Friday, October 22, 2021

የአባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ራብዓይ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ 

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኃላፊ፣ የአርሲ ሀገረ ስብከት እና የምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የሲዳማ ክልል፣ የጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፡-

 በዚህ ሐዋርያዊ ጉባኤ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ እንድንወያይ በየጊዜው የሚሰበስበን እግዚአብሔር አምላካችን ከዚህ ዕለትና ሰዓት ስላደረሰን ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ወደዚህ ዓመታዊ ዓቢይ ጉባኤ እንኳን ደhና መጣችሁ።

<<ዕቀብ ማኅፀንተከ ዘተወፈይከ ከመ ትስብክ ቃሎ ቀዊመከ>> ቆመህ ቃሉን ትሰብክ ዘንድ የተቀበልከውን አደራ ጠብቅ”1 ጢሞ 4፡14)፡፡

 በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው በዓለም ያለው ኃላፊነት ሁሉ መንፈሳዊውም ሆነ ሥጋዊው ያለ አደራ የሚሰጥ አይደለም። ይልቁኑም ለቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ አደራ ከሁሉም የላቀ እንደሆነ አንስተውም። ምክንያቱም ከሰው ሳይሆን በቀጥታ ከእግዚአብሔር የተሰጠ አደራ ከመሆኑም በተጨማሪ በሰማይም ሆነ በምድር ገደብ የለሽ  ኃላፊነት በመሆኑ ነው። ሌላው ተልእኮ የምድሩን ብቻ ሆኖ ከዚያም በጂኦግራፊ ወይም በመልክዐ ምድር ወይም በድንበር ወይም በሥጋዊና ዓለማዊ ጉዳዮች የተገደበ ነው የቅዱሰ ሲኖዶስ ተልእኮ ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው። በምድር ላይ ምንም ዓይነት ድንበርና ወሰን ስለሌለው ገደብ የለሽ ነው። ምክንያቱም ራሱ አደራ ሰጪው አምላክ <<ሑሩ ወመሀሩ ውስተ ኲሉ አጽናፈ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኲሉ ፍጥረት>> ወደ ዓለም ዳርቻዎች ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ”በማለት አዞናልና ነው። ተልእኮው ይህ ከሆነ ዘንድ ኃላፊነቱም በዚህ ልክ ተሰጥቶናል ማለት ነው። የቅዱስ ሲኖዶስ አደራ በመንፈስ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ምእመናንን በነፍሳቸውም ሆነ በሥጋቸው በምልአት መጠበቅን የሚመለከት ነው። ማለትም ተልእኮአችን የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑት ምእመናን በምድርም ሆነ በሰማይ፣ በሥጋም ሆነ በነፍስ ለጉዳት እንዳይጋለጡ መጠበቅ ነው ማለት ነው፡፡ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት


ንዋይ ኅሩይ የተባለው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ በላከለት መልእክት የተሰጠንን አደራ እንዴት መወጣት እንዳለብን በሚገባ አስረድቶናል። ይኸውም ተግቶ ቃሉን በመስበክ አደራችንን መጠበቅ እንዳለብን ነው። ምክንያቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ከእግዚአብሔር ቃል የበለጠ የሰውን ሕሊና የሚረታና የሚያሳምን ሌላ ኃይል የለውምና ነው። ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሺሕ ዓመታት ተልእኮዋ የሕዝቡንና የአሕዛቡን ሕሊና ማርካ፣ መንፈሱን አርክታ ከጎኗ በማሰለፍ ለእግዚአብሔር ማቅረብ የቻለችው በዚህ ቅዱስና ኃያል ቃል ነው። በመሆኑም እኛም ሆን የዘመኑ ትውልድ ከቃሉ የበለጠ ሌላ ኃይል እንደሌለ በውል ተገንዝበን፣ ለዚህም አጽንኦት ሰጥተን በትጋት መሥራት ግዴታችን ይሆናል ቅዱስ ቃሉን በትጋትና በጥራት፣ በተመስጦና በብቃት እያስተማርን መሆናችንና አለመኖናችንን የሚመሰክረው በምድሩ ላይ ያለው  ተጨባጭ ውጤት እንደሆነም ማስተዋል ይገባናል። ምእመናን እየበዙ በአገልግሎታችንና በትምህርታችንም እየተደሰቱ ከሆነ፣ እውነትም ቃሉን በትክክል አሥርፀናል። ሠርተናልም ማለት ነው። ተቃራኒው ከሆነ ግን ገና ይቀረናል ማለት ነው። ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ጉባኤ ማየት መገምገምና ተጨባጭ የማስተካከል ሥራ መሥራት ያለበት በዚህ ዙሪያ ነው፡፡


ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት


መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ሥራ በአግባቡ ለማከናወን የሰላም መኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ሰላም ከሌለ ሃይማኖታዊ አገልግሎትና አስተምህሮም መቆሙና መቋረጡ አይቀሬ ነው። ሰላም ሲጠፋ አማንያንም ሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ጉዳት ላይ ይወድቃሉ ይህም በመሆኑ ዛሬ በሀገራችን በተከሠተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱት ጉዳቶች በቤተ ክርስቲያናችን ሊከሠቱ ችለዋል፡፡ ይህ አሳዛኝ ክሥተት በሃይማኖት በወገንና በሀገር ላይ እያደረሰ ያለው ከባድ ጉዳት እንዲያበቃ ወደ እግዚአብሔር መጸለይና መማፀን ይኖርብናል። ነገሮች ሁሉ ከእግዚአብሔር በታች እንጂ በላይ ስላይደሉ መፍትሔው እሱ እንዲያመጣልን ወደ እርሱ አጥብቀን መጸለይ ይኖርብናል። ከዚህም ጋር በጦርነቱ የተጐዱ ወገኖች ተደራራቢ ችግር እንዳያጋጥማቸው ሕዝቡን በማስተባበር ልንረዳቸውና ልንደርስላቸው ይገባል፡፡


በመጨረሻም


በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በተደነገገው መሠረት በጥቅምት ወር በየዓመቱ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን የሚካሄደው ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት የተከፈተ መሆኑን በእግዚአብሔር ስም እናበስራለን።

እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!


አባ ማትያስ ቀዳማዊ 

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም

ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት


Let's save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

No comments:

Post a Comment

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤