደኾነ መግለጫው አትቷል፡፡
ይህን ነውረኛ፣ ውጉዝና የወንጀል ተግባር፣ በአገራችን ለማስፋፋት፣ በዚህም የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ቅድስና የሚጎዳ ተግባር ለመፈጸም፣ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የግብረ ሰዶማውያን አስጎብኚ ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ማስታወቁን ቅዱስ ሲኖዶሱ ተቃውሟል፤ ቅዱሳት መካናትንም እንዳይጎበኝ አውግዟል!!!
ቅዱስ ሲኖዶሱ አያይዞም፣ ላልተወሰነ ጊዜ በተራዘመው 4ኛው ዙር የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ፣ ካህናትና ምእመናን፣ በምልአትና በትክክል እንዲቆጠሩ በየአህጉረ ስብከቱ ሊሰጥ የሚገባውን ትምህርትና ግንዛቤ አፈጻጸም የሚከታተል ኮሚቴ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ መሠየሙን በመግለጫው አስፍሯል፡፡ መንግሥት፣ ዜጎችእንዲቆጠሩ በያዘው መርሐ ግብር መሠረት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች በትክክል እንዲቆጠሩ፣ ቆጠራውምበሰላም እንዲከናወንና አገራዊ ተልእኮውም እንዲሳካ፣ በየአህጉረ ስብከቱ ትምህርት እንዲሰጥ፣ አስፈላጊውምክትትል እንዲደረግ የኮሚቴ አባላት እንዲሠየሙ ተደርጓል፤ ብሏል መግለጫው፡፡
በውጭ አገር የሚገኙ አህጉረ ስብከትን በማጠናከር መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎታቸውን ማስፋፋት እንዲቻል፣ ከቃለ ዐዋዲው እና ከየአገሮቹ መንግሥታት ጋራ የተጣጣመ ደንብ እንዲዘጋጅና ለጥቅምቱ 2012 ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ መወሰኑን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
የቋሚ ሲኖዶስ ሥልጣንና የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ተከሠቱ በተባሉ የሥራ አፈጻጸሞችና ታዩ በተባሉ ግድፈቶች፣ ጉባኤው በሰፊው ተነጋግሮ፣ በቀጣይ ማንኛውም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርጎ እንዲሠራ መመሪያ ሰጥቷል፡፡ በዚህ የመግለጫ ነጥብ፣ ኹነኛ የጉባኤው ማሳያ የነበረው፣ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውዝግብ ነው፡፡ በቋሚ ሲኖዶሱ የተወሰነው፣ የኹሉምወገኖች አቤቱታ ሳይታይና የሀገረ ስብከቱ ሚና ሳይጠየቅ፣ በአጠቃላይ የቅሬታ አቀራረብ(ይግባኝሥርዓቱሳይጠበቅ በመኾኑ፣ ዳግም ወደዚያው ተመልሶ አፈጻጸሙ እንዲታይ ተስማምቷል፡፡
ከአገር ውስጥ፥ የከፋ፣ ከውጭ አህጉረ ስብከት የደቡብ አፍሪቃ፣ የኢየሩሳሌም ገዳም፣ የአትላንታ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና የፊላዴልፊያ ቅዱስ ዐማኑኤል አብያተ ክርስቲያናትን በተመለከተ፣ በአጣሪ ልኡካን የቀረቡ ሪፖርቶችን ተመልክቶ፣ መፍትሔ የተባለ ውሳኔ ቅዱስ ሲኖዶሱ መስጠቱን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
እውነታው ግን፣ ውሳኔዎቹ፣ ፍጹም መፍትሔ ሊኾኑ አለመቻላቸው ነው!!! ከውሳኔዎቹ አንዳቸውም፣ አቤቱታ አቅራቢ ወገኖችን እንዳላስደሰቱ፣ ለተጨማሪ ውዝግብና ለምእመናን መራቅ ምክንያት እንዳይኾኑ ስጋት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ይልቁንም፣ ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ብቻ ናት ወይ?”፤ አባትነት ወይስ አገዛዝ?”፤ ከሲኖዶሳዊ አንድነት ወደ ሲኖዶሳዊ ማጥራት መቼ?” የሚሉ ጥያቄዎችን በብርቱ እያስነሡ ያሉ መኾናቸው ነው፣ እውነታው!
Holy Synod Rekibe Kahinat2011
አዲስ አበባን ጨምሮ በየአህጉረ ስብከቱ ያለው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር፣ አካል ገዝቶ መልክ አውጥቶ በዐደባባይ ገንፍሎ እያመሰን፣ ከቫይረስ የረቀቀ ይመስል ዐሥሬ ይጠና እየተባለ፣ ተጠንቶ ልሞና ደቆ የቀረበውና በመሳቢያ የተቆለፈበት የለውጥ ሰነድ፣ በአማሳኞች ተንኰልና ዛቻ እንዲሰወር፣ መፍትሔው ኾነ ተብሎ እንዲዘገይና እንዲርቅ እየተደረገ ያለበት ኹኔታ፣ በዚኹ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ በግልጽ ተንጸባርቋል፡፡
 • ከጥቅምት 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ኹለንተናዊ ችግሩን ከነመፍትሔው ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ከአንድም ሦስት መሠረታዊና ጥልቅ ጥናቶች እያሉና እኒህም ከወቅቱ ጋራ ተጣጥመውና በበጀት ተደግፈው እንዲተገበሩ ምልአተ ጉባኤው በተደጋጋሚ አጽድቋቸው እያለ፣ እንደገና ሌላ የጥናት ማደንዘዣ የታዘዘበት፣ እንደገና ሌላ የኮሚቴ ድሪቶ ያየንበት መደበኛ ስብሰባ ነው፣ ይህ የ2011 ግንቦት የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ!!!
 • የአስተዳደራዊ ለውጥን አስፈላጊነት በተሻለ ኹኔታ ይረዳሉ፤ በሠለጠነ አገርም እንደ መቆየታቸው በትግበራው ይደግፋሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው የውጭ ገቦችም ምንተ ዕዳዬ ያሉበት ይብሱኑ አንዳንዶቹ ለኑፋቄና ለተወገዙ መናፍቃን ሽንጣቸውን ገትረው ጉባኤውን ያለከልካይ የሞገቱበት አሸማቃቂ መደበኛ ስብሰባ ነው፣ ይህ ምልአተ ጉባኤ!!!
 • የገዛ ውሳኔውን እንኳ ማስታወስና ማስከበር ተስኖት፣ ሃይ ባይ ላጣው ፓትርያርካዊ ዓምባገነንት የተጎናበሰ ምልአተ ጉባኤ ነው፣ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ!!! 
 • ከመርሕና የርእሰ ጉዳይ ጭብጥ፣ የኹሉ አባትነትና ሚዛናዊነት ይልቅ የጎሠኝነት መደጋገፍና መነቃቀፍ በየአጀንዳው በግላጭ የታየበት ምልአተ ጉባኤ ነው፣ ይህ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ!
 • በተለይም፣ በአነጋጋሪ አጀንዳዎች፣ የድጋፍና ተቃውሞ ወሳኝ መነሻ በነበረው የዋና ጸሐፊ እና የዋና ሥራ አስኪያጅ የምርጫ አጀንዳ ላይ እንዳፈጠጠ፥ በአዳራሽና በውጭ፣ በገሃድና በኅቡእ እርስ በርሱ እየተሻኮተ ሰንብቶ፣ምርጫው ከተከናወነ በኋላና በማግሥቱ ደግሞ፣ የመሪ ዕቅድ ትግበራን ያህል የህልውና አጀንዳ ላይ ለመነጋገር መንፈሳዊ ወኔ የከዳው ግዴለሽነት የታየበት ምልአተ ጉባኤ ነው፣ ይህ መደበኛ ስብሰባ!!!
በመግለጫው ተ.ቁ(4)፣ “የአዲስ አበባንና የአህጉረ ስብከት ችግሮችን አጥንተውና ለይተው እንዲያቀርቡ፣ ብፁዓን አባቶችና ባለሞያዎች እንዲሠየሙ ተደርጓል” እያለ ማላዘዙ፣ የዚሁ ገጽታው ተጨባጭ ማረጋገጫ ነው!!!
በቤተ ክርስቲያን የሥልጣን መዋቅር ከፍተኛው አካልና ለተቋማዊ ዕድገቷም ውድቀቷም ግንባር ቀደም ተጠያቂ የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በአገር ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ያሳየውን የሚያስመሰግን አቋም፣ እጅግ ተፈላጊ በኾነው ወሳኝ ውስጣዊ አስተዳደራዊ ለውጥ አጀንዳዎች ላይ አልደገመውም፡፡ በውጫዊ ጉዳዮች ተደማጭነቱና ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ፣ በውስጣዊ ተቋማዊ አንድነቱና ጥንካሬው ላይ የተመሠረተ ስለ መኾኑ ከቶ እንደምን ማስረዳት እንደሚቻል የጨነቀ ኾኗል፡፡
ብዙ የተደከመበትን የመሪ ዕቅድ ትግበራ ሒደት፣ በጊዜ የለንም ንቃትና ዝግጁነት፣ በቀዳሚ አጀንዳነት አንሥቶና የምር ገምግሞ ተገቢውን አቅጣጫና መመሪያ መስጠት ሲገባው፣ በተሰላቸበት የመጨረሻ ቀን ወደ ኋላ እንዲመለስ፣ ተንገራግጮም እንዲቆም በር ለሚከፍት ዓምባገነናዊ ውሳኔ አሳልፎ ሰጥቶቷል!!
ዋናው ተጠያቂ ፓትርያርኩ ቢኾኑም፣ በሲኖዶሳዊ ሥልጣኑ ገሥጾ ሊገራቸው ሲገባ በዋዛ ያልፋቸዋል፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስም፣ ሐሳቡን ያመነጨኹት እኔ ነኝ፤ የእኔ ሐሳብ ነው፤ እያሉ በቃለ ነቢብ በየመድረኩ የሚመጻደቁበትን፣ በተጨባጭ ግን በየሰበቡ የሚያጓትቱን ወሳኝ የአስተዳደራዊ ለውጥ አጀንዳ፣ ከፀረ ለውጥ አማሳኞች ጋራ በጨለማ እየዶለቱ አግተውት ይገኛሉ!!

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ አስተዳደራዊ መዋቅሩ ለተመሠረተበት የካህናትና ምእመናን ኅብረት አቤቱታዎች ፍትሕ ሳያይ፣ ለሊቃነ ጳጳሳቱ አድልቶ እንደ ወሰነ ብዙዎች ታዝበዋል፡፡ ይህ በድምር፣ ረጅም በማይባል ጊዜ ውስጥ ለሚያስከትለው ከቅንዓት የመነጨ የተቆርቋሪ ወገኖች አድማሳዊ ምድር አንቀጥቅጥ ቁጣ ግን ራሱን ያዘጋጀ አይመስልም፡፡
Source: Hara Zetewahedo 

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤