Saturday, June 20, 2020

የአፍሪካ ኅብረቱ መስጊድ እና ሕጋዊነቱ

 • የቦታው አሰጣጥ፥ በሃይማኖት ተቋማት የአምልኮ ማካሔጃ ቦታ አፈቃቀድ መመሪያ ከተዘረዘሩት መሳፍርት አንዳቸውንም አያሟላም፤
 • ከነባሩ ደብር 100 ሜትር በማይርቅ ቦታ መስጊድ እንዲተከል መፍቀድ፣ የእምነት ነፃነትን መጋፋት እንጂ ማስከበር ሊኾን አይችልም፤
 • የከተማዋን ማስተር ፕላንም የተከተለ አይደለም፤ ደብሩ በልማት ስም ለተወሰደበት ቦታ ትክ ሳይሰጥ ከማስተር ፕላኑ ጋራ በሚጋጭ መልኩ ለሌላው መፍቀድ አግባብ አይደለም፤
 • “ለልማት ይፈለጋል” በሚል ብዙኃን ምእመናን በጥድፊያ ከተፈናቀሉ ከ5 ዓመት በኋላ፣ ከደብሩ በቅርብ ርቀት ለመስጊድ ቦታ መስጠቱ ከፍተኛ ጥርጣሬንና የመገፋት ስሜትን ፈጥሯል
 • ያላቸውን ቦታ ከኦርቶዶክሳውያን ጋራ እያነጻጸሩ፣ “እኛ አንሶናል” የሚሉ ተደጋጋሚ ጩኸቶች፣ የከተማ አስተዳደሩ ከሕግ ውጭ እንዲሠራ ጫና ሳይፈጥሩበት አልቀሩም፤
 • በኹለቱ እምነቶች ተከታዮች መካከል አላስፈጊ ግጭት የሚፈጥር ከመኾኑም በላይ፣ የአካባቢውን የድምፅ ብክለት ያንራል፤ የትራፊክ መጨናነቅም ያስከትላል፡፡
 • ስለዚኽም የቦታ አሰጣጡ፥ ከሕግ፣ ከአካባቢ ሰላም እና ደኅንነት አኳያ በድጋሚ በአጽንዖት መታየት ይኖርበታል። 
 
***
(ፍትሕ መጽሔት፤ ኹለተኛ ዓመት ቁጥር 83፤ ግንቦት 2012 ዓ.ም.)
ጌታነው ሙንየ
በማናቸውም ፍርድ ቤት
ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ
gechhabtie@gmail.com
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በሕግ እንደ አንድ ሰው የምትቆጠር ናት። በዚኽ መብቷም፥ ንብረት የማፍራት፣ ከሌሎች በስጦታም ኾነ በግዢ ንብረት የመቀበል፣ በንብረቷ የመጠቀም እና ንብረቱን ለሌላ አካል የማስተላለፍ መብት አላት። ይህን መብት፣ አህጉረ ስብከት እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እንደሚጠቀሙበት፣ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ቁጥር 398 እና 399 ደንግጓል። በዚኽም መሠረት ቤተ ክርስቲያን፥ ለአምልኮ፣ ለቀብር፣ ለባሕረ ጥምቀት እና ለመስቀል ደመራ ማክበሪያ፣ ለጠበል እና ልዩ ልዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች መስጫ፣ ይዞታዎችን ሕጉ በሚፈቅደው መንገድ እያገኘች መጠቀም ትችላለች፡፡ በተጨማሪም፣ ለቢሮ እና ልዩ ልዩ ልማታዊ አገልግሎት የሚውሉ ቤቶች እና ሕንፃዎች፣ ለትምህርት ቤቶች የሚያገለግሉ ሕንፃዎች የከተማ ቦታዎች(መሬቶች) ይገኙበታል፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40(3)፥ የገጠርም ኾነ የከተማ መሬት እና የተፈጥሮ ሀብት  ባለቤትነት መብት የመንግሥት እና የሕዝብ ብቻ ነው፤ ብሎ በመደንገጉ፣ በመሬት ላይ የባለይዞታነት እንጂ የባለቤትነት መብት የለም። የከተማ መሬትን በተመለከተ፣ በሥራ ላይ ያለው የከተማ ቦታን በሊዝ ስለ መያዝ ለመደንገግ የወጣው ዐዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 12(1)(መ)፣ የእምነት ተቋማት ለአምልኮ ማካሔጃ የሚውሉ ቦታዎችን በምደባ ማግኘት እንደሚችሉ ይገልጻል።
“ምደባ” ማለት በዐዋጁ አንቀጽ 2(10) እንደተገለጸው፣ በጨረታ ሊስተናገዱ ለማይችሉ ተቋማት የከተማ ቦታ በሊዝ የሚፈቀድበት አሠራር ነው። በአንቀጽ 5(1)፣ማንኛውም ሰው የከተማ መሬትን በዚኽ ዋጅ  ከተደነገገው  የሊዝ ሥርዓት ውጪ መያዝ አይችልም፤ በማለት የደነገገ ሲኾን አንቀጽ 5(3) ደግሞ፣ማንኛውም ክልል ወይም የከተማ አስተዳደርበዚኽ ዋጅ ከተደነገገው ውጪ የከተማ መሬትን መፍቀድ ወይም ማስተላለፍ አይችልም፤ይላል፡፡ ስለዚኽም የከተማ አስተዳደሩ፣ ለእምነት ተቋማት ቦታ የሚሰጠው፣ በምደባ ሥርዓት ነው ማለት ነው። ይህን ዐዋጅ ለማስፈጸም የወጡ ደንቦች እና መመሪያዎችም አሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአምልኮ ማካሔጃ ቦታን ስለ መፍቀድ የሚጠቀሱ ሕገጋትን ስንመለከት፣ የከተማ ቦታ ሊዝ ደንብ ቁጥር 49/2004 እና በከተማው አስተዳደር የከተማ ቦታ ሊዝ መመሪያ ቁጥር 11/2004 ተጠቃሽ ናቸው። የሃይማኖት ተቋማት የአምልኮ ማካሔጃ ቦታ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ሊሟሉ ስለሚገቧቸው መስፈርቶች እና ስለ ቦታ አፈቃቀድ ሒደት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት አምልኮ ማካሔጃ ቦታ አፈቃቀድ መመሪያ ቁጥር 1/2010” ዝርዝር ጉዳዮች የተካተቱበት በመኾኑ፣ ለያዝነው ጉዳይ ትክክለኛው ሕግ ነው። የመመሪያው አንቀጽ 5(3)፣ ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም የከተማ አስተዳደሩ ከሚመድብለት ቦታ ውጭ በግሉ ወስኖ የአምልኮ ማካሔጃ ቦታ መጠየቅ ወይም መያዝ አይችልም፤ ይላል፡፡
ይኹን እንጂ፣ በከተማ አስተዳደሩ ሓላፊነትን የመወጣት ጉድለትም ይኹን በሒደቱ ቢሮክራሲ መብዛት የተነሣ፣ ድንጋጌው ሲከበር አይስተዋልም። አብዛኛዎቹ የእምነት ተቋማት(በተለይም ፕሮቴስታንት እና እስልምና) ወደ አምልኮ ቦታነት የሚቀየሩት ከመኖሪያ ቤትነት እንደኾነ ልብ ይሏል። የአምልኮ ማካሔጃ ቦታ ለመመደብ መሟላት ስለሚገባቸው መስፈርቶች፣ በመመሪያው አንቀጽ 7 ላይ እንደሚከተለው በዝርዝር ተቀምጠዋል። እነዚኽም፡-
 • ለአምልኮ ማካሔጃ ሊመደብ የሚችለው ቦታ፣ ቅይጥ የመኖሪያ መሬት አጠቃቀም ውስጥ ኾኖ የመዳረሻ መንገዱ ስፋት ቢያንስ ሰብሳቢ(15 ሜትር) መኾን ይኖርበታል፡፡
 • በአካባቢው ከሚገኘው ከራሱ ነባር የአምልኮ ቦታ፣ ዐዲስ የተጠየቀው የአምልኮ ቦታ፣ ቢያንስ በኹሉም አቅጣጫ ሦስት ኪሎ ሜትር ራዲየስ የሚርቅ መኾን አለበት፡፡
 • በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባው ርቀት፣ 500 ሜትር ራዲየስ ይኾናል፡፡
 • ለአምልኮ ማካሔጃ አገልግሎት ቦታ የሚጠይቅ የሃይማኖት ተቋም፣ በሚጠይቅበት አካባቢ ማለትም በኹሉም አቅጣጫ፣ በ1.5 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ባለ በወረዳ ውስጥ የተመዘገበ ቢያንስ 7 ሺሕ ምእመን ነዋሪ መኖር አለበት፡፡ በተጨማሪም፣ በአካባቢው ተመሳሳይ የሃይማኖት ተቋም ካለ፣ በኹሉም አቅጣጫ እስከ 1.5 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ባለው ክልል ውስጥ ያሉት ምእመናን በዐዲሱ የሃይማኖት ተቋም ሊመዘገቡ አይችሉም፡፡
 • ከአምልኮ ማካሔጃ አገልግሎት ጋራ አብረው የማይሔዱ ማለትም፣ ከአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከጦር ካምፖች፣ ከዋና ዋና የንግድ ቦታዎች፣ ከቆሻሻ መጣያ ቦታዎች፣ ከደኅንነት ተቋማት እና ከሌሎች የአምልኮ ኹኔታን ሊያውኩ የሚችሉ የመሬት አጠቃቀም ቦታዎች ያለው ርቀት ቢያንስ ከ500 ሜትር በላይ መኾን አለበት፤ የሚሉት ናቸው፡፡
በእነዚኽ መሳፍርት ሲመዘን፥ በአፍሪካ ኅብረት አቅራቢያ፣ ከደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት፣ የከተማ አስተዳደሩ፣ ግንቦት 12 ቀን 2012 ዓ.ም፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መስጊድ እና እስላማዊ ማእከል እንዲገነባበት በሚል የሰጠው ቦታ፣ ከተጠቀሱት መመዘኛዎች አንዳቸውንም እንኳን አያሟላም። ከኹሉ በፊት፣ ቦታው፣ በዐዋጁ መሠረት ተጠይቆ በምደባ የተሰጠ አይደለም። ቦታው፥ ከአምስት ዓመታት በፊት፣ በአካባቢው ያሉ ምእመናን የ15 ቀናት መዘጋጃ እንኳን ሳይሰጣቸው ያውም በክረምት፣ ለልማት ይፈለጋል ተብለው ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉበትና ለአፓርትመንት መሥሪያ የተከለለ ነበር። ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ርቀቱ 110 ሜትር ነው፤ ቄራ ከሚገኘው ሰላም መስጊድ የሚርቀው ደግሞ 950 ሜትር ብቻ ነው። በአካባቢው ነዋሪዎች ስለሌሉ፣ ዐዲስ የአምልኮ ስፍራ ለመጠየቅ 7ሺሕ የእምነቱ ተከታዮች መኖር አለባቸው፤” የሚለውንም መስፈርት የሚያሟላ አይደለም። ከአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤት ዋናው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ያለው ርቀትም 180 ሜትር ስለኾነ፣ ከ500 ሜትር በታች ነው።
እንዲህ ዐይነት ሕግን ያልተከተሉ አካሔዶች፣ የሃይማኖት እና የእምነት ነፃነትን ይጋፋሉ። የሃይማኖት እና የእምነት ነፃነት፣ መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 97 በመቶ በላይ የሚኾነው “ሃይማኖተኛ” በመኾኑ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ጉዳይ ትልቅ ሥፍራ ይሰጠዋል፡፡ የእምነት ነፃነትን ለማስከበር፣ መንግሥት፥ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ(refrain) እና መከላከል (protection) ሓላፊነቶች አሉበት። ኹሉንም እምነቶች በእኩል ዐይን ማየት እና የአምልኮት ሥርዓታቸውን እንዲፈጽሙ ለኹሉም ምቹ ዕድል መፍጠር፣ ከአላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት መቆጠብ እና ደኅንነታቸውን መጠበቅ ግዴታው ነው። አንደኛውን እምነት ደግፎ ሌላውን በመግፋት አድልዎ መፈጸም፣ ከሕግ ውጪ ወይም ከሕጉ በተቃራኒ አንደኛውን የሚያስደስት ሌላኛውን የሚያስከፋ ድርጊት መፈጸም የጣልቃ ገብነት ወንጀል ነው። ሰሞኑን በአፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የኾነውም ይኸው ነው።
መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የሃይማኖት እና የእምነት ነጻነት በመተላለፍ ከቤተ ክርስቲያኑ በቅርብ ርቀት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መስጊድ እና እስላማዊ ማእከል መገንቢያ ቦታ በመስጠቱ፣ በእምነቶች መካከል አድልዎ በመፈጸም፣ የእምነት ነፃነትን የማስከበር ሓላፊነቱን አጉድሏል። ይህን የምለው፣ ቦታው ለሙስሊሞች ለምን ሰጣቸው በሚል አይደለም፡፡ ይልቁንም፣ ከሕገ መንግሥቱ እና ከሌሎች ሕግጋት በተፃራሪ፣ የተለያዩ የእምነት ተቋማትን የተቀራረበ ቦታ መስጠት፣ የአምልኮት ሥርዓታቸውን በነፃነት እንዳያከናውኑ ማወክ/ማገድ እንጂ መብታቸውን ማስከበር ስላልኾነ ነው፡፡ የትኛውም የእምነት ተቋም፣ አምልኮቱን በማኅበር በሚፈጽምበት ጊዜ ለአማኞቹ በሚሰማ ነገር ግን ሌላውን በማያውክ መልክ መኾን አለበት።
የሃይማኖት እና እምነት ነፃነት፥ የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ኹኔታ፣ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶች እና ነፃነቶች ለማረጋገጥ በሚወጡ ሕግጋት ሊገደብ እንደሚችል፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27(5) ይገልጻል። በማኅበር፣ ሥርዓተ እምልኮ ሲፈጸም፣ እንደ ድምፅ ማጉያ ያሉ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ስለኾነም፣ የተለያዩ የእምነት ተቋማት በአንድ ቦታ ያውም ፊት ለፊት በቅርብ ርቀት ሲኖሩ፣ በማኅበር አምልኮ ወቅት የድምፅ ብክለት ይፈጠራል፤ ሥርዓተ አምልኳቸውን በአግባቡ ማከናወን አይችሉም፡፡ ይህ እየታወቀ፣ ከነባሩ ደብር 100 ሜትር በማይርቅ ቦታ መስጊድ እንዲተከል መፍቀድ፣ የእምነት ነፃነትን መጋፋት እንጂ ማስከበር ሊኾን አይችልም፡፡ የአምልኮ ሥርዓትን ከማስተጓጎል ባሻገር፣ በአማኞች መካከል ግጭት የሚፈጥር እና የኹለቱን እምነቶች የመከባበር ልማድ አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡

በሌላ በኩል፣ ከተማዋ የምትመራበትን ማስተር ፕላንና የአምልኮ ቦታ አሰጣጥ መመሪያን ተከትሎ የተፈቀደ አለመኾኑ ነው። ምንም እንኳን የአምልኮ ስፍራዎች በማስተር ፕላን ውስጥ ባይካተቱም፣ ለመስጊድ መሥሪያ የተሰጠው ቦታ፣ ለአምልኮ ስፍራ የሚውል አይደለም። “ከማስተር ፕላኑ ጋራ አብሮ አይሔድም፤ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘ ነው፤ ቦታው ለልማት ይፈለጋል፤” ወዘተ በሚሉ ምክንያቶች፥ በተለያዩ አካባቢዎች ይዞታዎች ተነጥቀዋል፤ ቤቶች ፈርሰዋል፤ ዜጎች ጎዳና ወጥተዋል። በለገጣፎ እና በሱሉልታ የኾነው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው። ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ የተፈቀዱ ወይም የተሰጡ ቦታዎች፣ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያን፥ ሕገ ወጥ ናቸው ተብለው ፈርሰዋል። በአንድ በኩል እያፈረሱ፣ በሌላ በኩል፣ ከማስተር ፕላኑ ጋራ በሚጋጭ መልኩ መፍቀድ አግባብ አይደለም፡፡

የተሰጠው ቦታ ስፋት፣ ለአምልኮ ማካሔጃ ብቻ ሳይኾን፣ በጨረታ ሊሰጥ የሚገባው ተጨማሪ ግንባታዎችንም መፍቀዱ ጉዳዩን አግባብነት የሌለው ያደርገዋል። የእስልምና እምነት ተከታዮች እንደ ማንኛውም አማኝ የአምልኮ ስፍራ የማግኘት መብት አላቸው። ያላቸውን ቦታ ከኦርቶዶክሳውያን ጋራ እያነጻጸሩ አንሶናል በማለት ተጽዕኖ ለማሳደር የሚጥሩ የእምነቱ ተከታዮች አሉ፡፡ “የእምነት ተቋማት ይዞታ አንዱ በጋሻ ሌላው በትክሻ” በሚል ርእስ በ“ቀሰም መጽሔት” በሰፈረ ጽሑፍ፡-
“15ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ታላቁን አንዋር መስጅድን ጨምሮ በመዲናዋ የሚገኙ 47 መስጅዶች አጠቃላይ ድምር ስፋታቸው 86,483 ካሬ ሜትር ነው፡፡ ይህም በወረዳ 7 ውስጥ የሚገኘው ሰዓሊተ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ብቻውን ከያዘው 181,418.34 ካሬ ሜትር ጋራ ሲነጻጸር ግማሹን እንኳ አያክልም፡፡ የድኅረ ምረቃ ተማሪው መንሱር እንደሚለው ደግሞ 47 መስጅዶች ተደምረው የአንድ ቤተ ክርስቲያንን ግማሽ እንኳ የማይደርሱ ከኾነና ከነዚሁም ውስጥ ከ40 በላይ የሚኾኑት በግል ገንዘብ የተገዙ ከኾኑ፣ ሙስሊሞች በተለየ ተጠቅመዋል፤ መስጅዶችም በዝተዋል ማለት አንድም ኾን ብሎ መረጃ ማዛባት አልያም ጥልቅ ማይምነት ነው፤” ብለዋል። እንዲህ ዓይነት ተደጋጋሚ ጩኸቶች፣ በከተማ አስተዳደሩ ላይ ጫና ፈጥረው፣ ከሕጉ ውጪ እንዲሠራ ያደረጉት ይመስላል፡፡ ጩኸቱን በመስጋት፣ ከሕግ ውጪ የኾነ አካሔድን ተከትሎ የማይገባቸውን መስጠት መዘዙ ብዙ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ያረፈበት ቦታ ጠባብ በመኾኑ፣ ተጨማሪ ቦታ ቢጠየቅም እስከ አኹን መልስ አልተሰጠም፤ ለልማት ተብሎ በተወሰደበትም ቦታ ትክ አልተሰጠውም። ደብሩ፣ ከምሥረታው ጀምሮ ብዙ ፈተናዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። በአካባቢው የእስረኞች ማቆያ ስለነበር፣ ወታደሮች በምእመናን እና በካህናት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጽሙ ነበር። በምእመናኑ ትብብር አዲስ ቤተ ክርስቲያን ቢተከልም፣ ምእመናን እንዳይገቡ ስለተከለከሉ፣ ካህናት ብቻ ነበር እየገቡ የሚያገለግሉት። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚሉት፣ ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ፣ በአካባቢው ያሉ ምእመናን፣ ቦታው ለልማት ይፈለጋል ተብለው ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ተደረጉ።
ለልማት ይፈለጋል የተባለው ቦታ ለአምስት ዓመት ያለምንም ልማት ተቀምጦ ቆየ። ደብሩም ያለው ቦታ በቂ ስላልኾነ የማስፋፊያ ጥያቄው እንደ ልማቱ እንዲሁ በእንጥልጥል ቀረ። ይህም ኹሉ፣ በምእመኑ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬንና የመገፋት ስሜትን ፈጥሮ ሳለ፣ በቅርብ ርቀት ለመስጊድ መሥሪያ ቦታ መስጠት፣ በእሳት ላይ ጋዝ ከማርከፍከፍ አይተናነስም። አማኞችን ወደማያባራ የፍላጎት ተቃርኖ በመክተት ጉዳዩን ለክፋት ለሚጠቀሙ አካላት በር የሚከፍት ነው። ስለኾነም፣ የተሰጠው ቦታ፣ ዘላቂ ልማት እና ሰላም የሚያመጣ እንዲኾን ማድረግ ሲገባ፣ በኹለቱ እምነቶች ተከታዮች መካከል ቅራኔ የሚፈጥር ኾኗል፤ የአካባቢውን የድምፅ ብክለት ያንራል፤ የትራፊክ መጨናነቅም ያስከትላል፡፡ ስለዚኽም የቦታ ስጦታው፥ ከሕግ፣ ከአካባቢ ሰላም እና ከደኅንነት አኳያ በድጋሚ በአጽንዖት መታየት ይኖርበታል።
በአጠቃላይ፣ አጥቢያው፥ “የተወሰደብኝ ቦታ ይመለስልኝ” ጥያቄ እያቀረበ መልስ ባላገኘበት ኹኔታ፣ ከቤተ ክርስቲያኑም በቅርብ ርቀት ላይ ያለ በመኾኑ፣ መስጊድ ቢሠራበት፣ በኹለቱ እምነት ተከታዮች መካከል አላስፈላጊ ግጭቶችን የሚቀሰቅስ ስለኾነ፣ የከተማ አስተዳደሩ በአግባቡ ሊያስብበት ይገባል።

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤