Saturday, September 7, 2019

እነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን እስከ ነገ ጠዋት 3:00 ይቅርታ እንዲጠይቁ ቅ/ሲኖዶስ ገደብ ሰጠ፤ ጥያቄአቸው በመሪ ዕቅዱ ትግበራ ማሕቀፍ እንደሚፈታ ገለጸ

ጋዜጣዊ መግለጫው ለረፋድ 4፡00 ተቀጥሯል
Holy Synod Pagumen 2011
የጥያቄአቸው መነሻ በኾኑት በኦሮሚያ ክልል አህጉረ ስብከት፥ የስብከተ ወንጌል፣ የዕቅበተ እምነት እና የአገልጋዮች እጥረት… ወዘተ. ችግሮች ላይ ከምልአተ ጉባኤው ጋራ መግባባት ላይ ቢደረስም፣ ቀደም ሲል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የሰጠበት ጉዳይ እንደኾነ እያወቁ፣ “የክልል ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እናደራጃለን፤” ማለታቸውና የቋሚ ሲኖዶሱን ክልከላ ተላልፈው የሚዲያ መግለጫ መስጠታቸው ስሕተት እንደኾነ በብፁዓን አባቶች ተገልጾላቸዋል፤
የክልል ጠቅላይ ጽ/ቤትም ኾነ የክልል ሲኖዶስ የማቋቋም ዓላማ እንደሌላቸው የገለጹት እነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ በበኩላቸው፣ በክልል ደረጃ የአህጉረ ስብከትን ጉዳይ የሚከታተልና የሚያስፈጽም፣ ከክልላዊ መንግሥታዊ አካላት ጋራ የሚያገናኝ፣ የሚያጋጥማቸውን መጓተትና እንግልት የሚያስወግድ ተጠሪ እንዲሠየም ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፤ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይኾን፣ በሌሎችም ክልሎች ለሚገኙ አህጉረ ስብከትም እንደኾነ ጠቅሰዋል፤ “በአንዲት ቤተ ክርስቲያንና በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ እናምናለን፤ አንከፋፍልም፤ አንገነጥልም፤” ያሉት በጉባኤው ፊት የቀረቡት አምስት የኮሚቴው አባላት፣ “በክልሉ እየተባባሰ የመጣው የምእመናን ፍልሰት እና የመናፍቃን ወረራ ያሳስበናል፤” ብለዋል፤

በቤተ ክርስቲያን ሕግ እና የቃለ ዐዋዲ ደንብ ውስጥ የሚታዩ የአደረጃጀትና የአሠራር ክፍተቶችን ጨምሮ ለጥያቄአቸው መነሻ የኾኑት ችግሮች፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሥር በተጀመረው የመሪ ዕቅድ ትግበራ ማሕቀፍ እንዲመለስ በግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መውሰኑን ቅዱስ ሲኖዶሱ የውሳኔውን ቃለ ጉባኤ በመጥቀስ አስታውሷል፤ በመኾኑም፣ የኮሚቴው አባላት በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሥር በተቋቋመው “የመሪ ዕቅድ አመራር እና ትግበራ ዐቢይ ኮሚቴ” ውስጥ እንደሞያቸው መሳተፍ እንደሚችሉም አስታውቋል፤
ከዚህ በቀር፣ በሥራ ላይ በሚገኘው ሕገ ቤተ ክርስቲያንና የቃለ ዐዋዲ መተዳደርያ ደንብ መሠረት፣ የአህጉረ ስብከት ተጠሪነት ለቅዱስ ሲኖዶስ እና ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በመኾኑ፣ የተለየ ተጠሪ ይሠየም መባሉ፣ ሲኖዶሳዊ መዋቅሯን እንደሚጥስና ተገቢም እንዳልኾነ የምልአተ ጉባኤው አባላት አስረድተዋቸዋል፡፡
እነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ በማስከተል፣ “ጥያቄአችን በእናንተ በብፁዓን አባቶች ዘንድ ትክክለኛ ግንዛቤና ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማበላሸት ተንቀሳቅሰዋል፤” ያሏቸውን መንፈሳውያን የአገልግሎት ማኅበራት ለመክሠሥ ቢሞክሩም፣ “ከዚህ ጋራ መያያዝ የለበትም፤” በሚል በምልአተ ጉባኤው ውድቅ ተደርጎባቸዋል፤ “የአንድን ብሔር መጠሪያ የክርስትና፣ ሌላውን የአረሚ ያደርጋል፤” ያሏቸውን መጻሕፍት ቢጠቅሱም፣ “የግለሰቦች ነው፤ ቤተ ክርስቲያንን አይወክልም፤” በማለት ተመልሶላቸዋል፡፡
በመጨረሻም፣ ጉዳያችኹ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ተይዞ እየታየና መግለጫ እንዳትሰጡ ተከልክላችኹ እያለ ለምን ወደ ሚዲያ ለመውጣት ቸኮላችኹ፤ ለምን ሕዝቡን አሳዘናችኹ? በማለት ምልአተ ጉባኤው ጠይቋቸዋል፤ “ጥያቄአችን በግንቦቱ መደበኛ ስብሰባ ራሱን ችሎ ያታያል ብለን ጠብቀን ስለነበረ ነው፤ አልታየልንም፤” በማለት መልሰዋል፤
belay meko and co.የአደረጃጀትና የአሠራር ጥያቄአቸው በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሕግ እና ደንብ መሠረት ምላሽ እንደሚሰጠውና ለዚህም ከመካከላቸው ምሁራንና ባለሞያዎች የኾኑት በመሪ ዕቅድ ትግበራ ዐቢይ ኮሚቴ ውስጥ ተካትተው ሥራውን ማገዝና ማቀላጠፍ እንደሚችሉ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አቋሙን ገልጾላቸዋል፡፡ አያይዞም፣ ሕግ ተላልፋችኋል፤ ቸኩላችኋል፤ ወደ ሚዲያ መውጣት አልነበረባችኹም፤ ይቅርታ ጠይቁ፤ በማለትም አዟቸዋል፡፡
ጉዳዩ ከጠበቁት በላይና ውጭ መጮኹን እነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ ለምልአተ ጉባኤው አባላት ማመናቸው ተነግሯል፤ ነገር ግን፣ የኮሚቴው አባላት ጠቅላላ ቁጥር 13 በመኾኑ፣ ይቅርታ ለመጠየቅ ከኹሉም ጋራ መማከር እንዳለባቸው በመግለጻቸው፣ እስከ ነገ ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠዋት 3፡00 ድረስ በምልአተ ጉባኤው ገደብ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ አካባቢዎች በቀጣይነት እየደረሰባት በሚገኘው ተጽዕኖና ጥቃት ጉዳይ ወሳኝ አቋም በመያዝ አገልጋዮችንና ምእመናንን በነቂስ ለማነቃነቅ በጠራው አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ የሚደርስበትን የጋራ ውሳኔ ለማሳወቅ፣ ለነገ ረፋድ 4፡00 ብዙኀን መገናኛዎችን መጥራቱ ተጠቁሟል፡፡
በ2007 ዓ.ም. ተሻሽሎ በጸደቀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እና አገልግሎት በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት እንዲመራ ያደርጋል፤ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ያስጠብቃል፤ ያስከብራል፤ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን በተመለከተ ለጥፋተኞችና ለበደለኞች እንደ ጥፋታቸው መጠን ምሕረትን ይሰጣል፤ ይቅርታንም ያደርጋል፤ አስፈላጊም ከኾነ በቀኖና ይቀጣል፤ በአጠቃላይ፣ ቤተ ክርስቲያንንና የቤተ ክርስቲያንን ጉዳዮች በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
ምንጭ: ሐረ ዘተዋሕዶ 


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤