Wednesday, April 8, 2020

እውን በኢትዮጵያ መንግሥት አለ?


  •         ገዳማውያን ዛሬም እየተገደሉ ነው
  •         ስደት፣ መከራ፣ መሳደድ ቀጥሏል በዋልድባ
  •         ገዳማውያን ተሳደው በጎንደር ተጠልለዋል

በቅዱስ ዋልድባ ገዳም እንደ ትላንቱ መከራው ቀጥሏል፣ ትናንት ገዳማውያን ያለ ጥፋታቸው ታሥረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተሳደዋል፣ ተገለዋል፤ ታዲያ ይሄ ሁሉ ሲደርስ ጠቅላይ ቤተክህነቱም ምንም አለማለቱ መንግሥትም በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ ዓሕመድ አማካኝነት የገዳሙን ጉዳይ እንደሚመለከቱት ቃል ቢገቡም ሁሉም የውሃ ሽታ ብቻ ሳይሆን ከትናንት በባሰ ሁኔታ ዛሬ ጭራሽ ገዳማውያኑን እንደ ከብት አንገት ቀልቶ አርዶ መግደል ምን አይነት የክፋት ጥግ ነው ለገዳማውያኑ ገና ጥንት ቤቴን ንብረቴን ሳይሉ በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ገዳም ሲገቡ በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መልዕክት ፲፬ “ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳን መከራን ብትቀበሉ እናንተ ብፁዓን ናችሁ” ተብሎላቸው ወደ እዚህ ቀን ከሌሊት ስብሃተ እግዚአብሔር ከማይቋረጥበት ቃለ እግዚአብሔር እንደ ጅረት በሚፈስበት ገዳም የገቡት ያንን ጽድቁን ሽተው ብለሆነ፥ ከእነሱ የሚቀር የለም እንደ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በሰማዕትነት ክብር ተቀዳጅተው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደሚገቡ ምንም ጥርጥር የለውም።


ባሳለፍነው ሳምንት በአብረንታንት መድሃኒዓለም ገዳም አባ ነጻ በሚባለው ቅዱስ ሥፍራ ልዩ ስሙ ፍልፍል ዲማ በሚባል ቦታ ለዋልድባ ገዳም በንብ እርባታ የሚያገለግሉ በአርምሞ ይኖሩ የነበሩ አባት አባ ሀብተወልድ፥ በገዳሙ ውስጥ በኖሩበት ከ ዓመት በላይ ሲኖሩ ስማቸው በምንም የማይነሳው አረጋዊው መነኩስ፥ በምን ሁኔታ እኝህን የረከሰውን ዓለም ተጸይፈው እራሳቸውን በአርምሞ በሚኖሩበት በዚህ ቦታ በመሄድ አንገታውን በካራ ቀጥቅጠው በመግደል፥ አስከሬናቸውን ከአካባቢው እራቅ በማድረግ በሎሚ ዝፍ ሥር ጥለው ሄደዋል፥ እስካሁን ድረስ ማን ገደላቸው፣ በምን ሁኔታ ተገደሉ፣ ለምን ተገደሉ፣ የሚሉት የማጣራት ሥራዎች በየትኛውም የጸጥታ ክፍል ቢሮ በኩል ወይም ጠቅላይ ቤተክህነቱም በሚያዛቸው በሽሬ እንደ ሥላሴ ሃገረ ስብከት ወይንም በሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት በኩል ምንም አይነት የማጣራት ወይም የማረጋገጥ ሥራ እንዳልተሠራ ስንገነዘብ ልባችን በእጅጉ አዝኗል። ለምን በገዳማውያን ላይ ካራ??ዓለምን የናቁ፣ በብትውና የሚኖሩ፣ ከጸሎት እና ስግደት በስተቀር የሥውን የማይመኙ፣ የዓለሙን ብልጭልጭ ትተው በብትውና የሚኖሩ ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው እራፊ ለብሰው ለሃገር ለወገን የሚጸልዩን አባት በካራ ኸረ እንዴት ያለ ጭካኔ ነው እንዴትስ የሰው ልጅ በደካማ አረጋውያን ላይ እጁን በዚህ ደረጃ ሊያነሳ ይችላልፍርዱን መድኅኒዓለም ይስጥ ከማለት ሌላ ምን እንላለን።

ዋልድባ ገዳም በ፬፻፹፭ ዓ.ም. ገደማ እንደመሠረተ የተለያዩ የገዳሙ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ፥ በቀደሙት ነገሥታት ዋልድባ ለምሳሌ በአፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ዋልድባ በአራቱ ወንዞች የተከለለ ገዳም እንደ ሆነ እና መንግሥት በዚህ ቦታ እንደማይገባ እና ለቦታ ግብር ወይም መሰል የመንግሥት የሚጠይቀው ነገሮች እንደማይመለከተው እና ቦታው በብትውና ለሚኖሩ ብቻ የጸሎት እና የምናኔ ቦታ ሆኖ እንዲኖር በአዋጅ የወጣበት ዘመን ነበር፤ በዚህ ቦታም ከምሥረታው በነበረው የገዳሙ ሥርዓት “እህል አይግባብሽ ፥ ኃጢያት አሻገርብሽ” በሚል ውግዝ በመሆኑ ያንኑ ሥርዓት አክብረው ነገሥታቱ መኳንንቱ በመንግሥት ሥርዓት ሳይሆን በገዳሙ ሥርዓት ነገሥታቱ ወደ ገዳሙ ቡራኬ ለመቀበል በሄዱበት ጊዜ ሁሉ የገዳሙን ሥርዓት እንደ ትልቅ ሥርዓት ተቀብለው ይኖሩ እንደነበር የገዳሙ ዜና መዋዕል ይነግረናል። እንደ ምሣሌ ከሚጠቀሱት ነገሥታት አንደኛው አፄ ናዖድ ናቸው፥ እሳቸው ወደ ገዳሙ ለቡራኬ በመጡበት ጊዜ የገዳሙ ሥርዓት በገዳሙ ውስጥ “ሥምረት ያልጨበጠ” በገዳሙ ውስጥ ሥጋ ወደሙ ሊቀበል እንደማይችል ሥርዓት ስለነበረ አፄ ናዖድ ያንን ሥርዓት አክብረው፥ በወቅቱ የነበሩትን አበሜኔት አማክረው እንዴት እርሳቸው እና ባለቤታቸው ሲመጡ ሥጋ ወደሙ መቀበል እንደሚሉ ሲጠይቁ፥ ሥርዓቱ ለእነርሱ እንደማይፈቅድ ተነግሯቸው ነገር ግን ከገዳሙ ውጪ ሞፈር ቤት በሚባለው ቦታ ቤተክርስቲያን አሳንጸው በዚያም አረጋውያን መነኮሳት የሚጦሩበት፣ ገና ደጅ በመጥናት ያሉ ረድዕ የሚቆዩበት ቦታ ስለነበር በዚያውም ለእነርሱ መገልገያ እንዲሆነ እጣኖ ማርያም ተብሎ በአፄ ናዖድ ታንጾ በመጡ ጊዜ በዚህ ቦታ ሥጋ ወደሙ ተቀብለው እንደሚሄዱ፣ በዜና መዋዕሉ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

ሌላው ቀርቶ በጭካኔው እና በኮሚኒዝም መርሁ የሚታወቀው የደርግ መንግሥት እንኳን ያልደፈረው ቦታ ቢኖር ዋልድባ ገዳም ነበር፣ ነገር ግን ላለፉት ዓመታት ውስጥ ግን በገዳሙ በ፲፮፻ ታሪክ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ መልኩ በእጅጉ የገዳሙ ህልውናን እየተፈታተነው ይገኛል፥ ሕወሃት በጫካ በነበረበት ወቅት በገዳሙ ውስጥ በመመሸግ የደርግ ወታደሮች ስለማይገቡበት በቦታው ላይ ለበርካታ ወራት እና ዓመታት ተሸሽገው መቀመጣቸው፣ እንዲሁም ሰላዮችን ገዳማውያን ናቸው በማለት በማስገባት በገዳሙ ያለውን ሥርዓት በመየት እና ቅርሶችንም በማዘረፍ ለበርካታ ዓመታት ገዳሙን እጅግ እልክ አስጨራሽ በሆነ መልኩ ሲፈታተኑት ኖረዋል፣ በተለይ ላለፉት ዓመታት የወልቃይት ሥኳር ፋብሪካ ለመገንባት በታቀደው መሠረት ለመሥራት ታስቦ የበርካታ ቅዱሳንን አጽም በማፍለስ፣ ገዳማውያኑን በማስፈራራት፣ በማሳደድ፣ በማሠር፣ እንዲሁም የደረሱበት በማጥፋት፣ ግድያ በመፈጸም ለአዕምሮ እጅግ የሚዘገንኑ በደል ሲፈጸም ኖሯል፥ በገዳማውያኑ ላይ እየደረሰ ያለው በደል እና ግድያ እንዲሁም እሥራት ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፣ ገዳማውያኑም በጸሎት ጽሙድ ሆነው በሚቆዩባቸው ቦታዎች እየታደኑ ተደብድበዋል፣ አነስት መነኮሳይት ተደፍረዋል፣ ዓይናቸው ታሥሮ በገደል ተወርውረዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ዛሬም አንገታቸው በካራ እየተቀላ ተገለዋል፤ ይሄ ማለት ደግሞ ለቅድስት ቤተክርስቲያንም ሆነ ለአማኞች የሞት ሞት ነው፣ ምክንያቱም ገዳማውኑ ቀድመው እንዲህ ዓይነት መከራ እንደሚመጣባቸው ያውቁታል ለዚህም ነው መስቀሉት ተሸክመው እስከ ሞት ድረስ በመሄድ አምላካቸውን ክርስቶስን የመሰሉት፥ ነገር ግን ለእኛ ለምዕመናኑ በ፵ እና ፹ ቀናችን ክርስቲያን ተብለን ለተጠራን፥ ገዳማውያኑ ይሄን ያህል መከራ ሲደርስባቸው በዝምታ ለተቀመጥን፣ ወዮልን ለእኛ ሰምተን እንዳልሰማ ዓይተን እንዳላየን የገዳማውያኑ ጩኽት ከምንም ሳንቆጥር ነጠላውን ለብሰን ካህናቱም ፈረጅያውን ተላብሰን ቆቡን ደፍተን ለምንውተረተር ወዮልን፥ እግዚአብሔር አምላክ ዝም አይልም መልስም ይሰጣል ለእያንዳንዳችን እንደየ ሥራችን ሊከፍለን የታመነ አምላክ ነው።

የገዳማውያኑ መሳደድ እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ለአብነት ያህል ከሁት ወራት በፊት ከአበረንታንት ገዳም መነኮሳት ያለምንም ጥያቄ ወይም አግባብ ከገዳሙ በግፍ ተሳደዋል፥ ለዚህ መሰል ድርጊት ደግሞ በገዳሙ በመንግሥት ተሰይመው የተቀመጡ “አባ ገብረ ሕይወት መስፍን” ወይም “ሻምበል” በመባል የሚታወቁ መነኮስ አሉ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ የፀለምት አውራጃ መስተዳደር ክፍል ሃላፊ የነበረው አቶ ሲሳይ መሬሳ አዝማችነት ታጣቂዎችን በማስከተል ወደ ገዳሙ በመግባት፥ እንደ ገዳሙ ሥርዓት ጸሎተ ማርያም ተደርጎ ሁለት ወይ ሦስት ሱባኤ ተይዞ የሚመረጠው የአበሜኔት እና እቃ ቤት ሹመት በማን አለብኝ ባዩች የተሰጣቸውን የሕዝብ አደራ ወደ ጎን በመተው በግፍ በአፈሙዝ በማስገደድ ገዳማውያኑን በማስፈራራት አባ ገብረ ዋሕድ አበሜኔት እንዲሁም “አባ ገብረ ሕይወት” ሻምበል እቃ ቤት ሆነው በመንግሥት ቀጥተኛ ትዕዛዝ ከተሾሙ ጀምሮ በገዳሙ ውስጥ በርካታ በደል እና ግፍ እንዲሁም በርከት ያሉ ዝርፊያዎች ተፈጽሟል። አባ ገብረ ሕይወት ከአብረንታንት ገዳም በተለይ ከቤተ ሚናስ በርካቶችን አሳደዋል፣ አሳሥረዋል፣ በርካቶችንም ለመንግሥት ሚሊሻ አሳልፈው በመስጠት በግፍ ታስረዋል፣ ተገለዋል። እነዚህ በግፍ የተሰደዱ ገዳማውያን ወደ ጎንደር በመሄድ በገዳሙ የሚተዳደር ርስት ስላለ በዚያ ለማረፍ ሲሄዱ በቦታው የሚገኙ የእኒሁ አባ ገብረ ሕይወት ሹመኛ የሆኑ “ብርቁ” የሚባሉ ሰው በጎንደር የዋልድባ ርስት ለማረፍ በቅድሚያ ከገዳሙ የወጣችሁበትን መሸኛ ደብዳቤ አምጡ በማለት ገዳማውያኑን ለበርካታ እንግልት ዳርገው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፥ እግዚአብሔር ያሳያችሁ አባ ገብረሕይወት ከገዳም ያባርራሉ በውጪ ያሉት ደግሞ ገዳማውያኑን ማረፊያ በማሳጣት በማማረር ለስደት እንዲሁም የብትውና ሕይወታቸውን እንዲጠሉት ለማድረግ የተቀነባበረ ሥራ እነደሚሰሩ ማሳያ ነው፤ ነገር ግን በመጨረሻ የጎንደር ወጣቶች የቦታውን ተጠሪ የተባሉትን “ብርቁ” የሚባሉትን ሰው በማነጋገር ቦታው የገዳሙ እንጂ የማንም አይደለም እነዚህ ገዳማውያን ደግሞ ከገዳሙ የመጡ ናቸው በማለት እነዚህን በየአድባራቱ ሲንከራተቱ የነበሩትን   መነኮሳት ወደ ቦታው ገብተው እንዲያርፉ በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል።

 ይሄ እንግዲህ በቀደሙት የመንግሥት ሹመኞች በቀቢጸ ተስፋ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ፥ በቅድሚያ የኢትዮጵያን ገዳማት መፍረስ” በሚል የሞኝ ብሂላቸውን ለመተግበር የመጀሩት ነው፥ ላለፉት ዘጠይ ዓመታት የሥኳር ፋብሪካ ለማቋቋም ከ በላይ የተለያዩ የሕንፃ ተቋራጮች ቢመጡም የታለው የሥሏር ፋብሪካም ሆነ፥  የሸንኮራ አገዳ የሚያስችል ግድብ ለመስራት የሞከሩት ሙከራ የእምቧይ ካብ እንደሆነባቸው እኛም እናውቃለን እነሱም በደንብ ይረዱታል፥ ነገር ግን በዚህ ሳይማሩ ዛሬ ድረስ በእልህ የገዳሙን ህልውና ለማሳጣት አሉ የተባሉትን የተባህቶ አባቶች ቢቻላቸው በማሳደድ ካልሆነም ደግሞ ልክ ዛሬ ላይ እንዳደረጉት እንደ ከብት በማረድ ገዳማውያኑን ለማስፈራራት ብዙ ሙከራዎች ተሞክረዋል ብዙ ፈተናዎች ታልፏል፣ ገዳማውያኑም እንደጸኑ አሉ እነሱም የርኩሰት ሥራቸውን በመሥራት እንደቀጠሉ ነው፥ ምናልባት አያቅቁ እንደሆነ ነው እንጂ አይሁድ የክርስቶስን መንገድ ለማስቆም ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ሲወግሩ እዚያ ጋር ይቆማል ብለው ነበር ነገር ግን፣ እስጢፋኖስ ሲሞት ሺህ እስጢፋኖሶች ተነሱ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም አደባባይ ሲሰቀል በርካቶች የጴጥሮስ ሃዋርያ ሆነው ተነስተል፥ ዛሬም አባ ሀብተወልድን በማረድ ሌሎችን እናስፈራራለን ብለው ከሆነ ከታሪክ ተማሩ በሏቸው፥ በርካቶች የአባ ሀብተወልድን ፍኖት ተከትለው እንደሚነሱ ይታወቃል።

ይህ ሁሉ ሲፈጸም ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ምንም አይነት አቤቱታ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቅሬታ አለማቅረቡ በእጅጉ ቢያሳዝነንም የዋልድባን እንታደግ ማኅበር ባለፈው ሳምንት ለጠቅላይ ቤተክህነት ደብዳቤ በመጻፍ መላካችን የሚታወስ ነው። ሙሉውን ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ በዚህ መሠረት ማኅበሩ ቅሬታውን አቅርቧል በተመሳሳይ መልኩ ለተለያዩ የመንግሥት የክልል የጸጥታ ክፍል ሃላፊዎች፣ ለሰላም ሚኒስቴር፣ ለሊቃነ ጳጳሳት በየሀገረ ስብከታቸው ተያያዥ በማድረግ ልከናል፣ ነገር ግን ከየትኛውም የመንግሥትም ሆነ የቤተ ክህነቱ መሥሪያ ቤቶች ምንም አይነት መልስ አለመሰጠቱ በእጅጉ አሳዝኖናል።

ፍርድ ለመድኅኒዓለም
ይቆየንLet's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤