Saturday, March 27, 2021

በዋልድባ አበረንታንት ገዳም የወሬ ዘመቻ ተከፍቶበታል

የዋልድባ አበረንታንት አባቶች በሥራ ላይ

በዋልድባ አበረንታንት ገዳም የወሬ ዘመቻ ተከፍቶበታል

·       ዋልድባ ከ1000 በላይ መነኮሳት ተሰደዋል

·       ዙ መነኮሳት ተገለዋል

·       ፋኖ ሃይል በገዳም በመግባት ድብደባ ፈጽሟል በማለት የሐሰት ዜናዎችን በማሰራጨት የተጠመዱ መነኮሳት በምዕራቡ አለም

ዋልድባ አበረንታንት ገዳም ላለፉት 30 ዓመታት በርካታ ፈተናዎችን ማሳለፉን፣ በተለይ የቀድሞው የዘራፊው መንግሥት ኦርቶዶክሳውያንን ለመጉዳት ይልቁንም የሃይማኖታችንን መሠረት የሆነውን የዋልድባ አበረንታንት ገዳምን እንዲነጥፍ ያላሰለሰ ጥረት ሲያድጉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፤ የሥኳር ፋብሪካን እናቋቁማለን በሚል፣ የወርቅ ማውጫ በሚል፣ የእምነ በረድ ፋብሪካ እንገነባለን በሚል፣ የእጣን አዘጋጆች በሚል በተለያየ መልኩ ገዳሙን እና ክብሩን ባልጠበቀ ሁኔታ ብዙ ደባ ሲፈጸም እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።


እነዚህ ሃይሎች በተለይ ትላንት በርካታ መነኮሳት በዘራቸው ምክንያት ሲሰደዱ፣ ሲገደሉ፣ በእሥር ሲሰቃዩ፣ ብዙ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ በደሎችን ሲፈጸምባቸው በዚያው በገዳም ተቀምጠው ያው ሥርዓት እንዲቀጥል እና ገዳሙን የማፍረሱን ጉዳይ ሲደግፉ እና ጋሻ ጃግሬ ሆነው በማገዝ ሲተባበሩ የነበሩት ይልቁንም “የቤተ ጣዕመ” መነኮሳት በመባል የሚታወቁን፤ ትላንት “እኛ የልማት ተቃዋሚዎች አይደለንም” “ልማቱ ለገዳሙ የአሳ ምርት ይሰጣል” “በቅርባችን ሃኪም ቤት ቢሰራልን ጥሩ ነው” እና ሌሎችንም በመንግሥት ሚዲያ በመውጣት ሲናገሩ እና የማፍረሱ ሥራ ተባባሪዎች የነበሩ አባቶች ዛሬ ደግሞ በአንዳንት የቅዱስ ሲኖዶስ አባቶች መሪነት ገዳሙን ለቃችሁ ውጡ ተብለው ገዳሙን ለቀው መውጣታቸው ተሰምቷል።

በውጪ የሚኖሩት ደግሞ ትላንት በውጪ ሆነው “ይሄ መንግሥት የልማት መንግሥት ነው”፣ “ዋልድባን ቅጽር ቀጽሮ ቢያስጠብቅ ለቤተክርስቲያን ጥሩ ነው” “የልማቱን መንግሥት አንቃወም” የመሣሰሉትን በመናገር ሕዝበ ክርስቲያኑን በውጪ ሲያደናግሩ እና ግራ ሲያጋቡ የነበሩ የመነኮሳት ልብስ በመልበስ የፖለቲካ ሥራ ሲሰሩ የነበሩ እንደነበሩ እናስታውሳለን፤ ዛሬ ደግሞ ትላንት በሚሰደዱት መነኮሳት ሲሳለቁ የነበሩት፣ ልማት ፈላጊዎች ነን ሲሉ የነበሩት ደግሞ በተራቸው “1000 በላይ መነኮሳት ተሰደዱብን” በማለት በተለያየ ዓለማት ላይ በመሆን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን በውሸት በማደናገር ባስቸኳይ ቢቻላችሁ “100 ዩሮ ላኩ” ካልቻላችሁ “50 ዩሮ ላኩ” በማልት በኢጣልያ ከተሞች ሮም ላይ ተቀምጠው የሚያደናግሩ መነኮሳት ተነስተው የውሸት ፕሮፓጋንዳቸውን እያሰራጩ ይገኛሉ።

በዋልድባ አበረንታንት እንደሚታወቀው በቤተ ሚናስ እና ቤተ ጣዕመ ተብለው ላለፉት 50 ዓመት በላይ ሲወዛገብ የነበረ በቅዱስ ሲኖዶስ ሊፈታ ያልቻለ ትልቅ ፈተና ነበር፤ እርሱም የቤተ ጣዕመ መነኮሳት እምነት ጉዳይ ነው እርሱም “የጌታችንን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክነት” የማይቀበሉ አባቶች በመነሳታቸው ይልቁንም በመጽሐፍ ጽፈው “ምስጢረ ሥላሴ በአበው ሊቃውንት” በሚል ተጽፎ ሁለት ጊዜ ታትሞ ሲሰራጭ ከእነሱ የወጣው መነኩስ ነኝ ባይ “አባ ገብረ እግዚአብሔር አብርሃ” ተብሎ የሚታወቅ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዘ መጽሐፍ ጸሐፊ በመጽሐፉ የቤተ ጣዕመ መነኮሳትን እምነት ቁልጭ አድርጎ ያሳወቀ በመሆኑ በመጨረሻ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በሐምሌ 11 ቀን 2005 በቁጥር 455/513/2005 ባወጣው ደብዳቤ በውግዘት መጽሐፉ ከስርጭት እንዲታገድ ጸሐፊውም ወደ ገዳሙ እንዳይገባ ተወግዘው ተለይተው በተለያየ ጊዜ ወደ ገዳሙ ሰውየው በመጣ ጊዜ ውዝግቦች ተነስተው፤ እኛም በተለያየ ጊዜ ይሄንኑ ለምዕመናን ማሳወቃችን የታወሳል። ዛሬም እንደገና እነዚያው ሰዎች ተሰደድን ተገደልን በማለት የውሸት ፕሮፓጋንዳቸውን በውጪው ዓለም በማሰራጨት ጀመረዋል፣ ይሄንን እንድንል ያስገደደን ነገር በቅርቡ በጣሊያን ሮም ነዋሪ የሆኑ መነኮስ የሆኑ አባት እኔ የዋልድባ አባት ነኝ በማለት ይጀምሩና በመጨረሻ የገዳማውያኑን መሰደድ እና ከ1000 በላይ የሚሆኑ መሰደዳቸውን ይናገራሉ፤

እውነታው፤

1ኛ/በቅድሚያ በዋልድባ አብረንታንት በአባ ነፃ፣ በሞፈር ቤት፣ በትርህምት በአጠቃላይ አበረንታንት የሚኖሩት የቤተ ጣዕመ አባላት ከ250 እስከ 300 እንደሚኖሩ ይታወቃል፤ ነገር ግን መነኮስ ነኝ ባዩ አባት ከ1000 በላይ የሚሆኑ አባቶች ተሰደዱ መባሉ ቁጥሩን ከየት ተበድረውት ነው?

2ኛ/ የወጡት መነኮሳት አንደኛ የሽሬው ሊቀ ጳጳስ ባሰሰቡት መሠረት የዋልድባ አበረንታንት የቤተ ጣዕመ አብላት “ከገዳም ለቃችሁ ውጡ” ተብለው ግማሹ ወደ ደብረ አባይ፣ ግማሹ ወደ ሽሬ መሄዳቸው በቅርቡ እንደተሰማ ይታወቃል፤ እውነቱ ያ ሆኖ እያለ ለምን “1000 መነኮሳት ተሰደዱ ተብሎ ዜና መሥራት ተፈለገ?”

3ኛ/ እውነት ሰውየው እንደተናገሩት “1000 መነኮሳት ተሰደው ከሆነ” ለምን ስለመብታቸው አልጠየቁም? በነጻነት በገዳማቸው ሆነው እንዲገለገሉ? ወይንም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ይስጥልን አላሉም? ያሉት ነገር ቢኖር “ከቻላችሁ 100 ዩሮ ካላቻላችሁ 50 ዩሮ ላኩልን” በማለት ተናገሩ? ገንዘቡ እውነት ለመነኮሳት ወይስ ሌላ ጦርነት ለማገዝ?

4ኛ/ እውነት እንደተባለው ይሄን ያህል መነኮሳት ተሰደው ቢሆን ለምን ሌሎች የዜና ማሰራጫዎች አልተናገሩትም? ሰውየው ብቻ ለእርሳቸው የተለየ መረጃ ማን ሊሰጣቸው ቻለ? ዜናውንስ ማን አደረሳቸው? ምን አይነት መረጃዎችን ይዘዋል? የድምጽ ወይንም የቪዲዮ መረጃዎች አሉ ወይ? ተገደሉ የተባሉትስ መነኮሳት ስምና ማንነት የላቸውም እንዴ? ለምን ስለ ስማቸው እና ምን እንደሆኑ ለምን አልተናገሩም?

5ኛ/ እስከ ዛሬ ድረስ የተለያዩ ማጣራቶችን ስናደር በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የገዳሙን አባቶች እና ምዕመናን ለማጣራት ስንሞክር የቤተ ጣዕመ መነኮሳት በተነገራቸው መሠረት ወደ ደብረ አባይ እና ሽሬ ለመሄድ ሲነሱ እውነተኛ የትግራይ ተወላጆች እነ አባ ገብረ ዋሕድ የመሰሉ ታላላቅ አባቶች ለምን ገዳማችሁ ለቃችሁ ትሄዳላችሁ እባካችሁ ተሳስበን እንኑር በማለት በታላላቅ አባቶች ሲለመኑ አሻፈረን ብለው ሊቀ ጳጳሱ በሰጡት መመሪያ መሠረት ሄደው ሳለ ዛሬ በየት በኩል ነው ተገፍተው ወይንም የፋኖ ሰራዊት ደብድቦ አስወጣቸው ብሎ ማውራት በእውነት ከአንድ የሃይማኖት አባት የሚጠበቅ አይደለም፤ ይልቁንም የዘመኑን ሕዝቡን እርስ በእርስ ደም ለማቃባት የሚደረግ ጥረት ነው እንጂ በጎ ነገር ሊያመጣ የማይችል ነገር ነው እና ቢቆጠቡ እና ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ እንመክራለን።

የዋልድባ (ዋሊ)ገዳም በእራሱ በክርስቶስ የተመሠረት እንደመሆኑ መጠን በወሬ ወይንም የራሳቸውን ዘውግ ይዘው ገዳሙን ለማመስ የሚነሱም ሆነ በገዳሙ ላይ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት በሐሰት የሚያነሱትን ሁሉ አምላከ አቡነ ሣሙኤል ዛሬም ልቦናውን ይስጣችሁ እንላለን፤ በዋልድባ አበረንታንት በ30 ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሱባኤውን በሥርዓት ሌሊት በሰዓታት፣ ጠዋት በኪዳን ምሽት በመሐረነ አብ (ነግህ) ጸሎት በማድረግ ያለምንም ፈተና መነኮሳት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ እንዳለ ሰምተናል፤ በዚህም እግዚአብሔርን በማመስገን መጪውን ዘመንም እግዚአብሔርን እየለመኑ፤ የሀገራችንን መጻዒ ዘመን የሰላም እንዲያደርግ ቀን ከሌሊት በመጸለይ ወደ ፈጣሪያቸው ወደ ፈጣሪያችን በማመለከት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፤ በአካባቢው መጠነኛ የሆነ የጸጥታው ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ የተረጋጋ ባይሆንም አልፎ አልፎ የጥይት ድምጽ እና የከባድ መሣሪያ ድምጽ መሰማቱ አልቀረም ያም ሆኖ ግን ገዳምውያኑ ለሃገር ህልውና ለዜጎች ደህንነት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ወደ ፈጣሪያቸው ይለምኑልናል፤ የእነሱም ጸሎት እና ምልጃ ሃገራችን ከገባችበት የዘረኝነት ቅርቃር ውስጥ እንደሚያወጣት እናምናለን፤ አምላከ አበው፣ አምላከ ሳሙኤል ዛሬም ሥራውን የሰራል፤ እነዚያ ለአርባ ዘመናት በአንድ ቦታ ሆነው አምካቸውን የለመኑ አባቶች ያሉበት ቦታ ዛሬም ተከብሮ የአባቶችን ቡራኬ እየተቀበልን ሃገራንን በሰላም በመከባበር እንድትኖር እርሱ ይርዳን፤

በመጪው የመጋቢት መድኅኒዓለም ታላቅ ክብረ በዓል ላይ በርከት ያሉ ምዕመናን ወደ ቦታው በመሄድ ከበረከቱ ለመካፈል ስለሚሄዱ ሁኔታዎችን በዓይን በማየት መፍረድ ያቻላል፤ ነገር ግን የሽብር ወሬ በማውራት በሬ ወለደ በማለት ምዕመናንን የሚያሸብሩትን፣ በሬ ወለደዎችን እግዚአብሔር አምላክ ልቦና ይስጥልን፤ እነሱንም ሰውን በወሬ ከማተራመስ ተቆጥበው የክብር ወንበር ስባ ላከበረቻቸው ቤተክርስቲያን የበኩላቸውን መጪውን ትውልድ በመቅረጽ እንዲተባበሩ እንመክራለን፤ ውሸት በማውራት ቤተክርስቲያንን ማመስ ወንጀልም ሃጢያትም ነው እና ወደ ልቦናቸው ይመለሱ እንላለን፤

ይብቃን ይቆየን

ዋልድባን እንታደግ

Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤