Tuesday, October 13, 2020

ቤተ ክርስቲያን የሚዘንብባትን መከራ ለመግታትና ለመቋቋም፣ ልጆችዋን አስተባብራና አደራጅታ ራስዋን ወደ መጠበቅ እንድትሸጋገር ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሰቡ

  • ከምንም ጊዜ በላይ ታጥቀን ለቤተ ክርስቲያን ህልውና መቀጠል እና ለሕዝበ ክርስቲያኑ የሕይወት ዋስትና መረጋገጥ በአንድነት የምንቆምበት ጊዜ ነው፡፡

***

በየዓመቱ ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የሚካሔደው፣ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ 39ኛ ዓመታዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባውን ዛሬ ማክሰኞ፣ ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋድ ማካሔድ ጀምሯል፡፡

ዐዲስ በተገነባው እና “ጽርሐ ተዋሕዶ” ተብሎ በተሰየመው አዳራሽ በጸሎተ ወንጌል በተጀመረው በዚኹ ዓመታዊ አጠቃላይ ጉባኤ መክፈቻ ላይ፣ “ወይኩን ቅኑተ ሐቈክሙ ወኅትወ መኃትዊክሙ፤ ወገባችኹ የታጠቀ፣ መብራታችኹም የበራ ይኹን፤”(ሉቃ. 12፥35)በሚል ርእስ መልእክት ያስተላለፉት ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፥ ቤተ ክርስቲያንን ከገጸ ምድር ለማጥፋት በየአቅጣጫው የተነሡ ኃይሎች በተበራከቱበት እና የሚፈጽሙባትም ግፍ እየተባባሰ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ፣ ጥቃቱን ለመመከት እና መከራውን ለመግታት፣ መላውን አገልጋዮች እና ምእመናን አስተባብሮ እና አደራጅቶ ራስን ወደ መጠበቅ አማራጭ መሸጋገር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፤ ጉባኤውም ተገቢውን መፍትሔ እንዲያስቀምጥ ኣሳስበዋል፡፡


፠፠፠

ኹሉንም ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር አምላካችን፣ መከራውንና ፈተናውን አስችሎ በዚኽ ታላቅ ጉባኤ ስለሰበሰበን ስሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡

“ወይኩን ቅኑተ ሐቈክሙ ወኅትወ መኃትዊክሙ፤ ወገባችኹ የታጠቀ፣ መብራታችኹም የበራ ይኹን፤”(ሉቃ. 12፥35)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ይህን ኃይለ ቃል የተናገረው እና ያስተማረው፣ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንደኾነ ኹላችንም እናውቃለን፡፡ ትምህርቱ ለጊዜው አጠገቡ ለነበሩት ሐዋርያት የተነገረ ቢኾንም፣ ፍጻሜው እስከ ዕለተ ምጽአት ለሚነሡ ደቀ መዛሙርት ኹሉ እንደኾነም እናውቃለን፤ ከእነርሱ ውስጥ በአኹኑ ጊዜ በየደረጃው በሓላፊነት የምንገኝ ደቀ መዛሙርትም፣ ቃሉ በቀጥታ እንደሚመለከተን አንዘነጋውም፡፡

በመኾኑም፣ ከዚኽ እውነታ ተነሥተን፣ ጌታችን፣ “ወገባችኹ የታጠቀ፣ መብራታችኹም የበራ ይኹን፤” ሲል፣ እኛን ያዘዘበት እና ያስተማረበት ምክንያት ምን ይኾን? የሚለውን ጥያቄ አንሥተን ማየት ከኹላችን ይጠበቃል፡፡ ኹላችንም እንደምንገነዘበው፣ የትጥቅ ነገር የሚነሣው፣ ተቃራኒ ኃይል ራስን ወይም ወገንን ለማጥቃት እንደተዘጋጀ ሲታወቅ ነው፤ መብራትንም ማብራት የሚያስፈልገውም፣ ጨለማ መኖሩ ሲታወቅ ነው፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አፅራር፣ ምንጊዜም የማይተኙ መኾናቸውን በአምላክነቱ ኃይል የሚያውቅ እግዚአብሔር አምላካችን፣ ኹልጊዜ ወገባችንን ታጥቀን መንጋውን እንድንጠብቅ አዞናል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ ብርሃናዊት፣ ሰማያዊት እነማ ዘላለማዊት ብትኾንም፣ ለጊዜው ያለችው ጠላት በብዛት ባለበት እና በጨለማው ዓለም ውስጥ ነውና፣ በጠላት እንዳትጠቃ፣ በጨለማውም እንዳትዋጥ ኹልጊዜ መብራት እንድናበራላት ታዘናል፤ ይህ የእኛ የክርስቲያኖች ቀዳሚ እና መደበኛ ሥራችን ነው፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤

ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤

በአሁኑ ጊዜ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ካለው መከራ አንጻር፣ ከምንም ጊዜ በላይ ታጥቀን ለቤተ ክርስቲያን ህልውና መቀጠል እና ለሕዝበ ክርስቲያኑ የሕይወት ዋስትና መረጋገጥ በአንድነት የምንቆምበት ጊዜ ነው፡፡

ለሦስት ሺሕ ዘመናት አገርን የገነባች እና የጠበቀች፣ ኹሉንም በእኩልነት ያስተናገደች፣ በማንም ላይ ግፍን ያልፈጸመች ቤተ ክርስቲያናችን፣ ዛሬ፥ “ከገጸ ምድር እናጥፋሽ” የሚሉ በምሥራቅም በምዕራብም እየጠበራከቱ መጥተዋል፡፡ ከዛሬ ነገ ይሻል ይኾናል፤ ፍትሕም እናገኝ ይኾናል፤ እያልን በተስፋ ብንጠባበቅም ሲኾን አናይም፤ ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ነገሩ እየተባባሰ፣ ክርስቲያን ልጆቻችንም ለተደጋጋሚ ጥቃት እየተዳረጉ በክርስቲያንነታቸው ብቻ የግፍ ግፍ እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን፣ በተለያዩ ጊዜያት ባደረገችው ጥሪ፣ ከልዩ ልዩ በጎ አድራጊዎች እና ከሕዝበ ክርስቲያኑ፣ ለተጎዱ ምእመናን የተወሰነ ድጋፍ ለማድረግ ቢሞከርም፣ ከችግሩ ስፋት የተነሣ የሚያረካ አልኾነም፡፡

አበው ሲናገሩ፣ “ከራስ በላይ ነፋስ” እንደሚሉት፣ ቤተ ክርስቲያናችን እየገጠማት ያለውን ችግር ለመቋቋም፣ ልጆችዋን አስተባብራ እና አደራጅታ ራስዋን ወደ መጠበቅ አማራጭ ካልተሸጋገረች፣ ዕጣ ፈንታዋ እጅግ አስጊ እየኾነ መጥቶአል፤ ክርስቲያን ልጆቻችን ተሸማቅቀው፣ ነፃነታቸው ተገፎ፣ በአገራቸው እና በወገናቸው መካከል የመኖር እና ሃይማኖታቸውን የመከተል መብት አጥተው ባሉበት ኹኔታ፣ ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቅን ነው ማለት አይቻልም፡፡

ስለኾነም፣ ሕዝበ ክርስቲያንን የመጠበቅ እና የማጽናናት ሓላፊነት ከኹሉ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ጫንቃ ላይ ያረፈ እንደመኾኑ መጠኝ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚዘንበውን መከራ ለመግታት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በዚኽ ጉባኤ ተገቢውን መፍትሔ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡

Source:https:Hara Zetewahedo 


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤