Friday, October 25, 2019

ከመንግሥት ጋራ የሚደረገው ውይይት ለቤተ ክርስቲያን ቋሚ የደኅንነት ዋስትና የሚያረጋግጥ ሊኾን ይገባል፤ “ለቋሚ ስጋታችን ቋሚ የደኅንነት ዋስትና ውል ላይ መደረስ አለበት”


EOTC and PM Office
  • መግለጫውን ከውይይቱ በኋላ ለመስጠት ታስቦአል፤ ወደተመረጡ የችግሩ አካባቢዎች የሚሰማሩ ብፁዓን አባቶች ይመደባሉ
***
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ዛሬ ከቀኑ 10፡00 ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ከሚመራው የመንግሥት ልኡክ ጋራ የሚያደርገው ውይይት፣ የብሔር እና የሃይማኖት አክራሪዎች ቋሚ የጥቃት እና የተጽዕኖ ዒላማ እየኾነች ለምትገኘው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ቋሚ የደኅንነት ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት የሚደረስበት ሊኾን እንደሚገባው ተጠቆመ፡፡

ብሔርንና ቋንቋን ዐቢይ እና ቀዳሚ የማንነት መገለጫ ከማድረግ አልፎ በአመዛኙ የጠርዘኝነት ዝንባሌ የሚታይበት ያለፉት 27 ዓመታት የአገራችን የፖሊቲካ አስተሳሰብና ሥርዐት፣ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክትና ተቋም ኾና የኖረችውን ጥንታዊትና ታሪካዊት እናት ቤተ ክርስቲያን፣ የጥቃትና የተጽዕኖ ዒላማ ማድረጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገታ ባለመኾኑ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ መንግሥት ቋሚ የደኅንነት ዋስትና በሚሰጥበት ኹኔታ ላይ በግልጽ ሊነጋገር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
ባለፉት ኹለት ቀናት ብቻ ለግለሰብ ድጋፍ በሚል በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተካሔዱ ሰልፎች፣ በቅጽበት የብሔርና የሃይማኖት መልክ ይዘው፣ ወገን ለይተው ምእመናንና ቤተ ክርስቲያንን የጥቃት ዒላማ ያደረጉበት ኹኔታ እየተለመደ መምጣቱ የደኅንነት ዋስትና ውሉ የግድ አስፈላጊ መኾኑን ያሳያል፤ ተብሏል፡፡
ካህናትንና ምእመናን በአሠቃቂ ኹኔታ በመግደል እና አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል፣ ንብረታቸውን አውድሞና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን አሽመድምዶ ከቀዬአቸው በማፈናቀል እየተገለጸ ያለው ጥቃትና ተጽዕኖ በመሠረቱ፣ ርእዮተ ዓለማዊ እና መዋቅራዊ መነሻ እንዳለው አፈጻጸሙ በግልጽ የሚያሳይ በመኾኑ፣ ከመንግሥት የሚጠበቀው የደኅንነት ዋስትናም በዚያው ትይዩ፣ መዋቅራዊና ሥርዐታዊ እንጂ በቃላት ሽንገላና ባዶ ተስፋ ሊታለፍ እንደማይገባው ተገልጿል፡፡
73372231_2554682827955774_6698097589415313408_n
ከኹሉ በፊት፣ መዋቅራዊ እና ሥርዓታዊ የደኅንነት ዋስትናው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የብሔርና የሃይማኖት አክራሪዎች ተከታታይና ቋሚ የጥቃት ዒላማ እየኾነች ያለችበትን ሐቅ በነባራዊነት አምኖና ተቀብሎ ጥቃቱን ከማስቆም እንደሚነሣ አስተያየት ሰጪዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ይኸውም፣ ቅምጥ/ግልጽ የደኅንነት ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በጋራ ለይቶና የጸጥታ ዕቅድ አውጥቶ የታሰበውን ጥቃት አስቀድሞ ያመክናል፤ ይከላከላል፤ አደጋ ሲደርስም በፍጥነት ደርሶ ጉዳትን ይቀንሳል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን የሀገራዊ ሰላምና ደኅንነት ዋነኛ አጋር ለማድረግና በዘላቂነት አብሮ ለመሥራት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋራ ግልጽ ስምምነት ላይ መድረስ ይኖርበታል፤ ብለዋል፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ሌላው መዋቅራዊ እና ሥርዐታዊ የደኅንነት ዋስትና ማረጋገጫ፣ የሰሞኑን ጨምሮ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት ሲፈጸም ሓላፊነታቸውን ያልተወጡ፣ በቀጥታ ይኹን በተዘዋዋሪ ተባባሪ የኾኑ ባለሥልጣናትን በሕግ ተጠያቂ በማድረግ፣ ተጎጂዎችንም በተገቢው በመካስ ፍትሕን ማረጋገጥ ነው፡፡
ሦስተኛው እና መሠረታዊው ደግሞ፣ በኢሕአዴጋዊ ርእዮተ ዓለም እና ፕሮግራም መነሻነት፣ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ማንነቷና አገራዊ ውለታዋ ተዘንግቶ፣ የአንድ ወገንና የጨቋኞች አጋር ተደርጋ በትውልዱ ዘንድ የተሣለችበትን ያለፉት 27 ዓመታት ስሑት ፖሊቲካዊ ትርክቶች፣ ከመንግሥት የሥልጠና እና የትምህርት ሰነዶች እንዲታረሙ ማድረግ እንደኾነ አብራርተዋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው፣ ዛሬ ቀን 10፡00 ላይ ከባለሥልጣናቱ ጋራ ከሚያደርገው ውይይት ቀደም ብሎ፣ ከ17ቱ አጀንዳዎቹ መካከል በአስቸኳይነት የለያቸውን፣ የ2012 የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በጀት መርምሮ ያጸድቃል፤ በግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው የሠየመውን የሀገራዊ ሰላም እና አንድነት ዐቢይ ኮሚቴ ጥናት እና ሪፖርት ላይም ይነጋገራል፡፡
ከዚኹ ጋራ በተያያዘ፣ የጥቃት መከላከል እና የኮሚዩኒኬሽን ኀይለ ግብሮችን(በአጀንዳው ውስጥ በተቀመጠበት አገላለጽ፥ “የሕዝብ ግንኙነት እና የወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ”) የማቋቋም ጉዳይንም እንደሚያነሣ ይጠበቃል፡፡ ከግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ማግሥት ተቋቁሞ ሲንቀሳቀስ የቆየው የመንፈሳውያን ማኅበራት ኅብረት አስተባባሪ ኮሚቴ ያከናወናቸው ተግባራትም በዐቢይ ኮሚቴው ሪፖርት የተካካተ ሲኾን፣ ከዚህ በኋላ የሀገራዊ ሰላም እና አንድነት ዐቢይ ኮሚቴው አካል ኾኖ የሚቀጥልበት ይኹንታ ከምልአተ ጉባኤው እንደሚሰጠው ተጠቁሟል፡፡ 
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ከባለሥልጣናቱ ጋራ ከተወያየና ወደተመረጡ የችግሩ አካባቢዎች የሚሰማሩ ብፁዓን አባቶችን ከመደበ በኋላ፣ ቀሪ አጀንዳዎችን በሌላ ጊዜ ተረጋግቶ ለማየት በመቅጠር መደበኛ ስብሰባውን በአጭሩ እንደሚያጠናቅቅ ተነግሯል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤