Saturday, October 24, 2020

ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያንን ከጥቃት ለመከላከል በሚያስችሉ ስልታዊ አማራጮች ላይ እየተወያየ ነው

በቤተ ክርስቲያንና በምአመናን ላይ እየተባባሱ የመጡ በደሎችንና ጥቃቶችን ለማስቆም፣ ኹነኛ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ የጋራ አቋም ላይ የደረሰው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ድርጊቱን ለማስቆም በሚያስችሉ ስልታዊ አማራጮች ላይ እየተወያየ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በዛሬ ጥቅምት 13 ቀን የቀትር በፊት ውሎው፣ ልዩ ልዩ ጥቃቶች እየተፈጸሙባቸው ከሚገኙት አህጉረ ስብከት መካከል ሦስቱ፣ በሚመሯቸው ሊቃነ ጳጳሳት አማካይነት በንባብ ያቀረቡትን ሪፖርት አድምጧል፡፡

የምዕራብ አርሲ – ሻሸመኔ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ፣ የሐዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ እና የጋሞጎፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ በምእመናንና በቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ላይ የደረሰውንና አሁንም የቀጠለውን ጥቃት እና በደል፣ በሪፖርታቸው በስፋት አስረድተዋል፡፡ ይህንም፣ በትላንቱ የቅዱስነታቸው የመክፈቻ ቃለ ምዕዳን ከተሰጠው ሐሳብ እና በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 39ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ከተላለፈው ውሳኔ ጋራ በማዳመር፣ የጥፋት ድርጊቱን ለማስቆም በሚያስችሉ ስልታዊ አማራጮች ላይ ጉባኤው ውይይቱን መቀጠሉ ተገልጿል፡፡

ሕግን የማስከበር ሓላፊነት የተጣለበት መንግሥት፣ ጥረት እያደረገ እንደኾነ ቢገልጽም፣ ከአንዱ ወደ ሌላው እየተዛወረ እና ተባብሶ እየቀጠለ ባለው የግፍ ጥቃት እና ልዩ ልዩ መዋቅራዊ ተጽዕኖ፣ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ቀዳሚ ሰለባዎች ከመኾን እንዳልዳኑ ጉባኤው ተመልክቷል፡፡ ጉዳዩን ለመንግሥት በመተው አልያም የውግዘት መግለጫ በማውጣት እና ኮሚቴ በማቋቋም ብቻ ሊገታ እንደማይችል ተገንዝቧል፡፡ አክራሪዎቹ እና ተቃራኒዎቹ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት አልመው የሚፈጽሙት የማያባራ ጥቃት፣ ለጠቅላላ ህልውናዋ አስጊ እየኾነ በመምጣቱ፣ አደጋውን በሚመጥን ደረጃ መዘጋጀት እና መቋቋም እንደሚያስፈልግ አምኖበታል፡፡

በመኾኑም፣ ራስን በራስ የመከላከል ስልት ቀይሶ እና ምእመናንን አደራጅቶ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማስቻል፤ አኃት አብያተ ክርስቲያናትን፣ ጥንታውያን ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናትንና የዓለም አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ የክርስትናውን ወገን በዓለም አቀፍ ተራድኦ እና አጋርነት ማሰለፍ፣ ኦርቶዶክሳውያን የሕግ እና ተጓዳኝ ባለሞያዎችንና የቤተ ክርስቲያን ወዳጆችን በሀገር ውስጥ በየአህጉረ ስብከቱ እና በውጪም በየክፍላተ አህጉሩ በማሰባሰብ እና በማደራጀት አጥፊዎችን እያጋለጡ ለፍርድ የማቅረብ ሥራ እንዲሠራ የሚሉትና የመሳሰሉት ስልታዊ አማራጮች በጉባኤው ውይይት እየተካሔደባቸው ይገኛል፡፡

በተጨማሪም፣ ለውጭ ጥቃት ያጋለጡን የአስተዳደር ድክመቶች፣ ውስጣዊ አንድነትንና ሰላምን የሚፈታተኑ የጎሠኝነት፣ ጎጠኝነት እና ጥቅመኝነት አሠራሮች፣ በአሰረ ክህነት እየታዩ ያሉ ጫፍ የወጡ ሥነ ምግባራዊ ብልሽቶች፣ ቀደም ሲል በተላለፉት ውሳኔዎች መሠረት በአስቸኳይ መታረም እና መስተካከል እንደሚገባቸው በመደበኛ ስብሰባው ተነሥቷል፡፡

ምልአተ ጉባኤው፣ በቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ፈተና ላይ የጀመረውን ውይይት ከቀትር በኋላም ሲቀጥል፣  ተጨማሪ ሪፖርቶችንና መረጃዎችን በመገምገም፣ ራስን በራስ በመከላከል ስልታዊ አማራጮች ረገድ፣ ጠበቅ ጠንከር ያለ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን፣ አክራሪዎች እና ተቃራኒዎች በግልጽ እና በኅቡእ ከሚፈጽሙባት ተደራራቢ መዋቅራዊ እና ሥርዓታዊ ጥቃት የተነሣ በከባድ ፈተና ላይ እንዳለች፣ ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል፡፡

Source: Hara Zetewahedo 
Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤