Thursday, October 15, 2020

አጠቃላይ ጉባኤው: ለቅዱስነታቸው ራስን በራስ የመከላከል ጥሪ የጋለ ድጋፍ በመስጠት ዝግጁነቱን ገለጸ፤ ባለ15 ነጥቦች መግለጫ በማውጣት ዓመታዊ ስብሰባውን አጠናቀቀ

  • ቅዱስ ሲኖዶስ ግፉን ከመሠረቱ ለማስቆም፣በምልአተ ጉባኤው ጠንክሮ እንዲወያይበት ጠየቀ
  • በዓላትን በየሰበቡ የማስተጓጎል አድሏዊ አካሔድ እንዲታረምና ወጥ አሠራር እንዲበጅ አሳሰበ
  • የቅድመ አደጋ ስጋት ክትትልና መከላከል ሥርዓት እንዲዘረጋ የተወሰነው እንዲፈጸም አዘከረ
  • ቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት መልእክት ቤተ ክርስቲያናችንን ለማዳን ራሳችንን እናዘጋጅ፡፡

***

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የግፍ ጥቃት ለመግታት እና ፀራውያንን ለመቋቋም፣ ቤተ ክርስቲያን ልጆችዋን አስተባብራ እና አደራጅታ ራስዋን በራስ ወደ መጠበቅ እንድትሸጋገር፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለአቀረቡት ማሳሰቢያ የጋለ ድጋፉን የሰጠው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ መላ አገልጋዮች እና ምእመናን ለተግባራዊነቱ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አስተላለፈ፡፡

አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው፣ ካለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 3 ቀን ጀምሮ ሲያካሒድ የቆየውን 39ኛ ዓመታዊ ስብሰባውን ዛሬ ቀትር ላይ፣ ባለ15 ነጥቦች የጋራ መግለጫ በማውጣት ያጠናቀቀ ሲኾን፣ “ቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት መልእክት፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ለማዳን ራሳችንን እናዘጋጅ፤” በማለት፣ ራስን በራስ ለመጠበቅ እና ለመከላከል ለተላለፈው ፓትርያርካዊ ጥሪ ድጋፉንና ዝግጁነቱን አስታውቋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በአጠቃላይ ጉባኤው መክፈቻ ላይ፣ “ወይኩን ቅኑተ ሐቌክሙ ወኅትወ መኃትዊክሙ = ወገባችኹ የታጠቀ፣ መብራታችኹም የበራ ይኹን፤”(ሉቃ. 12፥35) በሚለው መሪ ቃል ባስተላለፉት መልእክት፤ ኦርቶዶክሳውያን በማንነታቸው ብቻ እየደረሰባቸው ያለው ማቆሚያ የሌለው ጥቃት እና እየተባባሰ የቀጠለው ግፍ፣ ለቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ህልውና እጅግ አስጊ እየኾነ መምጣቱን አስገንዝበዋል፡፡ ምእመናን፥ በማንነታቸው ተሸማቅቀው፣ ነፃነታቸው ተገፎ፣ በአገራቸው እና በወገናቸው መካከል የመኖር እና ሃይማኖታቸውን የመከተል መብት አጥተው ባሉበት ኹኔታ፣ ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቅን ነው፤ ለማለት ስለማይቻል፣ በአንድነት ተባብሮ እና ተደራጅቶ ምንጊዜም የማይተኙትን አፅራር መቋቋም ብሎም ራስን በራስ ወደ መጠበቅ አማራጭ መሸጋገር እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል፡፡

ይኸው የርእሰ መንበሩ መልእክት፣ የአጠቃላይ ጉባኤው የጋራ መግለጫ መግቢያ እና መደምደሚያ ኾኖ በንባብ በተሰማበት ወቅት፣ ከ731 በላይ የኾኑ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አህጉረ ስብከት ተሳታፊ ልኡካን፣ የጋለ ድጋፋቸውን በጭብጨባ ገልጸዋል፡፡ መላው አገልጋዮች እና ምእመናንም፣ ማሳሰቢያውን ተግባራዊ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳን ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ፣ አጠቃላይ ጉባኤው በጋራ መግለጫው ጥሪ አስተላልፏል፡፡

በሌላ በኩል፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከመጪው ጥቅምት 12 ቀን አንሥቶ በሚያካሒደው የመጀመሪያ ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባው፣ ውሳኔ ሊያሳልፍባቸው ይገባል ያላቸውን ጉዳዮች፣ አጠቃላይ ጉባኤው በጋራ መግለጫው አካትቶ አቅርቧል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተባባሰ ያለውን በደል እና ጥቃት አስመልክቶ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፥ ጠንካራ ውይይት እንዲያደርግ፣ ግፉንና መከራውንም ከመሠረቱ ለማስቆም የሚያስችል ውሳኔ እንዲያሳልፍ አጠቃላይ ጉባኤው በአጽንዖት ጠይቋል፡፡

መንግሥት የሕግ ማስከበር ሓላፊነቱን አጠናክሮ በአግባቡ እንዲወጣ በማሳሰብ፣ ባለፈው ዓመት በተለይ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ዞኖች፣ በማንነት ላይ ተመሥርቶ በተፈጸሙ ጥቃቶች የተጎዱትን ምእመናን፥ መልሶ እንዲያቋቁም፣ እንዲክስ እና ጥፋተኞችን ለሕግ አቅርቦ እስከ መጨረሻው ፍትሕ ርትዕ ማስፈኑን እንዲቀጥል አጠቃላይ ጉባኤው ጠይቋል፡፡ የአስቸኳይ ዐዋጁ ገደቦች ከተነሡ በኋላ እና የኮሮና ወረርሺኝን ሰበብ በማድረግ፣ አክብሮ በዓላትን ኾነ ብሎ የማስታጎል አድሏዊ አሠራሮች እና ርምጃዎች በመንግሥት አካላት በኩል እየተበራከቱ እንደኾነ በጋራ መግለጫው የጠቀሰው አጠቃላይ ጉባኤው፤ በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር እና በዛሬው የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ክብረ በዓል፥ ይዞታዎችን በመቀማት እና የተሳላሚ ምእመናንን ጉዞ በማስተጓጎል የፈጠራቸውን ችግሮች በማሳያነት ጠቅሷል፡፡ ይህ አካሔድ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዐተ አምልኮ በማስተጓጎል ለወደፊቱም ጨርሶ እንዲቀር የማድረግ ዓላማ ያለው ነው፤ በማለት ተችቷል፡፡

በመኾኑም፣ ወረርሺኙን መከላከልን ያገናዘበ፣ ለኹሉም በእኩልነት የሚተገበር ወጥ አሠራር እንዲዘረጋ መንግሥትን አሳስቧል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም፣ የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር እንዲታጎል ምክንያት የኾኑ አካላትን በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ፣ አላግባብ የተነጠቁ እና የተከለከሉ የበዓሉ ማክበርያ ዐደባባዮችም እንዲመለሱ እንዲያደርግ በመግለጫው ጠይቋል፡፡ አያይዞም፣ የኮቪድ-19 ወረርሺኝ በአጭር ጊዜ የሚጠፋበት ኹኔታ እንደሌለ በመገለጹ፣ አገልጋዮች ራሳቸውን እየጠበቁ፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱን እንዲያስቀጥሉ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው የተጨባጭ ኹኔታዎች ግምገማ እንደሚያመላክቱ በጋራ መግለጫው ያስገነዘበው አጠቃላይ ጉባኤው፣ በስጋት ደረጃ አስቀድሞ መረጃ በማሰባሰብ የሚያጠና እና የሚተነትን፣ አደጋ ሲያጋጥምም ፈጥኖ የሚደርስ እና የሚከላከል፣ የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት እና የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ተቋም እንዲመሠረት፣ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተላለፈው ውሳኔ በአስቸኳይ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተፈጻሚ እንዲኾን አሳስቧል፡፡

በመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሁም በልማት ዘርፎች፣ የቤተ ክርስቲያናችንን አካላት እንቅስቃሴ አስመልክቶ መረጃ የሚሰጥ እና በወቅቱ የሚያሳውቅ የሕዝብ ግንኙነት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ በመምሪያ ደረጃ እና በአህጉረ ስብከት ደግሞ በዋና ክፍል ደረጃ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩን የጠቆመው የጋራ መግለጫው፣ ይኸው ተጠናክሮ እንዲሠራበት አሳስቧል፡፡

የአጠቃላይ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ፣ ቀደም ሲል በወጣው መርሐ ግብር፣ እስከ ነገ በስቲያ ጥቅምት 7 ቀን ለማካሔድ ታቅዶ የነበረ ቢኾንም፣ “በወቅታዊ ችግር”[በኮሮና ወረርሺኝ] ቅድመ ጥንቃቄ ምክንያት በኹለት ቀናት አስቀድሞ እንዲጠናቀቅ መደረጉን፣ የጉባኤው ሰብሳቢ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ በመዝጊያው ሥነ ሥርዓት ላይ ገልጸዋል፡፡ በይቀጥላልም፣ የመርሐ ግብሩን ሰፊ ጊዜ የሚወስዱት የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች፣ በተዘጋጁ ቅጾች መሠረት አሰናድቶና በአጭሩ አሰምቶ በማጠናቀቅ፣ ለውይይት ሰፊ ጊዜ የሚመቻችበት አሠራር እንደሚዘረጋ አስታውቀዋል፡፡

ቅዱሳን ፓትርያርኮችን፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ከሀገር ውስጥ 54፣ ከውጭ ደግሞ 33 አህጉረ ስብከትን ጨምሮ ከ731 በላይ ልኡካን የተሳተፉበት የአኹኑ 39ኛ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ 40ኛ ዓመታዊ ስብሰባውን በታሪካዊ መሰናዶዎች እንደሚያከብር፣ የጉባኤው አዘጋጅ ዐቢይ ኮሚቴ በጋራ መግለጫው ጠቁሟል፡፡

Source: ሐራ ዘተዋሕዶ 


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

1 comment:

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤