Wednesday, May 13, 2020

በወረርሺኙ ተጽዕኖ: የቤተ ክርስቲያን ቤቶች ኪራይ እየተጠና ቅናሽ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፤ ስብሰባውን አጠናቀቀ፤ ነገ ረፋድ መግለጫ ይሰጣል

  • በተስፋ ልኡክ ዐቢይ ግብረ ኃይል የተከፈቱ ሦስት የድጋፍ ማሰባሰቢያ አካውንቶች፣ ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያን ድጎማ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፤
  • ገዳማት፣ የአብነት ት/ቤቶች፣ ዐቅም የሌላቸው አድባራት፣ የሕፃናት እና አረጋውያን መርጃዎቻችን፣ ቤተ ክርስቲያንንን የተጠጉ ነዳያን በቅደም ተከተላቸው ተለይተዋል
  • ለደረቅ ምግቦች እና ለጽዳት ግብኣቶች መግዣ 4.2 ሚሊዮን ብር፣ ከልማት ኮሚሽንና ከሌሎች አካላት ጋራ በመኾን ለ51 ገዳማት ተደልድሎ ተግባራዊ በመኾን ላይ ነው፤
  • ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መቀጠል ላሳለፈው ውሳኔ ውጤታማ አፈጻጸም፣ የአህጉረ ስብከት ክትትል ወሳኝነትን አሥምሮበታል፤
***


በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕንፃዎች እና ቤቶች አስተዳደር እና ልማት ድርጅት ሥር ያሉ የመኖርያ እና ንግድ ቤቶችን ተከራይተው አገልግሎት ለሚሰጡ ተከራዮች፣ ችግራቸው በቋሚ ሲኖዶስ እየተጠና የኪራይ ክፍያ ቅናሽ እንዲደረግላቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡
ምልዓተ ጉባኤው ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ተከራዮች፣ የኮቪድ-19 ወረርሺኝ በቢዝነስ እንቅስቃሴአቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰው የኪራይ ክፍያ ቅነሳ እንዲደረግላቸው በቋሚ ሲኖዶስ አማካይነት የጠየቁት፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ ቀርቦ ከታየ በኋላ ነው፡፡
ከኪራይ ክፍያው የሚሰበሰበው ገንዘብ፣ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ መደበኛ በጀት እና ለአህጉረ ስብከት ድጎማ የሚውልና በጉዳዩ ላይ የመወሰን ሥልጣኑ የቅዱስ ሲኖዶስ እንደመኾኑ፣ በአጀንዳነት የመቅረቡን ተገቢነት ምልዓተ ጉባኤው አምኖበታል፡፡ ወረርሺኙ ከጤና ቀውስ ባሻገር ኹለንተናዊ ጫና እያሳረፈ በሚገኝበት በዚኽ ወቅት፣ የተከራዮችን ጥያቄ ተቀብሎ ቅናሽ ማድረግም፣ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ሓላፊነቷን የምትወጣበት አንድ መንገድ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡ በመኾኑም፣ የተከራዮቹ የእያንዳንዳቸው ችግር በቋሚ ሲኖዶስ በኩል በተናጠል እየተጠና የክፍያ ቅናሽ እንዲደረግ ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡
በአንጻሩ፣ ወረርሺኙን ለመከላከል የተወሰዱ የጥንቃቄ ርምጃዎች፣ በገጠር አብያተ ክርስቲያንና ዝቅተኛ ዐቅም ባላቸው የከተማ አድባራት ገቢ ላይ ጫና በማሳደሩ፣ ለካህናት ደመወዝ መክፈል እንዲችሉ፣ አህጉረ ስብከት እና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከካዝናቸው እያወጡ እንዲደጉሙ ሐሳብ ቢቀርብም፣ በተለይ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ለዚህ የሚኾን በቂ ገንዘብ እንደሌለው፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በኩል ለምልዓተ ጉባኤው አስታውቋል፡፡ “የተረከብኹት 350 ሚሊዮን ብር ባለፈው ጥቅምት መደበኛ ስብሰባ፣ የዓመቱ በጀት ኾኖ ጸድቋል፤ እስከ 20 ሚሊዮን ብር ለቋንቋዎች አገልግሎት፣ እስከ 10 ሚሊዮን ብር ለሰላም ተልእኮ መድበናል፤ ሌላ ምንም የቀረ ገንዘብ የለንም፤” በማለት ሌሎች አማራጮች እንዲፈለጉ ብፁዕነታቸው ጠይቀዋል፡፡
በምልዓተ ጉባኤው የተሻለ አማራጭ ኾኖ የታየው፣ የተስፋ ልዑክ ዐቢይ ግብረ ኃይል ሥር የሚንቀሳቀሰው፣ የድጋፍ አሰባሳቢ እና ፋይናንስ ኮሚቴ በቅርቡ የከፈታቸው የባንክ አካውንቶች ናቸው፡፡ ቋቱ ቀደም ብሎ እንዲከፈት፣ ግብረ ኃይሉ የተለያዩ አማራጮችን ቢሞክርም፣ በበጎ ፈቃድ ማነስ መጓተቱ ሥራውን በወቅቱ እንዳይጀምር ችግር እንደፈጠረበት በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ዘግይቶም ቢኾን፣ የባንክ አካውንቶቹ በሦስት ባንኮች እንዲከፈቱ ውሳኔ ተሰጥቶበታል፤ በተጨማሪም፣ በኢንተርኔት አማካይነት ገንዘብ ለመሰብሰብ እንዲረዳ በአይ.ሲ.ቲ ቡድኑ ሥራዎች ተሠርተዋል።
በተያያዘም፣ የተለየ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውንና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አካላት ለይቷል፡፡ እኒኽም እንደቅደም ተከተላቸው፥ ገዳማት፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ዐቅም የሌላቸው አድባራት፣ የቤተ ክርስቲያናችን የሕፃናት እና አረጋውያን መርጃዎች ውስጥ ያሉ ሕፃናት እና አረጋውያን እንዲሁም፣ ቤተ ክርስቲያንን ተጠግተው የሚኖሩ ነዳያን እንደኾኑ ገልጿል። በተለየ ኹኔታ ሊጎዱ ይችላሉ የተባሉ ገዳማትም፣ ከልማት እና ተራድኦ ኮሚሽንና ከገዳማት አስተዳደር መምሪያ ጋራ በመኾን ተለይተዋል። ለደረቅ ምግቦች እና ለጽዳት ግብኣቶች መግዣ የሚኾን 4.2 ሚሊዮን ብር ርዳታ፣ ከልማት ኮሚሽኑ እና ከሌሎች አካላት ጋራ በመኾን ለ51 ገዳማት ተደልድሎ ተግባራዊ በመኾን ላይ እንዳለ አስታውቋል።
በሌላ በኩል ምልዓተ ጉባኤው፣ የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት፣ የሀገር ሀብት እና የሉዓላዊነት ምልክት በመኾኑ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፉን ገልጿል፡፡ ለሀገር ሰላም እና ለዜጎች አንድነት መጠበቅ፣ ቀደም ሲል ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት በሰላም እና ዕርቅ ዐቢይ ኮሚቴው በኩል የጋራ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስቧል፡፡
የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤው በመጨረሻም፣ እስከ መጪው ዓመት ጥቅምት መደበኛ ስብሰባ ድረስ ለቀጣዮች ስድስት ወራት፣ የቋሚ ሲኖዶስ ተለዋጭ አባላት ኾነው የሚያገለግሉ አራት፣ አራት ብፁዓን አባቶችን መድቧል፡፡ በዚህም መሠረት፡-
ከግንቦት እስከ ሐምሌ 30 ቀን ባሉት ሦስት ወራት፡- የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል፣ የደቡብ ኦሞ-ጂንካ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁእ አቡነ መልከ ጼዴቅ ተመድበዋል፡፡
ከነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ደግሞ፡- የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ የአዊ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቶማስ እና የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ ኾነው እንዲያገለግሉ ተመድበዋል፡፡   
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በዘመነ ኮሮና ቫይረስ/ኮቪድ-19 ወረርሺኝ አጣብቂኝ ውስጥ ያካሔደውን የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባውን፣ ለወትሮ ከተለመደው የቀናት ስብሰባ በተለየ፣ በአንድ ቀን ጀንበር አጠናቋል፡፡ ነገ ኃሙስ፣ ግንቦት 6 ቀን ረፋድ 4፡00 ላይ መግለጫ እንደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡
በወረርሺኙ እግዳት እና አስገዳጅ አሠራሮች ሳቢያ፣ ከጠቅላላው 73 የምልዓተ ጉባኤው አባላት መካከል 31 ያኽሉ ብቻ የተገኙበት ነው፣ የ2012 ዓ.ም. ግንቦት ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ፡፡ ይህም ኾኖ፣ ወረርሺኙን በማመካኘት በኀይል የተዘጉ የቤተ ክርስቲያን በሮች የጥንቃቁ ርምጃዎች ተጠብቀው እንዲከፈቱ ያሳለፈው ውሳኔ በልዩነት እንዲታወስ ያደርገዋል፡፡ ዛሬ ከቀትር በፊት ባሳለፈው በዚኹ ውሳኔው ላይ ከቀትር በኋላ ቃለ ጉባኤ የተፈራረመ ሲኾን፣ ለውጤታማ አፈጻጸሙ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እና ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ ባላነሰ፣ አህጉረ ስብከት ማድረግ የሚጠበቅባቸውን የቅርብ ክትትል ወሳኝነት አሥምሮበታል፡፡
በቀደመው ዘገባ ያስታወቅነው የምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ዐበይት ነጥቦች ለማስታወስ ያኸል፡-
  • የቤተ ክርስቲያን ሥርዐታዊ እና ቀኖናዊ አገልግሎት(ጥምቀተ ክርስትናው፣ ምስጢረ ቊርባኑ፣ ምስጢረ ተክሊሉ እና ሥርዐተ ጋብቻው እንዲሁም፣ ጸሎተ ፍትሐቱ) ይቀጥላል፤
  • የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ሓላፊነቱን ወስደው፣ የአገልግሎት መለያ ልብስ(ዩኒፎርም) የለበሱ የሰንበት ት/ቤቶችንና የአካባቢ ወጣቶችን በማስተባበር፣ በፀረ ኮቪድ-19 መከላከል የጥንቃቄ ተግባራት መሠረት(አካላዊ መራራቅንና ንጽሕናን) መንፈሳዊ አገልግሎቱን ያስፈጽማሉ፤ የማንቂያ፣ የግንዛቤ ትምህርቱን ይሰጣሉ፤ በመኾኑም የፖሊስ ኀይሉ፣ ሲጠየቅ እና አስፈላጊ ካልኾነ በቀር፣ ከቤተ ክርስቲያን ደጆች እንዲነሣ ወስኗል፤
  • በክብረ በዓላት ወቅት፣ ታቦታት ወጥተው በዐውደ ምሕረቱ ዑደት ያደርጋሉ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ግን ዑደት ሳያደርግ ርቀቱን ጠብቆ በተመደበለት ተራ እንደቆመ አከባበሩን ይሳተፋል፤
  • አህጉረ ስብከትም፣ በሥራቸው ባሉት የወረዳ አብያተ ክህነት ጽ/ቤቶች አማካይነት፣ የውሳኔውን አፈጻጸም በቅርበት ይከታተላሉ፡፡
Source: Hara Zetewahedo
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤