Thursday, November 5, 2020

አካባቢን በንቃት በመጠበቅ ከልብ በኾነ ለቅሶ ወደ ፈጣሪ በመጮኽ ጸሎት የሚደረግበት ጊዜ ነው – ብፁዕ አቡነ አብርሃም

  • ከኅዳር 1 እስከ 7 ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ በቅዱስ ሲኖዶስ የታወጀውን፣ ምእመናን በየአጥቢያቸው እየተገኙ እንዲሳተፉ ጥሪ አስተላለፉ፤
  • በግድያ እና ማፈናቀል ተጎድተው በምግብ እና በሰላም ዕጦት የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ላሉ ወገኖቻችን፣ ሕዝብ እና መንግሥት እንዲደርስላቸው ተማፀኑ
  • በተለይ በዓመታዊ በዓላት፣ በቅርሶች እና በምእመናን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ወጣቱ ተገቢውን ፍተሻ በማካሔድ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ አሳሰቡ

***

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እና ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃም አሳሰቡ፡፡ ወቅቱ፣ ከልብ በኾነ ለቅሶ ወደ ፈጣሪ በመጮኽ ጸሎት የሚደረግበት ጊዜ እንደኾነም ብፁዕነታቸው አስታውቀዋል፡፡


ብፁዕነታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳሳሰቡት፣ አካባቢን በንቃት በመከታተል ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ከድንገተኛ ጥቃት መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመለያየት እና በጦርነት፥ ማነስ እንጂ መብዛት የለም፤ በጦርነት የበለጸገ አገር እና መንግሥትም የለም፤ ጦርነት የተሠራውን ያፈርሳል፤ የተገነባውንም ይንዳል፤ ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ከታሪክ በመማር ወደ አንድነት መምጣት እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ጥላቻን በፍቅር ማረም ካልተቻለ ውጤቱ የከፋ እንደሚኾን አመልክተዋል፡፡ የዐድዋን ድል መታሰቢያ በየዓመቱ የምናከብረው፣ አገርን ነፃ ለማውጣት የተከፈለውን የአገር ፍቅር ለማንጸባረቅ እንደኾነ ለአብነትም አንሥተዋል፡፡

“ፈጣሪ የሰውን ልጅ ከሁሉ አስበልጦ የፈጠረው ታላቅ ፍጡር በመኾኑ የዘር ሐረጉ፣ ሃይማኖቱ፣ በአጠቃላይ ማንነቱ ታይቶ ሳይኾን፣ ሰው በመኾኑ ብቻ ተከብሮ ሊኖር ይገባል፤” ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡ የሰውን ደም በግፍ በማፍሰስ የተገነባ ሀገር የለም፤ ይልቁንም በግፍ የሚፈስሰው የንጹሐን ደም ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ደርሶ በአገራችን ላይ መቅሠፍት እንደሚያመጣ ታውቆ የሰውን ደም በግፍ የሚያፈሱትን፣ ኹሉም በአንድነት ሊያወግዛቸው ይገባል፤ ብለዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ባለሥልጣናት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ብዙኃን መገናኛዎች፣ ስለ ሰላም የሚያቀርቡትን አካላት ሐሳብ በመቀበል፣ ሕዝቡ በሰላም የመኖር መብቱ እንዲጠበቅ ሊሠሩ እንደሚገባም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ በልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍሎች በደረሰው የነፍስ ማጥፋት እና ማፈናቀል የተጎዱ ወገኖች፣ በርካቶች እንደኾኑ ብፁዕ አቡነ አብርሃም አንሥተዋል፡፡ በምግብ እና በሰላም ዕጦት እስከ አኹን እየተሠቃዩ እና የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ያሉ ዜጎች ስላሉ፣ ሕዝብ እና መንግሥት ሊደርስላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከዚህም ጋራ ተያይዞ፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እና ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ ብፁዕነታቸው ጥሪ አቅርበዋል። በተለይም ዓመታዊ በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ፣ ወጣቱ ተገቢውን ፍተሻ በማካሔድ በምእመናንና በቅርሶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉም በንቃት መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ጾም እና ጸሎት የማይፈታው ችግር ባለመኖሩ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ከኅዳር አንድ እስከ ሰባት ቀን ድረስ፣ በኹሉም አድባራት እና ገዳማት ጸሎተ ምሕላ እንዲያዝ፣ ለኹሉም ሕዝበ ክርስቲያን ጥሪ መቅረቡን አስታውቀዋል፡፡ “ምእምናንና ካህናት፥ እንደ ነነዌ ሰዎች ከልብ በኾነ ለቅሶ ወደ ፈጣሪ በመጮኽ ጸሎት የሚደረግበት ጊዜ በመኾኑ፣ ምእመናን በየአጥቢያው በመገኘት በጸሎት እንድትሳተፉ” ሲሉ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ምንጭ፡- AMM 


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤