ከኛ ምን ይጠበቃል?

App for your computer or phone 
To download እዚይ ጋር ይጫኑ 
click here for pdf
                          ‹እኛና መንፈስ ቅዱስ› ማለት ሊቀር ነውን?

ቅዱስ ሲኖዶስ የፓትርያርኩን እንደራሴ ሹመት በተመለከተ ለመወያት የያዘው አጀንዳ የመንግሥት ተወካይ ባለበት እንዲታይ መወሰኑን ዛሬ ጠዋት ሰማን፡፡ ከብጹዐን ጳጳሳት በቀር ካህናትና ቆሞሳት እንኳን የማይገቡበት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አማኝ ይሁን ኢአማኒ፣ ሙስሊም ይሁን ክርስቲያን የማይታወቅ የመንግሥት ተወካይ እንዲገኝበት መጋበዙ የደረስንበትን የውርደት ደረጃ የሚያሳየን ነው፡፡
በአንድ በኩል የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ወሳኝ አካል መሆኑን ስናስበው፤ በሌላ በኩል የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚደረገው በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ነው፤ ውሳኔውም በሐዋርያት ሥራ እንደተገለጠው ‹እኛና መንፈስ ቅዱስ› የሚባልበት ነው(የሐዋ. 15፣29) የሚለውን ስናየው ‹የመንግሥት ተወካይ ይኑርልን› የሚለውን ውሳኔ ኢሃይማኖታዊ ነው ያሰኘዋል፡፡ ለአንድ የሲኖዶስ ጉባኤ የመንፈስ ቅዱስ መገኘት አልበቃው ብሎ ነው የመንግሥትን ተወካይ የሚጋብዘው? ‹ሱባኤ ይዘን፣ ጸሎት አድርገን፤ አንድ ገዳም ወርደን፣ ከእግዚአብሔር ጋር መክረን› አይደለም ይሉን አባቶቻችን፡፡ ‹የመንግሥትን ተወካይ ጋብዘን› ነው ያሉን፡፡ እንዲያውም ቀኖናው የሊቀ ጳጳሳቱ(ፓትርያርኩ) ጉዳይ ሲታይ ‹በመቀመጫቸው መካከል አንድ ወንበር አስቀምጠው፣ ቅዱስ ወንጌሉን በዚያ ላይ አኑረው፣ ሊቀ ጳጳሳቱ በፊታቸው ተቀምጦ፣ አንድነት ተነሥተው በሩን ዘግተው ይጸልዩ፤ የተሰበሰቡበትንም ጉዳይ በሥውር(በኅቡእ) ይመርምሩ› ነው የሚለው(ፍ.ነ. ዐ.168)፡፡ እንዴት ተደርጎ ነው የመንግሥት ተወካይ ባለበት የሚታየው? አግዚአብሔር ያየናል የሚለው ጠፍቶ ታዛቢ ቢያስፈልግ እንኳን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለታዛቢነት አይበቁም? ቅዱስ ጳውሎስ ‹በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን?› (1ኛቆሮ. 6፣5) ያለው ለዚህ ጊዜ አይሆነንም?


በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ የመንግሥት ተወካይ እንዲገኝ መጋበዙ በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልና የሚነካ በሌላ በኩልም ሕገ መንግሥቱን የሚጥስ፤ በመጨረሻም ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚያፈርስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነትና ታዛቢነት የራስዋን ጉዳዮች በራስዋ ሕግጋት፣ ቀኖናና ሥርዓት መሠረት የመወሰን መብት አላት፡፡ አባቶቻችን ከንጉሥ ሐርቤ ዘመን ጀምረው ከግብጽ ሲኖዶስ ጋር ሲሟገቱ የኖሩት ይህን ሉዐላዊነት ለቤተ ክርስቲያናቸው ለማስገኘት ነው፡፡ ጳጳሳትን ለማግኘት የግብጽ ሡልጣኖች መለማመጥ፣ የግብጽንም ፓትርያርኮች መለመን ሰልችቷቸው፡፡ ከግብጽ ቀድማ ክርስትናና የተቀበለች ሀገር፣ የራስዋን ጉዳይ ለመወሰን አለመቻሏ አስደናቂ ስለሆነባቸው፡፡ ከቤተ ክርስቲያንዋ ታላቅነትና ከሀገሪቱ ክብር ጋር ስላልተመጣጠነላቸው፡፡
ዛሬ ያ ሁሉ ተረስቶ መንግሥትን በገዛ ፈቃዳቸው ‹አንተ በመካከላችን ካልተገኘህ አንሰበሰብም› የሚሉ አባቶች መጡ፡፡ ቀደምት አበው ‹አንተ ከኛ ጋር ሁን› የሚሉት ፈጣሪያቸው ነበር፡፡ ዘመን ተቀየረ፡፡ በቀደመው ጊዜ ‹መንግሥት ለምን በጉዳያችን ውስጥ ይገባል?› ነበር ክርክሩ፡፡ ‹አሁን መንግሥት ከሌለ ይህንን አጀንዳ አናይም› የሚባልበት ዘመን ላይ ደረስን፡፡ የፓትርያርክ እንደራሴ ጉዳይ የሃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ እንደራሴውም የሚፈጽመው ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ነው፡፡ የሥልጣን ክልሉም በቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን ክልል ነው፡፡ ታድያ ለምንድን ነው መንግሥት ያስፈለገው? ይህንን ጥያቄ ፓትርያርኩ ጠይቀውት ይሆናል፡፡ እንደመከራከሪያ ቢያቀርቡት አይገርምም፤ ቢያሳዝንም፡፡ የምልዐተ ጉባኤው መቀበል ግን ሕመም ነው፡፡
መንግሥትስ ቢሆን ምን ብሎ ነው ተወካይ የሚልከው? ምናልባት ‹ጠሩኝ፣ ሄድኩ› ካላለ በቀር፡፡ ሕገ መንግሥታችን መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ በግልጽ እየደነገገ እንዴት አድርጎ ነው በቀኖናዊ ስብሰባ ላይ የሚገኘው? ውሳኔውንስ ከየትኞቹ የቀኖና መጻሕፍት ጋር ሊያገናዝብ ነው? በጉባኤው የሚኖረውስ ሚና ምን ሊሆን ነው? ምን ዓይነት ወኪልስ ነው የሚወክለው? በየትኛው ሥልጣንና ሕግ ነው የሚገኘው? የዚህ ዓይነቱ አሠራርስ መጨረሻው ምን ይሆናል? በጉባኤው ላይ የሚተላለፈው ውሳኔ የማን ውሳኔ ነው? ‹የእኛና መንፈስ ቅዱስ› ወይስ ‹የእኛና የመንግሥት›? መንግሥትም ጉዳዩን ሊያስብበት ይገባል፤ ‹ሲጠሩት አቤት› ሳይሆን ‹ሲጠሩት ለምን?› መሆን አለበት፡፡
የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ኤጲስ ቆጶስ በዚህ ዓለም መኳንንት ርዳታ አንዳይቆም ያዝዛል፡፡ በእምነቱና በእግዚአብሔር ቃል ብቻ እንዲጸና፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ 176፤ረስጠብ 21) በዲድስቅልያም ላይ ‹ከቤተ ክርስቲያን ሹሞች በቀር ሕዝባዊ አይፍረድ› ይላል (ዐንቀጽ 71)፡፡ ታድያ በምን ሕግ ነው የመንግሥት ተወካይ ባለበት የቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤውን የሚያደርገው?
ዛሬ እንደዋዛ የሚከፈተው በር ነገ እንዝጋህ ቢሉት አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ አባት የመንግሥት ተወካይ ይገኝልኝ ባለ ቁጥር የሚፈቀድ ከሆነ፤ ነገ ደግሞ ወንድሜ ባለበት፤ እናቴ ባለችበት፤ ሐኪሜ ባለበት፣ ፖሊስ በተገኘበት ይሄ አጀንዳ ይታይ የሚል ነገር መስማታችን አይቀሬ ነው፡፡ ጋባዡም፤ ተጋባዡም ቆመው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ መቼም እንደዘንድሮ የእንጦንስና ጳውሊ ራእይ በተግባር የታየበት ዘመን የለም፡፡ 
----------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------                                    
ከ”አሜን ባሻገር”ን በዐይነ-ደብተራ አሻግረን ባየናት ጊዜ!
(በአማን ነጸረ በፌስቡክ እንደጻፉት):- መጽሐፊቱ ጓዘ-ብዙ ናት፡፡ ታሪክ፣ፖለቲካ፣የጉዞ ማስታወሻ ትነካካለች--መጽሐፊቷ፡፡ የታሪክ ማጠንጠኛዋ አጼ ምኒልክን ማዕከል ያደርጋል፡፡ ጭብጧአጼ ምኒልክ ያገሪቱን ማዕከላዊና ደቡባዊ ክፍል እስከ ጠረፉ ባስገበሩበት ጊዜ ከብሔር ብሔረሰቦች ቀደምት አበው፡- የሌላውን ብሔር ያልተነኮሰ፣በራሱ የብሔረሰብ አባላት ላይ -ሰብአዊ ድርጊት ያልፈጸመ፣በውስጡ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ያሰፈነ የብሔር ወይም የጎሳ ባላባት ያለው ብሔረሰባዊ ምሁር የምኒልክን አጽም በድንጋይ ይውገርየምትል ሆና ተሰምታኛለች፡፡ መከራከሪያው ቅጣት ማቅለያ ይሆን እንደሆነ እንጅ አንዱ ብሔር በሌላ ብሔር ተወላጅ ባላባት ሲጨቆንና በራሱ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔረሰብ ሲጨቆን ስሜቱ እኩል አይመስለኝም፡፡ በዚህ ላይ ያለነው ብሔር-ተኮር ክልላዊ አረደጃጀትና ሕገ-መንግሥታዊ ቁመና በገነነበት ጊዜ ነውና የጨቋኙ ብሔረሰባዊ ማንነትም ለወገናዊ ትረካው አስተዋጽኦ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ዞሮ ዞሮ የምወደው በዕውቀቱ በጉዳዩ ጭንቅ ገብቶት እንደ አንድ ኃላፊነት ያለበት ወጣት ደራሲ የሚሰማውን ባነበበው ልክ አዋዝቶ መጻፉ አያስከፋኝም፤እንኳን ጻፈ!ያገባኛል ስሜትያንጻል እንጂ አያናውጽም፡፡ ቢናወጸም ንውጽውጽታውን አረጋግቶ ማጽናት የባለሙያዎቹ ሥራ ነው፡፡ በበኩሌ በዚህ ጉዳይ ከዚህ በላይ ማለት አልችልም፡፡ አነሳሴም እንዲያ አይደለም፡፡ ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር በተነሱ ርእሶች ብቻ ከአሜን ባሻገርን አሻግሬ ለማየት እሞክራለሁ--በዐይነ-ደብተራ፡፡
 በእይታዬ ስሜታዊ የሆንኩ አይመስለኝም፡፡ የሰለቸኝን በተጻራሪነት ተሰልፎ ልክ ልኩን ንገረውመንገድ አልተከተልኩም፡፡ በቲፎዞነት ቆሞወያላው ዝምዘይቤም አልተከተልኩም፡፡ ሳነብ የተሰማኝን እንደወረደ አቀርባለሁ፡፡ እይታዬ 3 አዝማች አርእስት አሉት፡፡ እነሱም፡-
 1. ከአሜን ባሻገር፡- አዳራሽ እና ቤተመቅደስ!
 2. ከአሜን ባሻገር፡- ባይካተቱ የምላቸው አገላለጾች
 3. ከአሜን ባሻገር፡- ያልተሻገራቸው ጥቂት የግዕዝ ቃላት ግድፈቶች
1. አዳራሽ እና ቤተመቅደስ!
1.1. አዳራሽ፡- በግዕዝ ቋንቋ ያለው መጠሪያ!
በግዕዛችንአዳራሽየሚለውን ቃል ለመግለጽ የሚያገለግሉ በእኔ ትውስታ እንኳ 5 ስያሜዎች አሉ፡፡ (1) መርጡል፡- መርጡለ-ማርያም ስንል የማርያም አዳራሽ ማለት ነው፡፡ (2) ተሥላስ፡፡ (3) ማኅፈድ፡፡ (4) ጽርሕ፡- ጽርሐ-አርያም ወይም ጽርሐ-ንግሥት ወይም ጽርሐ-ፓትርያርክ ስንል በሁሉም ቃላት ውስጥ ያለው የጽርሕ ትርጉም አዳራሽ ነው፡፡ (5) ታዕካ፡- ታዕካ-ነገሥት ስንል የነገሥት አዳራሽ ማለት ነው፡፡ በእነዚህ ቃላት ውስጥ፡- መርጡል፣ጽርሕ እና ታዕካ የሚሉ ቃላት የአብያተ-ክርስቲያናት ቅጽሎች ናቸው፡፡ ትርጓሜያቸውአዳራሽነው፡፡ ታዲያ እየተስተዋለ!ትርጉምና መጠሪያ ይለያያል!ትርጉም አንድምታ/ትንታኔ/ሐተታ ነው!
1.2. አዳራሽ፡- በመጽሐፍ እና አንድምታ!
በማርቆስ ወንጌል 14 13 ጌታ ደቀመዛሙርቱን የመጨረሻውን እራት በጸሎተ-ሐሙስ እንዲያሰናዱለት ትእዛዝ ሲሰጥበደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅአዳራሽያሳያችኋል፤በዚያ አሰናዱልንይላል፡፡ በቅዳሴ ማርያም እመቤታችንንምስራቅ እፁት-ዘሕዝቅኤልይላታል አባ ሕርያቆስ፡፡ አበው ይሕን ምሳሌያዊ ገለጻ ሲያብራሩሕዝቅኤል በጽኑ መቆለፊያ የተቆለፈችአዳራሽያየብሽ ምሥራቅ አንቺ ነሽ፡፡ ሕዝቅኤል ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ከቤተመቅደስ ሲገባ ታላቅአዳራሽበጽኑ መቆለፊያ ተቆልፋአይቷታል፡፡ አዳራሽየእመቤታችን፣ቁልፍ የማኅተመ-ድንግልናዋ ምሳሌ …” ሲሉ ያመሰጥሩታል (ቅዳሴ ማርያም ንባቡና ትርጓሜው፡ገ.59)፡፡ አባ ሕርያቆስ አክሎም እመቤታችንንጽርሕ ንጽሕት ዘሚልክያስይላታል፡፡ ትርጓሜው የሚልክያስ ንጽሕት አዳራሽ ማለት ነው፡፡ እየተስተዋለ!አዳራሾች ሁሉ እኩል አይደሉም!ሕዝቅኤልና የሚልክያስ አዳራሽ ተምሳሌታዊ ትርጉም ሌላ ነው!የኢሰማኮ እና አፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ትርጉም ሌላ ነው!ተሰብሳቢውና የስብሰባው ምስጢርም ሌላ!ሌላ!በስም ቃላዊ ፍቺው ከመመሳሰሉ በቀር አንዱ ካንዱ የተለየ ነው--የቀደመው አዳራሽ ቅዱስ የሚል ቅጽል አለው፡፡
1.3 ስም እና ቅድስና!
ቅጽር-ቤተክርስቲያን የገባ እና የተገነባ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ነው፤መለየቱ በስያሜው ይገለጻል፡፡ ቤተክርስቲያን የገባ መባዕ ሁሉ ይቀደሳል፡፡ መቀደስ ማለት መለየት ነው ቀጥተኛ ፍቺው፡፡ መቀደሱን ተከትሎ ስሙም ይቀየራል፡፡ ምዕመኑ በስሙ አይጠራም፤በክርስትና ስሙ ነው--ተለይቷላ ለፈጣሪው፡፡ ቤ/ የገባ ስንዴ ስሙመገበሪያነው--ተለይቷላ!እንጨቱ የሰሞን እንጨት ይባላል--ተለይቷላ!በቧንባ ኮለል ብሎ ቤተመቅደስ የሚያመራው ውሃ ከመቅደሱ ሲደርስ ስሙማይነው፡፡ አስቀዳሾች ዲያቆኑን ማይ/ፀበል ስጠን ይላሉ እንጂ የተቀደሰበት ውሃ ስጠን አይሉም--ተለይቷላ፤ተቀድሷል፤ስሙ ተቀይሯል፡፡ በቁርባን ጊዜ ደሙን የምንቀበልባት ንዋይ ስሟ በቤታችን ያለው የሻይ ማማስያ ስም አይደለም፤ዕርፈ-መስቀል ትባላለች--በቅድስና ስለተለየች ስሟም ልዩ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን መገልገያዎች ሁሉ እንዲህ ናቸው፤ቅጽሩ ውስጥ ሲገቡ ዓለማዊ ስማቸውን አውልቀው አዲስ ማንነት ይላበሳሉ--ልክ እንደ ምዕመኑ ልብ!
1.4 አዳራሽ እና ቤተመቅደስ!
በትውፊታችን እንደሚታወቀውና በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 1 እንደተመለከተው የቤተክርስቲያን ሕንጻ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ቢያንስ 7 ተራዳኢ ካሕናትና ዲያቆናት ያስከተለ ጳጳስ አዲሱን ሕንጻ እና በውስጡ ያሉትን ንዋያት ከነታቦቱ በሜሮን ያከብራል(ይቀባል)፡፡ በ4ቱም የቤ/ መዐዝናት ባሉ በሮች ዑደት በማድረግ ምስባክ ይሰበካል፣ወንጌል ይነበባል እንዲሁም ምልጣን እየተመራ ይዘመራል፡፡ ሥርዓተ-ዑደቱ እና ቡራኬው ሲጠናቀቅ ታቦቱ ገና በዕለቱ የገባ አዲስ / ከሆነ የደብሩ እና የአስተዳሪው አለቃ ስያሜም ብዙ ጊዜ አብሮ በዕለቱ በተገኙት ጳጳስ ይሰየማል፡፡ ከዚያ በኋላ ሜሮን የተቀባው ሕንጻ ስሙ ቤተመቅደስ ይባላል፡፡ ቤተመቅደስ ማለት ማመስገኛ፣ጸሎት ማሳረጊያና መሥዋዕት ማቅረቢያ ማለት ነው፤ለእግዚአብሔር ተለይቶ የተቀደሰ ቤት--ቤተ መቅደስ፡፡ በውስጡ ያሉት መገልገያዎች ንዋየ-ቅድሳት፡፡ መቅደሱ የሰው መሰብሰቢያ እስከሆነ ድረስአዳራሽቢባልስ የሚል ቢኖርባንዴራ ማለት ጨርቅ ነውያሉት መሪ ያገኛቸውን ጣጣ ወይም አንድ ወቅት በሐዋሳ ዪኒቨርሲቲቁርዐን ማለት ወረቀት ነውበሚል የተፈጠሩ እሰጥ አገባዎችን ወይም 1997 . በነበረው ክርክርሕገ-መንግሥቱ ወረቀት ነውየሚሉ ክርክሮች እንዴት እየተበለቱ ተናጋሪዎቹን ላልሆነ ትርጉምና ወቀሳ እንዳጋለጡ ያላስተዋለ ሰው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የምወደው በዕውቀቱ ሥዩምአዳራሽ የቤተመቅደስ ተለዋጭ ሥም አድርጎ መጠቀሙ በመርሕ ደረጃ ስሕተት ነው፡፡ ሆኖም የወንድ በር ደግሞ አንከለክለውም፡፡ መቋሚያችንን በቁጣለይሑዳ ወልዱ ወውለደ ውሉዱ ይደምሰስብለን ለመቀወር ከማንሳታችን በፊት እናስሾልከው!
1.5 የገድለ ቅዱስ ላሊበላ መግቢያ ለበዕውቀቱ የሰጠው የወንድ በር!
ከላይ የተጠቀሱት በግዕዝ ቋንቋ አዳራሽን ለመግለጽ የተቀመጡ ቃላት ቅጣት ለማቅለል ያህል ይሆኑ ይሆናል እንጂ የበዕውቀቱን ዳህጸ-ብዕር (የብዕር ሸርተቴ) ስርየት የሚያስገኙለት አይሆኑም፡፡ አሁን የማቀርባቸው ምክንያቶችም እንዲሁ ለመሹለኪያ ንጂ ለንጽሕና ማረጋገጫ አያግዙም፡፡ እንዲያም ሆኖ ደግሞ በዘራፍ-ሞቅታ እየተነሱ ልጁ ላይ በኢ-ሚዛናዊነት ውርጅብኝ የሚያዘንቡበትን ስልጡን ፈራጆች አሰላስለው እንዲናገሩ በመጎትጎት ለወንድማችን ፋታ ማግኛ የወንድ በር ከቅዱሱ ንጉሥ ገድል ላይ አግኝተንለታል፡፡ በ2003 . በደብሩ ሰበካ ጉባኤ አማካይነት በፕሮግረስ ማተሚያ ቤት በግእዝና አማርኛ የታተመው ገድለ ቅዱስ ላሊበላ በመግቢያው ገጽ 16 የቅዱስ ላሊበላን ሕንጻ በአድናቆት እያነሳሳ አንባብያኑን ለመንፈሳዊ ግብዣ ይጠራል፡፡ ለጉብኝት ሲጋብዝ በብዛት የሚጠቀመው ቃልአዳራሽየሚለውን ነው፡፡ አብረን እንየው፡፡ “… በላሊበላ እጅ የተሠሩትን አብያተ-ክርስቲያናት ሕንጻ ያይ ዘንድ የሚወድ ሰው ቢኖር ይምጣ፤ባይኖቹም ላይ እንደ ሙሴ ድንኳን የላሊበላአዳራሾችሕንጻዎች የሚያረጁ አይደሉምና፡፡ የላሊበላ (ገብረ መስቀል) ‹አዳራሾች ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እስክትታይ ድረስ አይነዋወጡም፤አይጠፉምምይላል፡፡ ይቺን የገድለ ቅዱስ ላሊበላ መግቢያ ያየ የበዕውቀቱ ኀያሲ ውግዘቱን ረገብ ያደርጋል ብለን እናምናለን፡፡ የወንድ በር ማለት ይሄው ነው!በዚህ ላይ በዕውቀቱ እኔ በአቅሜ ነቅሼየላስታ ገጸ በረከትከምትለዋ መጣጥፉ ለማውጣት እንደ ሞከርኩት አዳራሽ ከሚለው 9 ጊዜ መላልሶ የተጠቀመው ቃል በተጓዳኝ ሕንጻ የሚል ቃል 6 ጊዜያት፣ቤተክርስቲያን የሚል ቃል እንዲሁ 6 ጊዜያት፣እንዲሁም መቅደስ የሚለውን ቃል 5 ጊዜያት በተለዋጭነት ተጠቅሟል፡፡ የገድለ ላሊበላ መግቢያ በሰጠው መሹለኪያ ላይ እነዚህ ተለዋጭ ቃላት ሲታከሉ ፍርዱን ባያስቀሩለትም ያለዝቡለታል፡፡
 2. ከአሜን ባሻገር፡- ባይካተቱ የምላቸው አገላለጾች!
የሳይኮሎጂ አስተማሪያችን በአንድ ንግግር ውስጥ 3 ነገር አለ ብሎን ነበር፡፡ ንግግር፣ተናጋሪና መናገሪያ፡፡ ለእነዚህ 3 ያለን አመለካከት በመረዳት ፍላጎታችንና አቅማችን ላይ ተጽእኖ አለው፡፡ ተናጋሪውን መውደድና አለመውደድ በንግግሩ አረዳዳችን ላይ ተጽእኖ አለው፡፡ የንግግሩ ይዘት በራሱ አሉታዊና አዎንታዊ የአሰማም ጫና አለው፡፡ ለመናገሪያውን ሚዲያ ያለን አተያይ አረዳዳችንን ይቀርጸዋል፡፡ በኢቲቪ የሚነገር ሁሉ ማይዋጥለት አለ፤በኢሳት የተነገረ ሁሉ የሚያንገሸግሸው እንዲሁ፡፡ እኒህ ሰዎች ተናጋሪውንና ንግግሩን ሳይሆን መናገሪያውንም ፈርጀውታል፡፡ ወደ ወንድም በዕውቀቱ ስንመለስ ገና መጽሐፉ ሳይወጣ ርእሱከአሜን ባሻገርመሆኑን ሲያውቁ አስቀድመው ያወገዙ አጋጥመውኛል፡፡ ተናጋሪውን አልተቀበሉትም!ምዕናባዊ ጽሑፍና ተአምራዊ ጽሑፍን እያምታታ በአንዱ መነጽር አንዱን ያያል የሚሉም አሉ፡፡ እነዚህኞቹ ጋር ስላስማማ አልቀርም፡፡ ከማሳያ ጋር ላቅርባቸው፡፡
2.1. በዕውቀቱ በገጽ 25 “የላሊበላ አዳራሾች በቃላት ወይም በፊልም ለማስረዳት መሞከር አሪፍ ቅኔን በዱዳ ቋንቋ ለመተርጎም እንደ መሞከር ነውይላል፡፡ ይሕን የመሰለ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም አለ፡፡ ቅዱሱ መጽሐፍሽባው ተተረተረ፤ዲዳው ተናገረ፤መጻጉዕ ተፈወሰ፤ጎባጣው ቀና፤ለምጻሙ ነጻ፤ዕውሩ አየ፤አንካሳው ዘለለማለትን ያዘወትራል፡፡ የገድለ ላሊበላ ጸሐፊም ለቅዱስ ላሊበላ ያለውን አድናቆትአንደበተ-ዲዳ ለሆንኩ ለእኔስ በጥበብም ሆነ በጽድቅ መልክከመሬታውያን ሁሉ የከበረ የዚህን የከበረ ሰው ትሩፋቱን ሁሉ እጽፍላችሁ ዘንድ ተሳነኝይላል (ገድለ ቅዱስ ላሊበላ፡ገ.269)፡፡ እነዚህ በቅዱሱ መጽሐፍና በገድሉ ውስጥ የሚገኙ ቃላትን መፋቅ/መቀየር አንችልም፡፡ አመለካከታችንና የቃላቱን አረዳድ ግን መቀየር እንችላለን፡፡ ይሄን ለመቀየር ደራሲያን ያላቸው አቅም አይታበልም፡፡ መቀየሩ የቃላቱን አጠቃቀም በድርሰት ሥራዎቻቸው ከዘመኑ በማጣጣም የሚጀምር ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንጻር በዕውቀቱዱዳየምትለዋን ቃል ለማንጸሪያነት ባይጠቀም ጥሩ ነበር እላለሁ፡፡
2.2. የላሊበላ ተጓዥ ምዕምናን አንዱ ላንዱተው ማርልኝእያሉ በጉዟቸው ወቅት የሚያቀርቧቸውን መንፈሳዊነት ያላቸውን አራኅራኅያን ዝማሬዎች በዕውቀቱ በገጽ 37 የገለጸበት ቋንቋቅዱስ ላሊበላም በኒህ ዘፈኖች እየተዝናና በውክልና መማሩን ይቀጥላልየሚል ነው፡፡ ይሕ /ነገር ይተንተን ቢባል ነገሩ ነገርን ይወልዳል፡፡ ያስቀይማል!ላሊበላን ከጎጃም መርጡለ-ማርያም አባይን በዋና እየተሻገሩ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ላሊበላን ስመውና ቆርበው የተመለሱ አረጋውያን አያቶችን ዝማሬ በዕውቀቱ ሲጎደፍርብኝ ለአፍታ ቅሬታ አላደረብኝም ብዬ አልዋሽም፡፡ ምነ!ይቺን /ነገር ባላስገባት ብያለሁ!
2.3. በጥቅሉ ስለእግዚአብሔር እና በመጽሐፍ ቅዱስ ስላሉ አበው ያሰፈራቸው የተወሰኑ አገላለጾች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የአቤልንና የቃኤልን መሥዋዕት በሚመለከት በገጽ 90 እግዜርን እንደ ጥሎሽ ተቀባይ የገለጸበት መንገድ፤እንዲሁም የእነ ኖኅንና ሎጥን የወይን ጠጅ ስካር ከኦሪቱ ወስዶ በገጽ 33 እነሱን ቀምቃሚዎች ማለቱ አንድም አነጋገሩ ከኢ-አማኒው በዕውቀቱ ስለሆነ ከመክበዱ በቀር የእውነት እርሾ ስላለው፣ሲቀጥልም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በሚመለከት ባለቤቶቹ ኦርቶዶክሳውያን ብቻ ስላልሆንን በተለየ መልኩ የጥቃት ስሜት አልተሰማኝም፡፡ ይልቅስ ያልወደድኩለትን 3 ተጨማሪ ማንጸሪያዎችን ላምጣ፡፡
2.4 “ይምርሃነ የሚባል ቅዱስ ንጉሥ ካላጣው ሜዳ እንደ ገመሬ ዝንጀሮ እዚያ ላይ የወጣበት ምክንያት ምንድን ነው?>> ሲል ይጠይቃል በዕውቄ በገጽ 162፡፡ ለንጽጽር የተጠቀመው ቋንቋ ደስ አያሰኝም፡፡ ደስ የማያሰኘው እሱ ስለተናገረውና ንግግሩ ሰምና ወርቅ ስለሌለው ነው፡፡ ንግግሩ ሰምና ወርቅ ኖሮበት አማኒ ሰው ቢናገረው ክፋት አይኖረውም ነበር፡፡ ላስረዳ፡፡ ቶማስ-ዘመርዐስ የተባለ በዘመነ-ሰማዕታት ስለዕምነቱ ጽናት በአላውያን ሕዋሳቱ በየቀኑ ይቆራረጡ የነበረ ሰማዕትን ተጋድሎ እና የአቡነ ተክለሃይማኖትን ለጸሎት በመቆም ብዛት ስብረተ-አጽም ማጋጠም የምትተረክ ቅኔ አብነት ትሁነን፡፡ ቅኔዋ በሰም ሰማዕቱ ቶማስን ዶሮ፣ጻድቁ ተክለሃይማኖትን ዶሮ ተመጋቢ አድርጋ ታስቀምጣለች፤በወርቅ ግን ተጋድሎአቸውን ነው የምታጠይቅ፡፡ ይቻትና፡-
 ተክለ-ሃይማኖት፡ይትፌሣህ፡በተጠብሆ-ቶማስ፡ዶርሖ፣
 ሐጺር፡እግር፡እስመ-ለተክለ-አብ፡በጽሖ፡፡
 ትላለች፡፡ ቀጥተኛ ትርጉሟ፡-ቶማስ ዶሮው ሲበለት ተክለ ሃይማኖት ደስ ይለዋል፤ለተክለ ሃይማኖት አጭር እግር ይደርሰዋልና የሚል ነው፡፡ ምስጢራዊ ትርጉሙ ግን ከላይ እንደተገለጸው ተጋድሎውን ነው የሚተርከው፡፡ ይሕ ቅኔ ተቀባይነት ያገኘው ተናጋሪው አማኒ በመሆኑና ቅኔውም ሲፈታ ወርቁ ጥሩ መልእክት ስላለው ነው፡፡ ይቺ ለኦርቶዶክሳዊው ባለቅኔ የተሰጠች መብት ለበዕውቀቱ አታገለግልም፡፡ መብቱ ወሰን አለው!-አማኒ ነኝ ካሉ በኋላ በአማንያን ቤት ዘው ብሎ መተንተን መዘዙ ብዙ!
2.5. በገጽ 237 የቀረበው ”God Bless America” እና 12 ጊዜ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ንጽጽር ከጊዜ አጠቃቀም አንጻር ማስፈገጉ ባይካድም ተጋፊነቱ ያይላል፡፡ ደህና ሲያስቀኝ የቆየው የደብረ ማርቆሱ ርዕሶም የድል አጥቢያ ተጋዳይነትና የቆየ ታጋይ መስሎ ራሱን ማዋደድ ገጽ 241 ሲደርስከኪሱ ውስጥ የስዕለት ግምጃ የሚያክል መሀረም ጎልጉሎ አውጥቶ ከመጠን በላይ እየተናፈጠ በመጠኑ ያለቅሳልየሚል ገለጻ በስዕለት ገንዘብ የሥዕለት ግምጃ የለበሰ መጽሐፍ ዘርግቼ እየተማርኩ ትምህርቱን ስጨርስ መጽሐፉን ከነግምጃው ስሜ ወንበር እያጠፍሉ ላደኩት የቄስ ልጅ ቅር የሚያሰኝ አገላለጽ ነውና እዚች መስመር ላይ ስደርስ ሳቄን ገታሁት፤አቆምኩት፡፡ ከዚያ መልሼ በዕውቀቱእንደ ቄስ በቅሎ በየገጹ አትቁምቢለኝስ  ብዬ በመስጋት ንባቤን ቀጠልኩ፡፡ በልቤ ግን ይሄ ቅብጢ እንዴት ወበራ!ሳልል አልቀረሁም!
2.6. ያም ሆኖ በገጽ 106 የስም መቀየር በተነሳ ቁጥር ቤተክህነትን ብቻ ነጥሎ መውቀስ እንደማይገባ ለማሳየት የቀድሞው ቱሉ እስልምናን ሲቀበል አባ ጅፋር መሰኘቱን፣የሳሆው (ኤርትራ) ሙስሊም የነበረው ግለሰብ ከእስልምና ወደ ፕሮቴስታንትነት ሲቀየር ሳሙኤል ጊዮርጊስ መባሉን አስረጂ መቁጠሩ ደስ አሰኝቶኛል፡፡ መጀመሪያስም እና ማንነትለሚለው መጣጥፉ ቆሜ ማጨብጨቤን አልደብቅም!ብራቮ በዕውቀቱ ሥዩም በዳዳ ወዬሳ!ብዬ ነበር!ምን ያደርጋል!ገጽ 164 ላይ ስደርስ በዕውቄአሁን ሐረር ውስጥ ነኝ፡፡ የዛሬ መቶ ዓመት አባቶቼ በወራሪነት የረገጡበት ቦታ ላይ በቱሪስትነት ቆሜ ስለጦርነት ገጸ በረከቶች እያሰብኩነው ሲል ራሱን ከተወራሪ ብሔር ተወላጅነት ወደ ወራሪ ወራሪ ተለወላጅነት ቀይሮ እዋ!አሰኘኝ!አሁን ተምንጊዜው ወራሪ ሆንሽ!ልለው ስል አባትነት በእናት ወገን በኩል ሊኖር ይችላል፤ወይም የሸዋ ኦሮሞ በሐረር ጦርነት ስለተሳተፈ የነ ኦቦ በዳዳ ወዬሳ ተሳትፎ በዚያ በኩል ሊኖር ይችላል ብዬ ራሴን ኄስኩ!በገጽ 169 እና 170 ስለመቻቻል ያነሳቸው ነጥቦችና ትዝብቶች ግነት በዝቶባቸዋል ብልም ስጋቱ ስጋቴ ነው!ለቢላደን ጺምና ለግራኝ መሐመድ ያለው አመለካከት ከተርታው ሕዝብ የተለየ ስላልሆነና የሮም ካቶሊካውያን ለብፁዕነት ያጨየዋቸውን አባ ማስያስ በገጽ 221 በዘረኝነት መክሰሱ ዘለፋው ለሁሉም ሃይማኖቶች በፍትሐዊነት ይዳረስ ለሚሉ ኀያስያን ማለዘቢያ ሳይሆነው አይቀርም፡፡ በግሌ የበዕውቀቱ ሌሎችን ሃይማኖቶች መተቸት በተወሰኑ ለኦርቶዶክሳዊ ምዕመን ተጋፊ ለሆኑ ጽሑፎቹ ስርየት ያስገኛል የሚል ዕምነት ባይኖረኝም ከገፋ ሁሉንም ይግፋ ለሚሉት ተቺዎቹ እነዚህን መስመሮች እጠቁማለሁ፡፡ ለምሳሌ፡- ገጽ 106107 እና 221፡፡

3. ከአሜን ባሻገር፡- ያልተሻገራቸው ጥቂት የግዕዝ ቃላትና ትርጉዋሜያት ግድፈቶች
በዕውቀቱ ትጉሕ መዛግብት አገላባጭ ይመስለኛል፡፡ ሲያገላብጥ ያገኛቸውን በግዕዝ ቋንቋ የተሰደሩ እምቅ ሐሳቦች ለመጽሐፉ ግብዐት በማዋሉ ደስ ብሎኛል፡፡ ሆኖም የበለጠ ደስ እንዲለኝ በሣልሳይ ኅትመቱ ውስጥ ቢያቃናቸው የምላቸውን ጥቂት የቃላት ግድፈቶች በቅንነት ልጠቁም፡፡
 3.1. ገጽ 62 ላይ በዕውቀቱ፡-
 አመ-ሠላሳ፡ቀን፡ጎበና፡ባይፀና፣
 ይካፈሉን፡ነበር፡እነ፡ቱፋ፡ሙና፡፡
 ካለ በኋላአመ-ሠላሳ፡ቀንማለቱ ጦርነቱ የፈጀውን ጊዜ ለመግለጽ እንደሚመስለው ይጠቁማል፡፡ መሰለኙ አልሰራም፡፡ አመየሚለው የግዕዝ ደቂቅ አገባብ-” ወይም “-ጊዜወይም-” የሚል ትርጉም ነው ያለው፡፡ ስለዚህአመ-ሠላሳ፡ቀንማለት30 ለታወይም30 ጊዜወይም30” የሚል ትርጉም ነው ያለው፡፡ አንድ ቀንን ያቺውም 30ኛዋን ቀን ብቻ ያመለክታል፡፡ መላውን 1 ጀምሮ እስከ 30 የሚደርሱ ቀናት አያመለክትም፡፡ ከዚሁ ተያይዞእግዚአብሔር፡ንጹሕ፡ባሕርይ፡ነውሲል የጠቀሰውን ቃልእግዚአብሔር፡ንጹሐ-ባሕርይ፡ነውቢለው የቀና ይሆናል፡፡ ንፁሕ ባሕርይ የምትለዋን ንፁሐ-ባሕርይ ማለት!
 3.2. ገጽ 90 “ አዛል ብእሲ ምንተ ያስተክዘከ(ምን ያስተክዘሀል?)” ሲል ያሰፈራት ጥቀስ አዛል ብእሲ ምንት ያቴክዘከ”(አንቱ ብርቱ ሰው ሆይ!ምን ያስተክዘሀል?)” ቢባል የግዕዙን መልእክት ይሸከመዋል፡፡ ያስተክዘከ አይባልም፤ያቴክዘከ ነው፡፡
 3.3. ገጽ 146 ላይ የሰፈረችው ጉርድ መወድስ (ለዓለም) የመሰለች በዘመነ-አጼ ገላውዴዎስ ተደረገች ያላት ቅኔ ከመጠነኛ የፊደልና የትርጓሜ ስሕተት ውጭ ጥሩ ሆና ቀርባለች፡፡ እሷን አቃንቼ በዕውቄን እሰናበተዋለሁ፡፡ ቅኔዋ ከኋላ ያለው ማንጸሪያዋ ተጎርዶ እንደቀረ በደንብ ታስታውቃለች፤ጉራጁ ካለው ለቀጣይ ኅትመት ቢያሟላው ጥሩ ነው፡፡
 ወለተ-ኢትዮጵያሰ፡ትትከደን፡አዕዳለ-ዘማዕስ፡ወአነዳ፣
 ወትለብስ፡ሰቀ፡ከመ-ሰሌዳ፣
 ወትዕንቅ፡ጋጋ፡ህየንተ-ሐብለተ-ወርቅ፡ዘውስተ-ክሳዳ፣
 ወህየንተ-ቤተ-ወይን፡ወማኅሌተ-ፅጌ፡እለ-ይላሁ፡ትረሲ፡ዐውዳ፣
 ወትክዐው፡ጸበለ፡ዲበ-ርእሳ፡ህየንተ-መዓዛ-ዕፍረት፡ወማየ-ጽጌረዳ፡፡
 ትላለች፡፡ የድሮ ቅኔ ስለሆነ ዜማ የጠበቀ አይደለም፡፡ ንጽጽሩና ሐሳብ አገላለጹ ግን በወቅቱ (16ኛው /) ሀገራችን የነበረችበትን የሰቆቃ ኑሮ ሸጋ አድርጎ ይገልጻል፡፡ በዚህ ቅኔ ውስጥ በዕውቀቱ የገደፋቸውን ቃላት ለማውጣት ያህል፡- በመጀመሪያው መስመር ላይኢትዮጵያሰማለት ሲገባውኢትዮጵያስብሎ ግዕዙን ወደ ዐማርኛ ጎትቶታል፡፡ ልዩነቱእናነው፡፡ በስም መጨረሻ ስትገባ ያላት የግዕዝ ትርጉምግን/ነገር ግንማለት ነው፡፡ 4ኛው መስመር ላይ ያለውይላሕውየሚል ቃል በዋናው መዝገብ እንዲያ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም በዘመናዊው ግዕዝይላሁቢባል ነው ሸጋ፡፡ 5ኛው ቤት ላይደባለየምትለዋ ፊደልጸበለመባል ነበረባት፡፡ ጸበልቀጥተኛ ትርጉሙ ትቢያ ማለት ነው--እሱም ጥሩ ተርጉሞታል፡፡
 ሰሌዳ የሚለው ቃል ትርጉም በዕውቀቱ በተዛማጅ ትርጓሜው እንዳመለከተው አይደለም፡፡ ሰሌዳበግዕዝ የለሰለሰ ወይም ልዝብ ብራና(ሌዘር) ማለት ነው፡፡ ቃሉ አሉታዊ አይደለም፡፡ ወትለብስ፡ሰቀ፡ከመ-ሰሌዳሲባልልብስ በማጣቷ ሌዘር ይመስል ማቅ ለበሰችማለት ነው፡፡ የተቀሩትን ቁልፍ ቃላት ለመተርጎም ያህል፡-አዕዳል--ልብስ፡፡ ማዕስ--ያልለፋ ጀንዲ፡፡ አነዳ--ቁርበት፡፡ ሰቅ--ማቅ፡፡ የቀረውን ከበዕውቀቱ ተዛማጅ ትርጉም፡-
 የኢትዮጵያ ልጅ፤ቁርበት ደርባ፣
 እንደ ሰሌዳ፤ማቅ ተከናንባ፣
 በወርቅ ድሪ ሐብል ፋንታ፤አንገቷ ቀንበር ጠልቆላት
 የዘፈን ቤቷ ፈርሶ፣
 አደባባይዋ በለቅሶ፣
 የትካዜ ጭጋግ ለብሶ፣
 በሽቶ መዓዛና በጽጌረዳ ፈሳሽ ፋንታ
 በገጽዋ ትቢያ ነስንሶ፡፡
 ይለናል በዕውቀቱ ሥዩም፡፡ በአጠቃላይ በዕውቀቱ -አማኒ ነኝ ካለ ወዲህ በአማንያን አይን የሚኖረው እይታ እንደ ድሮው ስላልሆነ የሚጠበቅበት ጥንቃቄ መክበዱን ማስተዋል ይገባዋል፡፡ አመክንዮና ሃይማኖት የሚነጻጸሩበት መነጽር እየቅል የሚሆንበት ጊዜ አለና መስመሩን ላለማምታት ቢጥር ሸጋ ነው፡፡ ከወዲህ ደግሞ ሥራውን ከመተቸት ይልቅ ሰብዕናውን ማዕከል ያደረጉበድፍረቱ፣በውሸቱ፣666ቱ፣ሞሳዱ…” የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ ካባ የተጎናጸፉ ስድቦችን የሚያስወነጭፉ ወንድም/እኅቶች ከተራ ስድብ እና ፍረጃ ድርደራ እንዲሁምከቁንጫ መላላጫአይነት ግልብ ኂሶችን ከመስጠት ይልቅ ጠቅላላ የጽሑፉን ዐውድ በማገናዘብ ምግባር ያልተለየው ኂስ ቢሰጡ ደስ ይለኛል፡፡ እከዚያው ግን በዕውቀቱ ሥዩም ለኢ-አማኒነት አበቃኝ ያለውን ጽሑፍ ለመዳሰስ ከአሜን ባሻገርን ትተን በዚህ http://www.pdf-archive.com/2014/10/19/sigmund-freud-the-future-of-an-illusion/sigmund-freud-the-future-of-an-illusion.pdf በኩል ተሻገረናል፡፡


-------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ ከESAT ራዴዮ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስበመጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ቁጥራቸው ከ1200 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በዋሽንግተን ዲሲ ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተው ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል፣ ነገር ግን የኤምባሲው ኃላፊዎች የተለያየ ምክንያቶችን በመፍጠር ለሰላማዊ ሰልፉ ከወጡት ተወካዮች የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች ተቀብለን ልናነጋግራችሁ ፈቃደኛ አይደለንም ብለው እንደምክንያት ያቀረቡት ኢ.ሐ.ፓ. የተባለው ድርጅት እዚህ ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ስለተገኙ ይህንን ፓርቲ ደግሞ የቀድሞው የደርግ መንግስት ያሸነፈው ፓርቲ ስለሆነ ከእነሱ ጋር ምንም ዓይነት ንግግርም፣ ግንኙነትም የለንም የሚል መልስ ነበር ለሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች የተሰጠው መልስ፥ እንደእውነቱ ከሆነ የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎችም ሆኑ በአጠቃላይ በሰልፉ የተገኘው 99% የሚሆነው በእነዚህ የፓርቲው ሰዎች ሊወክሉት አይችሉም፣ ሰዎቹ በቁጥር እንኳ ሃያ የማይሞሉ እንዴት ይህን የኅብረተሰቡን ክፍል ሊወክሉ ይችላሉ ተብለው ሲጠየቁ፣ በሚቀጥለው ቀን መጥታችሁ ደብዳቤያችሁን ልታቀርቡ ትችላላችሁ ነገር ግን ለዛሬ በራችን ለእናንተ ዝግ ነው በማለት ነበር የመለሱት። የሰልፉ አስተባባሪዎችም ደብዳቤውን በUS Post office በኩል በcertified letter ለኤምባሲው ልከዋል የደብዳቤውን ሙሉ ቃል ለማየት እዚህ ይጫኑ 
ቸር ይግጠመን

                                               ዋሽንግተን ዲሲ (Washington, DC) March 26, 2012


                                               ኒውዮርክ ሲቲ (New York City) March 26, 2012
                                            ቤይ ኤሪያ ካሊፎርኒያ (San Jose, CA) April 29, 2012

ዝምታ ይብቃ! ድምጻችንን እናሰማ!

                                               
በካናዳ ቶሮንቶ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ
በቶሮንቶ ካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን "የገዳማቱ ህልውና ይከበር!" በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል፣ ይህ ባለፈው ሳምንት የተደረገው ሰላማዊ ሕዝባዊ ትዕይንት በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ እንዲሁም የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች እንዲሁም ምዕመናን እና ምዕመናት የተገኙበት ትዕይትንት ብዙ ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ ነበር።
የኢትዮጵያ ገዳማት ህልውና ይከበር!
በ June 4, 2012 ሊደረግ የታሰበው ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ በመላው ዓለምበሎንዶን እንግሊዝ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዋልድባን እንታደግ ብለው ድምጻቸውን ባሰሙበት ወቅት የESAT ዜና ዘጋቢ
ሰላማዊ ሰልፉን ተከታትሎት ነበር።
በተለያዩ ዓለማት የምንገኝ የተዋሕዶ ልጆች ድምጻችንን እናሰማ! ክርስቲያናዊ ግዴታችንን እንወጣ!
                                     ታሪካዊና ጥንታዊ ገዳማቶቻችን ይከበሩ

1 comment:

  1. ዘገየን :ሊቁ አለቃ አያሌው ታምሩ የሰጡንን ምክር ቀደም ብናረገው ኑሮ መልካም ነበር:: ግን ይሁን የባሰ ሳይመጣ አሁን ጅምሩ መልካም ነው:: የፈጠረን የደንግል ማርያም ልጅ ጾሎታችን ይስማን አሜን::
    በ 27 መድኋኔአለም MD ያገናኘን::

    ReplyDelete

እግዚአብሔር ያክብርልን ስለ አስተያየትዎ ከልብ እናመሰግናለን፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት መልሰን እናገኝዎታለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን አሜን፤